ከአራት አመት በፊት በተዘጋጀው የሩሲያ የዓለም ዋንጫ አንድም አፍሪካዊ ሀገር ከምድብ ጨዋታ ማለፍ አልቻለም ነበር። በወቅቱ በውድድሩ የተሳተፉት አምስቱ የአፍሪካ ሀገራት በጠቅላላ ያስመዘገቡት ነጥብ ስምንት ብቻ ነበር። በኳታሩ የ2022 አለም ዋንጫ ግን ይህ ታሪክ በሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን(የአትላስ አንበሶች) ታድሷል።
ተያይዞ ማለፍ ተያይዞ መውደቅና ሌሎችንም ያልተጠበቁ አስደናቂ ትእይንቶች ያስመለከተው የኳታሩ የአለም ዋንጫ የምድብ ጨዋታ ከትናንት በስቲያ ወደ ሩብ ፍጻሜ ምእራፍ ተሸጋግሯል። በውድድሩ ከተሳተፉ አምስት የአፍሪካ አገራት ሶስቱ በጊዜ ከምድብ ጨዋታዎች ቢሰናበቱም ምእራብ አፍሪካዊቷ ሴኔጋል እንዲሁም ሰሜን አፍሪካዊቷ ሞሮኮ አስራ ስድስት ውስጥ ገብተው በመፋለም የአፍሪካ ድምቀት ኳታር ላይ በጊዜ እንዳይደበዝዝ አድርገዋል። ያምሆኖ የቴራንጋ አንበሶች በአለም ዋንጫው ከዚያ የተሻለ ጉዞ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል።
ለሩብ ፍጻሜ ፍልሚያ ብቸኛዋ የአፍሪካ ተስፋ የነበረችው ሞሮኮ በታታሪዎቹ የአትላስ አንበሶች ተጋድሎ በዚህ የአለም ዋንጫ አለምን በማስደመም የአፍሪካ ኩራት መሆናቸውን ቀጥለዋል። ለዋንጫ ከታጩ አገራት አንዷ ከሆነችው ስፔን ጋር ለ120 ደቂቃ ተፋልመውም በመለያ ምት ሩብ ፍጻሜ መቀላቀል ችለዋል። ይህም ከካሜሩን(1990)፣ሴኔጋል(2002)፣ ጋና(2010) የአለም ዋንጫ ቀጥሎ ሞሮኮ ለሩብ ፍጻሜ ፍልሚያ የደረሰች አራተኛዋ አፍሪካዊት አገር እንድትሆን አስችሏታል። የአትላስ አንበሶች በጨዋታው የነበራቸው ታታሪነት ሞሮኮን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የሩብ ፍጻሜ እንድትፋለም ከማድረግ በዘለለም በአለም ዋንጫ የዘጠና ሁለት አመታት ታሪክ እዚህ ደረጃ የደረሰች የመጀመሪያዋ የአረብ ሊግ አባል አገርም ያደርጋታል።
የአትላስ አንበሶች ትልቅ ድል እኤአ በ1986 የአለም ዋንጫ 16 ውስጥ ብቻ የመግባት ታሪካቸውን ኳታር ላይ ወደ ሌላ ደረጃ እንዲያሸጋግሩ አድርጓቸዋል። በተመሳሳይ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለመቀላቀል በተደረገው ፍልሚያ ጃፓን ሶስት የመለያ ምቶችን እንዳመከነችው ሁሉ ስፔንም ተመሳሳይ ታሪክ በ24 ሰአት ልዩነት እንድትደግም ያስገደዳት የጨዋታው ኮከብ የሆነው የአትላስ አናብስቱ ግብ ጠባቂ ያሲን ቦኖ ለዚህ ድል የአንበሳውን ድርሻ ተወጥቷል።
እኤአ በ1982 በግማሽ ፍጻሜ ፍልሚያ ምእራብ ጀርመን ፈረንሳይን 5ለ4 ባሸነፈችበት የአለም ዋንጫ ሃራልድ ሹማቸርስ ሁለት መለያ ምቶችን በማዳን ትልቅ ታሪክ የሰራ ሲሆን ይህ ግብ ጠባቂ በ1982ና1986 የአለም ዋንጫዎች አራት የመለያ ሜቶችን አድኗል። ይህን ክብረወሰን አርጀንቲናዊው ሰርጂዮ ጎይኮቺያ እኤአ በ1990 አለም ዋንጫ ተጋርቶትም ነበር። ክሮሺያዊው ግብጠባቂ ዳንሄል ሱባሲችም ባለፈው የሩሲያ አለም ዋንጫ ይህን ታሪክ መጋራት የቻለ ሲሆን ትናንት ከተመሳሳይ አገር ሌላ መለያ ምት የማዳን ምትሃት ያለውን ግብ ጠባቂ ተመልክተናል። ዶሚኒክ ሊቫኮቪች በአንድ ጨዋታ ሶስት መለያ ምቶችን በማዳን በአለም ዋንጫ ታሪክ ሶስተኛው ተጫዋች ሆኗል። ፖርቹጋላዊው ግብ ጠባቂ ሪካርዶ እኤአ 2006 ላይ የእንግሊዝን ሶስት መለያ ምቶች በማክሸፍ ሲታወስ ዳንኤል ሱባሲች ደግሞ የዴንማርክን ሶስት መለያ ምቶች ባለፈው የሩሲያ የአለም ዋንጫ ማዳን የቻለ ክሮሺያዊ ነበር። ከአፍሪካዊቷ አገር ሞሮኮ ይህን ታሪክ የደገመው ያሲን ቦኖውን ፈጥራለች። ይህም ድንቅ የአትላስ አናብስት የግብ ዘብ ስፔንን በሶስት አጋጣሚዎች በመለያ ምት ከውድድር ውጪ የመሆን ታሪክ ያላትን ጣሊያንን በልጣ እንድትገኝ አድርጓታል።
ሞሮኮ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1970 የአለም ዋንጫ የተሳተፈች ሲሆን የዘንድሮው ስድስተኛዋ ነው። በዚህ የአለም ዋንጫ የተሳትፎ ታሪኳም 1986 ላይ ብቻ ነበር ከምድብ ጨዋታዎች ማለፍ የቻለችው። ዘንድሮ ግን በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋ በፊፋ የደረጃ ሰንጠረዥ ከአለም ሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ቤልጂየምን 2ለ1 ከማሸነፍ በተጨማሪ ካለፈው የአለም ዋንጫ የፍጻሜ ተፋላሚዋ ክሮሽያ ጋር ሳይቀር ነጥብ በመጋራትና ምድቧን በበላይነት በማጠናቀቅ የማይረሳ ታሪክ ለመስራት በቅታለች።
የሞሮኮ አስደናቂ የአለም ዋንጫ ጉዞ የአፍሪካውያንን ስኬት ለመቀበል ለሚተናነቃቸው ወገኖች ህልም እንጂ እውን አልሆነም። ያምሆኖ የአትላስ አንበሶች ጄነራሉ ዋሊድ ሬግራጉይ በዓለም ዋንጫው ቡድኑን ሩብ ፍፃሜ ያደረሰ አፍሪካዊ አሰልጣኝ ሆኗል። ይህ የማይረሳ ታሪክ መስራት የቻለ አሰልጣኝ ከዓለም ዋንጫው በፊት ቡድኑን በ3 ጨዋታዎች ላይ ብቻ ነበር መምራት የቻለው::ባለፈው ግንቦት ወር እሳት በሚተፋው በመሀመድ 5ኛ ስታድየም በደማቁ ደጋፊዎቹ ታግዞ በአፍሪካ ቻምፕየንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ የአፍሪካ ሀያሉን አል አህሊን በማሸነፍ ዊዳድ አትሌቲክ የሞሮኮ ኩራት እንዲሆን አደረገ። መስከረም ወር መጀመሪያ ላይ የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን እንዲያሰለጥን ተሾመ። ባደረጋቸው አራት የአለም ዋንጫ ጨዋታዎችም ቡድኑ ጎል አላስተናገደም።
ዋሊድ ራግራጉዊ አፍሪካን ካኮራ ድሉ በኋላ የአፍሪካን ስኬት ለመቀበል ከሚዳዳቸው መገናኛ ብዙሃን “አረቦችን ወክላችሁ ነው ወይ ወደ አለም ዋንጫው የመጣችሁት” የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው የሰጡት አንጀት አርስ መልስ የበርካቶች መነጋገሪያ ሆኗል። አሰልጣኙ ለጥያቄው ምላሽ ሲሰጡ እንዲህ አሉ “ እኔ እዚህ ያለሁት ፖለቲከኛ ሆኜ አይደለም፣ እኛ የምንወክለው ሞሮኮን ነው፣ እኛ ልክ እንደ ሴኔጋል ጋና እና ካሜሩን አፍሪካውያን ነን ስለዚህ እኛ ከፍ አድርገን የምናውለበልበው የአፍሪካ እግርኳስ ባንዲራን ነው።”
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ህዳር 29 ቀን 2015 ዓ.ም