የ 75 ሺህ ዓመቷ ኒያንደርታል ሴት ፊት ይፋ ሆነ

የሳይንስ ሊቃውንት የኒያንደርታል ሴት በሕይወት እያለች ምን እንደምትመስል የሚያሳይ አስደናቂ ምስል ይፋ አድርገዋል። ምስሉን መሠረት ያደረጉት ደግሞ በቁፋሮ የተገኘ ለስላሳ አጥንት ላይ መሆኑ ተገልጿል። ተመራማሪዎች አጥንቶቹን እንደገና ከመገጣጠማቸው በፊት ማጠናከር ነበረባቸው። በኋላም ባለሙያዎች ልዩ የ3ዲ ሞዴል ለማዘጋጀት በቁ።

ምስሉ ‘የኒያንደርታልስ ምስጢሮች’ በሚለው ዘጋቢ ፊልም ላይ ለዕይታ ቀርቧል። የዘጋቢው ፊልም ዓላማ ከ40 ሺህ ዓመታት በፊት ስለጠፉት የሰው ዘሮች ስለሚታወቁ ነገሮች ለመመርመር ነው። ቅርጹ ለእነዚህ ሰዎች ፊት ያዘጋጅላቸዋል።

“ከማንነታቸው ጋር እንድንገናኝ የምትረዳን ይመስለኛል” ሲሉ በኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ፓሌአትሮፖሎጂስት የሆኑት ዶክተር ኤማ ፖሜሮይ ተናግረዋል። “ከየትኛውም አካል ጋር መሥራት መቻል በጣም አስደሳች እና ትልቅ ዕድል ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ሞዴሉ የተሠራበት የራስ ቅል በኢራቅ ኩርዲስታን ሻኒዳር ዋሻ ውስጥ የተገኘ ነው። እአአ በ1950ዎቹ ቢያንስ 10 የሚደርሱ የኒያንደርታል ወንዶች፣ ሴቶች እና ህጻናት ቅሪተ አካል የተገኙበት ድንቅ ቦታ ነው። እአአ በ2015 አንድ የብሪቲሽ ቡድን በኩርድ ባለሥልጣናት ግብዣ ቀረበለት። ብዙም ሳይቆይ ሻኒዳር ዚ የሚል ስያሜ የተሰጠው እና አከርካሪ፣ ትከሻ ፣ ክንዶች እና እጆችን ጨምሮ የግለሰቡን የላይኛው አካል ያካተተ አዲስ ቅሪተ አካል አገኙ።

የራስ ቅሉ ወደ 2 ሴንቲ ሜትር ገደማ ተጨፍልቋል። ይህም ከበርካታ ዓመታት በፊት ከዋሻው ላይ በወደቀ ድንጋይ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለ። በሻኒዳር አዲሱን ቁፋሮ የመሩት የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ግሬም ባርከር “ራስ ቅሉ ልክ እንደ ፒዛ ጠፍጣፋ ነበር” ብለዋል።

“ከዚያ አሁን ወደምታየው መሸጋገር በጣም አስደናቂ ጉዞ ነው። አንዳንድ ጊዜ እንደ አርኪኦሎጂስት የተለየ ነገር ላታገኝ ትችላለህ። ያለፈውን ነገር በመዳሰስህም ትገረማለህ። ልዩ የሆነ ነገር ምን እንደሆነ እንረሳዋለን።” በአካባቢው የጥንታዊ ቅርሶች ቢሮ ፈቃድ፣ የራስ ቅሉ ስብርባሪዎች ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ተወስደው እንዲገጣጠሙ የተደረገ። ውስብስብ የሆነው ሥራ ለማጠናቀቅ ከአንድ ዓመት በላይ ፈጅቷል።

የተገጣጠመው የራስ ቅሉ በየአቅጣጫው ፎቶ እንዲነሳ ተደረገ። ይህም በ3ዲ ህትመት ስመጥር ለሆኑት የደች አርቲስቶች አድሪ እና አልፎንስ ኬኒስ ተሰጠ። አርቲስቶቹ የጥንት ሰዎችን በ3ዲ በማዘጋጀት ተክነውበታል። ሴት መሆኗን እርግጠኛ ናቸው። የዳሌ አጥንቶች ለማረጋገጥ ቢረዱም ከላይኛው የሰውነት ክፍል ጋር አልተገኙም።

ይልቁንም ተመራማሪዎቹ ከሴት ዘረመል ጋር በተያያዙ እና ጥርስ ውስጥ በሚገኙ የተወሰኑ ዋና ዋና ፕሮቲኖች ላይ ተመርኩዘው ሴት መሆኗን አረጋግጠዋል። የቅሪተ አካሉ ቁመት አነስተኛ መሆኑም ድጋፍ ይሰጠዋል ተብሏል።

በ40ዎቹ አጋማሽ ላይ እንደሞተች ይገመታል። ይህንንም እስከ ሥሩ ድረስ በበሰበሱ ጥርሶቿ መለየት ተችሏል።”ጥርሶች በዚህ ደረጃ በሚበሰብሱበት ጊዜ እንደቀድሞው ማኘክ አይሆንለትም። በመሆኑንም እንደቀደመው መብላት አትችልም” ሲሉ ዶ/ር ፖሜሮይ ተናግረዋል።

“ሌሎች የጥርስ ጤንነት መጓደል ምልክቶች አሉ። አንዳንድ ኢንፌክሽኖች እና የድድ በሽታም ነበሩ። በወቅቱ ወደ ተፈጥሯዊ የሕይወቷ መጨረሻ እየደረሰች ነበር ብዬ አስባለሁ።” ነው ያሉት፡፡ኒያንደርታሎችን ከእኛ ዝርያ ጋር በማነጻጸር አደገኛ እና ያልተወሳሰቡ እንደሆኑ አድርገው ሳይንቲስቶች ለረዥም ጊዜ ይቆጥሩ ነበር።አነዚህ አመለካከቶች ግን በሻኒዳር ከተገኙት ቅሪተ አካሎች በኋላ መለወጣቸውን መረጃዎች ያረጋግጣሉ።

ዋሻው የቀብር ሥርዓት ስለመኖሩ ማሳያ ነው። አስከሬኖች ከረዥም የድንጋይ ምሰሶ አጠገብ ባለው ጉድጓድ ውስጥ በጥንቃቄ ተቀምጠዋል። ሁሉም አስከሬኖች የተቀመጡበት መንገድ ተመሳሳይ ነው። አንዳንዶች እነዚህ ኒያንደርታሎች አበቦችን ተከትለው ዋሻዎቹ ውስጥ የገቡ ሊሆኑ እንደሚችሉ እንዲከራከሩ አድርጓቸዋል። ይህም ምናልባት መንፈሳዊ መነቃቃትን ወይንም ሃይማኖትንም ሊያመለክት ይችላል መባሉን ተመልክቷል።

የብሪታንያ ተመራማሪዎች ቡድን ግን የአበባው ብናኝ እዚያ የተገኘው ንቦች ወይም ደግሞ በአከስሬኑ ላይ ከተቀመጡ የአበባ ቅርንጫፎች ሊሆን እንደሚችል ያስባሉ። “በአበቦቹ ምክንያት ሳይሆን ቅርንጫፎቹ እራሳቸው ጅቦችን ወደ አስከሬኑ እንዳይገቡ መከላከል ይችሉ ነበር” ሲሉ የሊቨርፑል ጆን ሞሬስ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባው ፕሮፌሰር ክሪስ ሃንት ተናግረዋል።

“ቀብር የሚለውን ቃል ለመጠቀም አልደፍርም። ከቀሳውስት እና ከቤተክርስቲያን ሃሳብ ለመራቅም ‘ማስቀመጥ’ የሚለውን ቃል የምጠቀም ይመስለኛል። ይህንን ወግ እንደያዙት ምንም ጥርጥር የለውም” ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ሚያዚያ 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You