ሥርዓት ውስጥ ሻጭና ገዢ ዋጋ ቆርጠው ግብይት እንዲፈጽሙ ከሚያስችሏቸው መለኪያዎች አንዱ ሚዛን ነው። ከሚሊ ግራም እስከ ኪሎ ግራም ያሉ መለኪያዎችን እንደ አስፈላጊነቱ እየተጠቀምን የምንገበያየው ሚዛን በሻጭና በገዢ መካከል የቃል ኪዳን ማሰሪያ ውል በመሆኑ ነው።
አንድ ኪሎ ስጋ፣ ግማሽ ኪሎ ሽንኩርት፣ አንድ ኪሎ ሙዝ ወዘተ እንደየ ወቅቱ የገበያ ሁኔታ ተመን የሚወጣላቸው ቢሆንም መለኪያቸው ግን ሚዛን በመሆኑ ሸማቹ ባስመዘነው መጠን ልክ ሂሳብ እንዲከፍል ሻጩም በተጠየቀው ልክ መዝኖ እንዲያስረክብ ስምምነቱ ያስገድዳቸዋል።
ባለንበት ዘመን በውስጣዊም ይሁን ውጫዊ ምክንያቶች መሽቶ በነጋ ቁጥር በሸቀጦችና በምግብ ፍጆታዎች ላይ የዋጋ ጭማሪን መስማት የተለመደ ጉዳይ ነው። ከዚህ የሚከፋው ደግሞ ሚዛን የሚቀሽቡ ነጋዴዎች የመበራከታቸው እውነታ ሲሆን ፤ ችግሩም ለሸማቹ ማህበረሰብ ላይ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› ከሆነ ውሎ አድሯል።
በተለይም ከዕለት ተዕለት ኑሯችን ጋር በተገናኘ በምንሸምታቸው የምግብ ፍጆታዎች ላይ የሚደረገውን የሚዛን ቅሸባ የመንደራችን አትክልት ቤቶች፣ ዳቦ ቤቶችና ሥጋ ቤቶች የማይደብቁት እውነታ ነው።
ሌብነት መልኩ ብዙ ነው፤ ደረጃውና በሕብረተሰቡ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖም ይለያያል። ለምሳሌ የመንግሥትን መሬት በመሸጥና ጨረታን በማጭበርበር የሚፈጸም ሌብነት የሀገርን ኢኮኖሚ ከማቆርቆዝ አንጻር ጉዳቱ ከፍተኛ እንደሚሆን አያጠራጥርም። እንዲህ አይነቱ ሌብነት ጉዳቱ የሚታየው በሂደት ስለሆነ በሕብረተሰቡ ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ ከመቅጽበት ልናየው አንችልም።
ይህ ሲባል ጊዜያዊ ችግር አያስከትልምና ችላ እንበለው ለማለት አይደለም። በየቢሮው ተሰግስገው የሚዘርፉ ሌቦችን መንግሥት በጀመረው መንገድ እያደነ ለፍርድ በማቅረብ ከሌብነት የጸዳ አሠራርን ማስፈን እንዳለበት እናምናለን።
ከዚህም በተጨማሪ በዕለት ተዕለት ኑሯችን ላይ ፈታና የሆኑና በልቶ የማደርና ያለማደራችንን ጉዳይ እየወሰኑ ያሉ ሌብነቶችም ተመሳሳይ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል።
በመንግሥት ተቋማት አካባቢ የተጀመረው ሌባን የማጽዳት ዘመቻ በቢሮ ደረጃ ብቻ ተወስኖ መቅረት የለበትም። ይልቁንም ከጉሮሮ ላይ ወደሚናጠቁ ሚዛን ቀሻቢዎች ፊቱን አዙሮ ለሕብረተሰቡ የእለት ተእለት ጥያቄ አፋጣኝ መልስ መስጠት እንዳለበት ይሰማኛል።
አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል ዕለት ተዕለት ከሚጠቀማቸው የምግብ ፍጆታዎች መካከል ዳቦ የመጀመሪያው ነው። ዳቦ በተለይም ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ሰዎች በቀላሉ ገዝተው የሚጠቀሙት የቀን ደራሽ ምግብ ነው። የቀን ሥራ እየሠሩ በሚያገኙት ገንዘብ በየቀኑ ዳቦ እየሸመቱ ልጆቻቸውን የሚያሳድጉ ወላጆችም በርካቶች ናቸው።
በእርግጥ መንግሥት የዳቦ ገበያውን ለማረጋጋት ቀደም ሲል ከውጭ በሚያስገባው ስንዴ ላይ ድጎማ ከማድረግ ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ የሸገር ዳቦ ፋብሪካን በመገንባት ለከተማዋ ነዋሪዎች የዳቦ አቅርቦትን በስፋት ተደራሽ ለማድረግ የቻለውን ሁሉ አድርጓል። አሁንም የማስፋፊያ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።
ሸገር ዳቦ ከሚሸጥበት ተመጣጣኝ ዋጋ አንጻር ሕብረተሰቡን እየደጎመ መሆኑ ባይካድም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን የዳቦ ፍላጎት መልሷል ማለት ግን አይቻልም። በዚህ የተነሳ ዛሬም ድረስ አብዛኛው ሕዝብ ከዳቦ ቤቶች እየሸመተ የሚያድር በመሆኑ ግራም እየቀሸቡ ለሚሸጡ ነጋዴዎች ተጋላጭ ሆኗል።
የሀገሪቱ የደረጃ መስፈርት የአንድ ዳቦ አነስተኛ ክብደት 100 ግራም እንዲሆን የሚያስገድድ ቢሆንም ነጋዴዎች ግራሙን በመቀሸብ አንድ ዳቦ መሆን የሚገባውን ሁለት ዳቦ እያደረጉና ዋጋ እየቆለሉ ሕብረተሰቡን ለከፍተኛ ወጪ እየዳረጉት መሆኑ የሁላችንም ትዝብት ነው።
ኢትዮጵያ ስንዴን አምርታ ኤክስፖርት ለማድረግ በተዘጋጀችበት በዚህ ወቅት ዳቦ ዋጋው ተቆልሎ ፤ ግራሙ አሽቆልቁሎ መመልክት የሚያሳፍር ነው። ዳቦ ተገቢውን ግራም አሟልቶ ለገበያ እንዲቀርብ የሚመለከተው ባለድርሻ አካል ቁጥጥር ማድረግ ይኖርበታል።
የቀድሞው ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በአንድ ወቅት በሚዛን ላይ የሚደረግ እንዲህ አይነት ማጭበርበርን ለመቆጣጠር ዲጂታል ሚዛኖች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ይደረጋል ማለቱ ይታወሳል። ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ ተግባራዊ ባለመደረጉ እና ቁጥጥሩ አናሳ በመሆኑ የዳቦ ነጋዴዎች ከደሃው ጉሮሮ እየነጠቁ የማይገባቸውን ጥቅም እያግበሰበሱ ይገኛሉ።
የዳቦን ግራም እየቀነሱ የሚሸጡ ነጋዴዎች በኑሮ ውድነቱ ላይ ብቻ ሳይሆን በማህበረሰቡ ሥነ ልቦና ላይ የሚፈጥሩት ጫና ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። ሰዎች ያለፈውን ዘመን ካሉበት ዘመን ጋር እያነጻጸሩ በዚህ ዘመን መኖራቸውን እንደበረከት ሳይሆን እንደ እርግማን እንዲመለከቱት የሚያደርግ እና የመኖር ተስፋንም የሚያጨልም ነው።
ዛሬ ገበያ ላይ ቀርቦ የምናየው ዳቦ የመጠኑ ማነስ ብቻ ሳይሆን የጥራት ችግርም ያለበት ነው። ገና ከተቀመጠበት አንስተን ልንቆርሰው ስንሞክር ልብሳችን ላይ ተፈርፍሮ የሚቀረውን ቤቱ ይቁጠረው።
የዳቦን ጉዳይ ‹‹የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል›› በሚለው ብሂል ብቻ መለካት የለብንም። ጉዳዩ ሀይ ባይ ካላገኘ ግላዊና ማህበራዊ ቀውስ ከመፍጠር አልፎ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ወደ መሆን መሸጋገሩ አይቀርም። ለነገሩ በዳቦ ላይ አተኮርኩኝ እንጂ በአትክልትና ፍራፍሬ ፣ በሥጋ ፣ በነዳጅ ወዘተ ያለው ቅሸባ ስር የሰደ ደና ተመሳሳይ አንድምታ ያለው ነው።
ባለፈው የኢህአዴግ መንግሥት ሌብነት እንደ አንድ የሥራ መስክ እውቅና ከተሰጠው ወዲህ ሁሉም በተሰማራበት ሥራ በአቋራጭ መክበርን እንደ ጥሩ ስልት በመያዙ ነባሩ በታማኝነት የማገልገልና እና የጨዋነት እሴታችን ፈተና ላይ ወድቆ መክረሙ የሚታወስ ነው።
አሁን ከሌብነት የጸዳ ሥርዓትን ለመፍጠር የተጀመረው ንቅናቄ በመንግሥት ተቋማት ብቻ ተወስኖ ሳይቀር ፊቱን ወደ ሚዛን ቀሻቢዎችም በፍጥነት ማዞር ቢችል ብዙኋኑን በተለይም ዝቅተኛውን የህብረተሰብ ክፍል ከስግብግብ ነጋዴዎች መታደግ ይቻላል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2015