ኢትዮጵያ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በትውልድ ቅብብሎሽ በምታፈራቸው ከዋክብት አትሌቶቿ አማካኝነት ዓለም ‹‹የሯጮች ምድር›› ብሎ የክብር ካባ ደርቦላታል። ይሁን እንጂ አትሌቶቿ በዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ መድረኮች የነገሱትን ያህል ትልልቅ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮችን በሯጮቹ ምድር ለማስተናገድ አልታደለችም።
የውድድሮቹ ደረጃ አከራካሪ መሆኑ እንዳለ ሆኖ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሚዘጋጁት ዓመታዊ ‹‹የአበበ ቢቂላ ማራቶን›› እና ‹‹የጃን ሜዳ ኢንተርናሽናል ሀገር አቋራጭ ውድድር›› መኖራቸው ይታወቃል። ኢትዮጵያን የሚመጥን ገጽታዋንም በመገንባት ረገድ አንድ ውጤታማ ውድድር ግን በጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ የተመሰረተው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ነው።
ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በሁሉም ረገድ እያደገ የመጣው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዐይነ ግቡ ሆኖ የተለያዩ ዓለም አቀፍ እውቅናዎችን ማግኘቱን ቀጥላል። በቅርቡም ለጎዳና ላይ ውድድሮች እውቅናና ደረጃ የሚሰጠው የዓለም አትሌቲክስ ደረጃ ውስጥ አስገብቶታል። ይህም በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ውድድር አድርጎታል።
የዓለም አትሌቲክስ በዓለም ላይ ለሚካሄዱ የጎዳና ላይ ውድድሮች የተለያዩ መመዘኛዎችን አስቀምጦ ‹‹ሌብል›› በሚል ይሰይማል። በዋናነት ኢሊት ሌብል፣ ጎልድ ሌብልና ፕላቲኒየም ሌብል የሚሉ ስያሜዎች እንደየውድድሮቹ ደረጃ ይሰጣል። ውድድሮች እነዚህን ደረጃና ስያሜዎች በሂደት ከማግኘታቸው በፊት ግን በደፈናው ‹‹ሌብል›› የሚል ስያሜና እውቅና ያገኛሉ። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ያገኘውም ይህን ‹‹ሌብል›› የተሰኘ እውቅናና ደረጃ ነው።
የዓለም አትሌቲክስ እነዚህን እውቅናዎች ወይም ደረጃዎች ለመስጠት በዋናነት የውድድሩን አጠቃላይ ዝግጅትና ጥራት፣ ደህንነት፣ የተወዳዳሪዎች ልምድ፣ የሕዝብና የመንግሥት አካላት ድጋፍ፣ የአበረታች ንጥረ ነገሮችን ተጠቃሚነት ለማስቀረት በፋይናንስ ረገድ የሚደረግ ያላሳለሰ ጥረት ወዘተ እንደ መስፈርት ይጠቀሳሉ። የዓለም አትሌቲክስ ቀጣይ ደረጃና ስያሜዎችን ለመስጠት ደግሞ ከቴክኒክ ጋር የተያያዙ የተለያዩ መስፈርቶችን ይመለከታል፡፡
ዘመናትን ለተሻገረው የኢትዮጵያና አትሌቲክስ ጠንካራ ትስስር ታላቁ ሩጫ ያስመዘገበው ስኬት በቂ ባይባልም በዚህ ስኬቱ ማግስት በኢትዮጵያ ስፖርት ቱሪዝም ፈርቀዳጅ ሆኖ ዘንድሮ በዚሁ ህዳር ወር ለ24 ጊዜ ሊካሄድ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ይገኛል። መነሻና መድረሻውን በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ባደረገው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 10 ኪሎ ሜትር ዓመታዊ ውድድር ዘንድሮ 50 ሺ ሰዎች የሚሳተፉበት ሲሆን፤ ይህም ከአፍሪካ ተሻግሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ቁጥር ያለው ህዝብ በማሳተፍ ከጥቂቶች መካከል አንዱ አድርጎታል።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አሁን ላይ በርካታ ሺ ኢትዮጵያውያን የሚናፍቁት፣ ከተለያዩ የዓለም ሃገራት ዓመቱን ጠብቀው በመምጣት በህብረቀለም ያሸበረቀው ውድድር አካል ለመሆን የሚመኙት ሆኗል። ትልቅ ስም ካላቸው ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አንስቶ የረጅም ርቀት ውድድሮች ከዋክብት የሆኑ የዩጋንዳ እና ኬንያ አትሌቶች የዚህ ታላቅ ውድድር ተፎካካሪ መሆናቸውም እየተለመደ መጥተል።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከጊዜው ጋር ራሱን ማዘመኑ እንዲሁም ጥራቱን እንደጠበቀ መቀጠሉ አሁን ላገኘው እውቅናና ደረጃ ዋነኛው ምክንያት ሆኗል። ከዚህ በኋላም ጥቂት ቀሪ መስፈርቶችን ካሟላ ወደቀጣዩ ደረጃ (ሌብል) ለመሸጋገር እንደማይከብደው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ ዳግማዊት አማረ ገልፃለች፡፡
እንደ ዳግማዊት ማብራሪያ፤ አስቀድሞም በዓለም አቀፍ የጎዳና ሩጫዎች ላይ ያሉ ልምዶችን በኢትዮጵያዊ መንገድ መተግበር ከመቻሉ ባለፈ ደረጃ ለማሟላት የተለየ ስራ ሲከናወን ለዚህ መብቃት ኩራት ነው። ከዚህ ዓመት አንስቶም ስፖርቱን የሚቆጣጠረው የዓለም አትሌቲክስ ከሚያስቀምጣቸው መስፈርቶች ውስጥ የሚቀሩትን ወደ ተግባር ለመቀየር በጋራ ይሰራል። በተለይም ዓለም አቀፍ የሚድያ ተደራሽነቱን ማሳደግ፣ የአየር ብክለትን ከመቀነስ አኳያ ያለውን ስራ ማጠናከር፣ በርካታ ታዋቂ አትሌቶች በውድድሩ የሚካፈሉ ቢሆኑም ከምሥራቅ አፍሪካ ባለፈ የሌሎች ሀገራትንም ማካተት፣… ትኩረት የሚደረግባቸው ናቸው። ከዚህም ጋር ተያይዞ ዓለም አቀፍ የአንድ ቀን ውድድሮችን ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሌላኛው ግቡ ነው።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ድጋፍና ለዓለም አትሌቲክስ ግብረ መልስ መስጠቱም ለዚህ እንዳበቃው የጠቆመችው ሥራ አስኪያጇ፣ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ እዚህ ለመድረሱ ከራሱ ጥረት ባለፈ አብሯቸው የሚሰራቸው ባለድርሻ አካላትም ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ተናግራለች። በቀጣይም ከኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስትር ባለፈ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በቅርበት የሚሰራ ይሆናል። በጋራ ተጋግዞ መስራት ከተቻለ በርካታ ለውጥ ሊመጣ ይችላል የሚል እምነትም አላት።
‹‹መሰል ታላላቅ ውድድሮችን ወቅቱን ጠብቆ ማካሄድ በርካታ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩትም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በቅርበት መስራት መቻሉ ሁኔታዎችን አቅልሏል ። በመሆኑም በሩጫው የራሳቸውን ጠንካራ ሚና በመወጣት ላይ ላሉ አካላት ምስጋና ይገባቸዋል፡፡›› ብላለች።
ከቀናት በኋላ ህዳር 8/2017 ዓ.ም የሚካሄደው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 10 ኪሎ ሜትር ውድድር 50ሺ ሰዎችን የሚያሳትፍ ሲሆን፤ በሁለት መነሻም ይካሄዳል። ይኸውም 10ሺ የሚሆኑት ፈጣን ሯጮች መነሻቸውን ከጊዮን ሆቴል የሚያደርጉ በመሆኑ ከ1ሰዓት በፊት ስፍራው ላይ መገኘት ይኖርባቸዋል። የተቀረው የመዝናኛ ሯጭ ደግሞ በተለመደው ስፍራ መነሻውን ያደርጋል።
ዘንድሮ በውድድሩ አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች የሽልማት ገንዘብ መጠንም ጨምሯል፤ ለዚህም 1ነጥብ31 ሚሊዮን ብር ተዘጋጅቷል። ከኢትዮጵያዊያን ባለፈ የዩጋንዳና ኬንያ አትሌቶች እንደተለመደው በውድድሩ የሚካፈሉ ሲሆን፤ በቅርቡ በተካሄደው የቺካጎ ማራቶን የዓለም ክብረወሰንን ያሻሻለችው ኬንያዊቷ አትሌት ሩት ቼፕንገቲች በክብር እንግድነት ትገኛለች።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ህዳር 5/2017 ዓ.ም