(ክፍል ሁለት)
በመጀመሪያው ክፍል ለንባብ በበቃው መጣጥፌ በምናባዊ ገንዘብ ወይም በክሪፕቶ ከረንሲ ኢንዱስትሪው በ3ኛ ደረጃ የሚገኘው ግዙፉ FTX EXCHANGE እንዴት እንደተነሳና እንደተንኮታኮተ አውስቻለሁ ። ዛሬ ደግሞ የዚህን ግዙፍ ኩባንያ ብልሹ አሰራር ፍንጭ ስለሰጠው ተቋምና ኢንዱስትሪው ምን ያህል ለሌብነትና ለዘረፋ የተጋለጠ መሆኑን የሚያሳይ ተጨማሪ አብነት አነሳለሁ ።
የFTX የፋይናንስ አቅም ጉዳይ አደጋ ላይ መሆኑን ፍንጭ የሰጠው ኮይንዴክስ በተባለ ድረ ገጽ ነው ይለናል ቢቢሲ ፤ በዚሁ ድረ ገጽ የወጣው ዘገባ ፤ የFTX እህት ኩባንያ የሆነው አላሜዳ የሚደገፈው በራሱ በFTX በተቋቋመ ፈንድ እንጂ በገለልተኛ ተቋም አለመሆኑን የሚያጋልጥ ነው ።
ወዲያው”The Wall Street Journal “ አላሜዳ የሚጠቀመው ከFTX ደንበኞች ቁጠባ መሆኑን ይፋ አደረገ። የመጨረሻው መጀመሪያ የFTX ተፎካካሪ የነበረው ባይናንስ ከቀናት በኋላ ከFTX የተገናኙ የክሪፕቶ ሽርክናዎችን መሸጡ የተሰማለት ነው ይላል ቢቢሲ ።
የባይናንስ ክሪፕቶ ከረንሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ ቻንግፔንግ ዣው 7.5 ተከታዮች ወዳሉት ቲዊተሩ ይሄድና ኩባንያው FTX ላይ ያለውን ሽርክና ሊሸጥ እንደሆነ ይፋ አደረገ ። በነገራችን የ22ኛው የአለም ዋንጫ ስፓንሰር ከሆኑ ድርጅቶች አንዱ ባይናንስ አንዱ ሲሆን በፓርቹጋላዊው ኮከብ ክሪስቲያን ሮናልዶ አማካኝነት ማስታወቂያውን እያስነገረ ይገኛል ። የFTXን ማስታወቂያም እነ ማት ዲመን ሲሰሩለት እንደነበር እዚህ ላይ ልብ ይሏል ።
ከዚህ በኋላ ነጮች እንደሚሉት የተቀረው ታሪክ ነው። The rest is history . በሁኔታው የተደናገጡ የFTX ደንበኞች ፤ ከFTX ክሪፕቶ ከረንሲ የነበራቸውን በቢሊየን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘባቸውን ከባንኮች አወጡ። የክሪፕቶ ከረንሲ ንጉሰ ነገስት ሳም ባንክማን ፍሬድ እንደ ሮማን ኢምፓየር ተንኮታኮተ ። ሚሊየኖችን ለኪሳራ ዳረገ ።
ባለሽርክናዎች ገንዘባቸውን እንዳያወጡ ከተደረገ በኋላ ባንክማን ፍሬድ FTXን ከውድቀት የሚታደጉ ኩባንያዎችን ማፈላለጊ ጀመረ ። መክሰሩን አውጆ ጣጥሎ ከመሔዱ በፊት የሚታደጉትን ኩባንያዎች እያፈላለገ ሳለ ባይናንስ ሊደርስለት ቃል ከገባ በኋላ ፤ መልሶ FTX ፈንዱን አላግባብ ስለተጠቀመ መንግስት ምርመራ ስለከፈተበት ልታደገው አልችልም በማለት ሸሸ። ከአንድ ቀን በኋላ FTX መክሰሩን ይፋ አደረገ። ንጉሰ ነገስቱ ዘውዱንም ዙፋኑንም በአንድ ጊዜ አጣ። የሚሊየኖች የFTX ሽርክና አጣብቂኝ ላይ ወደቀ። ገንዘባቸውን ስለማግኘታቸው እርግጠኛ አለመሆናቸውን ተረዱ ።
ሳም ባንክማን ፍሬድ በቲዊተር ገጹ ለተፈጠረው ሁሉ ይቅርታ እጠይቃለሁ በማለት ከFTX ዋና ስራ አስፈጻሚነት ለቀቀ። በቲዊተር ሁኔታዎች በዚህ መልኩ በመጠናቀቃቸው ደንግጫለሁ። ነገሮች ይስተካከላሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ አለ። ይሄን ተከትሎ የቢትኮይን ዋጋ አሽቆለቆለ ፤ ብዙዎች የነገው ተረኛ ከሳሪ ክሪፕቶ ከረንሲ ማን ይሆን አሉ ። አዲሱ የFTX ኃላፊ ጆን ሬይ 3ኛ በሰራሁባቸው አመታት ሁሉ እንደዚህ ያለ ዝርክርክ ድርጅት ገጥሞኝ አያውቅም ማለታቸውን የእንግሊዙ ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ ያወሳል።በአሜሪካ አንቱ የተባሉት የኩባንያዎች መዋቅር ማሻሻያ ጠበብት ጆን ሬይ የFTXን አወዳደቅ ታይቶ የማይታወቅ ሲሉ ይገልጹታል ።
በነገራችን ላይ ጆን በግዙፉ የኢነርጂ ኩባንያ ኢንሮን ኪሳራ ወቅት የመዋቅር መሻሻያ በማድረግ ባመጡት ለውጥ ስማቸው በበጎ ይነሳል ።በዘርፉ አራት አስርት አመታትን የተሻገረ የካበተ ልምድ ያላቸው ጆን እንደ FTX በብልሹ አሰራር የጨቀየና የቁጥጥር ስርዓት የሌለው ስድ ኩባንያ አላየሁም ይላሉ ። FTX አቅምና ብቃት በሌላቸው ጥቂት ግለሰቦች የሚመራ እና የማይታመን የፋይናንስ ሪፓርት ያለው ድርጅት መሆኑን ይናገራሉ። አብዛኛው የFTX ሀብት ተሰውሯል ወይም ተዘርፏል። ለዚህ የበቃው ኩባንያው በጥቂቶች መዳፍ ስር በመውደቁ ነው ይላሉ ጆን ሬይ ፤
የኩባንያው መንኮታኮት የክሪፕቶ ከረንሲውን ገብያ ክፉኛ አናግቶታል ። የቢትኮይን የገብያ ዋጋ ያሽቆለቆለ ሲሆን ፤ በርካታ የክሪፕቶ ከረንሲ ኩባንያዎች ደግሞ ኪሳራ እያስመዘገቡ ነው ይለናል ጋዜጣው ። መጭው ዘመን ለዘርፉ ፈታኝ ነው ።
የFTX ዋና መስሪያ ቤት በሚገኝበት ባሀማስ ለሰራተኞችና አማካሪዎች በድርጅቱ ፈንድ ቤትና መኪና ይገዛ ነበር ይላሉ አዲሱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ። ድርጅቱ ይሄን የሚያደርገው መርህን በመጣስ መሆኑ ሳያንስ ምንም አይነት ሰነድ አለመያዙ ያሳዝናል ። ዞሮ ዞሮ ከዚህ እንዝህላልነትና ኬረዳሽነት በላይ አደገኛ ማጭበርበርና ዘረፋ መፈጸሙ ልብ ሊባል ይገባል ይላሉ ጆን ።
በፋይናንሽያል ታይምስ ጋዜጣ እጅ የገባ ሚስጥራዊ ሰነድ FTX ከመውደቁ አንድ ቀን በፊት 1 ቢሊየን ዶላር የሚደርስ ፤በቀላሉ ሊተላለፍ የሚችል ገንዘብና የተለያዩ ንብረቶች የነበሩት ሲሆን እዳውም 9 ቢሊየን ዶላር ነበር። ጆን ሬይ ወደ ኩባንያው ከመጡ በኋላ ግን በFTX ካዘና የተገኘው የ740 ሚሊየን ዶላር ዋጋ ያላቸው የተለያዩ ክሪፕቶ ከረንሲዎችን ብቻ ናቸው ።በካዘናው የተገኘው ከኩባንያው አጠቃላይ ሀብት ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ይላሉ ዋና ስራ አስፈጻሚው ።
የFTX መጠባበቂያ ፈንድ የሚያስተዳድረው አላሜዳ ለቀድሞው ዋና ስራ አስፈጻሚ ሳም ባንክማን፤ 1 ቢሊየን ዶላር አንስቶ በብድር መስጠቱን እና ለምህንድስና ዳይሬክተሩ ኒሻድ ሲን 543 ሚሊየን ዶላር እንዲሁ ማበደረጉ ጆን ሬይ ይፋ አድርገዋል ።የቀድሞው ዋና ስራ አስፈጻሚ ባንክማን ፍሬድ በስሩ ካሉም ሆነ ከእህት ኩባንያዎች ጋር የሚጻጻፈው ፤ ደብዳቤዎቹንና መልዕክቶችን ወዲያው ወዲያው ብዙም ሳይቆዩ በገዛ እጁ የሚያጠፋ መተግበሪያ በመጠቀም ስለሆነ ማስረጃ ማግኘቱን ፈታኝ አድርጎታል ።
ብዙዎቹ የFTX ውሳኔዎችና አሰራሮች በስራ አመራር ቦርዱ ሳይጸድቁ ይፈጸሙ ስለነበር ለዚህ አስደንጋጭ ውድቀት ዳርጎታል ይላሉ ባላደራው አዲሱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ።በመላው አለም የሚገኙ ተቆጣጣሪዎች በFTX ላይ ምርመራ ጀምረዋል ይላል The Economist መጽሔት። የአሜሪካ ፍትሕ ሚንስቴርና የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት/ሴኔት/አበክሮ ምርመራ መጀመሩ ከፍ ብሎ ተመልክቷል ። በFTXና በእህት የክሪፕቶ ከረንሲ ኩባንያው ብልሹ አሰራር መኖሩ እንደተሰማ በ72 ሰዓት ውስጥ ሸሪኮቹ ተሯሩጠው 6 ቢሊየን ዶላራቸውን ወስደዋል። አበው ”በእንቅርት ላይ ቆረቆር ”እንዲሉ መክሰሩን ለመንግስት አመልክቶ ከለላ እንደጠየቀ ውስጥ አዋቂ እንደሆነ የሚገመት የኮምፒውተር ሰርሳሪ/hacker/470 ሚሊየን ዶላር እንደመነተፈው መጽሔቱ ይገልጻል ።
ነገርን ነገር ያነሳዋልና አለምን ጉድ ስለሰራችው የክሪፕቶ ንግስት ላንሳና ምናባዊ ገንዘብ ምን ያህል ለማጭበርበር እንደተጋለጠ ተጨማሪ አስረጅ እንመልከት። ፈልጎ አስፈልጎ ያጣት ኤፍቢአይ/FBI/ሰሞኑን በጥብቅ ከሚፈልጋቸው 10 አደገኛ ተጠርጣሪዎች ዝርዝር አካቷታል። የታይም መጽሔት በሰው ልጆች ታሪክ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ማጭበርበር ይለዋል። ትውልደ ቡልጋሪያ ጀርመናዊ ናት ። ዋንኮይን ከተሰኘው አጭበርባሪ ኩባንያ ጋር ተያይዞ ስሟ በአለም ናኝቷል። ቢቢሲ የውሃ ሽታ የሆነችው የክሪፕቶ ንግስት ሲል የምርመራ ዘገባ ሰርቶባታል ።
ምን አልባት ተገድላ ይሆናል የሚሉ አሉ ። አይ በፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ማንነቷን ቀይራ ጀርመን እየኖረች ነው የሚሉም አልታጡም ። አይ ዱባይ ታይታለች ፤ የለም ራሽያ ነው ያለችው እየተባለች መንፈስ ሆና አርፋዋለች። በማጭበርበር ወንጀል ተጠርጥራ በመላው አለም እየታደነች ነው ። ከተሰወረች 5ኛ አመቷን ይዛለች ። ከ4 እስከ 15 ቢሊየን ዶላር በማጭበርበር የምትጠረጠረውና የክሪፕቶ ንግስት በሚል ቅጽል የምትታወቀው ዶ/ር ሩጃ ኢግናቶቫ ዕምጥ ትግባ ስምጥ ከተሰወረች 5ተኛ አመቷን ይዛለች።
ኤፍቢአይ ቢታክተው ማንነቷን ሳትቀይር አልቀረችም ማለት ጀምሯል ። በፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ወይም በሌላ መንገድ መሆኑ ነው ። ዕድሜዋ በ40ዎቹ የሚገመተው የቡልጋሪዋ ዕንስት አፍቢአይን ጨምሮ በኢንተርፓል የምትታደነው ዋንኮይን/Onecoin/በተሰኘ ክሪፕቶከረንሲ በተፈጸመ እጅግ ከፍተኛ ማጭበርበር ነው ።
ኤፍቢአይ በ2017 ዓም የዕስር ማዘዣ ይዞ ለጥያቄ ማፈላለግ ሲጀምር ነው የክሪፕቶ ንግስቷ ድንገት የውሃ ሽታ የሆነችው ይላል የቢቢሲው ሊዎ ሳንድስ። ነገሩ ወዲህ ነው በ2014 ዓም ራሱን ክሪፕቶከረንሲ ብሎ የሚጠራው ዋንኮይን፤ ከረንሲውን ለሚያሻሽጡለት ኮሚሽን እንደሚከፍል ይፋ አደረገ። ሆኖም ዋንኮይን እንደሌሎች ክሪፕቶከረንሲዎች ዋስትና ወይም መተማመኛ የሚሰጥ የብሎክቼይን አሰራር አልዘረጋም።
የኤፍቢይ መርማሪዎችም ሆነ የፌደራል አቃቢ ሕጎች ዋንኮይን ክሪፕቶከረንሲ ሳይሆን የማጭበርበሪያ ስልት ነበር የሚሉት ለዚህ ነው ። የማንሀተኑ አቃቢ ሕግ ዳሚን ዊሊያምስ ንግስቷ የማጥመጃ መረቧን የጣለችው ሕዝበ አዳም ከክሪፕቶከረንሲ ጋር እልል በቅምጤ የሚልበትን ትክክለኛ ጊዜ መርጣ ነው ይላሉ ። ኤፍቢይ ባለፈው ሰኔ 23 በ8 የተለያዩ ወንጀሎች ጠርጥሮ የከሰሳትን የክሪፕቶ ንግስት ያለችበትን ለጠቆመ 100ሺህ ዶላር በወሮታ እንደሚከፍል ቃል ገብቷል።
ኤፍቢአይ ይሄን ማስታወቂያ ማስነገሩ ዶ/ር ኢግናቶቫን ለመያዝ ያግዘዋል ይላል የዋንኮይንን ማጭበርበር በምርመራው ያጋለጠው የቢቢሲው ጄሚ ባርትሌት ፤ የክሪፕቶ ንግስቷን መያዝ አዳጋች ያደረገው እጇ ላይ ይገኛል ተብሎ የሚገመተው ረብጣ ግማሽ ቢሊየን ዶላር ነው ይላል የምርመራ ጋዜጠኛው ባርትሌት።
አበውስ ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ አይደል የሚሉት ፤ ሀሰተኛ ማስረጃዎችን በማዘጋጀት የተካነች መሆኗና ገጽታዋን መቀያየሯ በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚደረገውን ጥረት ፈታኝ ያደርገዋል ይላል ባርትሌት፤”ዶ/ር ኢግናቶቫ ለመጨረሻ ጊዜ የታየችው በ2017 ዓም ከትውልድ ሀገሯ ቡልጋሪያ ወደ ግሪክ ስትበር ነው ይለናል ቢቢሲ፤ በተለይ ባርትሌት እንዲያውም ሞታም ሊሆን ይችላል እስከ ማለት ደርሷል ።
በዋንኮይን ገንዘቧን የተጭበረበረችው ጄን ማክአዳም እሷም ሆነች ጓደኞቿ እስከ 250ሺህ ፓውንድ የሚደርስ እንደተበሉ ለቢቢሲ ተናግራለች ። ጓደኛዬ ሊያመልጠን የማይገባ የኢንቨስትመንት እድል ስትል መልዕክት ትልክልኛለች። ከዚያ ወዲያው በዌቢናር ሊንኩን ተጠቅሜ ዋንኮይንን ተቀላቀልሁ ትላለች ማክአዳም ያቺን ዕድለ ቢስ ቀን ስታስታውስ ።
መጭበርበሬን የተረዳሁት ከወራት በኋላ ነው ። ራሷን የክሪፕቶ ንግስት ብላ የምትጠራው ዶ/ር ሩጃ ኢግናቶቫ ቢትኮይንን የሚፎካከር ዋንኮይን የተሰኘ ክሪፕቶከረንሲ ፈጥሪያለሁ በማለት በማይጨበጥ ተስፋ እየሞላች ቢሊዮኖችን ኢንቨት እንዲያደርጉ ታግባባ ነበር ሲል ያስታውሳል የቢቢሲው ባርትሌት ፤ በ2016 ሰኔ ግም ሲል ዓም የዛን ጊዜዋ የ36 አመት የንግድ ሰው ዶ/ር ሩጃ ኢግናቶቫ ከአፍ እስከ ገደፍ በአድናቂዎቿና በተከታዮቿ በተሞላው በታዋቂው የዌምብሌ አሪና/የመሰብሰቢያ አዳራሽ/በውድ ቀሚሲ ተውባ በአልማዝ ጉትቻ አጊጣና ደማቅ ቀይ ሊፕስቲክ ተቀብታ ብቅ ስትል አዳራሹ በጩኸትና በፉጨት አስተጋባ ።
ዋንኮይን በአለማችን ታላቁ የክሪፕቶከረንሲ ለመሆን እየገሰገሰ መሆኑን ፤ በየትም ቦታ ማንኛውንም ክፍያ መፈጸም እንደሚያስችል ለአድናቂዎቿ ገለጸች ይለናል ባርትሌት ፤ ቢትኮይን ዋጋው ከሽርፍራፊ ሳንቲሞች ተነስቶ በ2016 ዓም አጋማሽ ላይ ወደ መቶ ዶላሮች ማሻቀቡ የብዙ ኢንቬስተሮችንና ሌሎችን ቀልብ መሳቡና ተፈላጊነቱ ማደጉ ይነገራል ። ዶ/ር ሩጃ ዋንኮይን ቢትኮይንን በቅርቡ እንደሚዘርረውና በሁለት አመታት ውስጥ ማንም ስለቢትኮይን እንደ ማያወራና ታሪክ እንደሚሆን በመፎከር በአሪናው የታደሙ የደጋፊዎቿን ልብ አሞቀች ።
ወቅቱ በመላው አለም የሚገኙ ሰዎች ዋንኮይን ላይ ኢንቨስት በማድረግ የዚህ አዲስ ክስተት አካል ለመሆን የቋመጡበት ነበር ይላል የምርመራ ጋዜጠኛው ባርትሌት ፤ ለቢቢሲ ሾልኮ የደረሰ ሰነድ በዚሁ አመት የመጀመሪያዎቹ 6 ወራት ብቻ እንግሊዛውያን 30 ሚሊየን ፓውንድ ኢንቨስት ማድረጋቸውን ያስረዳል። እንግሊዛውያን በአንድ ሳምንት ብቻ ዋንኮይን ላይ 2ሚሊየን ፓውንድ ኢንቨሰት አድርገዋል። ከነሐሴ 2014 እስከ 2017 ዓም ከመላው አለም ከፓኪስታን እስከ የመን ፣ ከብራዚል እስከ ፓሊስታይን ፣ ከሆንግኮንግ እስከ ኖርዌ 4 ቢሊየን ፓውንድ ዋንኮይን ላይ ኢንቨስት አድርገዋል።
የሚያሳዝነው ይላል የምርመራ ጋዜጠኛው እነዚህ ሁሉ ኢንቨስተሮች ያላወቁት ነገር ይልና ፤ ከዚያ በፊት ግን ክሪፕቶከረንሲ እንዴት እንደሚሰራ ያብራራል ። በዘርፉ ሙያ የሌለው ማንኛውም ሰው በቀጥታ ድረ ገጽ ውስጥ ገብቶ ስለ “ክሪፕቶከረንሲ”ቢጎለጉል ፤ ግራ የሚያጋቡና የሚያምታቱ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ውጤቶችን ይዘረግፍለታል። ስለሆነም ገንዘብን የሚያህል ነገር እንዲህ ባልለየለት ነገር ላይ ማፍሰስ አይመከርም ይላል ባርትሌት። ለዛሬ በዚህ ላብቃ ። ፈጣሪ የተጀመረውን ሰላም ያጽናልን !
አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ኅዳር 28/ 2015 ዓ.ም