ሕይወት ፈርጀ ብዙ ገጽታዎች አሏት። መውጣት እንዳለ ሁሉ መውረድም ይኖራል። ከመውረድ ውስጥም በትጋት መውጣት ይቻላል። አግኝቶ ማጣት እንዳለ ሁሉ አጥቶም ይገኛል።ይህ የህይወት እውነታ ነው። በጥቂቶች የህይወት መውጣትና መውረዶች ውስጥ ብዙዎች ይማራሉ። የህይወትን ፈተናዎችም ያውቃሉ። በከፍታ ውስጥ የሚገኙት ‹‹ እንዲህም ይኖራል እንዴ?›› ብለው ራሳቸውን ይጠይቃሉ።
ለተቸገሩት ያዝናሉ። ካላቸው ቀንሰው የሌሎችን ችግር ይካፈላሉ። በተጨማሪም ችግር ብልሃትን ያስተምራል እንዲሉ ከችግር ጋር ተላምዶ ከመኖር ይልቅ ለመፍትሄ የሚታትሩትንም ያበረታታሉ። በመሆኑም ‹‹እንዲህም ይኖራል›› ብለን በከፈትነው አምዳችን ህይወትን በየፈርጁ ታስተውሉበት፤ ¸አስተውላችሁም ትማሩበት ዘንድ ጋበዝናችሁ። ለአስተያየቶቻችሁ፤ ለመሰል ታሪኮች ጥቆማችሁ እንዲሁም ለድጋፋችሁ የዝግጅት ክፍላችን አድራሻ ትጠቀሙ ዘንድ ጋበዝናችሁ።
በሲያደብር ከእለታት አንድ ቀን
አቶ አጥናፉ በቀለ ይባላሉ። የ78 ዓመት አዛውንት ናቸው። አቶ አጥናፉ በሲያደብር ቀበሌ «መጥሪያ» በምትባል ጎጥ ‹‹ጫንጫ›› በተባለው ዋሻ ውስጥ ነው እትብታቸው የተቀበረው። «የእናት አባቴ ቀዬ፣ የማይነጥፈው ውርሴ» ይሉታል ይህንኑ ዋሻ። እሳቸውም ቢሆኑ ዋሻውን ለመጪው ትውልድ ማውረስ ይፈልጋሉ።
በዚህ መንደር እንደ አብዛኛው የኢትዮጵያ ገጠራማ ክፍሎች በሣር ቤት ውስጥ ኑሯቸውን ያደረጉ ጎረቤታሞች የሉም። ከጎጆዎች ውስጥ ቦለል እያለ አካባቢውን የሚያውድ ጭስም አይታይም። ስለምን ካሉ ደግሞ አቶ አጥናፉ የሚኖሩት በሳር ቤት አይደለምና። የእሳቸው ኑሮ በዘመናዊ ቆርቆሮ ቤት ውስጥም አይደለም። አጥናፉ ሀብታቸው ሁሉ የተከማቸው አገሬው ‹‹ጫንጫ›› ብሎ በሚጠራው ዋሻ ውስጥ ነው። ከእርሳቸው ቀደም ብሎም ስድስት ትውልድ በዋሻው ውስጥ ኖሯል። እርሳቸውም ዋሻውን ከአባታቸው መውረሳቸውን ይናገራሉ።
ዋሻው ውስጥ በመጀመሪያ ኑሯቸውን የመሰረቱት አቶ ምህረቴ የሚባሉ ሰው ነበሩ። አቶ ምህረቴ ከሲያደብር በ50 ኪሎ ሜትር ርቀት ከምትገኘው እነዋሪ ልዩ ስሙ «ሰርጠጦስ ማርያም» ከሚባል ስፍራ ነበር ኑሯቸው። ከዕለታት በአንድ ቀን ግን ለጉዳይ ወደ ሲያደብር ሄዱ። በአካባቢው በወቅቱ ሺምልጃሽ የሚባሉ ባለርስት ወይዘሮ ስለነበሩ በዚያው አቶ ምህረቴንም ባለርስት አደረጓቸው።
ከዓመታት ቆይታ በኋላ አቶ ምህረቴ ኃይሉ የሚባል ልጅ ወለዱ። ኃይሉ ደግሞ እንዳላማው የሚባል ልጃቸውን ተክተው አለፉ። እንዳላማው በቀለን፣ በቀለ ደግሞ አጥናፉን ወለዱ። ታዲያ እነዚህ ሁሉ አባወራዎች በየጊዜው ዋሻውን ኖረውበታል።
የ78 ዓመቱ ዕድሜ ባለፀጋ አቶ አጥናፉም ተራቸው በደረሰ ጊዜ በዚህ ዋሻ ውስጥ እየኖሩ ልጆቻቸውን ድረው ኩለዋል፤ የልጅ ልጅም አይተዋል። አቶ አጥናፉ ሰባት ልጅ ወልደዋል። የመጀመሪያዋ ሴት ልጃቸውም ሰባት ልጆች ወልዳለች። በዚህ ዋሻ ውስጥ ደግሞ ሰባት ትውልድ ኖሯል።
የማይታደሰው ቤት
ቤቱ ዝንተ ዓለም ጣሪያ የማይቀየርለት፣ ግርግዳው የማይታደስለትና ውበቱ የማይነጥፍ ነው። ይህ ደግሞ እሳቸውን ከወጪ ታድጓቸዋል። ከብቶቻቸውም ዝናብ አይነካቸውም፤ ፀሐይ አይደፍራቸውም። እንዲያውም በዋሻው ውስጥ ዘና ፈታ ብለው ይኖራሉ። አቶ አጥናፉ «ከብቱም ከዋሻው ተላምዷል፣ አሁን ደግሞ እኔና ባለቤቴ ‹‹እንደ አህያ ጡት ሁለት ብቻ ነን›› ይላሉ። ብቸኛ ወንድ ልጃቸውን ድረው ከዋሻው የተወሰነ ክፍል አጋርተውታል። «ያለኝ ሀብት ይኸው ነው እግዚአብሄር የሰጠኝ ዋሻ ስለሆነ በፍቅር አከፋፍላቸዋለሁ። እህል ለማስቀመጥም ጎተራውን ከዋሻው አንድ ጥግ አስቀምጦ በዚያው ማኖር ነው። አዚህ አይጥ አይቦረቡረውም፤ ሌባም አይደፍረውም። የእኛ ወጪ አልጋ እና ትንሽ የሌሊት ልብሶችን መሸመት ብቻ ነው ይላሉ።
ፍየሎችን የበላው ዋሻ
አቶ አጥናፉ የዋሻውን ስፋትና ጥልቀቱን መርምረው አያውቁም። የደርግ ሥርዓት አገሪቱን ማስተዳደር እንደጀመረ በአንዱ ቀን ቤተሰቦቻቸው ወደ ገበያ ባመሩ ጊዜ የዋሻውን ጥልቀት ለማወቅ ከታላቅ ወንድማቸው ጋር ወደ ዋሻው ውስጥ ገብተው እንደነበር ያስታውሳሉ። ይሁን እንጂ ግማሽ ቀን ሙሉ ረጅሙን መንገድ ተጉዘው ጥግ መድረስ አልቻሉም። ይህ በሆነ በሳምንቱ ደግሞ ሁለት ፍየሎች ወደ ዋሻው ሮጠው ገብተው የውሃ ሽታ ስለመሆናቸው
ዛሬም ቢሆን በትዝታ ያወጉታል።
አቶ አጥናፉና ወንድማቸው ዋሻው ውስጥ በገቡ በሳምንቱ ፍየሎቹ እንደገቡ መቅረታቸው ወላጆቻቸውን አስቆጣ፤ እነሱም አጥፍታችኋል ተብለውም ወንድማማቾቹ በአርጬሜ ተገረፉ። በዋሻው ብዙ ርቀት ከተጓዙ በኋላ መሬቱ በዱላ መታ መታ ሲደረግ በውስጡ የሚያረገርግ የባህር ድምጽ እንደሚሰማ ይናገራሉ። ምናልባት ፍየሎቹ እዚያ ውስጥ ገብተው ቀርተው አሊያም ሌላ አውሬ በልቷቸው ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ አሳድሯል። ከዛን ጊዜ በኋላ ወደ ዋሻው የሚወስደው መንገድ ተዘግቷል።
አቶ አጥናፉና ቤተሰቦቻቸው ፍየሎቹ አንድ ቀን ከዋሻው ይወጣሉ በሚል በጉጉት ሲጠብቁ ኖረዋል። መዳረሻቸው ወዴት እንደሆነ ሳያውቁና ምላሽ ሳያገኙ ግን ይኸው ግማሽ ክፍለ ዘመን ተቃርቧል። «እኛም ዓጂኢብ እንዳሰኘን እየኖርን ነው። ነገሩን ለሰዎች ስንናገርም ግራ እየገባቸው በማመንና ባለማመን መካከል ሆነው በአግራሞት ይመለከቱናል» ይላሉ አቶ አጥናፉ ነገሩን የኋሊት እያስታወሱ።
ዋሻው ሁለቱን ፍየሎች ካነከተ ወዲህ በስፍራው ክፉ ድርጊት አልገጠማቸውም። እነሱም ቢሆኑ ያለስጋት እየኖሩበት ነው። በአሁኑ ወቅት ዋሻው እንስሳትና ሰዎችን በፍቅር አሰባስቦ እያኖረ ነው። የሆነ ሆኖ በዚህ ታሪካዊ ዋሻ እርሳቸውን ጨምሮ ሰባት ትውልድ ኖረውበታል። በእሳቸው ግምት እያንዳንዱ ሰው 50 ዓመት ቢኖር እንኳን በትንሹ 350 ዓመት በዚህ ዋሻ ውስጥ ሳንከትም አንቀርም ባይ ናቸው።
ብዙ የሚነገርለት ይህ ዋሻ በውስጡ ምን እንደያዘ ማወቅ ቢቻልና የእነዚያን ፍየሎች መድረሻ የሚመልስ ሁነኛ ተመራማሪ ቢገኝ ለኢትዮጵያ አንዳች የጥናትና ምርምር ፍንጭ ሊኖር እንደሚችልም ተስፋ ያደርጋሉ – አቶ አጥናፉ።
ከቤትህ ውጣ!
በዘመነ ደርግ ‹‹ሠፈራ›› ወይንም ‹‹መንደር ምስረታ›› በሚባልበት ወቅት ከዋሻው ውጡ ተብለው ነበር። ግን አቶ አጥናፉ እና አባታቸው በቀለ እንደምን ብለን ከዋሻው እንፋታለን፤ ስለምንስ እትብታችን ከተቀበረበት ሥፍራ እንርቃለን ሲሉ አሻፈረኝ አሉ። ሰዎችስ ጓዛቸውን ሸክፈው፤ ጣሪያቸውን ነቅለው ይሄዳሉ። እኛስ ዋሻውን ተሸክመን ልንሄድ ነው ሲሉ የወቅቱን ባለጉዳዮች በጥያቄ አፋጠጡ። የኋላ ኋላ አገሬው በሙሉ በመንደር ምስረታ ወዲያ ወዲያ ሲኳትን በዋሻው የሚኖሩ ቤተሰቦች ግን በዚያው እንዲቆዩ ሆነ። እናም አሁንም ከዋሻው ጋር ያላቸው ወዳጅነት «ከተማ ለምኔ» አስብሏቸዋል። ዛሬም ቢሆን አቶ አጥናፉ «እሬሳዬ ከዚሁ ዋሻ ይወጣል እንጂ ወደ ሌላ ቤት እንግባ የሚባል ነገር የለም» ይላሉ።
የአቶ አጥናፉ ሁለት ልጆች ተምረው ሥራ ይዘው አዲስ አበባ ይኖራሉ። ታዲያ ልጆቹ የአዲስ አበባ የኑሮ ውድነት፣ የቤት ኪራይ አንገብጋቢነት ለአባታቸው በጨዋታ መልክ ያነሱላቸዋል። አቶ አጥናፉ ሁሌም የልጆቻቸው መጉላላት ያሳዝናቸዋል። ቢችሉ ከዋሻው ግማሹን ቢሰጧቸው በወደዱ ነበር። ዳሩ ከአንድ ሥፍራ የማይንቀሳቀስ ሀብት መሆኑ ያበሳጫቸዋል። ነገሩን ደጋግመው እያሰቡትም አግራሞት ይፈጥርባቸዋል፤ ዋሻውንም መከታዬ ሲሉ ይጠሩታል።
ልጆቻቸውም ቢሆኑ «ከተፈጥሮ ጋር ተስማምተህ በዚሁ እንድትኖር እንሻለን» ይሏቸዋል። የአቶ አጥናፉ ፍላጎትም በዚህ ዋሻ ውስጥ የሞቀ ትዳራቸውን መምራት ነው። ይህ ዋሻ የሰባት ትውልድ መኖሪያ ብቻ አይደለም። ብዙዎችንም ከአደጋ ታድጓል። ደርግ ወደ መውደቁ በተጠጋ ጊዜ ሲያደብር በሚባለው አካባቢ ከፍተኛ ጦርነት ነበር። ታዲያ የአካባቢው ሰዎች ከብቶቻቸውን፤ ልጆቻቸውንና ተንቀሳቃሽ ንብረቶቻቸውን ይዘው ክፉ ቀንን አልፈውበታል። ከዚያ በፊትም በአገሪቱ ውስጥ ጦርነቶች ሲካሄዱ ዋሻው ውስጥ ተደብቀው ቆይተዋል። ታዲያ ይህን ከመሠለ ባለውለታ ዋሻ ማን ይለየኛል ሲሉ ዛሬም በኩራት ይናገራሉ።
ከጅብ የሚሟገቱ ውሾች
ይህ ዋሻ ጠንካራና ደፋር ሰዎች የሚኖሩበት፤ በአቶ አጥናፉ አባባል ደግሞ
‹‹ምቾት የዳሰሰው›› ስፍራ ነው። ታዲያ በዚሁ አካባቢ ቁልቁል ቆላውን እያዩና ወደ ደጋው ቀና ብለው እያማተሩ ከሜዳው ብዙም የማይተዋወቁ ውሾች አሏቸው። የውሾቹ ጩኸት አካባቢውን ይነቀንቃል። አቶ አጥናፉን ደግሞ ሁሌም አንድ ነገር ያስደስታቸዋል። በዚህ ዋሻ አካባቢ ጅቦች ይመላለሳሉ። ሆኖም ሁለት ውሾቻቸው እየተባበሩ ጅቦቹን ቁልቁል ያሳድዷቸዋል። እናም ጅብ ሞግተው፤ አውሬ አግተው አካባቢውን ይጠብቃሉ።
ውሾቹ ከተራራ ተራራ እየዘለሉ ከዝንጀሮ ያልተናነሰ ኑሮን ይገፋሉ። አቅሟ አነስ ያለ የዱር እንስሳም የውሾቹ ሲሳይ የመሆን ዕድሏ የሰፋ ነው፤ ካገኟት ቅርጥፍጥፍ ያደርጓታል። አቶ አጥናፉ በውሾቻቸው ልባምነት እና በፈጣሪ መልካምነት ደስተኛ ናቸው።
ቱሪስቶችን የናፈቀው ዋሻ
በአንድ ወቅት ዋሻውን ‹‹ፈረንጆች›› መጥተው ጎብኝተውት ነበር። እርሳቸው ቤት በሌሉበት አንድ ቀን አላዩ ገረመው የሚባል ጋዜጠኛ ወደ ስፍራው እንደመጣ ተነግሯቸዋል። አሁን ዋሻውን እስከ ጥግ ድረስ ምን እንዳለ ማወቅ ይፈልጋሉ። በእርግጥ እርሳቸው አቅማቸው ፈቅዶ ያንን ማድረግ አይችሉም። በአንድ ወቅት ደግሞ አንድ ካህን ነኝ የሚሉ ሰው በህልማቸው ዋሻ ውስጥ ታቦት መኖሩን አይቻለሁና ገብቼ ልየው ብለው ይሁንታ ቢሰጣቸውም፤ የዋሻውን ግማሽ አካል ሳይደርሱ ተመልሰዋል። አቶ አጥናፉ ዛሬም በዋሻው ውስጥ አንድ ሚስጥር እንደሚኖር ያስባሉ። ግን በመንግስት በኩልም ቢሆን ሁነኛ ባለሙያዎች ጥናትና ምርምር ቢያካሂዱበት ይወዳሉ።
ከዋሻው የተጣላችው ጎረቤት
አቶ ወንድማገኝ እና አስቴር ስዩም ከዋሻው በአንደኛው ጥግ የሚኖሩ ባልና ሚስቶች ናቸው። አስቴር በዚህ ዋሻ ዘጠኝ ዓመታትን አስቆጥራለች። ይሁን እንጂ እርሷና ዋሻው መናበብ አልቻሉም። አስቴር ስፍራውን አልወደደችውም፤ ዋሻውም ቢሆን የወደዳት አይመስልም። እንዲያውም ዋሻው ክፉኛ እየጎዳኝ ነው ትላለች።
ዋሻው ውስጥ ማዕድ ቤት ቀይሳ ሥራ እየሠራች ድንገት ድንጋይ ከላይ እየወደቀ አስቸግሯታል። ከዋሻው ውስጥ ደግሞ በጎችና በሬዎችን አጎሩበት። አሁንም ግን ዋሻው በእነርሱ ላይ መጨከኑን ቀጠለ። ድንጋዩ በጎቹ ላይ እየወደቀ እርሷም የከብቶቹን እበት ስትዝቅ ተፈንቅሎ እየመታ አስቸገራት።
ባለፈው ዓመት አንዱን ቀን ምሽት ጨለማን የተገነ አስደንጋጭ ክስተት ተከሰተ። ከደጋ ተጠራቅሞ የመጣ ድንገቴ ጎርፉ ከተራራው አናት ላይ በርቀት መወርወር ጀመር። በሁኔታው ክፉኛ የደነገጠችው ሴት በድንጋጤ «ድረሱልኝ» ስትል ጮኸች፣ ተጣራች። ሰሚ አልተገኘም። መንገድ አሳብራ ወደ ደጋው እርዱኝ ለማለት ሄደች። ሰዎች «እሺ እንርዳሽ» ብለው ሲመጡ ጎተራዋ ከእነ እህሉ በጎርፉ ተወስዶ ጠበቃት። ለዓመት ያለችው ቀለብ በአንዲት ቀን ጀንበር ደራሽ ጎርፍ በላው።እነሱ ሳይበሉት ቀድሞ በውሃ ተበላ።
በወቅቱ አጠገቧ ያልነበረው ባሏ የሆነውን ሁሉ ከቀናት በኋላ ቢሲማ በድንጋጤ ወደቀ። ክፉኛም ታመመ፤ እርሷም ታመመች። አሁን ከዋሻው ውስጥ የተወሰነ ነገር ከማስቀመጥ የዘለለ ብዙም አልጠቀማትም። ጎረቤቶችዋ ግን ዘመናትን ያለ አንዳች ችግር ሲኖሩ ማየቷ ሁሌም ይገርማታል። «ለመሆኑ ዋሻውን ምን በድዬው ይሆን?» ስትልም ራሷን ትጠይቃለች።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 5/2011
በክፍለዮሐንስ አንበርብር