ኢትዮጵያ የሦስት ሺህ ዘመን ታሪክ ባለቤት ብትሆንም፤ ይህ ታሪክ ግን በአገሪቱ ዜጎች መካከል እንኳን ወጥና ሁሉንም በሚያስማማ መልኩ ተሰንዶ የተቀመጠ አለመሆኑንና ይህ ደግሞ የፖለቲካ ለውጥ በመጣ ቁጥር የታሪክ መዛባት እየተፈጠረ ስለመሆኑ ይነገራል፡፡ በተለይ በአገሪቱ በነበሩ የፖለቲካ ትኩሳቶች መነሻ ተደርጎ የሚወሰደው አንዱ ብሄር አንዱን ጨቁኗል የሚለው የታሪክ መዛባት ነው፡፡ በዚህም የሰማዕታት ሐውልቶች በመገንባት፣ በመማሪያ መጽሐፍት ላይ የተዛቡ ታሪኮችን በማስቀመጥና ብሔር ተኮር የፖለቲካ ፓርቲዎች በመመስረት አንዱ አንዱን እንዲጠላ ማድረግ ለታሪኮች መዛባት የራሳቸውን አሻራ የሚያሳርፉ ጉዳዮች ሆነው ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡
ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ሲስተዋል በነበረው ጠንካራ የህዝቦች ጥያቄ ውስጥም፣ ከመልካም አስተዳደር ቀጥሎ የብሔር ጭቆና ተደርጎብናል የሚሉ ጥያቄዎች ጎልተው ይነሱ ነበር፡፡ በአገሪቱ በተለያዩ ወቅቶች በነበሩ የፖለቲካ ለውጦች ምክንያት ታሪኮች እንደየአስተዳደሩ ሁኔታ እንዲዛቡ በመደረጋቸው ኅብረተሰቡ ሁነቶችን የኔ ነው ያንተ ነው ወደሚል ደረጃ አድርሶታል፡፡ ተዛብተው በተነገሩና በተፃፉ ታሪኮች ምክንያት የታሪክ ሽሚያ መከሰቱን የታሪክ ባለሙያው ይናገራሉ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው፤ በቀድሞ ጊዜ አንዳንድ ነገሥታት የራሳቸውን ዘመን ታሪክ ጎላ አድርገው ለማሳየት ከነሱ በፊት ባላንጣ ነው ብለው የሚቆጥሩትን ንጉሥ ታሪክ አሳንሶ ካልሆነ ደግሞ እንዳይነገር ያደርጉ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ለምሳሌ ልጅ እያሱ የተወሰነ የለውጥ እርምጃዎችን መውሰዳቸው በጎ ታሪክ ቢሆንም በተቀናቃኛቸው በአፄ ኃይለሥላሴ ሲታይ ጭራሹኑ ታሪካቸው እንዳይነገር መጥፎ መጥፎው ብቻ እንዲወራ መደረጉን ያስታውሳሉ፡፡
ነገሮች እየተባባሱ የመጡት የብሄር ጥያቄዎች ከመጡ በኋላ መሆኑን የሚናገሩት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፤ የብሔር ጥያቄ መቀንቀን የጀመረው ከተማሪዎች እንቅስቃሴና ብሔር ተኮር ድርጅቶች ከመጡ በኋላ እንደመሆኑ፤ ብሔር ላይ ያተኮሩ ግጭቶች ሲነሱ ብሔሬ ተበድሏል፣ የተለየ የፖለቲካ ጫና ደርሶበታል በሚል እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ በኑሮ ተመሳሳይ የሆነ፣ የታሪካዊ ግንኙነቱ በኢኮኖሚና በባህል እንዲሁም በሃይማኖቱ የተሳሰረ እና አገር በመከላከል ረገድ አብሮ መቆሙ ተረስቶ ይሄ ታሪክ የእከሌ ብሔር ነው፣ ይሄን ያደረገው ይሄኛው ብሔር ነው በሚል ወደ ግጭት መገባቱን ይናገራሉ፡፡ በዚህም ይሄኛው ንጉሥ የእከሌ ብሔር ነው እኛን የሚወክል አይደለም በማለት የተዛቡ ታሪኮች መውጣት መጀመራቸውን ያስታውሳሉ፡፡
በደርግ ዘመን በማርክሲስትና በሌኒንስት ርዕዮተ ዓለም የተቃኘ ታሪክ እንደመጣና ቀደም ብሎ የነበረው ታሪክ የገዥ መደቦች ታሪክ በመሆኑ እንደገና በትክክል እንዲፃፍ መደረጉን ይገልፃሉ፡፡ በወቅቱ የጭቁኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክ መፃፍ አለበት እየተባለ ጎን ለጎን ደግሞ እከሌ ጀግና ናቸው በተለይ በሚል አፄ ቴዎድሮስን፣ አፄ ዮሀንስንና አፄ ምኒልክን ጀግና ብለው አፄ ኃይለሥላሴን የማይረባ ንጉሥ ለጭቆና የዳረገ በሚል ጉራማይሌ ታሪኮች መፃፋቸውን ረዳት ፕሮፌሰር አበባው ይጠቁማሉ፡፡
እንደ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አባባል፤ በኢህአዴግ ዘመን ደግሞ ከመጀመሪያው ህወሓት ሲነሳ በአማራ ገዥ መደብ ምክንያትም የአማራ ህዝብ የትግራይ ህዝብ ታሪካዊ ጠላት ተደርጎ ተቆጠረ፡፡ ነገር ግን የትግራይና የአማራ ህዝብ በታሪክ፣ በሃይማኖት፣ በኢኮኖሚ፣ በአኗኗሩ፣ በባህሉና በነበረው የመሬት ግብር ሥርዓቱም ጭምር ተመሳሳይ ነበር፡፡ ለትግራይ ህዝብ መጨቆን ከመሀል አገር ለዘመቻ የመጣው ወታደር በዝብዞናል የሚል የሐሰት ታሪክ መጣ፡፡
‹‹የአገሪቱ ዴሞክራሲ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው የብሔር ብሔረሰቦች መብት ማስከበርና የእነሱን ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማጎናፀፍ ነው›› ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፤ ለዴሞክራሲ ትግሉ ደግሞ አንድ ጨቋኝ መደብ መፈጠር በማስፈለጉ የአማራን ብሔር ትኩረት ያደረገ ዘመቻ መከፈቱን ይጠቅሳሉ፡፡ በዚህም ትግራይን፣ ኦሮሚያን፣ ሲዳማን፣ ወዘተ. እንደዚህ ያደረገው አማራ ነው የሚል የተዛባ ታሪክ መሰራጨቱን ያስረዳሉ፡፡ ነገር ግን በእያንዳንዱ ብሔር ላይ ያሉት ጎሳዎች እርስ በርስ ይጨቋቆኑ እንደነበር በመጥቀስ፤ ገዥ መደቡ ከአማራ ብቻ የተወጣጡ ሳይሆን በወለጋ ላይ የራሱ የኦሮሞ ገዥ ነበረው፣ ጅማ ላይ በተመሳሳይ የራሱ መደብ ነበረው፣ ሐረርና ሱማሌ የየራሳቸው ባላባቶች በጋራ አካባቢዎቹን ያስተዳድሩ እንደነበር ያብራራሉ፡፡
እንደ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አባባል፤ የተዛቡ ታሪኮች ወደ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ ለምሳሌ፣ አፄ ምኒልክ ኢትዮጵያን ሲገዙ ኢትዮጵያን እንጂ አማራውን ወክለው አይደለም፡፡ ያኔ የነበረው ዘውዳዊ ሥርዓት የሚወክለው ዘመኑን እንጂ አማራውን አይደለም፡፡ በወቅቱ በርካታ የአማራ ገዥዎች እንደነበሩ አይካድም፡፡ የተማሪ መማሪያ መጽሐፍት ላይ ግን ታሪክ ተዛብቶ ተቀምጦ ነበር፡፡ ይሄ ባለበት ሆን ተብሎ የቆየን ታሪክ የጀግኖችን ታሪክ የማጠልሸት ከዚህም ባለፈ የሐሰት ታሪኮችን ለመፍጠር ሆን ተብሎ በፖለቲከኞች የተሠራ ሥራ ነው፡፡ በአንደኛና በመለስተኛ ደረጃ መማሪያ መጽሐፍት ላይ አጨቃጫቂ ታሪክ ሲካተት የወጣቱ ስሜት በማነሳሳት ይሄ ያንተ ነው፤ ይሄ ደግሞ የኔ ነው በመባባል እንዲህ ያደረከኝ አንተነህ ብሎ ያለፈ ታሪክ እንደ ትልቅ ነገር ተነስቶ የግጭት ምክንያት ሆኗል፡፡
የኢትዮጵያ ፖለቲካ መነሻው አሁን የሚደረግ ጭቆና ሳይሆን ከዚህ በፊት እንዲህ ተደረኩ የሚል በመሆኑ የብሔር ፓርቲዎች ሲቋቋሙ ወደ ኋላ ሄደው እንዲህ ስለሆንኩ ነው የማቋቁመው የሚል ምክንያት እንደሚሰጡ ይናገራሉ፡፡ አሁን ላይ ፓርቲ ሲመሰረት ማየት ያለበት የወደፊቱን መሆን እንዳለበት የሚጠቅሱት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፤ ባለፈው ጊዜ የተደረጉ የታሪክ ሁነቶችና ክንውኖች በጎውም ሆነ መጥፎው ታሪክ አንድ ላይ ለቀጣይ ትውልድ መማሪያነት መቀመጥ እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡
እንደ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው ገለፃ፤ ፖለቲከኞቹ የብሄር ፓርቲዎች አሁን ከምንገኝበት ነባራዊ ሁኔታ ላይ ጥያቄ ማንሳት አለባቸው፣ ግባቸው ከዚህ መነሳት አለበት፤ ከዛም መድረሻቸውን ማስቀመጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ባለፈ ታሪክ ላይ እንዲህ አድርገኸኛል እየተባለ እራሳቸው ፖለቲከኞች የኅብረተሰቡን ችግር እያባባሱ የግጭት መንስኤ መሆን የለባቸውም፡፡ አገሪቱ ላይ የሚሰጠው የታሪክ ትምህርት ሁሉንም ያካተተ መሆን አለበት፡፡ በተለይ በአገሪቱ የሚገኙት ክልሎች ከአፄ ምኒልክ በፊት ያላቸው ታሪክ መካተት የለበትም ማለት አይቻልም፡፡ መማሪያ መጽሐፍት ሲቀረፁ የሁሉንም ታሪክ ባካተተ መንገድ መሆን ይገባዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲዎች በሁሉም ትምህርት ክፍሎች ውስጥ ታሪክን እንደ አንድ የትምህርት አይነት መስጠት መቆም አልነበረበትም የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፤ ወጣት ዩኒቨርሲቲ ሲገባ መማር ያለበት የግድ የአገሪቱን ታሪክ ቢሆንም ይህ እየተሰጠ ባለመሆኑ በተዛቡ ታሪኮች ምክንያት ግጭቶች እየተከሰቱ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በቀጣይም የታሪክ መምህራን ማህበር በመመስረት የአገሪቱን ታሪክ በአግባቡ እንዲጠና ማድረግ ካልተቻለ በተዛባ ታሪኮች ምክንያት አሁን እየታዩ ያሉት መከፋፈሎች እንደሚባባሱ ይጠቁማሉ፡፡
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ፋንታሁን አየለ እንደሚሉት፤ በታሪክ ላይ ውዝግብ የሚነሳው ትክክለኛውን ታሪክ ካለመገንዘብ ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ ታሪክን ለፖለቲካ ጥቅም ለማዋል ሲሞከር ችግር ይፈጠራል፡፡ አሁን የሚታዩት ችግሮች ከዚህ የሚመነጩ ናቸው፡፡ ታሪክ በትክክለኛው የታሪክ አፃፃፍ ዘዴ እና በታሪክ ሙያ በሰለጠኑ ሰዎች ሲፃፍ ትክክለኛ ታሪክ ለትውልድ ሲተላፍ የሚፈጠር ችግር አይኖርም፡፡ እንደ ምክንያት ከመጀመሪያው የችግሩ ምንጭ ለመነሳት ለረጅም ጊዜ የኢትዮጵያ ታሪክ የሚፅፉት የውጭ አገር ሰዎች ናቸው፡፡ የውጭ አገር ሰዎች ደግሞ በትክክለኛው ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ሁሉንም አይፅፉም፡፡ ያንን ተከትሎ ደግሞ የነሱን ፅሁፍ የሚያነብ ሰው ደግሞ በተዛባ መልኩ ታሪክን ይረዳል፡፡
እንደ ዶክተር ፋንታሁን አባባል፤ አንድ ትልቅ ችግር የሚታየው ከሃያ ዓመት በፊት የታሪክ ትምህርት በዩኒቨርሲቲ ደረጃ በሁሉም ትምህርት ክፍል ለሚማሩ ተማሪዎች ይሰጥ ነበር፡፡ ትምህርቱ ጥሩ ግንዛቤ ከመስጠት ባለፈ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ያሉ ተማሪዎች የአገራቸውን ታሪክ በደንብ በጥንቃቄ የሚረዱበት ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ትምህርቱ መሰጠት አቆመ፡፡ በዚህ ተማሪዎች የአገራቸውን ታሪክ ሳያውቁ ይመረቃሉ፡፡ ይሄ ደግሞ ለተለያየ የታሪክ መዛባትና የተለያየ የአረዳድ ችግር ትውልዱን አጋልጧል፡፡ በተለያየ መንገድ የሚሰራጨው ትክክለኛ ያልሆነው ታሪክ ብዥታ ፈጥሯል፡፡
በየትምህርት ቤቶቹ በተለይ በአንደኛ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ ያለው የታሪክ ትምህርት አሰጣጥ በጣም በተበጣጠሰ መንገድ እየተሰጠ እንደሚገኝ የሚገልፁት ዶክተር ፋንታሁን፤ በትምህርት መጽሐፉ ውስጥ የተቀነጫጨቡ ነገሮች ያሉት በመሆኑ ትልቅ መሰረታዊ ችግር እንደፈጠረ ይገልፃሉ፡፡ በአሁን ወቅት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ደረጃም ለሁሉም ትምህርት ክፍል የታሪክ ትምህርት ባለመሰጠቱ ደግሞ ችግሩን በማባባስ ዋናው የችግሩ ምንጭ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
‹‹ከሌሎች አገሮች ብዙ የምንማረው ነገር አለ›› የሚሉት ዶክተር ፋንታሁን፤ በምሳሌነት አሜሪካ በታሪኳ የችርስ በርስ ጦርነት ያስተናገደች ብትሆንም ጦርነቱ ለቀጣይ ትውልድ ትምህርት ሰጥቶ በማለፉ አሁን ያለው የአሜሪካ ህዝብ ያንን እያነሳ እርስ በርስ ከመናቆር ይልቅ ወደ አገር ግንባታ መግባቱን ያነሳሉ፡፡ በተመሳሳይም በጀርመን አንደኛ የዓለም ጦርነትና ሁለተኛ የዓለም ጦርነት ላይ ብዙ ሰቆቃ ደርሶ ነበር፡፡ ይሄ ግን የህዝቡን አንድነት ጭራሽ አላናጋውም፡፡ ጀርመን በአውሮፓ ጠንካራ አገር ሆና እንድትቀጥል የህዝቡ አንድነት አስተዋፅኦ ማድረጉን ይጠቅሳሉ፡፡ ከታሪክ በጎ የሆነውን ነገር በትምህርትነት ወስዶ ወደሚቀጥለው መሸጋገር ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ ሁኔታ ግን በጣም የተለየ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በጣም የሚያኮራ ታሪክ እያላት፤ ነገር ግን ይሄ ተትቶ ወደ ግጭት በሚያመሩት ላይ ትኩረት መደረጉን ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም በርካታ ሥራዎች መከናወን ቢኖርባቸውም አልተሰራባቸውም፡፡ ለአብነት፣ በተለይ በትምህርት ቤቶችና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መሰጠት ያለበት ትምህርት ባለመሰጠቱና መገናኛ ብዙኃኑ የሚገባውን ሚና ባለመወጣቱ ታሪክን አጉልቶ ማቅረብ ሲገባ ብዙ የሚያኮራ ነገር እያለ እዚህ ላይ ግን ብዙ ሥራ አለመሠራቱን ይናገራሉ፡፡
ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሥልጣን ዘመን ጀምሮ መንግሥት ትክክለኛ ባልሆነ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ተጠምዷል፡፡ ለምሳሌ የደርግ መንግሥት የኃይለሥላሴን መንግሥት በመኮነን የተጠመደ ነበር፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት ደግሞ የመንግሥት ፕሮፓጋንዳ ወታደራዊ መንግሥት ላይ ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ያደርግ ነበር፡፡ ሁል ጊዜ በጎ ያልሆነውን ነገር እየተነሳ ለትውልድ ስለሚነገረው አሁን ያለውን ችግር እንዲመጣ አድርጓል፡፡ በጎ ነገሮች እያሉ መጥፎ ነገሮች ላይ ብቻ አተኩሮ ፕሮፓጋንዳ መሥራት ለዚህ ሁሉ ችግር መዳረጉን ዶክተር ፋንታሁን ያብራራሉ፡፡
የዚህ ችግር መፍትሄውም በተጠናከረና በትክክለኛው መንገድ የታሪክን ትምህርት ከስር ጀምሮ ለትውልዱ ማስተማር፣ ታሪክን ለፖለቲካ ዓላማ አለማዋል፣ የተጠናና ትክክለኛውን ታሪክ ማስተማር እና ታሪኮች በታሪክ ጸሐፊያን ብቻ እንዲፃፉ ማድረግ ነው፡፡ በቀጣይም በዚህ መልኩ ሠርቶ በጊዜ ያሉትን ችግሮች መፍታት ካልተቻለ ብሔራዊ መግባባት እንደማይኖር ይገልፃሉ፡፡ በተጨማሪም አሁን ባለው ትውልድ ከፍተኛ ችግር እንደሚፈጠር ይጠቁማሉ፡፡
እ.አ.አ መስከረም 2017 ዋሽንግተን ዲሲ በተደረገው አራተኛው የቪዥን ኢትዮጵያ ኮንፈረንስ ላይ ‹‹ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ለመገንባት ምቹ የሆነ የሶሺዮ ፖለቲካ ሥርዓት ወደ መፍጠር›› በሚል በገለታው ዘለቀ የቀረበ ጽሑፍ እንደሚያሳየው፤ ዘመናዊት ኢትዮጵያ ዘመናዊ አስተዳደር ማካሄድ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያ በተወሰነ የባህል ምስለት ውስጥ አልፋለች። የዘመናዊት ኢትዮጵያ መሃንዲሶች የሚባሉት ኣጼ ቴዎድሮስ፣ ኣጼ ዮሐንስና አጼ ምኒልክ ኢትዮጵያን ዘመናዊ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ የባህል ምስለት በተለያየ ደረጃ ተካሂዷል። በርግጥ በኢትዮጵያ ምድር ይህ የባህል ምስለት የተካሄደው በአማራና በሌሎች ብሔሮች መካከል ብቻ ሳይሆን፤ ቀደም ብሎ በኦሮሞ ብሔር መስፋፋት ጊዜም የባህል ምስለቶች ተካሂደዋል። ደቡብ አካባቢ ያሉትን እንደ ጌዲኦ፣ ቡርጂና ኮንሶ በመሳሰሉ ህዝቦችም ደግሞ የኦሮሞ ባህልና ቋንቋ ተጽእኖዎችም ይስተዋላሉ። ለምሳሌ፣ የጌዲኦ ህዝብ የገዳ ሥርዓትን የሚከተል ህዝብ ነው።
በጽሑፉ ላይ እንደተጠቀሰው፤ በእርግጥ ስለ ምስለት ሲወራ ቡድን የሚባለው በተለይም ብሔር በአንድ ቀን እንደ አዳምና ሔዋን ተፈጥሮ ምድር ላይ የተገኘ አይደለም። ብሔር የሚፈጠረው በመስፋፋት ምናልባትም በምስለት ነው። ስለሆነም ምስለቱን ጠለቅ ተብሎ ከታየ ዛሬ ምስለት ተካሂዶብናል የሚሉ ብሄሮች እነሱም ራሳቸው በምስለት ውስጥ አልፈው የመጡ ይሆናል። የሆነ ሆኖ ግን አዲሲቷ ኢትዮጵያ ማእከላዊ መንግሥትን ስታጠናክር በዛን ወቅት የነበሩ ቡድኖችን ስታሰባስብ የሰሜኑ ባህል በተለይም በከተሞች አካባቢ ተጽእኖ ፈጥሮ ቆይቷል። ዓለም በአብዛኛው የተፈጠረችው እንደዚህ ነው። ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያም ምስለት ባየለበት መንግሥት ስር ለብዙ ዓመታት ኖራለች። በዚያን ጊዜ የነበረው የሶሺዮ ፖለቲካ አስተሳሰብ አንድን ሃይማኖትና ባህል በመጫን ላይ ያተኮረ ነበር ማለት ይቻላል። ይህ ሁኔታ ብዙ ዓመት ከቆየ በኋላ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የዓለምን የሶሺዮ ፖለቲካ አስተሳሰብና አተያይ የሚቀይር አንድ ፍልስፍና ብቅ አለ።
ጽሑፉ እንደሚያብራራው ከሆነ፤ የማርክሲስት ሌኒንስት አስተምህሮ የዓለምን ወጣቶች ልብ ለተወሰነ ጊዜ ገዝቶ ነበር። ይህ አስተሳሰብ ከያዛቸው ትምህርቶች መካከል የብሔሮች ነጻነት፣ ራስን በራስ ማስተዳደርና የራስን ዕድል በራስ እስከ መወሰን ድረስ መሄድ የፍትህ ጥግ መስሎ ታየ። ያለፈውን ሥርዓት ማንነትን የደፈጠጠ በመሆኑ በቀል ተያዘበት። በመሆኑም የብሔሮች ጥያቄ በዘመናዊት ዓለም የፖለቲካ መለዮ ለብሶ እሳት ጎርሶ መጣ። ቀላል የማይባሉ የኢትዮጵያ ተማሪዎችም በ1960ዎቹ በዚህ ትምህርት ከነፉ። ኢትዮጵያም ይህንን ትምህርት መከተል ስትጀምር በሳህን በሳህን ለየብቻ ፖለቲካንና ኢኮኖሚን ማየት ተጀመረ። ኢትዮጵያ በምስለት ውስጥ አልፋለች ብሎ ቂም ይዞ የተነሳው አዲሱ የማህበረ ፖለቲካ አስተሳሰብ ሥልጣን ሲይዝ ብሔሮች ያገግሙና ጉዳታቸውን ይጠግኑ ዘንድ የፖለቲካ ማልያ እንዲለብሱ የሚያደርግ ፍልስፍና ነው።
በጽሑፉ እንደተቀመጠው፤ የታሪክ መዛባት ሌላው ችግር በየፖለቲካ ፓርቲው የሚያድጉ መሪዎች በዚህ የብሔር ፖለቲካ ድባብ ውስጥ ሲቆዩ በውስጣቸው አካባቢያዊ ማንነትን አሳድገው ስለሚመጡ ለሁሉም የሚሆኑ መሪዎች እንዳይኖሩ ያደርጋል። የሚመረጡት መሪዎች በመጀመሪያ ለራሳቸው ብሔር አድልዎ ላለማድረጋቸው ህዝቡ ዋስትና ያጣል። አስተዳደሩ ምቹ ስለሚሆን ሥልጣን ላይ ያሉ መሪዎች የአካባቢ መተባበር ፈጥረው አድልዎ ፈጻሚ እንዲሆኑ ያደርጋል።
በጽሑፉ እንደ ችግር የተቀመጠው ደግሞ አሁን ያለው የታሪክ አተያይ የብሔር አርበኞችን የሚያበዛ መሆኑ ነው። በርግጥ የብሔር አርበኝነት በራሱ ችግር አይሆንም። ነገር ግን አርበኝነቱ የሚገለጸው በፖለቲካም፣ በኢኮኖሚም፣ በግዛትም፣ በታሪክም ሲሆን፤ ጤነኛ አርበኝነት አይሆንም። እነዚህ አርበኞች ደግሞ የአንድነት ኃይል ነን ከሚሉ ብሔራዊ አርበኝነት ስሜት ከያዛቸው ጋር ይጋጫሉ። ከፍ ሲል ሁለቱ ማንነቶች ካልነው ሀሳብ ጋር ይዛመዳል። በአንድ የፖለቲካ ጥግ ስር እነዚህ ሁለት አርበኝነቶች እየበዙ ሲሄዱ የሀገሪቱን የሊሂቃን ክፍፍል በኃይል ይመታዋል። በዛሬው ጊዜ ኢትዮጵያ በሊሂቅ ክፍፍል ከፍተኛ ችግር ላይ ናት። ብሔሮች የተፈጥሮ ሀብትንና ኢኮኖሚን ሲከፋፈሉ በአጠቃቀሙ ዘንድ ግልጽነት ይጠፋል። በመሬት ኣጠቃቀመቸው ዙሪያ በተፈጥሮ ሀብት የማዘዝ ደረጃቸው ዙሪያ ብዙ ጥያቄዎች እየተመዘዙ ቢወጡም ምላሽ ግን አያገኙም።
ታሪክ አለማወቅ ማህበራዊ እንቅስቃሴ ላይ ትልቅ ጫና ያለው ሲሆን አንድ ዜጋ የራሱን አገር ታሪክ በጥልቀት ካላወቀ አገሩን አይወድም፡፡ በተጨማሪም በሂደት የአገሩን መውደድ ስሜቱ በጣም እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ ዋናው ነገር የታሪክ ትምህርት ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ድረስ በተጠናከረ መንገድ መሰጠት አለበት፡፡ በዚህ መንገድ እያንዳንዱ ዜጋ የአገሩን ታሪክ ያውቃል፡፡ ከዚህ በፊት በተከፈለ መስዋዕትነት ይቺን አገር በነፃነት ለማቆየት ምን ያክል እንደተሰራ ይረዳል፡፡ የራሱንም ኃላፊነት ያውቃል፡፡ በዚህ መንገድ ትውልዱን መታደግ ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 24/2011
በመርድ ክፍሉ