ከህመሟ በላይ “እኔ ብሞት ልጄ ምን ትሆናለች?” የሚለው ያሳስባታል። ልጇ እሷን ለማስታመም አብራት ስትንከራተት ከትምህርቷ ተስተጓጉላለች። “እናቴን በሞት ላጣ ነው እያለች ስታስብ እንደኔ ከሰውነት ተርታ ወጣች” ስለምትላት የመጨረሻ ልጇ ትጨነቃለች። ወይዘሮ ወይዘር ማሞን ያገኘናት ከልጇ ጋር ባረፈችበት ዓለም ፍሬ ፒንክ ሀውስ ካንሰር ፋውንዴሽን ነው። ያለፉትን አራት ዓመታት በመሃል ወደ ሀገሯ ራያ ቆቦ ብትሄድም አብዛኛውን ጊዜ በማእከሉ አሳልፋለች፡፡
ወይዘሮ ወይዘርን ከመንደሯ አርቆ ወደ አዲስ አበባ ያመጣት የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ህመም ነው። መጀመሪያ ከማህጸንዋ ያልተጠበቀ ደም መፍሰስ ጀመረ፤ የወር አበባ ማየት ካቆምኩ አምስት ዓመታት በኋላ እንዴት ይሄ ሆነ ? ስትል በአቅራቢያዋ ወደሚገኝ የጤና ተቋም አመራች። ህመሟ ከህክምና ተቋሙ አቅም በላይ በመሆኑ ወደ አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሪፈር ተጻፈላት። “ምን መጣብኝ” በሚል ድንጋጤ በእንባ ታጅባ ወደቤቷ ተመለሰች።
በወቅቱ በሥም እንጂ በአካል ከማታውቀው አዲስ አበባ የምታርፍበት ዘመድ የላትምና አልሄድም ብላ አንገራገረች ። ሆኖም በልጆቿ ጉትጉታ ሃሳቧን ቀይራ ወደ አዲስ አበባ መምጣት ቻለች ። የማታውቃት አዲስ አበባ በጥየቃ ብትደርስም የምታውቀው ሰው የለምና ለሁለት ቀናት የጥቁር አንበሳ ኮሪደሮች ላይ ካርቶን አንጥፈው ከልጇ ጋር ማደራቸውን ታስታውሳለች ። ከዛም ማረፊያ እንደሌላት ያዩ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ባለሙያዎች መጠለያ ለሌላቸው ችግረኛ ህመምተኞች ድጋፍ ከሚያደርግ የርዳታ ድርጅት ጋር የምትገናኝበትን ሁኔታ አመቻችተውላታል።
ይሄ ለእሷ ትልቅ እድል ነበር። ጤናዋን ያለ ችግር ለመከታተል በር ከፍቶላታል። ከቤቷ የተሻለ በልታና ጠጥታ ንጽህናዋን ጠብቃ በነጻነት እንደተቀመጠች ትናገራለች። ይህ ድርጅት ባይኖር ኖሮ እንኳን ረጅም ጊዜ ይቅርና ለሁለት ቀን ወጪዋን መሸፈን እንደማትችል ታነሳለች። በተለይ የመኖሪያ አካባቢዋ ሰላም አለመሆኑን ተከትሎ ያለሃሳብ ህክምናዋን እስክትጨርስ በድርጅቱ እንድትቀመጥ በመደረጉ የተሰማትን ደስታ ትገልጻለች ። የርዳታ ድርጅቱ መሥራች ዶክተር ፍሬሕይወት ደርሶ ነዋሪነቷ በአሜሪካ ሲሆን ፋውንዴሽኑን ለመመሥረት ያነሳሳት ዋናው ምክንያት ከ15 ዓመት በፊት እህቷን በጡት ካንሰር ማጣቷ እና ያ አጋጣሚ የሌሎች ህመምተኞች ሥቃይ እንድታይ መነሻ ስለሆኗት ነበር።
የጡት ካንሰር ሕብረተሰቡ በደንብ ያልተገነዘበው ሴቶችን ግን እየገደለ ያለ በሽታ ነው። በሀገራችን በቀዳሚነት የጡት ካንሰር በመቀጠል የማህጸን ጫፍ ካንሰር ሴቶችን በመግደል ቀዳሚ መሆኑን ትናገራለች። በወቅቱ እህቷ ስለጡት ካንሰር ምንም መረጃ አልነበራትም። ሆኖም አንድ ቀን ብብቷ ስር ከወትሮው የተለየ እባጭ ትመለከታለች፤ በወቅቱ በሠርግ ግርግር እቃ ሳወጣና ሳወርድ በተፈጠረ የሥራ ጫና ነው ብላ ደምድማለች። እብጠቱ ወደጡቷ ሲሻገርም ብዙም ትኩረት አልሰጠችውም ። እያደር ግን የጡቷ እብጠት ሲጨምር ጡቷ ከበዳት፤ ሕመምም ተሰማት ። ያኔ ወደ ህክምና ተቋም ሄደች፤ በወቅቱ “ኢጢሽ ወደ ነቀርሳ ተቀይሯል” ተባለች። በሽታውን በተገቢው ልክ አልተረዳችምና የተሻለ ሊያሳክሟት ለሚችሉት እህቶቿም ሳትነግር በሚስጥር ይዛው ቆየች፡፡
ቀላል እያለ ያልገባት በሽታ ወደ ደረጃ ሁለት ሲሸጋገር በደንብ እየተረዳችው ሄደች። ቀዶ ጥገናውን ለማድረግ በወረፋ ምክንያት ረዥም ጊዜ ጠበቀች። በወቅቱ እህቷን ለማስታመም ከአሜሪካ የመጣችው ዶክተር ፍሬሕይወት ስለካንሰር በሕብረተሰቡ ዘንድ ባለው አናሳ ግንዛቤ ሰው መገለልን በመፍራት በካንሰር መያዙን እንደሚደብቅ አስተዋለች። ሕክምናውን ለማግኘት ካሉበት የገጠር አካባቢ ወደ ከተማ የሚመጡት የተወሰነ ከተማ ዘመድ ያላቸው ብቻ ናቸው። ለህክምናው የመጡት አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ስለበሽታው ተገቢው መረጃ እንደሌላቸውና ከህክምና ባለሙያዎችም “እጢ አለብሽ፣ ነቀርሳ አለብሽ ወይም ወደ ካንሰር ተቀይሮአል” የሚል ጥቅል መረጃ ከመስጠትና የህክምና አማራጮችን ከማሳየት በዘለለ ብዙም ዝርዝር መረጃ አያገኙም። እህቷ በጊዜው ህክምና አልጀመረችምና ካንሰሩ በመሰራጨቱ ሕይወቷን አጣች። ያኔ ገንዘብ እያላቸው በወቅቱ ስለካንሰር መረጃ በማጣት እህታቸውን ካጧት ሌሎች ላይማ ችግሩ ይከፋል፤ በሚል እህቷን መታደግ ባትችልም በእሷ ሞት ሌሎች አለምጸሀዮችን ለመታደግ በሚል “ዓለም ፍሬ ፒንክ ሀውስ ካንሰር ፋውንዴሽን” ተቋቋመ።
ድርጅቱ በአዲስ አበባ ሥራውን የጀመረው በመንግሥት ተቋማት ክትትል ጀምረው ረዥም ወረፋ የሆነባቸውንና በግል ለመታከም አቅም የሌላቸውን የጡት ካንሰር ህመምተኞችን በግል የህክምና ተቋማት የሚታከሙበትን ወጪ በመሸፈን ነበር። ዶክተር ፍሬህይወት በቀጣይም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የካንሰር ታማሚዎችን የህክምና ሂደት ለማየት በሆስፒታሉ ተገኘች። በወቅቱ በርካታ ህክምና ፈላጊዎች በኮሪደር ላይ ለእንግዳ ማረፊያ በተቀመጡ አግዳሚ ወንበሮች ላይ ጎናቸውን አሳርፈዋል፤ ሌሎቹ ደግሞ መሬት ላይ ካርቶን አንጥፈው ተኮራምተው ተኝተዋል። የቀኑ ውሏቸው በዚህ መልኩ ያልፍና ሲመሽ በጥበቃ ሠራተኞች ይባረራሉ። መንገድ ሲወጡም ወጪ ወራጁ ይሰርቀን ይሆን በሚል ይጨነቃሉ፤ አለፍ ሲልም የያዟትን ጥሪት መዘረፍ ያጋጥማቸዋል ። በዚህ ምሬት የያዙትን ጥቂት ስንቅና ገንዘብ አራግፈው ተገቢ ህክምና ሳያገኙ ወደመጡበት እንደሚመለሱ በመስማቷ ለዚህ ችግር መፍትሄ ማፈላለጉን ሥራዋ አደረገች ። በመጀመሪያ አነስተኛ ቤት ተከራየች፤ አስፈላጊውን ቁሳቁስ በማሟላትና ባለሙያ በመቅጠር ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል መጠለያ የሌላቸውን የጡት ካንሰር ህመምተኞችንና አስታማሚዎቻቸውን ማገዝ ተጀመረ። በማረፊያ ማዕከሉ የምግብ፣ የመጠለያ፣ የንጽህና መጠበቂያ፣ የትራንስፖርት፣ የመድሃኒትና የካውንስሊንግ አገልግሎት ይሰጣል፡፡
ዶክተር ፍሬሕይወት እንደምትለው ፤ በአሜሪካ የተሻለ ስለ ካንሰር ግንዛቤና ህክምና ቢኖርም ከኢትዮጵያ የሄዱት አብዛኞቹ ችግሩን በጥልቀት የተረዱት አልነበሩም። አብዛኞቹ እናቶች ኢንሹራንስ ኖሯቸውም በጊዜ ወደ ህክምና ተቋም አያመሩም። “እናቶች እነሱ ሲኖሩ ነው ሥራ የሚሠሩት ፣ ልጆቻቸውን የሚያሳድጉት ነገር ግን በሽታው እንዳለባቸው እያወቁም ልጄ እስኪመረቅ፣ እዚ ደረጃ እስኪደርስ/እስክትደርስ ለማንም አልናገርም በማለት ያጋጠማቸውን ችግር ይደብቃሉ፡፡” ትላለች።
ፋውንዴሽኑ ይህንንና መሰል ሁኔታዎችን ለማስወገድ በአሜሪካ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የምክር አገልግሎት ይሰጣል። የቋንቋ ችግር ስለሚያጋጥምም የሀኪሞችንና የላብራቶሪ ውጤቶችን በመቀበል የማስተርጎም አገልግሎት ይሰጣል። በተጨማሪም እናት ህክምና ላይ በምትሆንበት ወቅት ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት የመውሰድና የመመለስ፣ የቤት ጽዳትና ቤት ኪራይ እስከመሸፈን ወጪን የመጋራት ሥራ ይሠራል ፡፡
ፋውንዴሽኑ በሀገር ውስጥ ከአዲስ አበባ በተጨማሪም በጎንደር ማረፊያ አለው። በሌሎች ከተሞች በተለያየ ጊዜ በመሄድ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራና የካንሰር ምልክት ያለባቸውን በመለየት ከህክምና ተቋማት ጋር የማገናኘት ሥራ ይሠራል። በቀጣይም በጎንደር ከከተማ አስተዳደሩ በተሰጣቸው ቦታ ላይ ትልቅ ማረፊያ የመገንባትና በሌሎች አካባቢዎች ቅርንጫፍ የመክፈት እቅድ አላቸው።
ዶክተር ፍሬሕይወት ቀጣይ ህልሟ ተንቀሳቃሽ ክሊኒክ መክፈት ነው። የትራንስፖርት ወጪ ሳይኖራቸውና ህክምና ወረፋ ሆኖባቸው በቤት ውስጥ ልሙት ብለው ቁጭ ያሉ እናቶችን መታደግ እፈልጋለሁ ትላለች። ለዚህም የሚያስፈልጋትን ድጋፍ የሚያደርግ አጋዥ ትሻለች።
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን ህዳር 5/2017 ዓ.ም