ከዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮች ሁሉ በተወዳጅነት ቀዳሚው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ስለመሆኑ አያጠራጥርም። እግር ኳስ የዓለም ቋንቋ ነው የሚባለውም ቢሊዮኖች ሃገራቸው በውድድሩ ብትሳተፍም ባትሳተፍም በአካልና በቴሌቪዥን መስኮቶች ስለሚከታተሉት ነው። የብዙዎች የልጅነት ትዝታ እና የአይረሴ አጋጣሚዎች ማህደርም ነው- ዓለም ዋንጫ። በአራት ዓመት አንዴ የሚካሄደው ይህ ውድድር የበርካታ እግር ኳስ ተጫዋቾች ሕልም፤ የሃገር ፍቅር ማሳያ፣ የሃገራት ሁለንተናዊ ስኬት መለኪያም ነው።
ዓለም ዋንጫ ከእግር ኳስ እና ስፖርታዊ ውድድርነቱ የተሻገረ ትርጉምም አለው። ማኅበራዊ ግንኙነት የሚጠበቅበት፣ ኢኮኖሚያዊ አቅም የሚፈተንበት እና ፖለቲካዊ ጉዳዮችም የሚንጸባረቁበት ግዙፍ አውድ ነው። ከሰሞኑ የዓለምን ህዝብ ዓይን፣ ጆሮ እና ትኩረት በእጅጉ የሳበችው ኳታርም ለዚህ ማሳያ ናት። በዓረብ ምድር ላይ ዓለም ዋንጫን በማዘጋጀት አዲስ ታሪክ ያስመዘገበችው ኳታር በተግባሯ ለሌሎች ተምሳሌት መሆን የምትችል ናት።
እንደሚታወቀው ሃገሪቷ የዓለም ዋንጫውን እንድታስተናግድ መመረጧ ከተሰማበት ቅጽበት አንስቶ በአብዛኛው የዓለም ሕዝብ ዘንድ የተንጸባረቀው ቅራኔ ነበር። የአዘጋጅነት ዕድሉን ያገኘችው በሙስና እንጂ በመቻሏ መሆኑን ማመን ያልፈለጉ አካላት በእጅጉ ሲያብጠለጥሏት ቆይተዋል። በዚህ እንደማይሳካላቸው ሲገባቸው ደግሞ አስቀድሞ ለስፖርት የተዘጋጀ መሠረተ ልማት ያልነበራት ሀገሪቷ በተቀመጠላት የጊዜ ገደብ ዝግጅቷን ታጠናቅቅ ይሆን የሚለውን ከጥርጣሬ የመነጨ ጥያቄ አቀረቡ። ከሚገነቡ ስታዲየሞች ጋር በተያያዘም የሰብዓዊ መብት ጉዳይን እንዲሁም ልዩ ልዩ የማሰናከያ ሃሳቦችን በማንሳት ከአዘጋጅነቷ እንድትነሳ ለማድረግ ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም። ኳታሮች ግን በቀላሉ እጅ የማይሰጡ መሆናቸውን የሚደርስባቸውን ጫና ተቋቁመው ይህን የመሰለ ታሪካዊ ውድድር በማሰናዳት አረጋግጠዋል። ለዓላማቸው የነበራቸው ጽናትና እንደ ሀገር በአንድ መቆማቸው ይበልጥ እንዲጠነክሩና የመጨረሻውን ድል እንዲያጣጥሙም ምክንያት ሆኗቸዋል።
ኳታር ለስፖርቱ በሰጠችው ከፍተኛ ትኩረት እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት ስታዲየሞችንና ሌሎች የስፖርት መሠረተ ልማቶችን ማሟላት ችላለች። ይህ የመሠረተ ልማት ግንባታ ደግሞ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማዘጋጀት የሚያስችላት ነው። ከዚህ ቀደም ሃገሪቷ ምናልባትም ትታወቅ የነበረው እንደ ሌሎች የዓረብ ሃገራት ባለጸጋዎች በአውሮፓ ታላላቅ የሚባሉ የእግር ኳስ ክለቦችን ድርሻ በመግዛት እንዲሁም ስፖንሰር በመሆን ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በቀጥታ በስፖርቱ ተሳታፊ በመሆንና ለስፖርትም አስፈላጊውን ዋጋ በመክፈል የስፖርት ውድድሮች ማዕከል የመሆን ፍላጎቷን በማሳካት ላይ መሆኗ በግልጽ እየታየ ነው።
እኤአ በ2019 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን ዶሃ ላይ ያስተናገደችው ሃገሪቷ፤ እኤአ በ2019 እና 2020 ደግሞ የፊፋ የክለቦች ሻምፒዮናንም አሰናድታ ነበር። በሌሎች ስፖርቶችም በተመሳሳይ በርካታ ሻምፒዮናዎችን የማስተናገድም ዕድል አግኝታለች። አሁን ደግሞ የዓለምን ሕዝብ በእግር ኳስ ዋንጫው አሰባስባለች። በዚህም ሃገሪቷ በቀጠናው፣ በአህጉሯ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ዕውቅና ከማሳደግ ባለፈ በቀጣይም ሌሎች ስፖርታዊ ውድድሮችን የማስተናገድ ተዓማኒነትን አግኝታለች። ይህም ኳታር እኤአ እስከ 2030 ለማሳካት ያለመችው ስትራቴጂክ እቅድ ሲሆን፤ ስፖርት ከነዳጅ ከምታገኘው 60 በመቶ ገቢዋ ባሻገር አዲስ የገቢ ምንጭ ይሆናት ዘንድ አሁንም አጠናክራ በመሥራት ላይ ትገኛለች።
ኳታር ዓለም ዋንጫውን ተከትሎ ለስታዲየሞች፣ ለሆቴሎች፣ ለመንገድና ሌሎች መሠረተ ግንባታዎች ከ220ቢሊየን ዶላር በላይ ያወጣችበት እንደሆነም ይነገራል። ይህ ደግሞ የዓለማችን ውዱ የዓለም ዋንጫ ያደርገዋል። ነገር ግን ከዚህ ውድድር ብቻ ከ6ነጥብ5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ትርፍ ታገኛለች ተብሎ እንደሚጠበቅም ዘ ኢኮኖሚክ ታይም ያስነብባል። ዓለም ዋንጫው ካወጣችው በላይ ትርፋማ የሚያደርጋት ሲሆን፤ ከአራት ዓመት በፊት ሩሲያ ካገኘችው ገቢ በ1ነጥብ3 ቢሊዮን ዶላር ብልጫ ያለው በመሆኑ በታሪክ ቀዳሚ ያደርገዋል።
ስፖርት የወቅቱ የዓለም ትኩረት የሆነውና ጭስ አልባ ኢንዱስትሪ የሚባለውን ቱሪዝምን እንደሚያበረታታም ይታወቃል። ሃገራት ከተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ መስህቦቻቸው ጎን ለጎን ቱሪስቶችን ለመሳብ በስፖርታዊ ውድድሮችንና ክንዋኔዎች ላይ እየሠሩ ነው። በመሆኑም ዓለም ዋንጫን መሰል ታላላቅ ውድድሮች ማዘጋጀት በሌላ መንገድ የስፖርት ቤተሰቡን መጋበዝ ነው። በዚህ ረገድ ኳታር ብዙ ተጠቅማለች። ሃገሪቷ ትንሽ እንደመሆኗ ያላት 2ነጥብ 6 ሚሊዮን ሕዝብ ብቻ ነው፤ ከእነዚህ መካከል የኳታር ዜግነት ያላቸው 313 ሺ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። በአንጻሩ 2ነጥብ3 የሚሆኑት ለሥራና በሌሎች ምክንያቶች በሃገሪቷ ነዋሪ የሆኑ ናቸው። በዚህ ወቅት ደግሞ የዓለም ዋንጫውን ተከትሎ ከ1ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የእግር ኳስ ወዳጆች በኳታር ከትመዋል። ከዚህም ሊገኝ የሚችለውን ጥቅም መረዳት አያዳግትም።
ዘርፈ ብዙ የሆነው ስፖርት ከውድድርና አካላዊ እንቅስቃሴነቱ ባለፈ በርካታ ጉዳዮችን እንደሚነካ ይታወቃል። አንድን ውድድር ወይም ስፖርታዊ ክንዋኔ ተከትሎ የሚገኘው ገጸበረከት ሰፊ በመሆኑ ሃገርና ሕዝብ የጥቅሙ ተቋዳሽ ይሆናል። ለአብነት ያህል ዓለም ዋንጫውን ተከትሎ የሚገነቡት ስታዲየሞች ብቻም ሳይሆኑ የአውሮፕላን ማረፊያዎች፣ ሆቴሎች፣ የገበያ ማዕከላት እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ናቸው። ይህም የውድድር አዘጋጇን ሁለገብ ሃገራዊ እድገትን የማፋጠን ሚና ይኖረዋል። በዚህ ደግሞ ዜጎች ተጠቃሚ ከመሆናቸውም ባለፈ አዳዲስ የሥራ መስኮችንም የመፍጠር ዕድሉ ከፍተኛ ይሆናል።
ምዕራባውያን ሃገራት ከዓረቦች ጋር በጥቅም ጉዳይ ካልሆነ በቀር ታሪካዊ ተቃርኖ ያላቸው ሃገራት መሆናቸው ግልጽ ነው። እንደ ዓለም ዋንጫ ያሉና በሚሊየኖች የሚቆጠሩ የስፖርት ቤተሰቦችን በአንድ የሚያሰባስቡ ውድድሮች ግን ፖለቲካን የማለዘብና ወንድማማችነትን የመቀስቀስ አቅማቸው ከፍተኛ ነው። በተለይ ሕዝብና ሕዝብን በማገናኘት፣ በባህል ልውውጥና መልካም ገጽታን በመገንባት ረገድ ሚናቸው እጅግ ከፍተኛ ነው። ኳታርም በዓለም ዋንጫ አስተናጋጅነቷ ካገኘቻቸው ጠቀሜታዎች መካከል ዋነኛው ገጽታዋን መገንባት መቻሏ ነው። ከመመረጧ አንስቶ ሲቃወሟትና በደሏን ሲያጋንኑ የነበሩ አካላት አሁን ላይ ተቃራኒ ሁኔታ መሆኗን ይረዳሉ።
የራሱ ባህልና እምነት እንዳለው ሀገር ኳታር የራሷን አቋም ያንጸባረቀችበት መንገድም አበረታች ነው። ዜጎች በራሳቸው ወግና ባህል መሠረት የፈለጉትን የማድረግ መብት እንዳላቸው ሁሉ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ምክንያት ሕዝቡን የማይወክልና ባህሉንም ሊበርዝ የሚችል ጉዳይን አሜን ብሎ የመቀበል ግዴታ የለበትም። በተለይ እንደ አፍሪካ ባሉ አህጉራት አሁንም ድረስ የማንነት መደበላለቅና የራስን ባህል ማሳነስ ከባድ ችግር ነው። ይህ የሚከሰተው ደግሞ በተለያዩ ሁኔታዎች በሚከሰተው የባህል መበረዝ ነው። ታዲያ ኳታር ከሕዝቧ ፍላጎት ውጪ የሆነን ነገር አለመቀበሏና በሌሎች ውድድሮች ላይ በመጠጥ ምክንያት ስፖርታዊ ጨዋነት እንዳይደፈርስ በማድረጓ ትውልዷ ሲያመሰግናት ይኖራል።
በመጨረሻም የስፖርታዊ ውድድሮች ሁሉ መደምደሚያ አሸናፊና ተሸናፊነት ነው። ኳታርም ጣፋጩን የአሸናፊነት ጽዋ ተጎንጭታለች። በአቋሟ በመጽናቷ እንዲሁም በስፖርት በማመኗ ያገኘችው ውጤት ኢትዮጵያን ጨምሮ ለብዙዎች ተምሳሌት ይሆናል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 1 /2015