ትራምፕ ቢሊየነሩን መስክን ሾሙ

ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቢሊየነሩ ኢለን መስክን አዲስ በሚቋቋመው ተቋም ሚና እንዲኖረው ከትናንት በስቲያ ሾመውታል።

ሹመቱ ለትራምፕ እንዲመረጡ በርካታ ሚሊዮን ዶላሮች ፈሰስ ያደረገው መስክን የበለጠ ተጽእኖ እንዲኖረው የሚያደርግ ነው ተብሏል።

መስክ እና የቀድሞው የሪፐብሊካን ፕሬዚዳንታዊ እጩ ቪቬክ ራማስዋሚ ትራምፕ የተጓተተውን የመንግሥት አሠራርን በማሳጠር ቀልጣፋ አሠራር እንዲኖር ያስችላል ያሉትን አዲስ የተቋቋመውን ‘ዲፓርትመንት ኦፍ ገቨርንመንት ኢፊሸንሲ’ ወይም የውጤማነት ቢሮ ይመራሉ።

ትራምፕ ባወጡት መግለጫ መስክ እና ራሜስዋሚ “የእኔ አስተዳደር የመንግስት ቢሮክራሲ እንዲያፈርስ፣ ብዙ መመሪያዎችን እንዲቀንስ፣ ብክነትን እንዲቀንስ እና የፌዴራል ኤጀንሲዎችን መዋቅር እንዲያስተካክል መንገድ ይጠርጋሉ” ብለዋል።

አዲሱ ዲፓርትመንት የሪፐብሊካን የረጅም ጊዜ ህልም እንደሆነ እና “ከመንግሥት ውጭ ሆኖ ምክር እና መመሪያ እንደሚሰጥ” የገለጹት ትራምፕ የመስክ እና የራማስዋሚ ሹመት የሴኔት ይሁንታ የማያስፈልገው ይፋዊ ያልሆነ ሹመት መሆኑን አመላክተዋል። መስክም በትራምፕ ከተሰጠው ኃላፊነት በተጨማሪ የግዙፍ ማህበራዊ ሚዲያ ኤክስ፣ የቴስላ እና የስፔስ ኤክስ ኃላፊ ሆኖ እንዲቀጥል ያስችለዋል ተብሏል።

ትራምፕ እንዳሉት አዲሱ ዲፓርትመንት “መጠነሰፊ የመዋቅር ለውጥ ለማፋጠን እና የቢዝነስ አሠራርን ለመፍጠር” ከኃይትሀውስ እና ከበጀት ቢሮ ጋር ይሠራል።

ሥራው የአሜሪካ ነጻነት በታወጀበት 250ኛ ዓመት መታበሲያ ዕለት ሐምሌ 2026 ይጠናቀቃል ተብሏል።

በፎርብስ መጽሄት የዓለም ቁጥር አንድ ሀብታም ደረጃን የተቆናጠጠው መስክ ኩባንያዎቹ በትራምፕ ድል ምክንያት በተሻለ ሁኔታ እንዲታዩ ለማድረግ እየሠራ ነው።

መስክ ለትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ከመስጠት ባለፈ በአደባባይ አብሯቸው በመታየት ድጋፉን ገልጿል።

መስክ በመንግሥት ሥራ መሳተፉ እንደ አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ እና ክሪፕቶከረንሲ ያሉት ኩባንያዎቹ የገበያ ዋጋ እንዲጨምር ሊረዳው ይችላል።

ዶናልድ ትራምፕ የዲሞክራቷን እጩ ካማላ ሀሪስን በማሸነፍ በድጋሚ ወደ ኃይት ሀውስ መግባት ችለዋል። ትራምፕ ለኃይት ሀውስ ኃላፊነት ጨምሮ ለበርካታ የመንግሥት የሥልጣን ቦታዎች አጋሮቻቸውን እየሾሙ እና እያጩ ይገኛሉ።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ህዳር 5/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You