የረሃብ ነገር ከተነሳ…!?

‘’ከረሃብ የፀዳች ዓለምን እውን ማድረግ ይቻላል፤’’ በሚል መሪ ቃል በመዲናችን ዓለም አቀፍ ጉባኤ ተካሂዷል። እውነቱን ለመናገር ጉባኤውን በሀገራችን መካሄዱ ተምሳሌታዊ ወይም ሲምቦሊክ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። አዎ ለበርካታ ዓመታት የድርቅና የረሃብ ምሳሌ ሆና ስሟ ሲወሳ በኖረች ሀገር፤ ይሄን የጠለሸ ስሟን ለማደስ ጥረት እያደረገች በምትገኝበት ወሳኝ መታጠፊያ ሀገር ጉባኤው መካሄዱ በብዙ መልኩ ተምሳሌታዊ ነው።

በጉባኤው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ኢትዮጵያ ባለፉት 6 ዓመታት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ሰፊ ሥራዎች ማከናወኗን፤ በተለይም ባለፉት ዓመታት በ3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት የስንዴ፣ ጤፍና ሩዝ ምርትና 40 ቢሊዮን ችግኝ በመትከል ገልጸዋል። የኩታ ገጠም ግብርና ለማስፋት፣ የግብርና ሜካናይዜሽን ለማሳደግ፤ በየደረጃው መስኖን በመጠቀም ዓመቱን ሁሉ ለማልማት የተሄደበት ርቀት፤ አንድም መሬት ጦም እንዳያድር የሚደረገው ጥረት እና እየተመዘገበ ያለው አበረታች ውጤት ተስፋ የሚያሰንቅ ሆኖ እያለ ነው እንግዲህ ይሄ ጉባኤ የተካሄደው።

ታሪካችን የአልበገር ባይነት፣ የነፃነት፣ የጥንታዊ ሥልጣኔ እንደሆነው ሁሉ፤ የጦርነትና የረሃብ ጭምር መሆኑን በልኩ ማጤን የነገውን መንገዳችንን ለመትለም ያግዛል። ስለሆነም የድርቅና የረሃብ ታሪካችን መለስ ብሎ መቃኘት ያሻል። በነገራችን ላይ ረሃብ በአውሮፓ በእስያ በላቲን አሜሪካ በአፍሪካና በመላው ዓለም ተከስቷል። ረሃብ በኢትዮጵያ የተጀመረ በኢትዮጵያም የሚያበቃ አይደለም። እያንዳንዱ ሀገር የድርቅ የረሃብ ታሪክ አለው። ከዘፍጥረት ጀምሮ የሰው ልጆችን ሲፈትን የኖረ ተፈጥሯዊ ክስተት ነው። ይሄን የምለው ግን ታሪካችንን በሌላ ታሪክ ለማጥፋት ወይም ረሃብ በእኛ የተጀመረ አይደለም ብሎ ለመጽናናት አይደለም። በምንጭነት ቆየት ያለ የአዲስ አድማስ ጋዜጣን ተጠቅሜያለሁ።

የረዥም ዘመኑን ረሃብ ለጊዜው እናቆየውና የዛሬ መቶ ዓመት አካባቢ በኢትዮጵያ ስለደረሰው ድርቅና ረሃብ በተለይም በፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት መጽሐፍ የሰፈረውን ስንመለከት። በኢትዮጵያ ከደረሱት በጣም ትልቅ የድርቅና የረሃብ ዘመናት አንዱ ከ1888-1892 ማለትም አጼ ዮሐንስ በሞቱበት ጊዜ የነበረው መሆኑን እናረጋግጣለን። በዚህ ጊዜ የነበሩት የሮም ሚሲዮኖች እንደመዘገቡት፤ የአየሩ ሁኔታ ባልተለመደ መልኩ ሞቃት ሆነ። ይህም የአየር ንብረቱን አዛባው። እንደ ሰደድ እሳትም መላውን ምድር አጥለቀለቀው።

የአየር ንብረቱ መዛባት ለሱማሊያና ለደቡባዊ ሀገሮችም ተረፈ። በወቅቱ ኢትዮጵያን የጎበኘ ማርቲ የተባለ ግለሰብ ስለ ድርቁ ሲገልጽ፡-‹‹በእራፊ አዳፋ ጨርቅ የተሸፈነ ሬሳ እዚህም እዚያም ወድቆ ይታያል። በዚያ ሐሩር ፀሐይ ላይ ወድቀው ከሚታዩት አስከሬኖች ክንዶችና እግሮች ላይ ነፍሳት ሲርመሰመሱ ማየት እጅጉን ያሰቅቃል። እንዲህ ያለው ድርቅ የተከሰተው ከ1888-1892 ብቻ አልነበረም። እንደ ማርቲን ያለ ፀሐፊ አያጋጥመው እንጂ በኢትዮጵያ የረሃብ ታሪክ ማህደር ሰፍሮ እንደምናገኘው÷ ከ1131-1145፣ በ1258፣ በ1261፣ በ1262፣ በ1274 ረሃብና በሽታ ደርሶ ነበር። ሆኖም መንስኤዎቻቸው እንደ አየር ንብረት መዛባትና ሰው ሠራሽ ችግሮች ሳይሆን እንደ ፈጣሪ ቁጣና አንድም ሕዝቡ ለንጉሦች ባለመታዘዙ ወይም ንጉሦች የተሰጣቸውን መለኮታዊ አደራ ባለመወጣታቸው እንደተከሰተ ተደርጎ ሲጠቀስ ቆይቷል። ስለዚህም ጉዳይ የታሪክ ጸሐፍቱ ሲገልጹ፡-

“እግዚአብሔር የረሱትን መንግሥታት በበሽታ፣ በረሃብና በጦርነት ይቀጣል። እነዚህ መንግሥታት እውነተኛውን እምነትና የተቀደሱ ሕግጋቱን ትተው በሐሰት ስለሚበከሉ የጥፋትንና የእርግማንን መንገድ የሚከተሉ ናቸው” ይሏቸዋል። በተለይም ከ1315-1344 በነበረው የአጼ አምደጽዮን ዘመን መንግሥት እጅግ አስከፊ ድርቅና ረሃብ እንደነበር ይነገራል። ይህንንም የድርቅ ዘመን አቡነ አሮን የተባሉ በቤጌምድር የነበሩ ቅዱስ ሰው፤ በአምደ ጽዮንና በሰይፈ አርአድ ዘመነ መንግሥት በተከሰተው ድርቅ፣ ረሃብና በሽታ በመላው ኢትዮጵያ ተስፋፍቶ እንደነበር ያወሳሉ። ያኔ ከአቡነ አሮን ተማሪዎች ብቻ 1400 ሞተው ቤተክርስቲያኗን ሞልተዋት ነበር።

የደብረ ቢዛን (ትግራይ) ገዳም መነኩሴ የነበሩት አባ ዮሐንስ (በኮንቲሮዝ ግምት ከ1369-1448) ባለው ጊዜ ድርቅ በገዳሙ እንደተከሰተና የገዳሙን መነኮሳት እንደጨረሳቸው ጠቅሰዋል። በ15ኛው ክፍለ ዘመን የደረሰውን የረሃብ እልቂት በተመለከተ የተጠናከረ መረጃ ባይኖርም አል-ማግሪቢ የተባለ የአረብ ታሪክ መዝጋቢ፣ በአጼ ዘርአያቆብ ዘመነ መንግሥት (1434-1568) በተለይም ከ1434-6 በነበረው ጊዜ ረሃብ ብዙ ሕዝብ እንደ ፈጀና በመላው ሀገሪቱ የሕዝብን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እንደቀነሰ ዘግቧል።

ከ1508-1540 በነበረው የአጼ ልብነድንግል ዘመን መንግሥትም በዝናብ እጥረት ምክንያት በርካታ ሰዎች አልቀዋል። ከአጼ ልብነድንግል በኋላም በተለይም በአጼ ገላውዲዮስ ዘመነ መንግሥት (1540-1569) ታይቶ ተሰምቶ የማይታወቅ ቸነፈር ደርሶ ነበር። በ1611 ማንንትታ፣ በ1683 ለባብል፣ በ1693 ታናካ የተባሉ በሽታዎች ብዙ ሕዝብ ጨርሰዋል። በአጼ እያሱ ዘመን መንግሥት በተለይም በ1706 የደረሰው ረሃብ፣ የጎንደርን ሕዝብ ከዚህ መቅሰፍት አድነን በማለት ንጉሠ ነገሥቱን እንዲማጸን አድርጎታል። ከዚህም በተጨማሪ በ1747 እና በ1748 በተከታታይ አንበጣ ሰማዩን እንደ ጉም ይሸፍነው እንደነበርና ይኸም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአንበጣ መንጋ የቆላውንና የደጋውን ሕዝብ ለረሃብ እንዳጋለጠው እንዲሁም ለጉንፋንና ለሌሎችም ብዙ በሽታዎች በመዳረግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ከምድረ ገጽ እንዳጠፋ ይታወቃል።

ከ1772/73 በነበረው ዘመን ቀጭኔ የሚባል ረሃብ እንደገባ፣ ከ1750-1769 በምጽዋ በተለይም በሐርቂቆ የተከሰተው ረሃብ ወደ ሌላው የሀገሪቱ ክፍል የተስፋፋ ሲሆን ከዚያም ከ1788/89 መላውን ክልል አዳርሶ፣ በ1796 ብዙ ወረዳዎችን አጥፍቷል። በ1842 ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የነበረው ቻርልስ ጆንሰን የተባለ እንግሊዛዊ ሐኪም እንደገለጸው፤ ከ1828-29 በሸዋ ውስጥ አሰቃቂ ድርቅና ረሃብ ደርሷል። በዚህም ጊዜ ጆይ ኤል ክራፍ የተባለ ሚሲዮናዊ፣ ረሃቡ የወሎን ሕዝብ እንደቅጠል አርግፎ እንደጨረሰው ዘግቧል። በ1889 በሸዋ፣ በሱማሌ፣ በከፋና በጅማ – በጥቅምት፣ በኅዳር፣ በግንቦት ብዙ ሰዎችንና ከብቶችን ገድሏል።

ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ቀደም ሲል የተጠቀሰውን “ዘ ሂስትሪ ኦቭ ፋሚን ኤንድ ኤፒደሚክ ኢን ኢትዮጵያ ፕራየር ቱ ዘ ትዌንቲዝ ሴንቺሪ” በሚል ርዕሰ ባሳተሙት መጽሐፍ በርካታ የታሪክ መጻሕፍት አጣቅሰው ሲያቀርቡ፣ ፕሮፌሰር መሥፍን ወልደማርያም ደግሞ ከዚያ ቀጥሎ ያለውን የረሃብ ዘመን ‹‹ሩላር ቨልነረብሊቲ ቱ ፋሚን ኢን ኢትዮጵያ›› በሚል ርእሰ በሳተሙት መጽሐፋቸው በዝርዝር አቅርበውታል። በመግቢያቸው ላይ ስለረሃብ ምንነት ሲገልጹም፡-“ረሃብ የተመሠቃቀለ ትዕይንትን ይፈጥራል። የሕመም ስቃይ ዝቅተኛ መሆንን፣ ተስፋ መቁረጥንና በአንደበት የማይገለጥ ነገር ግን አጥንት በአጥንት ከሆነ ፊት የሚነበብ ውስጣዊ ብስጭትን ያስከትላል።

ረሃብ ለመሞት የብዙ ወራት ጉዞ የሚደረግበት ነው። ረሃብ የሚታይ ጭንቀት፣ ሰቆቃና ፍርሃት ነው። ከሰዎች መካከል የታደሉት አይተውት ይሆናል። ግን ሞት አፋፍ ላይ ያለው ወይም ከእውነተኛው ሞት ጋር ፊት ለፊት የተጋፈጠው በእውን የሚያየውን ያህል አይሆንም። የረሃብን ያህል ሰው በሰው ላይ የሚፈጽመውን ኢ-ሰብዓዊነት የሚያጋልጥ የለም። የባሕልና የሃይማኖት ዋጋ ግብዝነትና መመጻደቅ እንደሆነ የሚያሳይም ረሃብ ነው። ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት አልበኝነት የሚፈጥርም ረሃብ ነው።

“… ያለፉትን በመቶ የሚቆጠሩ የረሃብ ዓመታት በትዝታ ዓይን እያየን እንለፋቸው እንዳንል ትግራይ ላይ በ1958 ተከስቷል። በዚያን ጊዜ ረሃቡን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳያውቀው ይፈለግ ስለነበር ለቤተክርስቲያንም ይሁን ለመስጊድ ማደሻ፣ ለመንገድም ይሁን ለትምህርት ቤት ማሰሪያ ብቻ ለምን እንደሆነ ለማያውቀው ጉዳይ ግን መዋጮ እንዲያዋጣ ተጠየቀ። ረሃቡ በገባ በሶስተኛ ዓመቱም በ1961 ላይ የአሜሪካ መንግሥት 7.5 ቶን እህል ሲረዳ መቶ ሺህ ያህል ሕዝብ አልቆ ነበር። ” ይላሉ።

ረሃብ ሲከሰት በሽታም ይከተላል። ያኔ ፈንጣጣ፣ ተስቦ፣ ክፉኝ፣ ወባ እና ሌሎችም በሽታዎች ምህረት የለሽ ክንዳቸውን ያሳዩበትና ሕዝብ እንደ ቅጠል የረገፈበት ጊዜ ነበር። ድርቁ በአንድ አካባቢ ብቻ አልረጋም። ወደ ሰሜን ወሎ በተለይም ወደ ዋግና ላስታ ተዛምቶ ሕዝቡን በጭካኔ ረፍርፎታል። ይህ ረሃብ ከሰሜን ወደ ማዕከላዊ ሀገር ተዛመተ። ተመሳሳይ እልቂትም ፈጽሞ ወደ ደቡብ ሸዋ ሽምጥ ሸለቆ፣ ሐረርጌ፣ ሲዳማ፣ ጋሞጎፋ፣ ኢሉባቦር፣ ወለጋ፣ ጎጃም ተስፋፋ።

በ1975/77 ደግሞ በድርቅ ተጠቅተው የማያውቁት አርጆ፣ ባህርዳር፣ ደብረ ታቦር፣ ጨቦና ጉራጌ፣ ሳይቀሩ በረሃብ አለንጋ ተገረፉ። ምንም እንኳን የአጼ ኃይለሥላሴ መንግሥት ረሃቡ በኢትዮጵያ ሕዝብና በዓለም ሕዝብ እንዳይታወቅ ለማፈን ቢፈልግም የሚቻል አልሆነም። በ121 አውራጃዎች 6,478,760 ማለትም በማዕከላዊ ግምት በየአውራጃው 53,543 ሰዎች ድርቁ ባስከተለው ረሃብ አልቀዋል። በዚህም ስሌት መሠረት፣ በ20 ዓመት ውስጥ የረሃብ ሰለባ የሆነው ሕዝብ 25,111,887 ይደርሳል። የመንግሥት መረጃ ደግሞ በ63 አውራጃዎች 263,578 እንደሆነ ያመለክታል። ይህስ ቢሆን በወቅቱ ደራሽ አጥቶ ታፍኖ ማለቅ ነበረበት?

ከአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በፊት በነበሩ መንግሥታት በፈጣሪ ቁጣ ወይም ነገሥታቱን ባለመታዘዝ ወይም በጥጋብ እንደተከሰተ ተደርጎ ሲወሰድ፣ ለአጼ ኃይለሥላሴ መንግሥት ደግሞ መንኮታኮቻ ምክንያት እንደሆነ ይታወቃል። ነገሩ “አንበሳን ፈርተው ዛፍ ላይ ቢወጡ ነብር ጠበቃቸው” እንደሚባለው ሆነ እንጂ የዚያን ሥርዓት ፈላጭ ቆራጭነት ባህርይም የበለጠ ጉልህ አድርጎታል።

ድርቅና ረሃብን በተመለከተ ገና በብዛት መጠናትና መጻፍ ያለበት ቢሆንም ከጤና አኳያ ከተነተኑት መካከል አብርሃ ግዛው የተባሉ ምሁር ‹‹ኤኮሎጂ ኦፍ ሄልዝ ኤንድ ዲዝዝ ኢን ኢትዮጵያ›› በሚል ርእስ ዜይን አሕመድ ዜን እና ሄልመት ኩልስ ባዘጋጁት መጽሐፍ (1988) ላይ እንዳሰፈሩት፤ ምንም እንኳን ከአብዮቱ በኋላ የርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ረሃብ ከመድረሱ በፊት የቅድሚያ ጥንቃቄ አገልግሎት እንዲሰጥ ጭምር ቢመሠረትም ረሃቡ እየተባበሰ እንጂ እየተሻሻለ ሲሄድ አልታየም።

እንዲያውም በወሎና በትግራይ የተከሰተው ዓይነት ረሃብ፣ በ1977 በኦጋዴንና በባሌ በተለይ በኤልካሬ፣ በኢሊባቦር፣ በተለይም በቡኖ በደሌ፣ በሰሜን ሸዋ ተስፋፋ። በ1979 ላይም ከፍተኛ ምርት በማምረት በምትታወቀው በአርሲ፣ በደቡብ ሸዋ፣ በሲዳሞ፣ በጋሞጎፋ ታየ። በ1981 ምሥራቅ ጎንደር በድርቅ ተመታ። የድርቁ ጥቃት አይሎ በቀጠለበት በ1984 ላይ የደርግ መንግሥት ከወሎ 367,016፣ ከሸዋ 108,241፣ ከትግራይ 89,716፣ ከምሥራቅ ጎጃም 16.425፣ ከምስራቅ ጎንደር 6387፣ በአጠቃላይም 600 ሺ ሰፋሪዎችን፤ በወለጋ 253,282፣ በጎጃም 101,785፣ በኢሊባቦር 147,915፣ በከፋ 72830፣ እና በምዕራብ ጎንደር 6378፣ አሰፈረ። ይህ ግን ድርቁና ረሃቡ የሚያስከትሉትን ችግሮች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊያስቀር የሚችል ርምጃ አልነበረም።

በመሠረቱ የተፈጥሮ ሰለባ የሆነችው ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን በሳህል በረሃ ውስጥ የሚጠቃለሉት ሀገሮች በተለይም ሱዳን፣ ናይጄሪያ፣ ማሊ፣ ኡጋንዳ፣ ሞሪታንያና ሌሎችም ሀገሮች ጭምር ናቸው። አንድ የጣና በለስ ፕሮጀክት መጽሔት (1985 አትሙ) እንደገለጸው፤ “በነዚህ ሀገሮች በተለይም በ1977 የደረሰው ድርቅ ባስከተለው የረሃብ ቸነፈር በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ሰዎች ሞተዋል።

የችግሩ ስፋትና ያስከተለው አሰቃቂ ጉዳት መላውን ዓለም ያስደነገጠ፣ የበለጸጉ ሀገሮች እንዲህ ያለው ጥቃት ለሚደርስባቸው ሀገሮች የሚቻላቸውን ድጋፍ ሁሉ እንዲያደርጉ ያነሳሳና ሥር የሰደደውን ችግር በአንድ ጊዜ ለማስወገድ ባይቻልም እንኳን ቀስ በቀስ ለመቅረፍ ሃሳብ የቀረበበት፤ የአፈር መሸርሸር፣ የአየር መዛባት፣ የተፈጥሮ ሀብት በትክክል ለመጠቀም አለመቻል ቴክኖሎጂያዊና ኢንዱስትሪያዊ እንቅስቃሴ እንዲዘረጋ የታመነበት ጊዜ ሆነ” ይላል።

አሰፋ ወልደ ገብርኤል የተባሉ ምሑር፤ ‹‹ዘ ኢኮሎጂ ኦቭ ሔልዝ ኤንድ ዲዝዝ ኢን ኢትዮጵያ›› በሚል ርእሰ በጻፉት መጽሐፍ እንዳቀረቡት፤ ኢትዮጵያ የግብርና ሀገር ብትሆንም፣ ከሕዝቧ 86% የሚሆነው ገበሬ መሆኑ ቢረጋገጥም፣ ሀገሪቱ በማንኛውም ጊዜ ሊታረስ የሚችል 15.8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት እንዳላት ቢታወቅም፣ 69 ሚሊዮን የቀንድ ከብት፣ 62 ሚሊዮን ዶሮ ቢኖራትም፣ እድገቷ ዝቅተኛ በመሆኑ እያንዳንዱ ሰው በቂ ምግብ አያገኝም።

ይህም የሆነው እርሻው የሚታረሰው ኋላቀር በሆነ ዘዴ በመሆኑ፣ በክምችት ወቅት በሚደርሰው ብክነት፣ በቂ የመጓጓዣ አገልግሎት ባለመኖሩ፣ ስለጤንነት ጉዳይ ትምህርት ባለመሰጠቱ፣ ስለ አመጋገብና ስለ ቤተሰብ ቁጠባ ባለማወቅ፣ በአንድ በልምድ በተመረጠ እህል ላይ የተመሠረተ አመጋገብ ጋር የሙጥኝ በማለት፣ በተላላፊ በሽታዎች መስፋፋት፣ ምግብ ለመግዛት አቅም በማጣትና ድርቅ በመኖሩ ነው። እንዲህ ያለውን ችግር ለማስወገድ ጥረት የተደረገ መሆኑን የሚጠቁሙ መረጃዎች ቢኖሩም ውጤቱ የሚያረጋግጠው ግን ለመፍትሔነት አለመብቃቱን ነው።

ይሁንና የኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በድርቅ አደጋ የመጠቃት፣ ከዚህም የተነሳ ሕዝቧ ለረሃብና ለእርዛት የመጋለጡ ጉዳይ በርግጥ የማይፈታ እንቆቅልሽ ነው? ሁኔታዎች ከተመቻቹለት 85 በመቶ የሚሆነው ገበሬ፣ ራሱን ችሎ 15 በመቶ የሚሆነውን ሕዝብ መደገፍ ይሳነዋልን? ብለን መጠየቃችን አልቀረም። ነገሩ በጣም ውስብስብም ነው። በመሠረቱ ያለፈውንም ሆነ ያለውን ሥርዓት በየምክንያቱ እየኮነንን መኖር ብቻውን የትም አያደርሰንም።

ሥር የሰደደው ችግራችን የተከሰተው ደጋግሞ በሚያጠቃን ድርቅ ምክንያት ነው። የአስተራረስ ዘዴያችን በጣም ኋላ ቀር በመሆኑ ነው። በመሠረቱ የኢትዮጵያ የግብርና ኢኮኖሚ ደካማ በመሆኑ ሕዝቡ በተደጋጋሚ ለረሃብ ይጋለጣል፣ ሲባልም ሆነ የዕለት ምግቡ ከአማካዩ ዝቅተኛ ካሎሪ እንኳን ያነሰ ነው ሲባል የአንድ ዓመት ወይም የሶስት አራት ዓመታት ችግር ውጤት ሳይሆን ከዚያ በፊት የነበሩት ሃያና ሰላሳ ዓመታትንም የሚዳስስ ነው።

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ህዳር 5/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You