አዲስ አበባ፡- መንግሥት በጦርነት ተጠምዷል በሚል የሀገር ሃብት ዘረፉ ላይ በተሠማሩ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር አበራ ብሩ ገለጹ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ19ኛ ጊዜ በሀገር ደረጃ ለ18ኛ ጊዜ የሚከበረውን የፀረ ሙስና ቀን አስመልክቶ በአቃቂ ክፍለ ከተማ በሚገኙ 12 ወረዳዎች ሲካሄድ የቆየው የፀረ ሙስና ትግል ንቅናቄ ማጠቃለያ በክፍለ ከተማ ደረጃ ባለፈው ሳምንት ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ ውይይት የመሩት የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር አበራ ብሩ እንደገለጹት፤ መንግሥት በጦርነት ተጠምዷል በሚል የሀገር ሃብት ሲዘርፉ የነበሩ ሰዎች ተለይተዋል። መንግሥት በነዚህ ከፍተኛ ሙስና በሠሩ አካላት ላይ የማያዳግም ርምጃ ይወስዳል።
ከዚህ በፊት የሙስና መከላከል ቀን ቢከበርም ሙስና እንደ አንድ የሥርዓቱ አካል ተዘርግቶ ስለነበር ከወረቀት ያለፈ ሥራ መሥራት ሳይቻል መቆየቱን ያነሱት ዶክተር አበራ፤ አሁን የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ ሙስናን በመከላከል ረገድ ወደ ተግባር መግባት ነው ብለዋል።
የሙስና ተግባርን በመረጃ ለማስደገፍ እጅግ ከባድ እና ውስብስብ መሆኑን ጠቁመው፤ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ በዚህ ጉዳይ ላይ የማይተካ ሚና ስላለው እና ከኅብረተሰቡ ተደብቆ የሚቀር ስለሌለ ማኅበረሰቡ በነቃ ተሳትፎ ሌቦችን ማጋለጥ አለበት ብለዋል።
መንግሥት ከባድ ትግል ውስጥ እንዳለ በመገንዘብ ኅብረተሰቡ በሙስና ጥቆማ ተሳትፎ ላይ ንቁ መሆን አለበት ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ በሙስና ላይ የሚደረግ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ መንግሥት ለሚወስደው እርምጃ ደጋፊ ስለሚሆን ችላ ማለት እንደማይገባ ጠቁመዋል።
በመድረኩ ላይ ሙስናን መታገል በተግባር በሚል ዙሪያ ለውይይት መነሻ የሚሆን ሰነድ ያቀረቡት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በአቅም ግንባታና ሁኔታ ግምገማ ማስተባበሪያ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዘነበ ወይሳ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በሙሰኝነት ሚዛን ከዓለም ሀገራት አንፃር ያለችበትን ደረጃ ማሻሻል የሚቻለው የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ሲያድግና ሙስናን ተመልክቶ አያገባኝም ብሎ የማያልፍ ትውልድ መፍጠር ሲቻል ነው ብለዋል።
ሙስና ነውር እንዲሆን ባለመሠራቱ እና በአኗኗር ዘይቤያችንና ሥነ ቃሎቻችን ሙስናን አሽሞንሙነን ስለያዝነው ኢትዮጵያ ታማለች ያሉት ኃላፊው፤ ሙስናን በቃል ሳናሽሞነሙን ሌብነትም ወንጀልም መሆኑን በማመን ሀገራችንን ልናክም ይገባል ብለዋል።
ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ ነዋሪዎች ሙስናን የመከላከል መድረክ መዘጋጀቱን አመስግነዋል።
ሆኖም በሙስና ጥቆማ ላይ ሲሳተፉ ከዛቻ ጀምሮ እስከ ድብደባ እንደሚደርስባቸው ገልፀው ይህ ሁኔታ ሙስናው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ እንዳለ እንዲጠራጠሩ እንዳረጋቸው ገልፀዋል።
በተጨማሪም ጥቆማ የተደረገባቸው የወረዳና ክፍለ ከተማ አመራሮች ላይ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ያሉበትን ቦታ ሲዘዋወሩ እንጂ እርምጃ ሲወሰድባቸው ባለማየታቸው ቅሬታ እንዳሳደረባቸው አንስተዋል።
በተለይ የመሬት አስተዳደር እና የክፍለ ከተማ የፍትሕ ተቋማት ላይ ፍተሻ እንዲያደርግ የክፍለ ከተማውን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጠይቀዋል። አመራሩ በቁርጠኝነት ለመታገል ከተነሳ ከጎናችሁ ነን ሲሉም የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ውብሸት ሰንደቁ
አዲስ ዘመን ኅዳር 28/ 2015 ዓ.ም