አቶ ዲባባ ተስፋዬ ይባላሉ፡፡ በእንግሊዝ አገር ለ30 ዓመታት ኖረዋል፡፡ በወቅቱ በአገሪቱ በነበረው የፖለቲካ ሁኔታ ተሰደው እንግሊዝ አገር ሲገቡ ‹‹ለምን በአገሬ ፖለቲካ ምክንያት ተበደልኩ?›› በማለት ፖለቲካ ለማጥናት ወሰኑ፡፡ ሙሉ ጊዜያቸውን ለትምህርት በመስጠት በታሪክ፣በፍልስፍና፣በሳይኮሎጂ፣በኢኮኖሚክስ እንዲሁም በኮምፒውተር ሳይንስ በመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርታቸውን በአንድ ጊዜ ቀጠሉ፡፡ ሆኖም ጊዜው ስላልበቃቸው የኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርትን አቁመው ሌላውን ማጠናቀቅ መቻላቸውን ይናገራሉ፡፡
በመቀጠልም የዓለም አቀፍ ሁኔታን ለመረዳት ከፍ ያለ ፍላጎት ስላደረባቸው ዓለም አቀፍ ግንኙነት፣የሰብዓዊ መብት ሕግ፣ ዓለም አቀፍ ሕግ ፣ ልማታዊ ጥናት ፣ ሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን፣ የአፍሪካ ጂኦ ፖለቲካ ስትራቴጂክ፣ የሰው ሃብት ልማት፣ የሰላም እና ግጭት አወጋገድ ጨምሮ ሌሎችም የተለያዩ ዘርፎችን በመማር ምርምር ሲያደርጉ ቆዩ፡፡
ካካሔዷቸው ጥናቶች መካከል በብዛት ያከናወኗቸው በአፍሪካ የድንበር ግጭት ላይ ነው። በተለይም በኢትዮጵያ እና በሱዳን፤ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ፣ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ከድንበር ጋር ተያይዞ ባሉ ሁኔታዎች ላይ ጥናት አድርገዋል፡፡ በኢትዮጵያ ዙሪያ ብቻ ሳይሆን፣በአፍሪካም የተለያዩ አገሮች ናሚቢያ፣ ሞዛምቢክ፣ ሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ አንጎላ፣ ኮንጎ፣ላይቤሪያ እና ሴራሊዮ ብጥብጥ ባሉባቸው አገሮች በመገኘት ምክንያቱ ምንድን ነው? በማለት ሲያጠኑ ቆይተዋል፡፡
በሰላም እና ግጭት አወጋገድ ላይ የአፍሪካን ልጆች ለማሰልጠን የልህቀት ማዕከል ለማቋቋም ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በዚሁ እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ በተለይም ትልቅ ውጤት ሊገኝባቸው በሚችሉ የጥናት መንገዶችን በሚመለከት እ.አ.አ በ2019 በስምንት ዩኒቨርሲቲዎች አስተምረዋል፡፡ በሰላም ጉዳይ ላይም ለሚመለከታቸው ተቋማት የማሰልጠን ሃሳብ አላቸው። ለዛሬ የ‹‹ዘመን እንግዳ›› አድርገን ከመረጥናቸው ከአቶ ዲባባ ተስፋዬ ጋር በሀገራዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ፣ በግጭት አፈታትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርገን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በፌዴራል መንግሥት እና በሕወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት አጠቃላይ ለሃገራዊ ሰላም እና የወደፊት እድገት የሚኖረውን አንድምታ እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ዲባባ፡- መጀመሪያ የሰላምን ፅንሰ ሃሳብ መረዳት አለብን:: ሰላም ሂደት ነው:: ይሔ ሂደት እንዴት ይመጣል የሚለውን ቀድሞ መረዳት ያስፈልጋል:: ቀድሞ የሰላምን ስረ መሠረቱን መረዳት ትልቁና የመጀመሪያው ደረጃ ነው:: ሌላው ይሄን ነገር መፍታት የምንችለው እንዴት ነው? የሚለው ላይ ምልከታ ያስፈልጋል:: ተቀራርቦ ዓይን ለዓይን ተያይቶ ሳይተፋፈሩ መተማመንን መገንባት የግድ ነው:: ለመተማመን ደግሞ የምላስ ድለላ ሳይሆን ከልብ በእውነት ላይ የተመሠረተ የሚታመን በግልፅ የሚታይ እውነተኛ ግንኙነት እና ንግግር መኖር አለበት:: እነዚህ ሳይኖሩ በፍፁም መተማመን መፍጠር አይቻልም::
በየትኛውም በኩል ያሉ ተስማሚዎች ወይም ተደራዳሪዎች በራስ መተማመን ያላቸው እና ብቁ መሆን አለባቸው:: በሚያደርጉት ነገር ግልፅ አቅጣጫ እና ግብ ሊኖራቸው ይገባል:: ግልፅነት ባለው መልኩ የጋራ ግብ ማስቀመጥ ያስፈልጋል:: ስምምነቱ ግልጽነት ከሌለው እና ድብቅ ፍላጎት ካለ አይሳካም:: በመጨረሻም ሕይወት ለመቀጠል በመተማመን በሰላም እና በእርቅ ላይ መመሥረት ይሻላል ወይስ ሸፍጥ መሥራት ይሻላል? የሚለው ፍርጥርጥ ብሎ መቀመጥ አለበት:: ማንም እያባበለ እና እያታለለ የሚፈፀም ሳይሆን በግልፅ ከሰላም የምናተርፈው ነገር እነዚህ … እነዚህ… ናቸው:: በእኩልነት ላይ በጤናማ ግንኙነት ላይ የተመሠረተ ሥርዓት ብንፈጥር ይሻለናል ወይስ ትርፍ የሚመጣው ሁልጊዜ እያጋደልን እና አንዱ ሌላውን እያቋሰለ ነው? የትኛው ይበልጣል? ጥቅም እና ጉዳቱን ቁጭ ብሎ ማፍረጥረጥ ሲቻል የጋራ ግብን ማምጣት ይቻላል::
በመጨረሻ ስምምነት ከኖረ እንዴት አድርገን ይህንን ወደ ሥራ እንለውጣለን? መሬት የምናወርደው እንዴት ነው? የሚለው በደንብ መታወቅ አለበት:: መጀመሪያ በሰላም ጉዳይ፣በአገር ጉዳይ፣በየትኛውም የስምምነት ጉዳይ ላይ መተማመን ካልተፈጠረ ማንኛውም ነገር ዋጋ የለውም::
ሰላም የሚፈጠረው እና ስምምነት ላይ ተደርሶ ውጤት የሚመጣው በሶስት መንገድ መሆኑ በሙያተኞች ተቀምጧል:: አንደኛው ዝግጁነት ነው :: ይሔ ጦርነቱን የሚያባብሱ ሰዎች ሲከዱ ወይም ዞር ሲሉ፤ ከኋላ ሆነው የራሳቸው ግብ ያላቸው ምናልባትም የውጪ ጠላቶች ሊባሉ የሚችሉ እየተንከባከቡ እና እየኮተኮቱ ሰላም እንዳይኖር የሚገፋፉ ሰዎች ሲሄዱ ወደ ስምምነት ይመጣል::
ሌላው የአንደኛው ወገን ኃይል ሲያመዝን ሌላኛው ወገን እጅ ይሰጣል:: እጅ የሚሰጠው አካል ከዚህ በላይ መጋፈጥ አንችልም ሲል ለስምምነት የዝግጁነት ደረጃ ላይ ተደርሷል ማለት ይቻላል:: ወይም ጦርነቱን የሚያቀጣጥሉ ሰዎች እድሜያቸው ሲገፋ ‹‹እንዴ ! ሳንበላ ልንሞት ነው? ›› ብለው መዋጋቱን ይተውታል:: እዚህ ላይ እንደምሳሌ የደቡብ ሱዳን ነፃ አውጪ ንቅናቄን ሲመራ የነበረው ጆን ጋራንግን መጥቀስ ይቻላል::
በባለሙያዎች (መዝጋት ወይም ማቋረጥ) የሚባለው ሌላኛው ወደ ሰላም የሚመጣበት መንገድ በሁለቱም በኩል መፈናፈኛ ሲጠፋ ነው:: በሁለቱም በኩል ምንም መንቀሳቀስ ሳይቻል ሲቀር እግር ሲታሰር እና አንገት ሲታነቅ ስምምነት ላይ መድረስ የግድ ይሆናል:: እዚህ ላይ ሦስተኛ ወገንም የሚካተት ሲሆን ሦስተኛ ወገን ‹‹ዱላ እሰነዝራለሁ›› ሲል፤ ሲያፈራርም ወደ ስምምነት ይመጣል:: ሶስተኛ ወገንም ‹‹ጥቅማ ጥቅም እሰጣለሁ›› ሲል የስምምነት በር ይከፈታል:: ይህንን የሚለው ለአንዱ ወይም ለሁለቱም ሊሆን ይችላል:: ልብ መባል ያለበት ሦስተኛው ወገን በስምምነቱ ላይ የራሱ ዓላማ ይኖረዋል:: የመጨፍለቅ እና በዛ ውስጥ ትልቅ ጥቅም የማግኘት እና የማኮላሸት ዓላማ ሊኖረው ይችላል::
ስለዚህ የሦስተኛ ወገን ዓላማ ሊኖር ይችላል:: ይሔን በደንብ ለማብራራት በጣም ጊዜን የሚጠይቅ በመሆኑ በቀላሉ በትንሽ ጊዜ ለመግለፅ ያስቸግራል:: ነገር ግን እዚህ ላይ አንዳንዴ ስምምነት አድራጊዎች የሦስተኛውን ወገን ሴራ የማይረዱበት አጋጣሚም ይኖራል:: ምክንያቱም ሦስተኛ ወገኖች በአብዛኛው የሚሠሩት በተንኮላዊ ጥበብ ነው:: ቦንብ ሲፈነዳ የሚፈነዳው እና የሚበታተነው እጅ የሚቆርጠውን እና አይን የሚያጠፋውን ብረት ማሳየት አይፈቀድም:: ከመፈንዳቱ በፊት የሚታየው ተሸፋፍኖ ነው::
አዲስ ዘመን፡- ስምምነትን አስመልክቶ ጥሩ ማብራሪያ ሰጥተውኛል:: ነገር ግን በቀጥታ በፌዴራል መንግሥት እና በሕወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት በተመለከተ ሃሳብዎትን ይግለፁልኝ::
አቶ ዲባባ፡- እንዳልኩት ይሔ ስምምነት በተናገርኩት ቅደም ተከተል መሠረት በወሳኞቹ ነገሮች መተማመን ላይ ከተመሠረተ እና መተማመኑ ደግሞ በግልፅ ዓላማ ላይ የተመሠረተ ከሆነ ጥሩ ነው:: ነገር ግን ሸፍጥ እየሸረቡ ከሆነ በፍፁም የፀና ሰላም ሊኖር አይቻልም:: ለቤት ዋናው መሠረቱ ነው:: መሠረቱ ጠንካራ ካልሆነ ቤቱ ይፈርሳል ወይም ይወድቃል:: መተማመን ላይ ለመድረስ በቅድሚያ ራስን ስለማኖር ይታሰባል:: እርሱ የሚጠፋ እና ሌሎች የሚኖሩ ከሆነ በራሱ ላይ መተማመን አይችልም:: ስለዚህ ተስማሚው አካል የሚመቸው ካልሆነ የማያስተማምን ነው:: ስለዚህ አንዱ ተስማሚው አካል ታማኝ አይሆንም::
ድምዳሜው ተስማሚው አካል በሁለት እግሩ ቆሞ ዓላማ ይዞ ቢሆን በራሱ ይተማመናል፤በራሱ መወሰን ይችላል:: ነገር ግን ሦስተኛ አካል ተስፋ እየሰጠው እና እያማለለው ከሆነ የማይቀረው ነገር መምጣቱ አይቀርም:: በአብዛኛው በኩል ያለው ተደራዳሪ በራሱ ፅኑ እምነት ላይ ተመሥርቶ ድርድር አድርጓል የሚል እምነት የለኝም:: ምናልባትም ሶስተኛ ወገን ወደ መንግሥት አድልቷል ብሎ በማሰብ ወደ ስምምነቱ መጥተው ሊሆን ይችላል:: ነገር ግን ምንም ቢሆን ምድሪቷን እና የራሱን ሕዝብ ሲዖል እናድርግ ብሎ የሚነሳ ከሆነ አተገባበሩም ችግር ነው::
አዲስ ዘመን፡- ምናልባትም ብዙዎች እንደሚገልፁት የፌዴራል መንግሥት አሸናፊነት በማየሉ ወደ ስምምነት ተመጥቷል ብለው ያስባሉ?
አቶ ዲባባ፡– አዎ! አንዱ ኃያል ሲሆን፤ ሌላው አንወጣውም ብሎ ሲያስብ ለስምምነት ዝግጁ መሆን ይኖራል::
አዲስ ዘመን፡- በየትኛውም መንገድ ቢሆን የሰላም ስምምነት ላይ ተደርሷል:: ይሄ የሰላም ስምምነት ለሃገራዊ ሰላም እና የወደፊት እድገት የሚኖረው አንድምታ ምንድን ነው?
አቶ ዲባባ፡- ጦርነት ለማድረግ ተስፋ መቁረጥ ተፈጥሮ ከሆነ እና ሁላችንም ከምናልቅ ብለው ሰላምን እንደመጨረሻ አማራጭ ወስደው ከሆነ የሚሳካበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል:: ምናልባትም መንግሥት የሚሔድበት ትልቅ ጥበባዊ መንገድ ሰላም ያመጣ ይሆናል::
አዲስ ዘመን፡- በትክክል ወደ ፊት ሰላም ይፈጠራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን:: ሰላም ሲኖር በተለይ አሁን በተለያየ ሁኔታ ለተጎዳው ኢኮኖሚ የሰላም መምጣት የሚኖረው ጠቀሜታ ምንድን ነው?
አቶ ዲባባ፡- ስለኢኮኖሚ ከተነሳ የመጀመሪያው እና ዋነኛው ጉዳይ ኢኮኖሚን የሚያሳድገው ነፃነት ነው:: ብዙ ሰው ኢኮኖሚውን የሚያሳድገው እርዳታ ወይም ኢንዱስትሪ ነው ይላል:: ነገር ግን ኢኮኖሚውን የሚያሳድገው በዋናነት ነፃነት ነው:: አንድ ሰው ሠርቶ የማይዘረፍበት ሥርዓት መኖር አለበት:: ድሮ ቆይቷል አያቴ ሱዳን እና ሶማሊያ ድረስ ለፍቶ ነግዶ ኬኒያም ሔዶ ሠርቶ ዘረፉት::
ሃብት የሚያመጣ በጣም ብዙ ሰው ቀጥሮ የሚያሠራበትን ሥርዓት ከአንገቱ ቆረጡት:: አያቴ ብቻ ሳይሆን ቀጥሮ የሚያሠራቸውም ብዙ ነገር አጡ:: ነፃነት ሲኖር ሰው የሚበረታታበት ሁኔታ ይፈጠራል:: ሰው ጥበቃ እና ደህንነት ይኖረዋል:: ያገኘውን ቆፍሮ መደበቅ ወይም ትራስ ውስጥ ማስቀመጡን ትቶ ወደ ሥራ ይገባል:: ጦርነት የአገር ኢኮኖሚን እንደሚጎዳ አጠያያቂ አይደለም:: ጦርነት ሲኖር ለሌብነትም ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል:: በመጥፎ አጋጣሚው ብዙኃን ሲያጡ አንዳንዱ በዘረፋ ይከብራል::
አዲስ ዘመን፡- አሁን ዘላቂ ሰላም እየመጣ ነው ብለን ተስፋ እናድርግ?
አቶ ዲባባ፡- ሰላም በተስፋ ብቻ አይመጣም:: ጥበብን ይጠይቃል:: ሰላም እና ኢኮኖሚ ከተባለ በኢትዮጵያ አካውንት ውስጥ እስከ አሁን ያወጣነው እና ያገኘነው (debit and credit) ቢሰላ በጥሬ ገንዘብ አይደለም ፤ በሌላ በኩል ክምችቱ ሀገርን የሚያጠነክር ነው ወይስ ሀገርን እና ትውልድን የሚበላ ነው? የሚለው መጠየቅ አለበት:: ኢትዮጵያ ለዘመናት ምን ስታከማች ኖረች? ፍዳና መከራ ወይስ ነፃነት፣ብልጽግና እና ዕድገት አሁን ያለው ነገር ምንድን ነው? የሚለው መፈተሽ አለበት::
ሰላም የሚኖረው በጥበብ እና በድርጊት ነው:: ሰላም በጠመንጃ እና በድሮን ሳይሆን በጥበብ የሚመጣ ነው:: ጥበብ ከሌለ ሰላም ሰፍኖ ኢኮኖሚን ማሳደግ አይቻልም:: ፍዳው ማቆሚያ አይኖረውም:: ለመኖር ማድረግ ነው፤ለማድረግ ደግሞ መወሰን ያስፈልጋል:: የሚወሰነው ብቃት እና ጥበብ ላይ ተመሥርቶ ነው:: እያንዳንዱ መረጃ በትክክል ቀርቦ፣ ተተንትኖ ፣ተበጥሮ ሲከናወን ውጤቱ ጥሩ መሆኑ አይቀርም:: ነገር ግን በሌላ ሰው ጭንቅላት ላይ ተመሥርተን የምናደርገው ከሆነ በተከታታይነት ፍዳው ይቀጥላል::
የሚወስነው ማን ነው? የመወሰንስ ብቃት አለ? ለመኖር ወስኖ ማድረግ የግድ ነው:: ነገር ግን ለማድረግ ስንወስን ውሳኔያችን ምን ላይ ተመሠረተ የሚል ጥያቄ ይነሳል:: ሰው በቀን መቶ ሲጋራ እያጨሰ ጨጓራዬን ታመምኩ ቢል ዋጋ የለውም:: ውሳኔና ድርጊት መገናኘት አለበት:: ላለመታመም እየወሰነ ሲጋራ ማጨስ ካላቆመ ችግር ነው:: በአብዛኛው አፍሪካ ላይ ያለው ተመሳሳይ ነው::
ኢኮኖሚ ሲባል ተለይቶ ግብርናው ላይ ጥልቅ ትንተና አድርጎ በደንብ ፈትሾ፣ ወቅጦ በወንፊት አሳልፎ ለዳቦና ለኬክ የሚሆን ዱቄት ለማግኘት ጭንቅላት ያስፈልጋል:: የድሃ ቤት እየተቃጠለ፤ ሕፃን ልጅ አንገቱ እየተቀላ ማድበስበስ አይቻልም:: ሁሉንም ፍርጥርጥ አድርጎ በግልጽ መነጋገር ያስፈልጋል:: አስፈፃሚውም የአገሪቷን ክምችት በግልፅ እስከ አሁን ያለው ይሔ ነው ብለው ማሳወቅ አለባቸው:: አገር በምኞት አትለወጥም::
በሰሜን ያለው ጦርነት ቢቆምም በሌላ ቦታም ሰላም ያሳጣ እንቅልፍ የነሳ ችግር አለ:: ኢትዮጵያን የማይወዷት ትልልቅ ጎጆ ያላቸው የኢትዮጵያ ጠላቶች በኢትዮጵያ ብዙ ቢሊዮን እያወጡ ትንንሽ ጎጆ ሠርተዋል:: ኢትዮጵያን ለማጥፋት የመደቡትን ገንዘብ ኢትዮጵያ እንድታድግ ግብርናው እንዲደገፍበት ቢያደርጉ ከተተከለው ዛፍ ጣውላ ከተገኘው የግብርና ምርት ርካሽ ምግብ ያገኙ ነበር:: ሕዝብ ተርቦ እንዲተላለቅ ከማድረግ ይልቅ ሕዝብ በልቶ እንዲጠግብ ቢያደርጉ ሰዎች ስለግጭት ከማሰብ ይልቅ ወደ ፈጠራ በመሄድ ለሁሉም የሚበጅ መልካም ነገር ይገኝ ነበር:: አሁን ግን የኢኮኖሚው ችግር የሰውን ጭንቅላት ሳይቀር አደህይቶታል:: ስለዚህ ሽሮ ለመብላት ብሎ ያምታታል፤ ያጭበረብራል::
ዋናው ነገር ሰላም የሚመጣው በውሳኔ እና በድርጊት ነው:: እኔ ከጎረቤቴ ጋር ችግር መፍጠርም ሆነ በሰላም መኖር እችላለሁ:: ሥራዬ ብዬ ለ24 ሰዓት ቤቴን የሚነቀንቅ የሙዚቃ ድምፅ ብከፍት ጎረቤት ዝም አይልም:: ግጭት ውስጥ ይገባል:: በተቃራኒው ሙዚቃ መክፈት ቀርቶ ቀን ሳይቀር በር ስከፍትና ስዘጋ ተኝተው ይሆናል ብዬ ከተጠነቀቅኩ በሰላም መኖር ይቻላል:: በግልፅ መነጋገር እንጂ መደባበቅ አያዋጣም::
ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካ ሀገራት በሙሉ ውዝፍ ዕዳ አለባቸው:: ይሔንን ውዝፍ ዕዳ በግልጽ መግለጽ እችላለሁ:: ደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ፣ ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ፣ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ፣ ጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ አምቦ ዩኒቨርሲቲ እና ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ለማስተማር ሄጃለሁ:: ሃዋሳ፣ ጂንካ እና እንጂባራ ዩኒቨርሲቲዎች ተጠርቼ ነበር:: መቀሌ ሳይቀር ልሔድ ነበር:: በ2009 ዓ.ም የተማሪ ብጥብጥ ስለነበረ እንጂ ወደ ሃያ ዩኒቨርሲቲዎች ለመሔድ አቅጄ ነበር:: በየዩኒቨርሲቲዎቹ የሔድኩት የትምህርት አመራር ለማስተማር እና ለምክር ብቻ ሳይሆን የችግሩን መንስኤ ለማወቅ ነበር::
የትምህርትን አመራር (academic leadership) እንዲሁ እንደተራ ነገር የሚታይ አይደለም:: ትልቅ ነገር ነው:: ጥበባዊ ሞኒተር እና ግምገማ ወይም ምዘና መኖር አለበት:: ኢትዮጵያ ውስጥ ምዘና እና ግምገማ የሚባል ነገር የለም:: እንግሊዝ ውስጥ ከፍተኛ ዋጋ በመክፈል ተቋማት ይመዘናሉ:: መዛኙ ተቋሙን በዚህ በዚህ ቦታ እየተጎዳችሁ ነው:: በዚህ በኩል ደግሞ እያተረፋችሁ ነው ተብሎ ያስቀመጥላቸዋል::
የማኅበራዊ ምዘና (social evaluation) ላይም ትምህርት ይሰጣል:: በአደባባይ ጦርነት ስላለ ብቻ አይደለም:: ዱርዬ እንደፈለገ የሚያደርግ ከሆነና ዝርፊያ ካለ ሰላም አለ አይባልም:: ያው ስጋት አለ:: ሰላም የለም:: ጠመንጃና መድፍ አይተኮስም እንጂ ሰላም የለም:: ለምሳሌ ብራዚል ውስጥ በግልፅ ጦርነት የለም:: ነገር ግን ከጦርነት የበለጠ በጣም የሚያስፈሩ ቦታዎች አሉ:: እንደውም በመግደል ማዕረግ ይጨመራል:: አንድ ዱርዬ የገደለ ፖሊስ ማዕረጉ ያድጋል:: ሪዲዮጄኔሮ ብዙ ጦርነት እንዳለ እዛው ከሚኖሩ ሰዎች ሰምቻለሁ:: ባንግላዴሽም በተመሳሳይ መልኩ ጦርነት የለም ነገር ግን ሰላም ነው ማለት አይቻልም::
በትክክል ሰላም ከሆነ ውጤቱ በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም:: ነገር ግን እውነተኛ ሰላም እንዲመጣ መተማመን ያስፈልጋል:: በጣም ግልፅ መሆን የግድ ነው:: በድብቅ በብብት ሳንጃ ተይዞ ከሆነ አስተማማኝ ሰላም ይኖራል ብሎ ማሰብ ይከብዳል:: አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ተዓምር ሊሠራ የሚችል ጥበብ ያስፈልጋል:: ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ከየትኛውም አካል ከዓለም ባንክም ሆነ ከየትኛውም እርዳታ እና ብድር ሰጪ አገር ምንም ዓይነት ገንዘብ ቢገኝ ኢኮኖሚውን ማሳደግ አይቻልም:: በተቦደሰ እንስራ ውሃ ቀድቶ ልጆች ለማጠጣት ማሰብ ትልቅ ስህተት ነው:: እርዳታ ሰጪ ሀገራትን ማመን አይገባም ::
አዲስ ዘመን፡- ጦርነት እና ሰላም እንዲሁም ደህንነት አለመኖሩ ስነልቦና ላይ የሚያስከትለው ቁስል እንደሚኖር አያጠያይቅም:: በዚህስ በኩል ምን መሠራት አለበት ይላሉ?
አቶ ዲባባ፡– በአማራ ክልል የአማራ ተቆርቋሪ መስሎ ሕዝብን መከራ የሚሳይ፤ በኦሮሚያ ክልልም ለኦሮሞ ተቆርቋሪ መስሎ መከራ የሚያሳይ እየዞረ የሰው ሚስት የሚቀማ እና የሚደፍር ፤የሰው ከብት የሚሰርቅ ይሔ ሁሉ አደብ መያዝ አለበት:: ግልፅ ጦርነት ብቻ ሳይሆን የደህንነት ችግርም ሥነልቦናን ይጎዳል:: ቢያንስ የሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎቶቹ ቢሟሉ ትልቅ ነገር ነው:: ምግብ አግኝቶ፣ ቢያንስ ውሃ ጠጥቶ ትንሽ ሕይወት እንዲዘራ መደረግ አለበት:: ቀጣይ ነገሮችን እናንሳ ካልን ከባድ ነው:: በመሠረታዊነት የቸገረን ነገር አለ::
አዲስ ዘመን፡- በአገራችን ጉዳይ ላይ ያገባናል ብለው የሚያምኑ በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ የሚኖሩ የተማሩ ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያ ሰላም እና ዕድገት ጋር ተያይዞ ምን ማድረግ አለባቸው ይላሉ?
አቶ ዲባባ፡– ስለሀገር አስተዳደር ሲፈተሽ በሰለጠነው ዓለም ከመንግሥት ባለስልጣናት አጠገብ እሳት የበሉ አማካሪዎች አሏቸው:: አማካሪዎቹ መሥሪያ ቤት ውስጥ ቁጭ አይሉም:: በሚያስፈልገው መጠን ባለስልጣኑን ያጎርሱታል:: አንድ የመሥሪያ ቤት ባለስልጣን እንዴት መሥሪያ ቤቱን መንከባከብ እንዳለበት እየፈተፈቱ ያጎርሱታል:: ምሑራኖችን በአማካሪነት የሚጋብዝ ሥርዓት መኖር አለበት:: በትምህርት ዘርፍ ብቁ ሲሆን፤ የትምህርት ሥርዓቱን የሚያግዝበት ሁኔታ መኖር አለበት:: ይሔ ስለአንድ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚው ዘርፍም ሆነ በሰላምና ደህንነት ጉዳይ ላይ ጥበበኞች ጥበባቸውን እንዲያመጡ ምቹ ሁኔታ መፈጠር አለበት::
እያንዳንዱ ፖለቲከኛ ሁሉንም ነገር እንዲያውቅ አይጠበቅም:: የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጁኒየር ጆርጅ ቡሽ ከስድስት ሺ በላይ አማካሪዎች ነበሩት:: ስድስት ሺ ሰው ተሰልፎ ፕሬዚዳንቱን አያገኘውም:: ነገር ግን በመጠን በመጠን እየተቀመመ ይሰጠዋል:: በኢትዮጵያ ስንት ቀማሚ አለ የሚለው ያጠያይቃል:: ለኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያውያን አርግዘው ለምን አይወልዱም? በዕውቀት እና በሳይንስ ላይ ብቁ ሆኖ ችግር የሚፈታ ካልተፈጠረ በዝምድና ሰዎች ተኮልኩለው ችግር ይፈታሉ የሚል እምነት የለኝም:: ከዚህ በፊትም የተደረገ ነገር የለም:: ምን ያድርጉ አይደለም እንዴት ያድርጉ የሚለው መጥራት አለበት::
የሰው ልጅ የሚኖረው በመዋጮ ነው:: በሀገር ሰው ሲኖር ለአገር መዋጮ ያስፈልጋል:: ለኢትዮጵያ መዋጮ ያስፈልጋል:: አንዱ ከሌላው ላይ ተዋጥቶለት ይኖራል:: የምሑራን ብቻ ሳይሆን ሁሉም ለአገሩ ማዋጣት አለበት:: ጥበበኛ በጥበቡ፤ ጉልበት ያለው በጉልበቱ ሁሉም በየዘርፉ እያዋጣ ይኖራል:: ጽዳት ሠራተኛው በአንድ በኩል ሲሮጥ፤ ሌላኛው እሳት አጥፊው እሳት ለማጥፋት ይሮጣል:: ምግብ ሠራተኛው ምግብ ለመሥራት ይሯሯጣል:: ሁሉም እያዋጣ የተሳለጠ ኑሮን ይኖራል::
ነገር ግን ሁለት ነገሮች መረሳት የለባቸውም:: አንደኛው አንድ አገር ጀግናዋን በጣም መንከባከብ አለባት:: ሁለተኛ ዶሮ ጫጩቶቿን እንደምትጠብቅና እንደምትንከባከበው ሁሉ ሀገርም ጥበበኞቿን ከጥቃት መጠበቅ አለባት:: ጥበበኞቿ የሚገደሉ እና የሚታሰሩ ከሆነ ሁልጊዜ አገር የምትኖረው በኪሳራ ነው:: ጥበበኞችን ከሌሎች አገሮች መበደር አይቻልም::
የኢትዮጵያ ችግር መፍትሔ መፍለቅ ያለበት ከውስጥ ሐሞት ሊሆን ይገባል:: ከእኔ አዕምሮ፣ ከእኔ ልብ፣ ከእኔ አጥንት ፈሳሽ ወጥቶ መቅኔዬ መረቅ ሆኖ ትውልድ ጠጥቶ አገሩን የሚያጠናክር መሆን አለበት:: ይሔንን ኢትዮጵያ ከገበያ ሔዳ በደላላ የምትገዛው ጉዳይ አይደለም:: ለእንግሊዝ አገር የደሙላት ከሐሞታቸው መፍትሔ ያፈለቁላት ዜጎች አሏት:: ለፈረንሳይም እንደዛው:: ለተለያዩ አገሮች ሐሞታቸውን ያፈሰሱላቸው ዜጎች አሏቸው:: ወደኋላ በመሔድ የዘመናትን ታሪክ አጥንቻለሁ::
ታሪክ ስፈትሽ ሀገርን ታላቅ የሚያደርገው የሀገሬው ሰው ነው:: ፍቅር መኖር አለበት:: ፍቅር ያለው ሰው ወገኑን እና አገሩን አይጎዳም:: ምድሩን አያዋርድም:: ፍቅር ምን እንደሆነ የማያውቅ የአውሬ መንፈስ ያለበት እንጂ ሕዝቤን ምድሬን እወዳለሁ የሚል በፍፁም ይደማላታል፤ ያለውን ይሰጣታል:: አይበድላትም::
አፍሪካ የተቸገረችው ፈጣሪ አሳንሷት ሳይሆን ልጆቿ መንፈስ ሆነውባት ነው:: በዛ ላይ ነጮች ቁማር የሚጫወቱባቸው ሆኖ ነው:: እከሌ የሚባል የውጪ ካምፓኒ ይህን ያህል አተረፈ ይባላል:: ወርቅና እንቁ እያዘረፉ ዱቄት የሚለምኑ የአፍሪካ ሀገራት አሉ:: በዚህ ላይ ትውልድ መንቃት አለበት:: ለምን አሁንም ከሞፈር እና ቀንበር መላቀቅ አቃተን የሚለው መታየት አለብን:: የእኛ አገር ድሃ ናት መባል የለበትም:: ኢትዮጵያ ድሃ አይደለችም:: ችግሩ በኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በንጉሥ ፋሲለደስ ጊዜ ሳይቀር ለጥበበኛ ቦታ እንደማይሰጥ ፈላስፋው ዘርያዕቆብ የፃፈው መጽሐፍ አለ::
ኢትዮጵያን ትተን በሱዳን መሬት ብቻ መጠቀም ቢቻል አፍሪካን መመገብ ይቻል ነበር:: ነገር ግን ሱዳን በየቀኑ እየተበጣጠሰች አንድ ነበረች ወደ ሁለት ተካፍላለች:: አንዱ ጄኔራል በአደባባይ የበለጠ ዶላር ለሚሰጠን እንታዘዛለን ብሏል:: ይሔንን ለማመን ይከብዳል:: ከእንደዚህ አይነት ሁኔታ መላው ኢትዮጵያውያን መውጣት አለባቸው::
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ::
አቶ ዲባባ፡- እኔም አመሰግናለሁ::
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/20215