በቅድሚያ፤
ርዕሱን የተዋስኩት ጎምቱው የሕግ ምሁር ከጻፉት መጽሐፍ ላይ ነው። ደራሲው በሳል የሕግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሽፈራው ወልደ ሚካኤል ናቸው። ከጀማሪ የሕግ ባለሙያነትና ከሕግ ት/ቤት መምህርነት እስከ የአገሪቱ የፍትሕ ሚኒስትርነት ደረጃ በመድረስ ሕዝባቸውን በቅንነት ያገለገሉት እኚህ አርአያ ሰብ ስለ ማንነታቸውና ስለ አገልግሎታቸው በዚሁ ጋዜጣ ጥቅምት አጋማሽ 2014 ዓ.ም ዕትም ላይ ታሪካቸውና ዜና መዋዕላቸው በሚገባ ተመዝግቦ አንብበናል።
እኚህ የአገር ፈርጥ የሆኑት አባት ለመጽሐፋቸው የሰጡት ርዕስ “የሰው ተመኑ ስንት ነው?” የሚል ነው። ሞጋች ብቻም ሳይሆን ወደ ይዘቱ ጠልቆ እስኪገባ ድረስ ብዙ ግርታ የሚፈጥሩ ጥያቄዎች በአእምሯችን እንዲብላሉ ምክንያት የሆነው ይህ መጽሐፍ ዕድሉ ባላቸው አንባቢያን ቢነበብ ፋይዳው እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ ጸሐፊው ምስክርነቱን ይሰጣል።
ይህ ዓምደኛ ለዚህ ጽሑፉ የተዋሰው የመጽሐፉን ርዕስ እንጂ በይዘቱ ላይ ሙሉ ዳሰሳ ወይንም ሥነ ጽሑፋዊ ሂስ ለማድረግ አልተዘጋጀም። እንዳስፈላጊነቱ ወደፊት ጊዜው ሲፈቅድ በይዘቱ ላይ አንዳንድ ሙያዊ ምልከታዎችን ለማድረግ ይሞከራል። ርዕሱን ለመዋስ ሁለተኛው ዋና ምክንያት ታኅሣሥ 1 ቀን 2014 ዓ.ም እኚሁ ደራሲ ከአፍ እስከ ገደፉ ጢም ብሎ ለተሰበሰበ ታዳሚ በመጽሐፉ ርዕስ ላይ በመመሥረት መሳጭና አስተማሪ ንግግር ሲያደርጉ ይህ ዓምደኛም በጉባዔው ውስጥ ተገኝቶ ስለነበር መልዕክቱ ልቡ ውስጥ ጠልቆ ስለገባ ለአንባቢያኑ ማጋራቱ ጠቃሚ መስሎ ስለተያው ነው። ርዕሱንና መሪ ሃሳቡን ላዋሱን ደራሲ ምሥጋናችን ይድረሳቸው።
የችግሮቻችን አበዛዙ፤ የመፍትሔ ሙከራችን ማነሱ፤
ይህ ብዕረኛ ለዚህ ታሪካዊ ጋዜጣ ቤትኛና ተባባሪ ዓምደኛ በሆነባቸው ባለፉት 30+ ዓመታት በብዕረ መንገድ ጉዞው ውስጥ ያላነሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች ስለመኖራቸው እርግጠኛ ለመሆን ይቸገራል። ከኪነ ጥበባ ሂስ እስከ የዕለት ተዕለቶቹ ሰፋፊ ማሕበራዊ ጉዳዮች፣ ከፖለቲካችን ቱማታ እስከ ኢኮኖሚያዊ ትርታችን፣ ከፍልስፍና እስከ ሃይማኖቶች ፋይዳ፣ ከግል የንባብ ተሞክሮ እስከ የውጭ ጉዞ ዜና መዋዕሎች ወዘተ. በምልከታው ላይ ገደብ ሳያደርግ የብዕሩን ቱሩፋት ለአንባቢያን ያለ ስስት ለማቅረብ ሙከራ አድርጓል።
በእነዚህ ረጅም ዓመታት ውስጥ ይህ ጸሐፊ የተረዳው መሠረታዊ እውነት የፖለቲካችን የግልፍተኝነትና የተለዋዋጭነት ባህርይና አካሄድ ግራ የተጋባ መሆኑንና ግራ እንዳጋባን መኖራችንን በተቀዳሚነት ይጠቅሳል። የኪነ ጥበባቱ ተፈጥሯዊ ሥሪትም አንዴ ጋል አንዴ ቀዝቀዝ የማለት ተፈጥሮ ስላለው ለስክነት ባዕድ መሆኑን ለማስተዋል ማናችንንም አይገድም። በየጊዜው ግርሻው እየተነሳ የሚታመመውና እኛንም ለማይድን ሕመም የዳረገን የኢኮኖሚችን ጉዳይም ዛሬም አልጋ ላይ ወድቆ እያጣጣረና እኛንም ለጣር አሳልፎ በመስጠት እንደ ጀገነ እነሆ የሌማታችንን ባዶነት እያመላከትን አቤት ማለቱን ገፍተንበታል።
አልፎም ተርፎ የዕለት እንጀራችን አዋይ ርቆት ጦም ውለን ጦም ለማደረ እስከ መገደድ ደርሰናል። “ሃይ!” ብሎ የሚያስቆመው አገራዊ ብርቱ የፖሊሲ አቅም መጥፋቱ ለእኛ ዜጎች “ዕንቆቅልህ ምን አውቅልህ” ከማለት ውጭ መፍትሔው ጠፍቶን “የእውር ድመት” ስሜት እንደተሰማን ቀን በመግፋት ላይ ነን።
የብዙኃኑ ሕዝባችን ማሕበራዊ ትሥሥር ድርና ማግ በጥቂት እኩያን ክፉ ድርጊቶች እንዲነትብ የሚደረገው የሌት ተቀን የሴራ ሽረባና ተግባርም መልኩና ገጽታው ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲወሳሰብ እንጂ ሲረግብ ለማየት አልታደልንም። የሃይማኖቶቻችንና የሃይማኖት መሪዎቻችን የእምነት ጉልበት ላልቶ ሲልፈሰፈስ እያየንም ፈጣሪን በመሞገት “ለምን? እንዴት?” እያልን በዕለት ጸሎታችንና ሱባዔያችን መሞገታችን አልቀረም።
ከላይ በተዘረዘሩት መልከ ብዙ ጉዳዮች ዙሪያ ይህ ጸሐፊ የዕውቀት አቅሙ የፈቀደውን ያህል ትዝብቱንና ቁጭቱን “መፍትሔ ከሚለው ግምቱና እምነቱ ጋር” ባለመታከት “ይድረስ ለአንባቢያን” እያለ ሲቃትት መኖሩ ለዚህ ጋዜጣ ቤተሰቦች እንግዳ አይሆንም። በዚህ ሁሉ የዓመታት ጉዞው የተማረው ትልቁ ቆም ነገር “ከሞከረነው ይልቅ ያልሞከርነው ነው የሚቆጨን” የሚለው አባባል እውነት መሆኑን ነው።
ከተዘረዘሩት አገራዊ ፈተናዎቻችን በከፋ ሁኔታ ግን ዛሬ ዛሬ እየሰማንና እያስተዋልን ያለነው ወቅታዊው የልብ ስብራታችን እጅግ የመረረ ስለሆነ በእርሱ ጉዳይ ላይ እንደለመድነው የምንቆዝመው የተዋስነውን ርዕሰ ጉዳይ ከሃይማኖታዊ እውነታዎች ጋር በማጎልበት ይሆናል። መቼም ለሰው ልጅ ዋና መጽናኛው ሃይማኖቱም አይደል።
የተዛነፈው የሰብዓዊነት መስፈርት፤
ከአሁን ቀደም ለማስታወስ እንደተሞከረው በዘጠና ዘጠኝ ነጥብ ምንትስ መቶኛ ስሌት መሠረት የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ በየሃይማኖቶቹ ጥላ ውስጥ የተጠለለ መሆኑን የስታስቲካችን መረጃዎች በይፋ ያረጋግጡልናል። በአጭሩ “የሃይማኖት የለሽ” ዜጎቻችን ቁጥር እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም እምነት የለንም የሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ይጠፋሉ ተብሎ ግን አይገመትም። የአምልኳቸው ባህርይና የተመላኪው ምንነት ልዩነት ይኖረው ካልሆነ በስተቀር “ሥጋና ነፍሳቸውን” ያቆራኙበት አንድ “የእኔ” የሚሉት ተመላኪ (ገንዘብ፣ ዕውቀት፣ ጉልበት ወዘተ. ሊሆን ይችላል) ሳይኖራቸው ይቀራል ለማለት ግን ያዳግታል።
በየትኛውም አገርና የዓለም ክፍል የሚገኙ የተጻፉም ይሁኑ ያልተጻፉ ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎችና ቀኖናዎች በጋራ ከሚያምኗቸው መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል አንዱና ዋነኛው የሰው ልጆች የፍጥረት መነሻ አፈር መሆኑን ነው። ይህ አዳማዊ የአፈር ገላ በፈጣሪ እስትንፋስ ነፍስ መዝራቱና የሕይወቱ ፍጻሜ የሚደመደመውም ከወጣበት አፈር “ግባ መሬቱ!” እየተፈጸመ መሆኑ በጽኑ ይታመናል። ሟቹን በድናቸውን የሚቀብሩትም ሆኑ የሚያቃጥሉ ሃይማኖቶች ይህንን እውነታ በፍጹም አይክዱትም።
የአይሁዶቹና የክርስቲያኖቹ ቅዱስ መጽሐፍ አስረግጦ የሚያስተምረው ይህንኑ እውነታ ነው። እንዲህ በማለት “ያህዌ/እግዚአብሔር አምላክም ሰውን (አዳምን) ከምድር አፈር አበጀው በአፍንጫውም ሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ” (ዘፍጥረት 2፡7) ከአዳም በኋላም የሰው ዘር በሙሉ በአንድ ወንድና ሴት ግንኙነት ሰው ሆኖ በማህፀን ውስጥ መፀነሱ የተገለጸውም እንዲህ ተብሎ ነው።
”አቤቱ ‘አምላኬ ሆይ!’…በእናቴ ሆድ ውስጥ
ሰውረኸኛል፣
ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬያለሁና
አመሰግንሃለሁ።
ሥራህ ድንቅ ነው፤ ነፍሴም ታውቀዋለች።
እኔ በስውር በተሠራኹ ጊዜ፣
አጥንቶቼ ከአንተ አልተሰወሩም።
ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ።
የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ፣
አንድ እንኳ ሳይቀር በመጽሐፍ ተጻፉ። (መዝሙር 139፡13-16)።
በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ተብራርቶ የተገለጸው የሰው ዘር ዘፍጥረትና ወደ አፈር የመመለስ ፍጻሜ ብቻም አይደለም። ከፈጣሪ የተሰጠውን ክብርና ሥልጣንንም በተመለከተ እንዲህ ተጽፏል።
”ታስበው ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው?
ትጎበኘው ዘንድስ የሰው ልጅ ምንድን ነው?
ከመላእክት እጅግ ጥቂት አሳነስኸው፤
በእጆችህም ሥራ ላይ ሾምኸው፤
ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዛህለት‘
(መዝሙር 8)።
ክቡሩ የሰው ልጅ “ከመላእክት ጥቂት ብቻ ያነሰ” ፍጥረታዊ ባህርይ እንዳለው ማረጋገጫውን የሰጠው ቅዱስ መጽሐፍ ስለሆነ ለጥርጥርና ለክህደት የሚጋብዝ አይደለም። እያንዳንዱ የሰው ልጅ የሁሉን ቻይ ፈጣሪ ስሪት ብቻም ሳይሆን “ነፍሱም” የከበረ ዋጋ እንዳላት፤ በከንቱ የሚፈሰው ደሙም ጠያቂና ተሟጋች እንዳለው እውቀት ብቻም ሳይሆን እምነትም ጭምር ነው።
የኢስላም እምነት ቅዱስ መጽሐፍም (ቁርአን) “በአላህ ዘንድ የዒሳ ምሳሌ እንደ አደም ብጤ ነው። ከአፈር ፈጠረው፤ ከዚያም ለርሱ (ሰው) ‹ኹን› አለው። ኾነም።” (ሱረቱ አል-ኢምራን 2፡59) ልክ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉ ቁርአኑም ከአዳም በኋላ የቀጠለውን የሰው ዘር መስፋፋት የገለጸው እንደሚከተለው ነው።
“በርግጥም ሰውን ከነጠረ ጭቃ ፈጠርነው። ከዚያም በተጠበቀ መርጊያ ውስጥ የፍትወት ጠብታ አደረግነው። ከዚያም ጠብታዋን (በአርባ ቀን) የረጋ ደም እርገን ፈጠርን። የረጋውን ደም ቁራጭ ሥጋ አድርገን ፈጠርን። ቁራጯንም ሥጋ አጥንቶች አድረገን ፈጠርን። አጥንቶቹንም ሥጋን አለበስናቸው። ከዚያም (ነፍስን በመዝራት) ሌላ ፍጥረት አድረገን አስገኘነው። ከሠዓሊዎችም ሁሉ በላጭ የሆነው አላህ ላቀ” (ሱረቱ አል-ሙእሚኑን 23፡12-14)።
እናስ የሰው ልጅ የዋጋ ተመኑ ምን ያህል ይሆናል?
ከላይ የተዘረዘሩትን የቅዱሳት መጻሕፍት ጥቅሶች አብዝተን ለማስታወስ የተገደድነው ወቅታዊው የአገራችን የንጹሐን ዜጎች ጭፍጨፋ ጉዳይ በፖለቲካውም ሆነ በማሕበራዊ አረደዳችን ላይ እጅግ ግራ ስላጋባን ነው። በዛሬይቱ ኢትዮጵያ የዜጎችን ደም በከንቱ የሚያፈሱ “የደም ጥማተኞች” ቁጥርና ዓይነት እንዲህ ነው ብሎ መዘርዘሩ አዳጋች የሆነ ደረጃ ላይ መድረስ ብቻም ሳይሆን እንደ አገር “ለዛሬ ብቻም ሳይሆን ወየው ለነገ ትውልዳችን!” እያልን መቃተት ከጀመርን ሰነባብተናል።
በዚህን መሰሉ የንጹሐን ዜጎች ጭፍጨፋ ላይ የተሰማሩት “ዱር አደር” አሸባሪዎችና ሽፍቶች እንደ አሸን የመብዛታቸው ዕንቆቆልሽ መፍትሔ ለማሰብ እስከምንቸገር ድረስ ነገሮች እንደ ተወሳሰቡን ጀንበሯ መሽታ እየጠባች ነው። ለመሆኑ በፈጣሪ የፍጹም ከሃሊነት ጥበብና እውቀት የተፈጠረን የሰው ልጅ እንደ ተራ የመስዋዕት እንስሳ ሕይወቱን ሲነጥቁት፣ በአልባሌ አገዳደል እስትንፈሱን ሲያጨልሙና ግድያውን ሲያስተባብሩ በደም የጨቀየው እጃቸው አይንቀጠቀጥም? በእብሪት ሞራ የተደፈነው ኅሊናቸውስ አይወቅሳቸውም?
የሰው ልጅ የነፍሱ ተመን የሚለካውና የሚቆጠረው በሰው ሠራሹ ቋንቋ፣ ባህል ወይንም በዘሩ ማንነት እየተሰፈረ ሳይሆን የሕያው ፈጣሪ እስትንፋስ እንዳለበት በማመን ሊሆን በተገባ ነበር። ለሰው ልጅ ሰው ሆኖ መፈጠር አንዳችም አስተዋጽኦ የማድረግ አቅምም ሆነ ክህሎት የሌለው ራሱ አፈር የተሸከመ ሟች ሰው እንዴት ወገኑን በግፍ እየጨፈጨፈ እንደ ጀግና ፎክሩልኝ፣ አቅራሩልኝ፣ አዳምቁልኝ እያለ እርኩስ ድርጊቱን በአደባባይ ሊገልጥ ድፍረት ሊያገኝ ቻለ? ምሥጢሩስ ምን ሊሆን ይችላል።
የፖለቲካ የበላይነት ለማግኘት?፣ የኢኮኖ ሚውን ቀኝ እጅ ለመጨበጥ?፣ በማሕበረሰቡ ውስጥ ጀግና ተብሎ የተለየ ክብር ለማግኘት? ዘሩና ብሔሩ ወይንም ቋንቋውና ባህሉ የተሻለ ሆኖ እንዲቆጠርለትና እንዲገንለት ለማድረግ? ወዘተ. ይህ ሁሉ ምኞቱና ግቡ ከንቱ የከንቱ ከንቱ እንደሆነና “የተሸከመው አፈር ወደ አፈር ሲቀላቀል” በፈጣሪ ፍርድ ተገቢውን የግፍ ዋንጫ እንደሚጎነጭ ሊረዳውና ሊገባው ይገባል። “የማታውቁ ከሆነ የእውቀት ባለቤቶችን ጠይቁ” የሚለው ኢስላማዊ ጥቅስ እዚህ ቦታ ቢታወስ አግባብ እንደሆነ ይታመናል።
እናጠቃለው፡- የሰው ልጅ ነፍስ በሰብዓዊ ፍጡር የዋጋ ተመን የሚለካና የሚመዘን አይደለም። የነፍሱ ባለቤትና ፈጣሪ አምላክ ራሱ ብቻ ነው። እንኳንስ የፈጣሪ ዋና ጉዳይ የሆነው የሰው ልጅ ቀርቶ ሌሎች የቤት ቁሳቁሶችም ቢሆኑ ባለቤትና “የእኔ” ባይ አላቸው። “የሰው ደም የሚያፈስ ሁሉ ደሙ ይፈሳል። ሰውን በእግዚአብሔር መልክ ፈጥሮታልና” (ዘፍጥረት 9፡6)። ይህ ጠቅላይ ሃሳብ ለፍርድም ለተማጽኖም በእጅጉ በቂና ከበቂ በላይ ነው። በሌላ አቀራረብ ይገባቸው ከሆነ ለገዳዮቹም ሆነ ለአስገዳዮች የሚጠቅም አንድ አገራዊ ብሂል እናስታውሳቸው፤ “በጎች ተደጋግመው የሚበሉ ከሆነ ችግሩ ከተኩላው ሳይሆን ከእረኛው መሆኑን መጠርጠሩ አይከፋም”።
ሰላም ይሁን።
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 5 /2015