ኢራን በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ጥፋተኛ የተባለ ዜጋዋን በስቅላት ቀጣች

ኢራን በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ጥፋተኛ የተባለ ዜጋዋን በስቅላት ቀጣች፡፡

የመካከለኛ ምስራቋ ሀገር ኢራን በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ተከሶ ጥፋተኛ የተባለ ዜጋዋን በአደባባይ ላይ በስቅላት ገድላለች፡፡

ሞሀመድ አሊ የተባለው ይህ ኢራናዊ የ43 ዓመት ጎልማሳ ሲሆን በርካታ ሴቶች እንደሚያገባቸው ቃል በመግባት አስገድዶ ደፍሯቸዋል ተብሏል፡፡

ግለሰቡ ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ በፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን ከአንድ ወር በፊት በተከሰሰበት የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች ጥፋተኛ ሆኖ እንደተገኘ አል አረቢያ ዘግቧል፡፡

እንደ ዘገባው ከሆነ መሀመድ አሊ ከ10 በላይ ሴቶችን አስገድዶ ደፍሯል የተባለ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ የተወሰኑት ከእሱ የጸነሱትን ልጅ እንዲያስወርዱ መድሃኒት ሰጥቷልም ተብሏል፡፡

በምዕራባዊ ኢራን ክፍል በምትገኘው ሀሜዳን ከተማ የሚኖረው ይህ ሰው ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ 200 ሴቶች ደፍሮናል ሲሉ ክስ መስርተውበት ነበር፡፡

በግለሰቡ ተደፍረናል ያሉ ሴቶች ቁጥር መጨመርን ተከትሎ በርካታ ኢራናዊያን ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድበት የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍም ተደርጎበት ነበር፡፡

ኢራን በየጊዜው በርካታ ዜጎች በስቅላት ከሚቀጡባቸው የዓለማችን ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን ተመድን ጨምሮ በርካታ ሠብዓዊ ድርጅቶች የሞት ቅጣት እንዲቀር በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡

እንደ አምንስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት ከሆነ የሞት ፍርድ ቁጥር እየጨመረ የመጣ ቻይና ብዙ ዜጎቿን በስቅላት በመቅጣት ከዓለማችን ቀዳሚዋ ሀገር ስትሆን በዓመት በአማካኝ አንድ ሺህ ዜጎችን ትገድላለች፡፡

ኢራን ደግሞ በየዓመቱ ከ570 በላይ ዜጎችን በስቅላት ስትቀጣ አፍሪካዊቷ ግብጽም ዜጎቿን በስቅላት ከሚቀጡ ሀገራት መካከል ተጠቅሳለች፡፡

ሳውዲ አረቢያ፣ አሜሪካ እና ሲንጋፖር በተጨማሪነት የተጠቀሱ ሀገራት ሲሆኑ ሀገራቱ ዜጎቻቸውን በሞት እየቀጡ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

 

አዲስ ዘመን ህዳር 5/2017 ዓ.ም

Recommended For You