ስኳር በአሁኑ ወቅት አንገብጋቢ ከሚባልበት የሰው ልጅ ፍላጎት ላይ ደርሷል፡፡የስኳር አቅርቦትና ፍላጎቱ ባለመጣጣሙም እጥረቱ ጎልቶ ዋጋውም አሻቅቦ ይገኛል። ‹‹በመጋዘን የስኳር ክምችት የለም›› የሚባልበት ደረጃም ተደርሷል። ለመሆኑ ይህ ችግር እንዴት ተከሰተ? አሁናዊ ችግሮችና ቀጣይ የተስፋ ጭላንጭሎች ምንድን ናቸው? ስንል የዝግጅት ክፍላችን ከኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የኮርፖሬት ጉዳዮች ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ከአቶ ዘመድኩን ተክሌ ጋር ቆይታ አድርጓል- መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የቀድሞ ስሙ ‹‹ስኳር ኮርፖሬሽን›› ነው።የተቀየረው ስሙ ወይስ ግብሩና ተልዕኮው ጭምር ነው?
አቶ ዘመድኩን፡- ከስያሜ ለውጡ ጋር የሚነገር ምንም ነገር የለውም።ዱሮ ስኳር ኮርፖሬሽን በሚባል ጊዜ ስኳር ላይ የሚሰሩትን ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶችን በሙሉ ይዞ ይሄድ ነበር።ስኳር ኮርፖሬሽን ቢባል ያን ያህል ለውጥ የሚያመጣ አልነበረም። ግን ስም አንዳንዴ ጊዜ የሚፈለገውን ስኬት ያላመጣ ከሆነ አብሮ መለወጥ ጥሩ ነው ስለሚባልና በዚህ ዕምነት ነው። ስኳር ኮርፖሬሽን በጣም ትልልቅ ሥራዎችን ሰርቷል፤ ግን የሚፈለገውን ያህል ውጤት የተገኘበት አይደለም። ውጤት የተገኘበት ባለመሆኑም እሱንም ጭምር ለመቀየር ነው።ተቋማት ተልዕኮ ሲለውጡ ስማቸውንም አብረው ስለሚለውጡ ከዚህ ጋር አያይዞ ማየት ጥሩ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ብዙ ህፀፆች የነበሩበት ተቋም በመሆኑ ሪፎርም ማድረጉ ይታወቃል።አሁን ምን ለውጥ ተገኘ?
አቶ ዘመድኩን፡- ስኳር ኮርፖሬሽን በ2003 ዓ.ም ሲቋቋም የሀገራችን የመጀመሪው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በሚል ሁላችንም እንደምናስታውሰው በጣም ሰፋፊ ስራዎች ታቅደው የተጀመሩበት ጊዜ ነው።በአንድ በኩል ፈጥኖ ለማደግ ካለ ፍላጎት የመነጨ በጎ አስተሳሳብ ነው ተብሎ ሊወሰድ ይችላል።በሌላ በኩል ደግሞ አቅምን በማገናዘብ በኩል የተሟላ ጥናት አድርጎ የሥራዎችን ባህሪ በመለየት ወደ ሥራ በመግባት ረገድ ጉድለቶች ነበሩት።ከዚያ ጋር ተያይዞ ኢንዱስትሪው ላይ ከበድ ያለ ጉዳት ያደረሱ ውሳኔዎችና ጅምር ስራዎች ተሰርተዋል።ምንም እንኳን በአንድ ጊዜ ሰፋ ያሉ ስራዎችን በመስራትና በማቀድ ለውጥ ለማምጣት የተገኙ ጥሩ ነገሮችና ብዙ ልንሰራ እንደምንችል የታዩባቸው ውጤቶች ያሉ ቢሆንም፤ የስኳር ፋብሪካ በባህሪው እና ስራው በጣም ውስብስብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ዘለግ ያለ ጥናት የሚፈልግ ነው፡፡
ትልቅ ኢንቨስትመንትና የተሟላ የሠው ኃይል የሚፈልግ ቢሆንም እነዚህ ባልተሟሉበት ሁኔታ በመላ ሀገሪቱ በሚባል ደረጃ በጥድፊያ በጣም ብዙ ሥራዎች ተጀምረዋል፤ ይህ እንዳሰብነው ውጤታማ ሊያደርገን አልቻለም።የሥራውን አዋጭነት፣ ስፋት፣ ለሥራው የሚስፈልገውን ግብዓት፣ ፋይናንስ፣ የሰው ኃይልና የመሳሰሉትን በደንብ አላየንም፤ በደንብ አላዘጋጀንም።በፍላጎትና በጥድፊያ የተገባበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በሀገሪቱ ላይ በጣም ትልቅ ኪሳራ አድርሷል፡፡
የስኳር ልማት የተጀመረው በመላ ሀገሪቱ በሚባል ደረጃ ነው። በአንድ በኩል የልማት ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ የሚል እሳቤም ከበስተኋላው ነበረው።የልማት ፍትሃዊነትን ማረጋገጥ ቢሆን በራሱ አውድ በደንብ መታየት የነበረበት ነገር ነው።ስኳር አዋጭ በሆነ ቦታ ስኳር፤ ሌላ ነገር በሚያወጣበት ቦታ ደግሞ ሌላ ነገር እያደረጉ ነው አካባቢን የበለጠ ውጤታማ የሚያደርገው። ይሁንና የልማት ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ ስኳር ያን ያህል አዋጭ ላይሆን ይችላል። መሠረታዊ የሚባሉት አየሩ፤ ውሃው፣ አፈሩና የመሳሰሉትን ታይተዋል።ነገር ግን ከዚህም በላይ ስኳር ልማት ላይ በደንብ መታየት የነበረባቸው ነገሮች አልታዩም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በደንብ መታየት የነበረባቸው ያልታዩት ምንድን ናቸው? አሁንስ እልባት አግኝተዋል?
አቶ ዘመድኩን፡- ዋና ዋና ችግሮቹ አንደኛው የአዋጭነት ጥናት ነው። ስኳርን ለሚያክል ትልቅ ፕሮጀክት ቀርቶ ለትንንሽ ፕሮጀክቶችም እንደቢዝነስ ሲታዩ አዋጭነታቸው መታየት አለበት።የሚሠራበት ፋይናንስ፣ የሚገኘው ምርት፣ የሚጠናቀቅበት ጊዜ እንዲሁም ገንዘብ መመለስ የሚጀምረው መቼ ነው የሚለውና የመሳሰሉት በደንብ መታየት ነበረባቸው። እዚህ ላይ የአዋጭነት ጥናት በደንብ አልታየም።በጥቅሉ ኢትዮጵያ ለአገዳ ልማት ሊውል የሚችል ተስማሚ አፈር፣ ውሃና አየር አላት ከሚል ጥቅል መነሻ የተነሳ ነው።ይህ ጥቅል መነሻ ጥሩ ቢሆንም በጣም በዝርዝር ኢኮኖሚያዊ ገጽታው በሚገባ መፈተሽ ይገባል።ስለዚህ ጥልቅ ጥናት አለመደረጉ አንደኛው ችግር ነው፡፡
ሁለተኛው የስኳር ልማት በጣም ሰፊ ነው።እንደ እኛ ሀገር ስኳር ኢንዱስትሪን ሙሉ አሟልቶ አንድ ላይ የሚሠራ ሀገር የለም።በሌላ ሀገር ብንሄድ ‹‹ሚለርስ›› ይባላሉ፤ ፋብሪካውን ነው የሚይዙት።መስኖ በሌላ አካል ይሰራል።ውሃ አቅራቢ ሌላ ሊሆን ይችላል። በእኛ ሀገር መሰረት ልማት፣ መስኖ፣ ፋብሪካ መገንባትና የመሳሰሉትን ትልልቅ ሥራዎችን በሙሉ በአንድ ተቋም ነው እንዲሠራ የተደረገው።እነዚህ ዝግጅት ይፈልጉ ነበር። ሌላው ቀርቶ በቂ ፋይናንስ እና ግምት አልተወሰደም ነበር።መደጋገም አሰልቺ ይሆናል እንጂ፤ የሀገር ውስጥን አቅም ማሳደግ በሚል እሳቤ ስራውን ለመሥራት የሄድንበት መንገድም ችግር ነበረበት።ለምሳሌ ‹‹ሜቴክ›› የሀገር ውስጥ ኮንትራክተር ሆኖ ብዙ ሥራዎችን በአንድ ጊዜ ጠቅልሎ የያዘበት ሁኔታ መስሪያ ቤቱንም ሀገሪቱንም ጎድቷል።
አዲስ ዘመን፡- አሁንስ አጠቃላይ ኪሳራው ታይቷል?
አቶ ዘመድኩን፡- የሆነው ነገር ተራ የባለሙያ ስህተት አይደለም። በባለሙያ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካሊ የተመራ ሥራ ነው። በመንግስትና በፖሊሲ አቅጣጫ የተመራ ሥራ ነው። ከዚህ አኳያ ያለፍንበት ሁኔታ መልሰን ብንደጋግመው ያሰለቻል፡፡
ልማቶች ይመሩበት የነበረው መንገድ ሙያውን በጣም የጨቆነ፤ የሙያ ሥራ ብዙ የማይሰማበት የፖሊሲ አቅጣጫው ገፍቶ የሚሄድበት ሁኔታ ነበር። ይህ አይሆንም ሲባል የሚሰማ አልነበረም፤ እንዲያውም እንደ አደናቃፊ የሚታይበት ሁኔታ ነበር።ለምሳሌ የስኳር ፋብሪካ በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ውስጥ አይጠናቀቅም።ግን በዚህ ላይ የሚሰጥ ሙያዊ አስተያየት እንደ አደናቃፊ ይታይ ነበር።እነዚህን የመሳሰሉት ከባድ ነገሮች ነበሩ።እንደ ሀገር፣ ዜጋ፣ ተቋም ከ2007 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ ነገሮች አለመሳካታቸው ሲታይ በተወሰነ ደረጃ ይህ ነገር አይሆንም መስተካከል አለበት በሚል በመስሪያቤታችን በኩልም ግፊት መደረግ ተጀመረ።
ሜቴክ ይመራና ይሰራ የነበረውን ሁኔታ እናውቀዋለን። በ2008 ዓ.ም ደግሞ ይህ ነገር ገፍቶ ቆመ። ለተሰራው የሥራ ክፍያዎችን መፈፀም የማቆም እና የመሳሰሉት ነገሮች ውስጥ መስሪያቤታችን ገባ።ስለሆነም የመጀመሪው ማስተካከያ እርምጃዎች ችግሩ ያስከተለው ጉዳት በጣም ሰፊ እንደሆነና በአጭር ጊዜ መመለስ እንደማይቻል በዝርዝር ታይቶ፤ ወደፊት በሚስተካከልበት ሁኔታ ነው ወደ ስራ የተገባው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በስኳር ልማት ስኬታማነት ጎን ለጎን የመንገድ፣ ትምህርት ቤት፣ የጤና ተቋማት መስፋፋት ያመጣል በሚል ሕብረሰቡ ተስፋ ነበረው።ይህ ባለመሆኑ የደረሰው የሥነ-ልቦና ጫና፣ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ኪሣራ ጥርት ብሎ ይታወቃል?
አቶ ዘመድኩን፡- በቢሊዮን የሚቆጠር ኪሳራ ደርሷል። አሁን ዓመታትን አስቆጥረን ጉዳቱን ለመርሳት እየሞከርን ነው። ሕብረተሰቡም ዘንድ የተፈጠረው ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ቀላል አይደለም።የመንግስት የልማት ፕሮጀክቶችን በወቅቱ ይጠናቀቃሉ ወይ ብሎ ያለማመን ችግር አስከትሏል፡፡
መሬቱን የለቀቀ፣ ሥራ ዕድል ለማግኘት ያሰበና ይህ ሳይሆን ሲቀር የሚፈጠረውን ችግር በቀላሉ የሚገመት አይደለም።ከዚህም በላይ እንደ ሀገር ያጣነው ሃብት ቀላል አይደለም። ሠርተን ልናመጣ የምንችለው ሃብት መቅረቱ ብቻ ሳይሆን፤ ያባከንነው ሃብት በጣም ብዙ ነው። ፋብሪካ ይደርሳል ብለን አገዳ ተክለን ቆርጠን አስወግደናል።ፋብሪካ በደረሰበት አገዳ መድረስ አቅቶት፤ አገዳ በደረሰበት ደግሞ ፋብሪካ አልደርስ ብሏል። ምክንያቱ ደግሞ በተናጠል ሁሉም እየሮጠ፣ ብክነት እያስከተለ የሄደበት ሁኔታ አለ።ይህ ስኳር ላይ ብቻ ሳይሆን ብዙ ቦታ ላይ አጋጥሟል።በመሆኑም በኢኮኖሚው፤ በማህበራዊ እና በመሳሰሉት ነገር የደረሰው ጉዳት በቀላሉ የሚገመት አይደለም።እነዚህን ነገሮች ደምረን ስንመለከታቸው የማስተካከል ሥራዎች በምን ላይ ያተኮሩ ናቸው ወደሚለው ይወስደናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአሁናዊ የማስተካከያ እርምጃዎች ምን ያህል ውጤታማ ሆናችሁ?
አቶ ዘመድኩን፡- በተለይ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በስፋት ሥንሠራ የነበረውና በኋላም ተጠናክረው የቀጠሉ አሉ። አንደኛው ፕሮጀክቶችን በህግና ፕሮጀክቶች በሚመሩበት አቅጣጫ መምራት የሚል ነው።በጣም ትልቁና እዚህ ቤት ያስፈልግ የነበረው አካል ፕሮጀክቶች በሚመሩበት ህጋዊ አግባብ መምራት ነው።መጀመሪያ ለማተስካከል የሞከርነው ይህንን ነው።ከዚህ በፊት ላልተሰራ ሥራ ክፍያ ይፈፀም ነበር።አሁን ኮንትራክተር፤ ደንበኛ፣ አሰሪ እና አማካሪ ሦስቱ ተቀናጀተው ነው ሥራ የሚሰሩት።ቀደም ብሎ ግን ይህ አልነበረም።ስለዚህ የኮንትራት አስተዳደር ህግን መተግበር የመጀመሪ ሥራችን ነበር፡፡
ሁለተኛው ስራችን የነበረው ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ኢንዱስትሪን በጣም የጎዳው ባለሙያዎች ከተቋሙ ተገፍተው እንዲወጡ ተደርገው ነበር።ሙያውን የማያውቁ ሰዎች ይመሩት ነበር።ይህን ወደባለሙዎች የመመለስ ሥራ ተከናውኗል።ሦስተኛው ፋብሪካ እና የአገዳ ልማትን የማጣጣም ሲሆን፤ በዚህ ላይ ትልቅ ጉድለት ነበር።ፋብሪካ በትክክል የሚደርስበት ጊዜ ተረድቶ፤ በዘርፉ ላይ እውቀት ያላቸውን ባለሙያዎች ወደ ሥራ አስገብቶ አገዳ ልማቱንም አብሮ የማስኬድ ሙከራ የተደረገበት የለውጥ ስራ ነው፡፡
አራተኛው ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ወደኋላ የቀሩ ፋብሪካዎችን ማጠናቀቅ ነው፤ በዚህም ትልቅ ለውጥ ተገኝቶበታል።ለምሳሌ በለስ ስኳር ፋብሪካ ለብዙ ዓመታት መቆሙ ብቻ ሳይሆን መጨረሻው ምን ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ነበር። በለስ በጀቱ የተያዘው ሜቴክ ሲገነባ በነበረ ጊዜ ነው። በጀቱ በሙሉ ግን ሥራው ሳይሠራ ተከፍሎ አልቋል። በዚህም የተነሳ በምን በጀት ማን ሰርቶ ይጨርሰዋል፤ እንዴትስ ይሰራል በሚል ትልቅ ችግር ነበር። ኦሞ አካባቢም ተጀምረው የነበሩና ያላለቁ ፋብሪካዎችን በተለየ ውሳኔና የመንግስት የቅርብ ክትትል ተጠናቀው ሥራ እንዲጀምሩ የተደረገበት ሁኔታ በጣም በትልቁና በለውጡ ሂደት ከተሳኩ ነገሮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የተቋሙ የፋይናንስ አሰራርም የራሱ ችግር ነበረበት። ለብዙ ዓመታት ሂሳብ እንደ ተቋም ተጠቃሎ አልተዘጋም። እዚህ ቤት የሚንቀሳቀሰው ገንዘብ በጣም ትልቅ ነው።እንደ ተቋም በየፕሮጀክቶቹና ፋብሪካዎቹ የገባው ገንዘብ ተጠቃሎ ከመዝጋት አኳያ ችግር ነበረበት። ይህም የተቋሙን የሃብት ቁመና ለማወቅ አስቸጋሪ አድርጎት ነበር። በመሆኑም ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ የመዝጋትና የማስተካከል ሥራ ተከናውኗል። ብክነት ለመቀነስም ብዙ ሥራ ተሰርቷል። ቀደም ሲል ሃብት በቁጠባ የመጠቀም ባህል አልነበረም።ፋብሪካ እና አገዳ ልማት አለመጣጣምና ብክነት ነበረበት። በተጨማሪም ስኳር መመረቱን እንጂ በምን ያክል ወጪ ቆጣቢ ነበር የሚለው ማወቅ አስቸጋሪ ነበር፡፡
ኢንዱስትሪ ደግሞ በቁጠባ ካልተመረ አትራፊ መሆን አይቻልም።በመሆኑም ይህን አሰራር ለማስተካከል ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል።በመሆኑም ቀደም ሲል ያልነበረና አሁን እየተተገበረ ያለ ነገር ቢኖር ለእያንዳንዱ ፋብሪካ የማምረቻ ወጪ የሚል ተሰልቶ እየተሰራበት ነው። በመሆኑም ይህ ውጤታማ እያደረገን ነው። ውጤታማ ያልሆኑ ፋብሪካዎችንና ሥራዎችን የማቆም ስራም ተተግብሯል።ለምሳሌ ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በአካባቢው አጋጥሞ ከነበረው ድርቅ አኳያ ለምቶ የነበረው 20ሺ ሄክታር የሸንኮራ አገዳ ልማት ሙሉ ለሙሉ ወድሟል።ይህም በመሆኑ ስራው ለማስቀጠል አልተቻለም፡፡
ሸንኮራ አገዳ ልማት ሰፊ ጊዜና ገንዘብ ይጠይቃል። ሙሉ ለሙሉ በእንስሳት ከመውደሙና ከጸጥታው ጋር ተያይዞ ስኳር ማምረት ስላልተቻለ ብክነት ማስቀረትና ነገሮች በአስተማማኝ ደረጃ እስኪረጋጉ ድረስ እዚያ አካባቢ ያለው ሥራ ሊያሰራ የሚችል የሰው ኃይልና ወጪ በመመደብ ወጪ ከመቀነስ አኳያ ተሰርቷል። ፕሮጀክቶችን ማጣመርና አንድ ላይ እንዲሰሩ የማድረግም ስራ ተከናውኗል። ለምሳሌ ኦሞ አካባቢ ኦሞ አንድ፤ ሦስት እና አምስት በአንድ ማኔጅመንት እየተመሩ ቆይተው በኋላ ሲሰፉና ሲያድጉ በየራሳቸው መቆም ሲያስፈልግ በዚያው አቅጣጫ የሚመሩ ይሆናል፡፡
ሌላው ትልቅ እርምጃ የሚባለው አምስት ፋብሪካዎች ራሳቸውን ችለው እንዲዋቀሩ የተደረገበት ነው። መሰረታዊ ነገር የመንግስት ፍላጎትም ተቋማችንም የሚያምንበት ነገር ነው። የፋብሪካዎቹ ታሪክ በሚታይበት ጊዜ ከሞላ ጎደል ውጤታማ ሆነው የነበሩት ራሳቸውን በራሳቸው ያስተዳድሩ በነበረበት ወቅት ነው። ስለዚህ ከስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ስር ከሚሆኑ ይልቅ በራሳቸው ቦርድ እየተመሩ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲመሩ መጋቢት 2014 ዓ.ም ወደ ሥራ የተገባ ሲሆን ከአምስቱ ፋብሪካዎች ከሰም እና በለስ ከአዳዲሶቹ ሲሆኑ፤ ወንጂ፣ መተሐራ እና ፊንጫ ስኳር ፋብሪካዎች ደግሞ ከነባሮቹ ናቸው። ይህም የለውጡ ትልቅ ማሳያ ነው። ይህ መደረጉ የስኳር ኮርፖሬሽን የነበረውን ተልዕኮ ለመቀነስ፤ ችግሮቹን በየፈርጁ ለማስተካከል ይረዳል። የተዋቀረው ቦርድም በፖለቲካ እና ሙሉ ተሳትፎ ውሳኔ ለመስጠት ዕድል የሚሰጥ ነው። ይህም ፋብሪካዎቹ ወደቀድሞ ዝናቸው ለመመለስ ያግዛል ተብሎ ይገመታል።እነዚህ ሪፎርሙ ከወሰዳቸው እርምጃዎችና ትልቅ ውጤት ያመጣሉ ብሎ ከሚጠበቅባቸው የሚጠቀሱም ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ፋብሪካዎቹ ማምረት ከማቆም በዘለለ ለስርቆት እየተጋለጡ ነው።ለመሆኑ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙት ፋብሪካዎች የጥበቃ ሁኔታ ምን ይመስላል፤ ቅድሚያ ትኩረትስ የሚሰጠው አለ?
አቶ ዘመድኩን፡- እውነት ለመናገር ሁሉም ፋብሪካዎች ትኩረት ይፈልጋሉ።የስኳር ፋብሪካ ኢንዱስትሪ በአንድ ጊዜ አይጎዳም፤ ከተጎዳም በአንድ ጊዜ አይመለስም።ለምሳሌ ወንጂ መተሐራና የመሳሰሉት ፋብሪካዎች የተጀመሩት በኔዘርላንድ ባለሃብቶች ነው።በዳበረ የአሰራር ስርዓትና በሂደት ነው የተጀመሩት።አንዱ ከተሰራ በኋላ ሌላው ሲቀጥልና ሲገነባ ነበር።አሁን እንደተጀመረው በአንድ ጊዜ በርከት ያሉት አልተጀመሩም።በዚህ የአሰራር መርህ ፋብሪካዎች በሂደት እየተጎዱ መጡ።በተለይ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ፋብሪካዎቹና ፕሮጀክቶቹ እየተጎዱ መጡ።
የስኳር ፋብሪካዎች ትልቁ በሽታ የሚጀምረው በ2003 ዓ.ም ነው። ፋብሪካዎች ከሚገኙት ገቢ የአገዳ ልማታቸውን እያሳደጉና ማሽኖቻቸውን እየተኩ እንዳይሄዱና ለፕሮጀክት ብቻ ፋብሪካዎቹ ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት አግባብ ፈርሶ ስኳር ኮርፖሬሽን ስር እንዲገቡ በመደረጋቸው ችግር ውስጥ ገብተዋል። ይሄ በሽታ የዓመታት ችግር አስቀመጠ። ሆኖም አሁን ከችግር ሊወጡ እየታተሩ ነው። ከችግሩ እንዲወጡ በራሳቸው ቦርድ ብዙ ተግባራትን እያከናወኑ ነው።ሆኖም ግን ሁሉም ፋብሪካዎች ትኩረት ይፈልጋሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሁሉም ፋብሪካዎች ትኩረት ሊፈልጉ ይችላሉ። ግን ተንዳሆና የመሳሰሉት ለሥርቆትም ጭምር ተጋልጠዋል።አንዳንድ ፋብሪካዎቸ ደግሞ ውጭ ሀገር ያረጁና ተነቅለው መጥተው የተተከሉ በመሆናቸው ወትሮም ሥራ አይሰሩም ይባላል።ለፀጥታ ችግርም የተጋለጡ አሉ።ከዚህ አኳያ ቅድሚያ የሚሰጣቸው የሉም?
አቶ ዘመድኩን፡- አንዳንዱ ዝም ብሎ የሚወራ ነገር ሊኖረው ይችላል። አንዳንዱ የተወሰነ እውነት ሊኖረው ይችላል። ፋብሪካዎቹን በተመለከተ የተሠራበት ነው የሚለው በእኛ ምርመራ የተረጋገጠ ነገር የለንም።የሰራ ማሽን ያስታውቃል፤ ውል አለው፤ ዕቃዎቹ ተጭነው ሲመጡ ወደብ ላይ ሄዶ የሚያረጋግጥ አካል አለ።ወንጂ እኮ ሲቋቋም 30 እና 40 ዓመት የሠራ ፋብሪካ ነው የተተከለው።ዋናው ችግር እሱ አይደለም።አንዱ ሌላው መክሰስ ጥቅም የለውም እንጂ ፋብሪካውን ያመጣው ሌላ አካል ነው።
ተንዳሆ ላይ ውድመት አጋጥሞናል።ማሕበረሰቡ ልማቱን አምኖበት አይደለም የገባው።ሌላው ቀርቶ የአስተዳደር አካሉ ባላመነበት ሁኔታ ገፍቶ ነው የገባው።መንግስት ሲወስን ለጅቡቲ ወደብ ያለውን ቅርበት በማየት ነው።የአየር ንብረቱንም በማየት ሊሆን ይችላል።በተጨማሪም አለግባብ የመጠቀም ፍላጎት በየአካባቢው አለ።በዚህም የተነሳ ፋብሪካው ስኬታማ አልሆነም።በመጨረሻ ደግሞ የአገዳ ልማቱ ሙሉ ለሙሉ በእንስሳት ወድሟል፤ ከውድመቱም በኋላ የንብረት ስርቆት በስፋት ያጋጥማል፡፡
በወሬ ደረጃ የምንሰማው የማይገመት አካል ጭምር እንደሚሳተፍበት ነው።በእኛ በኩል ለማስጠበቅ እንጥራለን፤ ግን ዝርፊያው ከእኛ አቅም በላይ ነው።በሲቭል ለማስጠበቅ ሞክረናል፤ ፌደራል ፖሊስም ለማስገባት ሞክረናል።የሚደርሰው ጉዳት ግን እነዚህ አካላት አቅም በላይ ነው።በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ባጋጠመን የፀጥታ ችግር ነገሩ እንዲባባስና ተጠያቂነት እንዳይሰፍን ዕድል ከፍቷል።እኛም በተደጋጋሚ በደብዳቤ ጠይቀናል። መሰል ችግሮችን ለማስታገስ ትንሽ ጊዜ ይወስዳል፡፡
በእኛ በኩል እስከቻልነው ድረስ ጠቃሚ ንብረቶችን ወደ ሌላ ቦታ ማንቀሳቀስና ጥቅም ላይ ማዋል በሚቻልበት ላይ እየሠራን ነው፡፡ይህም ቢሆን ቀላል አይደለም፤ የማህበረሰብ ንብረት ነው በሚል ጫናው የከፋ ነው። ነገር ግን እስከቻልነው ድረስ ንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ እያደረግን ነው።ነገር ግን ተንዳሆ ፋብሪካ ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ ብዙ ንብረት እየተዘረፈ ነው። ሌሎቹ ዘንድም ችግር ቢኖርም፤ እንደ ተንዳሆ የለየለትና ለመቆጣጠር ያስቸገረን አላጋጠመንም።በመሆኑም የተንዳሆን በተለየ ሁኔታ መያዝ ተገቢ ነው።
ከጸጥታና ጥበቃ ጋር ተያይዞ ያለው በደንብ ይታወቃል።አቅም በፈቀደ መጠን ጥበቃ ይደረጋል።ግን አብዛኞቹ ቦታዎች ከሲቭል መስሪያ ቤት አቅም በላይ ነው።ለምሳሌ አርጆ ደዴሳ፣ ፊንጫ ትንሽ አስቸጋሪ ነው፤ ሥራ ይፈልጋል። ሌላው ቀርቶ ቅርቡ መተሐራ እንኳን አስቸጋሪ በመሆኑ የመንግስትን ሥራ ይፈልጋል። ሪፖርት እናደርጋለን፤ መንግስት ወደ ሰሜኑ ትኩረት ስላደረገ ወጣ ገባ ያለ ነገር ነው ያለው።አሁን የሰሜኑ የራሱን መልክ እየያዘ ስለሆነ ይሻሻል የሚል እምነት አለን፡፡
አዲስ ዘመን፡-የስኳር አቅርቦት ቀጣይ ተስፋ ምን ሊሆን ይችላል?
አቶ ዘመድኩን፡- እውነቱን ለመናገር በየትኛው ጊዜም ቢሆን ስኳር የፍላጎቱን ያክል ቀርቦ አያውቅም። መሠረታዊ የሆኑ ፍላጎቱን በመለሰ መልኩ ሲመራ ነበር።ግን ከገጠር እስከ ከተማ ሙሉ ለሙሉ መልሶ አያውቅም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ ዘንድሮ ትልቅ ችግር አጋጥሞናል። ዘንድሮና አምና በክረምቱ በተለየ ሁኔታ የስኳር እጥረትና ችግር አጋጥሞናል፡፡
የስኳር ኢንዱስትሪ በአንድ ጊዜ አልሞተም፤ ልክ እንደ ካንሠር በሽተኛ በሂደት ነው የተጎዳው።በሂደት የማምረት አቅማቸው እየቀነሰ ባለፈው ዓመት አስደንጋጭ ደረጃ ደረሱ። ሦስት ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ስናመርት በጣም ዝቅተኛ ነው ብለን ነው የምንሳቀቅ የነበረው። ባለፈው ዓመት ግን ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ማምረት አልቻልንም፡፡
ትልቁን ምርት ያመርት የነበረው ፊንጫ ከፀጥታ ችግር የተነሳ ማምረት አልቻለም።መተሐራ ላይ 1000 ሄክታር መሬት የሸንኮራ አገዳ ልማት በጎርፍ ጠፍቷል፤ በዚሀ ላይ የፀጥታ ችግር ተጨመረበት። ወንጂ ፋብሪካም በተመሳሳይ ሁኔታ የአገዳ ችግር አጋጠመው። አንዳንዱ ችግር ያልተጠበቀ ነው።ከሰም በተመሣሣይ ሁኔታ አሚባራ የሚባል የግል ባለሃብት ነበር። እዚህ ላይ ከአዋሽ ወንዝ ሙላት ጋር በተያያዘ የጎርፍ አደጋ አጋጠመው። ስለዚህ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ተደራርበው ባላፈው ዓመት ችግሩን አባብሰውታል፡፡
የስኳር ፍላጎትን ለማሟላት ጥረት የምናደርገው ሀገር ውስጥ የሚመረተውና ጉድለቱን ከውጭ እያመጣን ነው። ባለፈው ዓመት የነበረውን የስኳር ጉድለት ለማሟላት ከውጭ ልናመጣ የነበረው በሀገራዊው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ ጥረታችን በፈለግነውና ባቀድነው ልክ አልተሳካም። እነዚህ ተደማምረው ነገሩን ረብሸውታል። በቅርቡ ፓርላማ ላይ ተነስቶ የነበረው ስኳር እጥረት ስለመኖሩ መግለፁ ነበር፤ አዎ እጥረት አለ።ግን በፍራንኮ ቫሉታ የገባ ስኳር አሁንም ገበያ ላይ አለ።ዋጋው ግን እስከ 70 ብር ነው። ትልቁ ችግር ስኳርን በግብዓት የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች ሕብረተሰቡ በሚገዛው አነስተኛ ዋጋ መውሰድ ይፈልጋሉ።ስለዚህ ሽሚያ ይፈጠራል። አሁንም መጠኑ ቢያንስም በዝቅተኛ ዋጋ ለከተሞች ስኳር እያከፋፈልንና ለማቃመስ ጥረት እያደረግን ነው። ችግሩን በጊዜያዊነት ለማቃለል ፋብሪካዎች የሚነሱበት ወቅት ነው። ወንጂ ሥራ ጀምሯል። ኦሞ አካባቢ ያለውም እየተስተካከለ ነው። በተመሳሳይ ሌሎችም ሥራ ይጀምራሉ። በመሆኑም በጋውን የስኳር አቅርቦት ችግር አያጋጥምም። የስኳር አቅርቦት ችግር ሙሉ ለሙሉ ባይፈታም ማስተጋስ ይቻላል።ከውጭም በአንድ ወር ውስጥ ይገባል። ከውጭ ስኳር ለማስገባት አሁን መስመር ላይ ሁለት ሚሊዮን ስኳር አለ በአንድ ወር ውስጥ ይገባል፡፡
በዘላቂነት ለመፍታት የተጀመሩት ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ስኳር በአቅማቸው ልክ እንዲያመርቱ ምን ያስፈልጋቸዋል፤ አሁናዊ ቁመናቸውስ ምንድን ነው፣ ነባር ፋብሪካዎቹስ ወደ ሙሉ አቅማቸው ለመድረስ ምን ያስፈልጋቸዋል የሚለውን የሚያሳይ የስትራቴጂ ፕላን ተዘጋጅቶ በሥራ አመራር ቦርድ እንዲፀድቅ ተደርጓል። የየፋብሪካዎቹም በየቦርዳቸው እንዲፀድቅ ተደርጓል። በዚህ መሰረት በ2020 ዓ.ም ስኳር ማምጣትን እናቆማለን ብለን እናስባለን፤ ለዚህም እየሰራን ነው። ለስኬቱ ደግሞ የሰው ኃይል ልማት፤ ፋብሪካና ፕሮጀክቶች ላይ መሥራት ይጠበቅብናል። በቀላሉ ውጤት አያመጣም፤ ግን የጀመርነው ሪፎርም ሥራም ለዚህ ያግዘናል። ሀገራዊ ሁኔታው መለወጡ እኛ ዘንድ ያለውን በእጅጉ ይለውጠዋል።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ በፀጥታ ችግር በዚህ ደረጃ እየተፈተነ ባለበት ሁኔታ በፕራይቬታዜሽን የውጭ ባለሃብቶችን መሳብ አይከብድም?
አቶ ዘመድኩን፡- እኛ ስትራቴጂክ እቅዳችን ስናወጣ ፋብሪካዎቹ እኛ እጅ ሆነው ቢቀጥሉ ብለን ነው።በዚህም 2020 ዓ.ም ግብን መሰረት አድርገን ስናስብ በመንግስት ቁጥጥር ሥር ቢሆኑ ብለን ነው።ስለዚህ ከፕራይቬታይዜሽ ጋር አይያያዝም፡፡በሁሉም ዘርፍ እየሰራን እንቀጥላለን፤ ችግሮቹን እየፈታን እንሄዳለን።
የሀገራችን ሁኔታ ፈጥኖ ከተተሻሻለና ባለሃብቶች ፈጥነው ከመጡ መንግስት በስኳር ኢንዱስትሪ ውስጥ ሁሉን ጠቅልሎ የሚሰራበት ሁኔታ የለም። በብዙ ሀገራት መንግስት ለስኳር ኢንዱስትሪ ድጋፍ ያደርግ ከሆነ እንጂ በግል የሚሰሩ ናቸው። በመሆኑም ይህ ተሞክሮ መምጣቱ ጥሩ ነው። ተወዳዳሪነት፣ ምርጥ ተሞክሮ፣ ቴክኖሎጂና በሌላው ዘርፍ ለውጥ ያመጣሉ። ስለዚህ እነርሱ ቢመጡ ውጤታማነታችን ይጨምራል። ከዚህ በፊት በነበረው የፕራይቬታዜሽን አካሄድ ትምህርት ስለተወሰደበት በመንግስት በኩል አስፈላጊ ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በመንግስት በኩልም የስኳር ፋብሪካዎችን ‹‹ፕራይቬታይዝ›› ለማድረግ የጨረታ ሂደት ላይ ነው።የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ደግሞ ፋብሪካዎችን በመምራት በ2020 ዓ.ም የስኳር ችግር እፈታለሁ ይላል።አካሄዳችሁ ከመንግስት አሠራርና ፍላጎት ጋር የተናበበ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ዘመድኩን፡- ፍላጎታችን የተናበበ ነው። የ‹‹ፕራይቬታዜሽን›› ጉዳይ አሁን የመጣ አይደለም። መንግስትም ‹‹ፕራይቬታዜሽንን›› ይፈልጋል።ዓለም ወደአንድ እየሄደች ስለሆነ እንደ ደሴት መነጠል አንችልም። እኛም በውጤታማነታችን ላይ ጥያቄ ይነሳበታል። የግሉ ዘርፍ ቴክኖሎጂ፣ አቅም፤ እውቀት አለው፤ ውድድሩ ፈጣን ነው። በመሆኑም ይህን ወስደን መንግስትም በሰጠን አቅጣጫ እየሠራ ይቆይ ነው። ዋጋው እየጨመረ ይሄዳል። አንድ የስኳር ፋብሪካ አንድ ትልቅ ከተማ ነው። ስለዚህ ይህን እየሠሩና እያስተካከሉ መሄድ ይገባል። እኛ ግን ከመንግስት የተለየ አቋም የለንም። ስለዚህ እየሰራችሁ ቆዩ በተባለው መሠረት እንሠራለን፤ ባለሃብቶች ሲመጡ ደግሞ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ይተላለፋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሁን ያለንበት ወቅት በስኳር ዘርፍ የቀውስ ወቅት ነው።በዚህ ወቅት ደግሞ ብልህ አመራር ይፈለጋል።እርስዎ በዚህ ወቅት የዚህም ተቋም አመራር በመሆንዎ ምን ይሰማዎታል።ከህዝቡ ጥያቄ አኳያ ጥሩ እንቅልፍ ይወስዶታል?
አቶ ዘመድኩን፡- ከባድ ነው፤ ማለትም የትኛው መሥሪያ ቤት ቢሆንም፤ በተለይ እንደዚህ ለምግብ ፍጆታ የሚውል ነገር ማቅረብ ላይ ፈታኝ ነው።ዘይትም አንድ ወቅት እንደዚህ ፈታና ነበር።በእርግጥ መንግስት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች አሉ። ከውጭ ለማስገባት ስናወራ ከዶላር ውስንነት የተነሳ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች ብዙ ናቸው።መድሃኒትና የመሳ ሰሉት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ናቸው። እንግዲህ ሥራው ፈታኝ ነው፡፡
እንቅልፍ ሲደክምህ ትተኛለህ እንጂ፤ ደስ ብሎህ አትተኛም። እጅህ ላይ በጣም አስቸኳይ ነገር ሲኖር ዘና ብሎ ለመተኛት በጣም ይቸግራል።ብዙ ተቋማት ተጨናንቀው ነው የሚሠሩት።የእኛ ዓይነቱና አቅርቦት ላይ የሚሠራ ደግሞ በእጥፍ እንደሚያጋጥመው መገመት አያዳግትም።በጣም በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ነው የምንሠራው።ዋናው ነገር የእኛ መጨነቅ ሳይሆን ስኳር ማቅረባችን ነው።ስኳር ከማቅረብ አኳያ አሁን በጋው ወቅት ላይ ስለደረስን ከችግሩ ወቅት ወጥተናል።በጣም አስጨናቂ ጊዜ አልፈናል፤ በአንድ ወር ውስጥ የተሻለ ነገር ይኖራል።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ በተቋማችን ሥም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ዘመድኩን፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 12 ቀን 2015 ዓ.ም