በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የኖሩ ነዋሪዎች ከተወለድንበት፣ ካደግንበት፣ እትብታችን ከተቀበረበትና ክፉ በጎን ካየንበት የሚያፈናቅለን አሰራር በመምጣቱ ስለነገው ስጋት ጥሎብናል፤ ለዛሬም በእጅጉ ተቸግረናል ሲሉ ነበር አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ድረስ በመምጣት መንግስት በደላችንን ይስማ፤ ህዝብ ይፍረደን ለታሪክም ይቀመጥልን ሲሉ ቅሬታቸውን ያቀረቡት።
የዝግጅት ክፍላችን ቅሬታውን በመቀበል ጉዳዩ ምን ያህል እውነት ነው ሲል ግራ ቀኝ የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር ‹‹ፍረዱኝ›› በሚለው አምዳችን አስቀምጠን፤ የሚመለከታቸው አካላት በሚጠበቅባቸው ልክ ኃላፊነታቸውንም እንዲወጡ ለማሳሰብና ህጋዊ አሰራሮች ይሰፍኑ ዘንድም ለመጠቆም ከመሻት የተነሳ ለንባብ አብቅተናል።
የአካባቢው ነዋሪዎች በብዛት የሚያቀርቧቸው ምክንያቶች በአንድም ይሁን በሌላ ተቀራራቢ ናቸው። ነገር ግን ተበድለናል የሚለው የበደላቸውን ጥግ ለመግለፅ የተለያዩ ቃላትን ተጠቅመው ይሆናል እንባቸውም የብሶታቸው መገለጫ ነው። ‹‹አቡ ጨፌ›› በሚባለው አካባቢ ለዘመናት ኖረናል የሚሉት ነዋሪዎቹ ለልማት ይፈለጋል በመባሉ ምክንያት የመተዳደሪያ መሬታችን እና በዓመት ሦስት ጊዜ ከምናመርትበት የጥሪት መሰረታችን ከሆነው ለም መሬት ተፈናቅለን የበይ ተመልካች ሆነናል ይላሉ።
‹‹የተወሰደው መሬት የምትታለብን ላም ከአንድ አርሶ አደር ቤት ከመውሰድ ቢገዝፍ እንጂ አይተናነስም ››ሲሉ የችግራቸውን ግዝፈት ለመግለፅ ይሞክራሉ። ከምን በላይ የሚያንገበግባቸው ደግሞ በወቅቱ ካሳ ተብሎ የተከፈላቸው በፍፁም ተቀባይነት የሌለውና ሁሉንም ነገር በጉልበት እንደነበር ያስታውሳሉ። በርካቶቹ አርሶ አደሮች በመሆናቸው በማስፈራራትና በግድ በማስፈረም የተከናወነ በመሆኑ፤ የሰብዓዊ መብታቸው ጥሰት እንደተፈፀመባቸው ይነገራሉ።
ለዓመታት ቅር ተሰኝተው ግማሹ ጥቂት ካሳ ወስዶ ከፊሉ ደግሞ ምንም ሳይወስድ በቁዘማ ውስጥ ዛሬም ድረስ በችግር ውስጥ መሆናቸውን ይነገራሉ። ለዚህም አስረጅ የሚሉትን በሙሉ ነዋሪዎች እንዲህ ያቀርባሉ።
በወረዳው የምክር ቤት አባል ነኝ ይላሉ ወይዘሮ አስካለ አያሌው። ይህ በደል ለዓመታት በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ የፈጠረ ስለመሆኑ ጠንቅቄ አውቃለሁ ይላሉ። ይህም ብቻ ሳይሆን እኔም በዚህ ሰበብ ከፍተኛ በደል እየደረሰብኝ ነው ባይ ናቸው። የአካባቢው ማህበረሰብ 10 ዓመት ሙሉ በደል ደርሶብናል፤ የመንግስት አካል ወረድ ብሎ ሊመለከተን ይገባል። እዚህ አካባቢ እንባ ጭምር ተመልካች አጥቷል ይላሉ።
እንደ ወይዘሮዋ ገለፃ፤ የአካባቢ ነዋሪዎች ቀደም ሲል በዓመት ከሦስት እስከ አራት ጊዜ ጎመን፣ ቲማቲም፣ ድንች፣ ቃሪያ እና የመሳሰሉትን እያለሙ ከእለት ጉርሳቸው ተርፎ ለነገ በማለት ይቆጥቡ እንደነበር ያስታውሳሉ። ከአቃቂ ቃሊቱ ፍራፍሬዎችን እና የጓሮ አትክልቶችን ወደ ፒያሳ አትክልት ተራ በመላክ ጠቀም ያለ ገንዘብ ከማግኘታቻው በተጨማሪ የተደላደለ ሕይወትም ይመሩ ነበር። ዳሩ ግን በልማት ስም ቦታውን እንዲለቁ ከተደረገ በኋላ እና ተመጣጣኝ ያልሆነ ካሳ እንዲወስዱ ከተወሰነባቸው በኋላ በርካቶች ለከፋ ድህነት ተጋልጠዋል፤ የመንግስት እጅ ጠባቂ ሆነዋል፤ ግማሹ ደግሞ ለሰው መትረፉ ቀርቶ የቀን ሠራተኛ ሆነዋል ሲሉ የአካባቢ ነዋሪዎች ይናገራሉ።
እኔም የወረዳው ምክር ቤት አባል እንደመሆኔ መጠን ጉዳዩን ደጋግሜ ሳነሳው ተቀባይነት አጥቻለሁ። ስለጉዳዩ ደጋግሜ ማንሳቴ ለሌላ ችግር ዳርጎኛል። በተለይም ደግሞ ነዋሪዎች መብታቸውን እንዲጠይቁ ትገፋፊያለሽ፤ የልማት ተቃዋሚ ነሽ በሚልና በሌላ ሰበብም በነገር ሸንቆጥ እንደሚያደርጓቸው ይጠቁማሉ። ይህም ብቻ ሳይሆን ይባስ ብሎ በገዛ ግቢያቸው ውስጥ ቤት ለመገንባት ፈቃድ ቢጠይቁም ተከልክለዋል። ሌላው ቀርቶ የመኖሪያ ቤታቸውን ለማደስ በአየር ካርታ እና መሬት ካርታ አይናበብም በሚሉ ተልካሻ ሰበቦች ምንም መስራት እንዳይችሉ መደረጋቸውን ይናገራሉ። ለግንባታ ብለው የገዙት አሸዋ እና ጠጠር በዓመታት ብዛት ጥቅም አልባ ሆኖ ሳር እንደበቀለበት በመጠቆም፤ አሁንም የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው ማሳሰብ እፈልጋለሁ፤ እንደ ምክር ቤት አባልነቴም በህጋዊ መንገድ መጠየቄን አላቆምም ብለዋል።
ከወቅቱ የኮሚቴ አባል እና ከነዋሪዎች አንደበት
ይህ ችግር ዓመትን ያስቆጠረ እና አሁንም ድረስ እልባት ያልተሰጠው ግን ደግሞ በየጊዜው ተደጋጋሚ ጥያቄ ያልተለየው መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ በወቅቱ የካሳ ክፍያ ኮሚቴ አባል የነበሩት አቶ ደሳለኝ ንስሮ ናቸው። ችግሩ የተወሰኑ ግለሰቦች ብቻ አይደለም፤ እኛ ኮሚቴዎች ጭምር ፍዳ የበላንበት ነው ሲሉ ያሳለፉትን የድካም ጊዜ ያስታውሳሉ ።
በወቅቱ የኮሚቴ አባል ብንሆንም ብዙ ትግል ሳደርግ ነበር የሚሉት አቶ ደሳለኝ ይህ ሁሉ ፈተና ደርሶብን አንዳችም ጠብ ያለነገር ሳናገኝ ይኸው ከዛሬ ደርሰናል ይላሉ። አሁንም ቢሆን ተስፋ አንቆርጥም ይልቁንም ህጋዊ መብታችን ለማስበር በተቻለ መጠን የአቅማችንን ሁሉ ተጠቅመን በህጋዊ መስመር ለመጠቀም ጥረት እናደርጋለን ብለዋል።
በወቅቱ ኮሚቴ ሆነን ይህ የካሳ ግምት ፈጽሞ አግባብ አይደለም ብለን ተቃውመናል። የአካባቢ ማህበረሰብ ልማት ቢፈልግም ከኑሮ መሰረቱ የሚያናጋውን ልማት ግን አንፈቅድም ብለን ተከራክረናል። እነርሱ ግን እኛን ለማሞኘት ብዙ ነገር ብለውናል። በሰፈራችሁ ትምህርት ቤት ይገነባላችኋል፤ ውሃና መብራት ይቀርብላችኋል፤ ጤና ጣቢያና ሌሎች መሠረተ ልማቶችም ይሟሉላችኋል ብለው ሊያረጋጉን ሞከሩ፤ ቃልም ገቡ ይላሉ። ቃል ከገቡት ውስጥ ግን የመስመር ውሃ አግኝተናል፤ ከዚያ ውጭ ሌላው የተገባልን ቃል የውሃ ሽታ ሆኗል።
እኛም በወቅቱ አንፈርምም ወይንም ደግሞ ይህ አግባብ አይደለም ስንላቸው የበላይ አመራሮች የነበሩት በከፍተኛ ደረጃ እያስፈራሩን፤ ግዴታ ያለመንበትን ነገር አድርጉ ብለውን ከህዝቡም ከራሳችን አጣልተውናል፤ አመኔታም እንድናጣ አድርገውናል ይላሉ። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ህዝቡን የሚሰማ መንግስት በመኖሩ መፍትሄ ሊሰጠን ይገባል።
አቶ ፀጋዬ ሽኩሬ ፍትህን ፍለጋ ከ10 ዓመት በላይ መንገላታታቸውን ይገልፃሉ። እስከዛሬዋ ቀን ድረስ ይህን ጉዳይ አታንሳ በሚል ከአንዳንድ ኃላፊዎች ማስፈራሪያ እና ዛቻ እየደረሰባቸው ስለመሆኑ ይናገራሉ። የመንግስት ልማትን ደግፈን ታዛዥ መሆናችን ችግር ይዞብን መጥቷል ባይ ናቸው። በወቅቱ የተባልነው ለአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን መስመር የሚዘረጋበት አካባቢ በመሆኑ የተወሰነ የእርሻ ቦታ ልቀቁ ብለውን በወቅቱ በደስታ ለቀናል።
መንግስት የሚሰራው ልማት በእጅጉ እንደግፋለን፤ በቀጣይም ልማት እንሻለን የሚሉት አቶ ጸጋዬ በርካቶችን እያፈናቀሉ ጥቂቶችን ብቻ ለማበልጸግ የሚፈፀም ስውር ወንጀል መቆም አለበት መንግስትም ችግራችንን ሊሰማ ይገባል ሲሉ ይናገራሉ። የ10 ዓመት ካሳ ተብሎ የተሰጠው እኛ በአንድ ዓመት ውስጥ የምናገኘው ሲሆን በአንድ ካሬ 37 ብር ታስቦ ነው የተሰጠኝ። ይህ ደግሞ በየትኛም ሳይንሳዊ መመዘኛ ተቀባይነት የሌለውና የወቅቱ አመራሮች በማስፈራራት የፈፀሙት ስለመሆኑ መረጃዎቹ በራሳችው ምስክሮች መሆናቸውን ይገልጻሉ። መሬታችሁ 10 ዓመት የሚሰጠውን ምርት አስበን ካሳ ከፍለናል ብለው ቢያስፈርሙንም የተሰጠን ካሳ ግን የአንድ ዓመት ብቻ ነበር ይላሉ። በዚህ ውስጥ ደግሞ እኔን ጨምሮ ካሳ ለወሰድነው፤ የዕጽዋት ግምት ያልተገመተልን አለን፤ እስካሁንም ከበደል ጋር እየኖርን ነው ብለዋል።
ተክሉ ንስሮ እና ኢንስፔክተር አብረሃም ፉጄ ለዓመታት የበደሉን ቀንበር ተሸክመን ይኸው ዛሬ ደርሰናል ሲሉ የምክር ቤቱን እና የወቅቱ የኮሚቴ አባላትን ሐሳብ ይጋራሉ። ዳሩ ግን ዛሬም ድረስ ችግሩ እንደ ችግር ከመወራት የዘለለ መፍትሄ አለመገኘቱ ግን ያንገብግባቸዋል።
‹‹የወተት ላም ተቀምተን ወተት እንዲያምረን፤ ኑሮ እንዲመረን ያደረገ ሥርዓት ነበር››፤ አሁንም የዚያ ሥርዓት ርዝራዦች በመኖራቸው በደላችንን እንኳን በመናገራችን እየመጡ ያስፈራሩናል። ይህን ጉዳይ ወደፈለጋችሁበት ብትወስዱትም የተለየ ነገር አታመጡም አርፋችሁ ኑሯችሁን ብትመሩ ይሻላችኋል እያሉ እንደሚያስፈራሯቸው ነው የሚናገሩት።
ኢንስፔክተር አብርሃም በወቅቱ በፖሊስ ሙያ ውስጥ ያገለግሉ እንደነበርና ጉዳዩን ሲከታተሉ እንደነበር ያስታውሳሉ። ዳሩ ግን በአጭር ጊዜ እልባት ይሰጠዋል የተባለው ጉዳይ ያለአንዳች መፍትሄ ዓመታትን ማስቆጠሩ እንዳሳዘናቸው ይጠቁማሉ።
በተለይም እንዳንዱ ድርጊት በምን ህግና ደንብ እየተከወነ ነው ብሎ ለሚጠይቃቸው መንግስት የወሰነው ነው ከማለት ውጭ የተለየ ህጋዊ አሰራር መከተል ያልፈለጉ አመራሮች እንደነበሩ ያስታውሳሉ። ዳሩ ግን ችግሩ እየተንከባለለ መጥቶ አሁንም መፍትሄ አለማግኘቱ ደግሞ የበለጠ አግራሞት እንደፈጠረባቸው ያስረዳሉ።
ሌላው ችግር
ይህም የካሳ ጉዳይ አልበቃ ብሎ እንደገና አካባቢውን የሚቀራመቱ ባለሃብቶች መንደሩን መክበባቸውንና የአካባቢውን ነዋሪዎች ያላማከለ እና በልማት ያላቀፈ ነውር እየፈፀሙ ተመልካች አጥተናል ይላሉ። አካባቢው ለትልልቅ ግንባታዎች የሚውል ልዩ ድንጋይ በአካባቢው አጠራር ‹ካባ›› የታደለ ቢሆንም ነዋሪዎች ከበረከቱ ከመቃመስ ተከልክለው ከመንግስት ጋር ሆድና ጀርባ እየሆኑ መጥተዋል።
ጥቂት ግለሰቦች ከመንግስት ፈቃድ አለን በሚል ሰበብ ብቻ አካባቢውን እየቆፈሩ በጉልበት እየወሰዱብን ነው። ሌላው ቀርቶ እኛ ያደግንበት፣ የተወለድንበት እትብታችን የተቀበረበት እንስሳቶቻችን ይወሉበት የነበረ የጋራ ሃብታችንና ንብረታችን ነው ብለን ለሚመለከተው ሁሉ አቤት ብንልም ሰሚ አጥተናል። ይህ ሁሉ ሆኖም ካሳ ይከፈለን ስንል ይከፈላችኋል ከመባል የዘለለ በተግባር ጠብ የሚል ነገር አለመኖሩ አሳዛኝና ህዝብና መንግስት ሆድና ጀርባ ያደረገ ልማት ነው በማለት ይኮንናሉ።
ቀደም ሲል የአካባቢው ነዋሪዎች ተደራጅተው ካባው አውጥው ይሸጡ እንደነበርና በዚያው መንገድ ተደራጅተው አሁን መስራት እንደሚችሉ ይጠቁማሉ። ነዋሪዎች ግን ከምንም በላይ አንድ ነገር ይጠይቃሉ። አንድ ግለሰብ ወይንም ድርጅት ባለሃብት በሚል ካባ ፈቃድ ሲሰጠው መስፈርቶቹ ምንድን ናቸው ሲሉ ይጠይቃሉ። ባለሃብት የቴክኖሎጂ ግብዓትና ሽግግር ካልጨመረ እና መሬት ውስጥ ብቻ ያለውን ድንጋይ ቆፍሮ ማውጣት ከሆነ ከእኛ ከአርሶ አደሮች የተለየ ብቃትና ብልሃቱ ከምን ላይ ነው ሲሉ ይጠይቃሉ። የአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ግብግብ በመግጠም ጥዋትና ማታ ፖሊስ እያቆመ ድንጋይ የሚያሸሹ ግለሰቦች እንዴት ባለሃብት ተብለው ሊጠሩ ይችላሉ፤ ከህዝብ ተጣልተው ለማንስ ይሠራሉ፤ ይህ ኢንቨስትመንት ሳይሆን በጠራራ ፀሐይ አርሶ አደሮችን መበዝበዝ ነው ሲሉ ምሬታቸውን ይገልፃሉ። አስገራሚ የሚሆነው ደግሞ ካባ ድንጋይን ሲያወጡ አካባቢው ላይ ያለውን አትክልት ከማበላሸትም በተጨማሪም በስፍራው ትልቅ ጉድጓዶችን ትተው ለህዝብ ሌላ መከራ እየጨመሩ መሆናቸውንም ያብራራሉ።
በወቅቱ የነበሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል
በወቅቱ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ድረስ በመሄድ ካሳ እና አርሶ አደሮችን ቅሬታ አስመልክቶ ህዝቡን ማወያየታቸውን የሚያስታውሱትና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበሩት ዶክተር ተመስገን ቡርቃ፤ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ስር ያሉ በርካታ አርሶ አደሮች ቅሬታ ማቅረባቸውንና መፍትሄ እንዲሰጣቸው አቅጣጫ መቀመጡን ይጠቁማሉ። በወቅቱ በአብዛኛው ይነሳ የነበረው ችግር የካሳ ግምቱ በጣም ዝቅተኛ ስለሆነ ፍትሃዊ አሰራር ይንገስ በሚል የቀረበ መሆኑን በማስታወስ መጨረሻ ላይ ግን ለልማት ሲባል የተፈናቀሉ አርሶ አደሮችን በተመለከተ በመንግስት ይሁንታ ጽህፈት ቤት እስከማቋቋም የደረሰ ነው። በመሆኑም የአርሶ አደሮቹ ችግር በዚህ አግባብ እንደሚፈታ እገምታለሁ ባይ ናቸው።
ምላሽ – የክፍለከተማው ዋናስራ አስፈፃሚ
ዶክተር አበራ ብሩ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዋና አስፈፃሚ ናቸው። የመልካም አስተዳደር ችግር በክፍለ ከተማው በስፋት መኖሩን የሚናገሩት ዶክተር አበራ፤ በክፍለ ከተማው አቡጨፌ አና መሐመድ ካፌ የሚባሉ ካባ የሚወጣባቸው ስፍራዎች መኖራቸውንና ነባር መሆናውንም ይገልጻሉ።
እዚህ ላይ ሁለቱም በራሳቸው ነባር ካባ (የድንጋይ መፍጮ) ናቸው። ይሁኑ እንጂ በዚህ አካባቢ የሚነሱ ጥያዎች መልክ ብዙ ናቸው። አንደኛው ማህበረሰቡ እኛ ራሳችን ካባውን አውጥተን ለመንግስትም አካል ይሁን ለሚፈለገው አገልግሎት ማዋል እንችላለን የሚል ነው። ሌላኛው ቅሬታ ደግሞ ካባውን ለማውጣት በሚደረግ ጥረት ፈንጂዎች መሬት ውስጥ ስለሚቀበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች በከፍተኛ ድምፅ እየረበሸ እና በህፃናትን ላይ ጭምር ከፍተኛ ድንጋጤ እያሳደረ ነው የሚል ተደጋጋሚ ቅሬታ ነበር። አካባቢውን እያወከና ለጤናችንም ትልቅ እክል እየፈጠረ ነው። ፍንዳታው የቤት እቃ እስከመስበር ደርሷል የሚል ነው።
ካባው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማ ከሚገኙ 13 ወረዳዎች መካከል በስምንቱ ውስጥ ይገኛል። ነገር ግን የወረዳ ስምንት ነዋሪዎች ለየት የሚያደርገው የራሱ የሆነ ምክንያት ሊኖር ይችላል። ነዋሪዎቹ ካሳ አልተከፈለንም በሚል በተደጋጋሚ ላቀረቧቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ጥረት ተደርጓል። በዚህም የተነሳ ለነዋሪዎቹ ካሳ እንደሚከፈል የማስተማመኛ ወረቀት ተሰጥቷቸዋል። ካሳ የሚጸድቀውም በከተማ አስተዳደሩ ሲሆን የክፍለከተማው መሬት አስተዳደር በሥርዓት ልኬቱን ሰርቶ መላኩን ይናገራሉ። ከዚህ በዘለለ ግን በአካባቢ ካባ እያወጡ ያሉ አካላት በየትኛው መንገድና ሁኔታ ለማየት በተደረገው ጥረት ሁሉም ህጋዊ መሆናቸው ያረጋግጣሉ። በመሆኑም አርሶ አደሮቹ ለሚያቀርቡት ቅሬታ ካሳ ከተማ አስዳደሩ በሚወስነው መሰረት የሚከፈል ይሆናል ብለዋል።
ዳሩ ግን የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ለምን ይሆናል ሲል ይጠይቃል። ‹‹አርሶ አደሮቹ ግብር ሲከፍሉበት በነበረበት ቦታ እና በቀጣይም ጥሩ ገቢ እናገኝበታለን ብለው በሚያስቡት ቦታ ላይ ምንም ግብር ሳይከፈል ለአልሚ መሰጠቱ ከህግና ከሞ ራል አኳያ እንዴት ይታያል፤ ባለሃብቱ እየተጠቀመ አርሶ አደሮቹን ካሳ ይከፈላችኋል ጠብቁ ብሎ ማንገላታት ህጋዊ ነውን፤ ባለሃብቶቹ ለአካባቢው ማህበረሰብ አንዳች የሚፈይድ ነገር ሳይሰሩ ካባ ብቻ አውጥተው መሄድ በምን አግባብ ይታያል ሲል ይጠይቃል። በተጨማሪም ካሳው መቼ እንደሚከፈላቸው እርግጠኛ ባልሆኑ አርሶ አደሮችና ቤተሰቦቻቸው ላይ ለሚፈጠር ሥነ-ልቦናዊ ጫና ማንስ ይጠየቃል ሲል ነበር ጥያቄውን ያቀረበው?
የትኛው የካሳ አሰራር በመን ግስት ህጋዊ አሰራር የሚመራ ሲሆን ከፋዩም መንግስት ራሱ ነው የሚሉት ዶክተር አበራ፤ ነገር ግን በቦታው የሚያለማው ባለሃብት ከመንግስት የሚጠበቅትን ግዴታ መወጣት አለበት። ይህን በማድረግ በኩል ባለሃብቶቹ ህጋዊ አግባብ ተከትለው እየሰሩ ስለመሆኑ ያገኘነው መረጃ ያረጋግጣል። አሰራሩ ይህ ከመሆኑም በተጨማሪ እኛ በአሁኑ ወቅት የሰጠው ካባ የለም፤ በአሁኑ ወቅት እያወጡ ያሉት ቀደም ሲል የወሰዱት ፈቃድ ስለሆነ ይህን ስራ አቁሙ ማለት አይቻልም። ይሁንና በአሁኑ ወቅት ካባ የማውጣት ፈቃድ የሚሰጠው ከማዕከል ነው ይላሉ። በመሆኑም ግብዓቱ ያለበትን ቦታ መረጃ ከመስጠት የዘለለ ሥራ አንሰራም። ከዚህ በተረፈ ግን ነዋሪዎችም የሚሉት ካሳው ዘገየ ነው፤ ይህ ጥያቄያቸው ግን ህጋዊና አግባብ ነው ከተማ አስተዳደሩ በተላከለት መረጃ መሰረት ወደታች ሲያወርደው በቅጽበት የሚከፈላቸው ይሆናል። ከዚህ በዘለለ ግን አልሚዎቹ ካባውን እያወጡ ያሉት መንግስት ለሚያከናውናቸው የመንገድ መሰረተ ልማትና ለመሳሰሉት ስለሆነ ሥራውን አቁሙ ማለት ችግሩን የባሰ ውስብስብ ማድረግና ልማቱን ማደናቀፍ እንደሆነም ያብራራሉ።
ዶክተር አበራ እንደሚሉት አቡ ጨፌ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎችም ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ የሚያቀርቧቸው ጥያቄዎችም በራሱ ማዕቀፍ የሚታይ መሆኑን ያብራራሉ። በወቅቱ ካሳ የተከፈላቸው ቢሆንም በቂ አለመሆኑን መረዳት ተችሏል። 10 ዓመት ሙሉ በካሳ ጉዳይ ጥያቄ እያቀረቡ ስለመሆኑ በቂ መረጃ የለኝም፤ ነገር ግን ጥያቄያቸው ካሳ ይከፈለን ሳይሆን የካሳ ልዩነት ይከፈለን የሚል ነው። ይህም በወቅቱ የተሰጠው የካሳ ግምትና በአሁኑ ወቅት ያለው ግምት እንደማይገናኝ መረዳት ችለናል ይላሉ። ካሳ ልዩነቱም እንደሚከፈል ከግምት ውስጥ ማስገባት የተቻለ ሲሆን፤ ለዚህም የማስተማመኛ ደብዳቤ የተሰጠ መሆኑን እናውቃለን።
እንደ ዶክተሩ ማብራሪያ፤ አርሶ አደሩ ዕትብቱ የተቀበረበትን ሰፈር እስከ መጨረሻው ሲለቅና ሲፈናቀል ሲሰጠው የነበረው ካሳ መልሶ የሚያቋቁማቸው አይደለም። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የልማት አካሄድም ፍትሃዊነት የጎደለው እንደነበር ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻልና ይህ ምንም አጠያያቂ እንዳልሆነ ይጠቁማሉ።
በነበሩ ፕሮጀክቶች ላይ ይዞታቸው ለሌላ አልሚ ወይንም የመሬት ባንክ የገባ መሬት መሆኑ ይታወቃል። ይሁንና ካሳ ልዩነት የሚከፈላቸው በወቅቱ ከነበረውና በአሁኑ ወቅት ካለው ግምት ጋር በማነፃፀር ነው። በወቅቱ አንድ ካሬ ከ60 ብር በማይበልጥ ግምት የተሰጣቸው ሲሆን ይህ ግን በአሁኑ ወቅት ማስተካከያ ተደርጎ የግጦሽ ወይንም እርሻ ሲሆን በካሬ ተሰልቶ 1800 ብር ይከፈላል። በመሆኑም በዚህ መሃል ለው ልዩነት ሲታይ እንደተከፈለ አይቆጠርም። ‹‹አንዳንድ ቦታ እየተጠየቀ ያለው ግን የካሳ ክፍያ ብቻ ሳይሆን የቀድሞ መሬታችንን መልሱልን የሚል ነው። አንድ ግን መታወቅ ያለበት ጉዳይ በሦስተኛ አካል ወይንም እጅ የገባ መሬት ወደ አርሶ አደር የመመለስ ዕድል የለም›› ብለዋል።
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በርካታ መልካም አስተዳደር ጥያቀዎች መኖራቸውን ይጠቁማሉ። ለአብነትም የኢንዱስትሪ መንደር በቂሊንጦ ሲቋቋም ከነጭራሹ ካሳ ያልተከፈላቸው አርሶ አደሮች አሉ። የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር በአቃቂ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 የገነባው ግንባታ ላይ አንዳች ካሳ አልከፈለም፤ ይሁንና በርካታ አርሶ አደሮች ተፈናቅለዋል። ከዚህም በተጨማሪ ከካሳ ጋር በተያያዘ ጥያቄ የሚያቀርቡ መኖራቸውንና እነዚህን በመረጃ ላይ በመመስረትና በማጥራት ካሳ እንዲከፈላቸው የከተማ አስተዳደሩ ወስኖ ወደ ሥራ መግባቱን ያረጋግጣሉ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 5 /2015