ባለፉት ጊዜያት በሀገራችን ሰላምና መረጋጋት ጠፍቶ ፈተናዎቿ አይለው በውስጥ ሆነ በውጭ ኃይሎች ሲደርስባት የነበረው ጫና በርትቶ ቆይቷል። አሁን ላይ ሰላምን ለማስፈን እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ተስፋ የሚፈነጥቁ ቢሆንም በሌላ በኩል ደግሞ የሀገር እድገት የሚገታው ሌብነት እየተስፋፋ ነው።
በሀገራችን ማህበረሰብ ዘንድ ሌብነት ነውርና ጸያፍ ተግባር መሆኑ ሲነገር ኖሯል፤ ሌባ የተባለ ወይም ሲሰርቅ የተገኘ ሰው በህብረተሰቡ ዘንድም የሚወገዝና የተገለለም ነበር። ይህም ሆኖ በመንግሥት ስልጣን ሲሆን ግን ‹‹ ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› በሚል ብሂል ሌብነት ሲበረታታ ይታያል። ህብረተሰቡ ሌባውን እያበረታታ ይብስ ብሎ ሌብነት የሚጠየፈውን የሚኮንንበት አጋጣሚዎችም አይጠፉም። እገሌ እኮ ባለስልጣን ሆነ ሲባል ብዙ ነገሮችን ከእሱ ይጠብቃል።
ሰውየው በባህሪው ሌብነትን የሚጠየፍ ቢሆን እንኳን ከራሱ ሰዎች ማለትም ከሚስቱ ጀምሮ ከቅርብ ሰዎቹ ሳይቀር ወደ ሌብነት የሚገፋፋው አካል አይጠፋም። ሁሉ በእጅህ ሁሉ በደጅህ ሆኖ ማድረግ እየቻልክ ለምን አታደርግም ። እገሌን አታየውም እንዴ በስልጣኑ ተጠቅሞ ከራሱ አልፎ ለዘመዶች ሳይቀር ያንበሸበሸውን ሀብትና ንብረት ተመልከት፤ ይልቅ ጊዜህን ተጠቀምበት የሚሉ ጎትጓቾች በዙሪያ አይጠፉም። በዚህ አጥፊ ምክርም በተፅዕኖ ውስጥ የሚወድቁ ሰዎች ይታጣሉ ማለት አይቻልም።
ስልጣን ላይ ያለው አካልም ስልጣን አግኝቶ በስልጣኑ ሳይጠቀም ቢወርድ ነገ እውን ሊቆጨው እንደሚችል በመገንዘብ መመዝበሩን ይያያዘዋል። ሰውየው በስልጣን ላይ እያለ ከተጋለጠና በህግ ጥላ ሥር ሆኖ ወደ ወህኒ ከወረድ በኋላ ደግሞ ሙስና በልቶ ነው በማለት ቀለል ሲያደርገው ይታያል። ይህ የሚፈጸመው ደግሞ ሌብነትን በጽኑ ይጠየፋል ከሚባለው ማህበረሰብ ውስጥ መሆኑ ለምን የሚለውን እንድንጠይቅና ያለፍንባቸውን ሥርዓቶች እንድንመለከት ያስገድደናል።
ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በሀገራችን የታየው ሌብነት እንኳን ብንመለከት በቂ ነው። በወቅቱ የነበረው መንግሥትም የሰረቁ ባለስልጣናት ላይ ህብረተሰብ ጥቆማ ሲሰጥ ለሌባው አካል ሽፋን እየሰጠ ከነበሩበት ስልጣን ላይ በማንሳት ከፍ ባለ የተሻለ የሚበዘብዙበት ስልጣን ሲሰጥ ይስተዋል ነበር። ይህ የሚያሳየን የመንግሥት መዋቅራዊ አሠራር ጭምር ለሌብነትና ለብልሹ አሠራር የተጋለጠ እንደነበር ነው።
ስርአቱ ለሌብነት የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ በመሆኑ በርካቶች ሌብነትን ለመከላከል የተበጁ ስርአቶችን ሳይቀር ሆነ ብለው በማፍረስ የህዝብን ንብረት ለራሳቸው ጥቅም ሲያውሉ በስፋት ተስተውሏል። ለዚህም ሩቅ መሄድ ሳያስፈልግ በአዲስ አበባ ከተማ በርካታ ባለቤት አልባ ህንጻዎች መገኘታቸው ሌብነቱ ምን ያህል ስር የሰደደ መሆኑን እና እንደ ህብረተሰብ ሌብነትን እየተለማመድን መምጣታችን ማሳያ ነው።
ከለውጡም በኋላ ቢሆን እየታየ ያለው ሌብነት ምንም አይነት መሻሻል የማይታየበት እንዲያው ከድጡ ወደ ማጡ የሚያስብል እየሆነ ነው። በተለይ ለህብረተሰብ አገልግሎት የሚሰጡ አካላት መንግሥት ደመወዝ እየከፈላቸው ለህብረተሰብ በነጻ አገልግሎት መስጠት እየተጠበቀባቸው ህብረተሰብን በማጉላላትና ለእንግልት በመዳረጋቸው ሳያንስ በግልጽ ጉቦን የሚጠይቁ አካላት ተበራክተዋል። ይህም የህብረተሰቡ የቀን ከቀን እሮሮ እየሆነ መጥቷል።
ሀገርን ከገባችበት ፈተና ለመታደግ ያላትን የሌላትን አቅም አጠራቅማ ደፋ ቀና በምትልበት በዚህ ወቅት የሀገርን ፈተና እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም መንግሥት አንዱን ቀዳዳ ሲደፍን ሌላ ቀዳዳ እያበጁ ለሌብነት እራሳቸውን እያዘጋጁ ያሉ ኃይሎች እየተበራከቱ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ በተካሄደበት ወቅት ለምክር ቤት አባላት በሰጡት ምላሽ እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ የሰፈነው ሌብነት በጣም አታካች ሁኔታ ላይ ደርሷል። በተለይ ሀገር የገጠማትን ፈተና እንደ እድል የወሰዱ ሰዎች ቀይ መስመር የተባለውን የሌብነት ቀይ ምንጣፍ አድርገው በነጻነት እየተንሸራሸሩበት ነው። ይህም በሀገር የኢኮኖሚ ላይ እያስከተለ ያለው ጫና ቀላል አይደለም።
ህብረተሰቡ አገልግሎት ፈልጎ ጎራ የሚልባቸው የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት ከማፈጠን ይልቅ ግልጽነት የሌለው ብልሹ አሠራር በመከተል ለሚሰጡት የተንዛዛ አገልግሎት ጉቦ በመጠየቅ የማይገባቸውን ጥቅም ለማጋበስ ሲጣጥሩ መታየታቸው የተዘረጋው አሠራር ተጠያቂነትን ያላሰፈነ እንደሆነ አመላካች ነው።
የሌብነት ድርጊቱ የሚፈጸመው በተወሳሰበ ሰንሰለት በጥቅም በተሳሰሩ አካላት መሆኑን ህብረተሰቡ ይናገራል። ከፈጻሚ አካል ጀምሮ እላይ እስከተቀመጠ አመራር ድረስ ለሌብነትና ለብልሹ አሠራር የተጋለጡ መሆናቸውን የሚናገሩትም ብዙዎች ናቸው። ለእነዚህ አካላት ባልተገባ ድርጊታቸው የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲኖር በማድረግ በመንግሥትና በህብረተሰቡ መካከል ቅሬታ በመፍጠር ህዝቡን ለምሬት የሚዳርጉ ናቸው።
ሌላው ቀርቶ በመንግሥት አፍንጫ ሥር ቁጭ ብለው ሌብነት የሚፈጸሙ አካላት ሳይቀር ቶሎ ሳይደረስባቸው በመቅረቱ መንግሥትን ሳይቀር እያሳሳቱ የመንግሥትን ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ እየከተቱ ይገኛሉ። ለአብነት በአዲስ አበባ የኮንደሚንየም ቤት እጣ አወጣጥ የተከሰተው ድርጊትን ማንሳት ይቻላል።
በመሬት ጉዳይ የሚነሱ ቅሬታዎችንም ብንመለከት በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ከመሬት ዝርፊያ ጋር በተያያዘ የወረዳ ዋና ስራ አስፈፃሚን ጨምሮ በመሬት ጉዳይ ይወስኑ የነበሩ አመራሮች፣ባለሙያዎች፣ ደላሎችና በዚህ ድርጊት የተሳተፉትን በመለየት ለህግ እንዲቀርቡ እንቅስቃሴ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ከ37 ተጠርጣሪዎች ውስጥ እስካሁን ድረስ 12 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉ ከተማ አስተዳደሩ ሌብነቱ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ተሰግስገው ባሉ አካላት ጭምር እንደሆነ አንዱ ማሳያ ነው ።
እንዲህ አይነት ሌቦች በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ተሰግስገው መገኘታቸው ሌብነትን ከሥር መስረቱ ለመንቀል የሚደረገው ሂደት ላይ እንቅፋት ሆኗል። አሁን ላይ መንግሥትም ሌብነትን ለመከላከል ሀገራዊ ኮሚቴ በማቋቋም እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት የሚበረታታ ቢሆንም ግልጽኝነት የሰፈነበት እና ተጠያቂነት ያለበት አሠራር መዘርጋት ደግሞ ከራሱ ከመንግሥት የሚጠበቅ ይሆናል።
ህብረተሰቡም በሌብነት ውስጥ ተቀባዩን አካል ብቻ ሳይሆን ሰጪውንም አካል ተጠያቂ የሚያደርግ በመገንዘብ ጉቦ ባለመስጠት፣ ሌብነትን የሚያስፋፉ ተግባራት ሲመለከት በመጠቆም የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት። ሌብነት የሚጎዳው ሀገርን ብሎም ህዝብን በመሆኑ ሁላችንም የድርሻችንን በመወጣት ሌብነትን የሚጠየፍ ተጠያቂ ዜጋን ማፍራት ይጠበቅብናል።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ኅዳር 28/ 2015 ዓ.ም