የሰሜን እዝ ጥቃትን ተከትሎ በሕወሓትና በፌደራል መንግስት መካከል የተደረገው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሁለት አመት ዘልቆ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተደረገ የሰላም ስምምነት ወደ ፍፃሜው እየሄደ ነው ።በዚህ ጦርነት በርካቶች ለሞት፣ ለአካል፣ ጉዳት እና ለስደት ተዳርገዋል ።ከፍተኛ የሆነ የአገር ኢኮኖሚም ወድሟል ።
ጦርነቱ የፈጠረውን ክፍተት በመጠቀምም የመንግስትና የህዝብ ሀብትን ለመመዝበር ሲታተርሩ የነበሩ ግለሰቦች በርካቶች ናቸው ።ከነዚህ ግለሰቦች መካከልም የመንግስት ባለስልጣናት ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ መንግስት ሀላፊነት የሰጣቸው ግለሰቦች አገር በከፍተኛ የህልውና ስጋት ውስጥ በወደቀችበት ሰዓት የስጋቱ አካልም ሆነው የታዩበት አጋጣሚ ተስተውሏል።
‹‹ግርግር ለሌባ ይመቻል›› እንደሚባለው እነዚህ የመንግስት ባለስልጣናት አገር ጭንቅ ውስጥ በገባችበት ወቅት ካላት ሃብት ላይ ለመዝረፍ ያላደረጉት ጥረት የለም ። ሕወሓት ገፍቶ ደብረሲና ሲደርስ መሀረብ አውጥተው እንኳን ደህና መጣህ ብለው ለመቀበል የተዘጋጁም ጥቂቶች አይደሉም ።
ይህም ምን ያህል የአገርን ህልውና ሳይቀር ለግል ጥቅም አሳልፈው ለመስጠት ከራሳቸው ጋር የመከሩ ራስ ወዳዶች የእነርሱ ጥቅም አይነካ እንጂ ማንም መጣ ማንም ሄደ በተፈጠረው አጋጣሚ ሁሉ ትርፍ ለማግኘት የሚጣጣሩ ሌቦች ስለመሆናቸው የቀደመም ታሪካቸው የሚያሳብቅባቸው ናቸው ።
ሌሎች በራሳቸው ይሁን ከነዚህ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር በመመሳጠር በሸቀጦች ላይ ያለተገባ ጭማሪ በማድረግ ዜጎች እንደአቅማቸው ሸምተው እንዳይገቡ ሲያደርጉ የነበሩ፤ ዛሬም እኩይ ተግባራቸውን እየደገሙ ያሉ ህገወጥ ነጋዴዎች ናቸው።
ለነዚህ ነጋዴዎች እስካተረፋቸው ድረስ በጦርነት እና በሰላም መካከል ያለው ልዩነት የሚታይ አይደለም። እነርሱ የሚፈልጉት ግርግር በተፈጠረ ቁጥር በምርት ላይ ያልተገባ ዋጋ እየጨመሩ ትርፍ ማግኘት ነው። በእነሱ ምክንያት የሚፈጠረው ማህበራዊ ምስቅልቅል ጉዳያቸው አይደለም ፤እንደ ዜጋም አያሳሰባቸውም።
በዚህ መንገድ የሰበሰቡትን ሀብት ለመጠቀም እንኳን /ለመብላት /አገር መኖር እንዳለባት ለማስተዋል የታደሉ አይደሉም ። በነሱ ምክንያት የሚፈጠር አገራዊ እሳት እነሱን እንደሚበላቸውም ለማሰብ የሚችል አእምሮ ባለቤትም አይደሉም።
ሌሎች ደግሞ በደህናው ጊዜ ያልገደሉትን ጉዳይ ግርግር ተጠቅመው እጅ መንሻ በመስጠት ለመቋጨት ረጅም ርቀት ሄደዋል ።ጉዳይ ፈፃሚውም ይህ ሁነኛ ጊዜ ነው ብሎ እጅ መንሻ አሰፍስፎ ተቀብሏል ።እዚህ ጋር ጉዳይ አስፈፃሚውም ሆነ ፈፃሚው እኩል በክፉ ቀን በአገር ላይ ወንጀል ሰርተዋል ።
እነዚህ የግርግር ሌባዎች አገር ችግር ሲገጥማት ለትርፍ ውርውር የሚሉ አገር ሰላሟ ሲመለስ ደግሞ ድምፃቸውን የሚያጠፉ ናቸው ።ግርግሩ ካለፈ በኋላ ምንም እንዳልተፈጠረ በህብረተሰቡ ውስጥ ተደብቀው የሚኖሩ ናቸው ።
ለመሆኑ እነዚህ ሰዎች ዛሬ ላይ ምንም እንዳልተፈጠረ ቆጥረው መደበኛ ስራዎቻቸውን እየሰሩ ነው? ወይስ በአገርና በህዝብ ላይ ለፈፀሙት ወንጀል ተገቢውን ፍርድ አግኝተዋል ? ይህን ጥያቄ የፍርድ አካላት የሚመልሱት ይሆናል ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተደጋጋሚ ቀርበው በሙስና ላይ የማያወላዳ አቋም እንዳላቸው ተናግረዋል ።በሙሰኞች ላይ የሚወሰደው ርምጃም ጠንካራ እንደሚሆን ገልጸዋል። እንደውም ስሙን ቀይረው ሙሰኛ ሳይሆን ሌባ ነው ማለት ያለብን ሲሊ ተደምጠዋል ።
ነገር ግን አሁንም ድረስ በሙሰኞች ላይ አስተማሪ የሆነ ቅጣት ሲተላለፍ አይታይም ።ፍርድ ቤቶችም በሙሰኞች ላይ የሚስተላልፉት የቅጣት ውሳኔ ለህዝብ ሲቀርብ አይታይም ።ይህም ሙሰኞች ከመሸማቀቅ ይልቅ በተፈጠረው አጋጣሚ ሁሉ ለተጨማሪ ሌብነት ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ አድርጓቸዋል ።
እዚህ ጋር ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ በነዚህ ሙሰኞች ምክንያት አገር ያላትን ሃብት እያጣች ነው። ለተለያዩ ህዝባዊ አገልግሎት መገንቢያ ሊውል የሚችል ገንዘብም ያለምንም ምክንያት በከንቱ እየባከነ ነው። ከሁሉ በላይ ደግሞ ይህ ሃብት የሚመዘበረው ምስኪኑ ማህበረሰብ ከሚከፍለው ግብር ላይ በመሆኑ ጉዳዩ ይበልጡኑ ያማል ።
በርግጥ ቻይናን የመሰሉና ሌሎች አገራት በሙስና ላይ የማያወላዳ አቋም ስላላቸው እርምጃቸው አንጀት አርስ ነው ።በተለይ በቻይና በሙስና ወንጀል ውስጥ መግባት በቢሊዮን የሚቆጠር ህዝቧ ላይ ቁማር እንደመጫወት ስለሚቆጠር የፍርድ ቤቶቿ ውሳኔዎች ከእድሜ ልክ እስከ ሞት ቅጣት ሊደርስ ይችላል። ከሰሞኑ እንኳን ቻይና አንድ ቱባ ባለስልጣኗ በሙስና ወንጀል ተዘፍቀው በመገኘታቸው በእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ አድርጋለች ።
እንዲህ አይነቱ ርምጃ በተመሳሳይ ሌሎችም በሙስና ወንጀል ውስጥ እንዳይገቡ አስተማሪ ይሆናል ።ሰርቶ ከማግኘት ውጭ በአቋራጭ መበልፀግ እንደማይቻልም መልእክት ያስተላልፋል ። በእንደዚህ አይነት አንጀት አርስ ውሳኔዎች ማህበረሰቡ ይደሰታል ።በመንግስት ላይ ያለው አመኔታም እንዲጨምር ያደርጋል ።ከሁሉ በላይ ደግሞ በመንግስትና በህዝብ መካከል ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲሰፈን ያስችላል ።
ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ መንግስትም በሙስና ላይ ያለውን የማያወላዳ አቋም በተግባር ማሳየት ይገባዋል።ያ ማለት በውስጡ በመንግስት አመራርነት የተሰገሰጉ ሙሰኞችን ማራገፍ ይኖርበታል ።አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም መረጃዎችን በማሰባሰብ ተገቢውን የፍርድ ሂደት በተከተለ መልኩ ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ ይጠበቅበታል ።ከመንግስት አመራሮች ባሻገር እነዚህን አመራሮች እንደ ድልድይ በመጠቀምና ሙስና በመፈፀም የራሳቸውን ጥቅም የሚያጋብሱ ግለሰቦችንም ሊታገስ አይገባም ።
በተለይ ደግሞ በአገሪቱ ግርግር በተነሳ ቁጥር ከአገሪቷና ህዝቦቿ ሃብት ላይ ለመዝረፍ የሚያቆቦቁቡ ስግብግብ ግለሰቦችና የመንግስት አመራሮች ሊቀጡና ሊቆነጠጡ ይገባል ።በጦርነቱ ወቅት ሀብትና ገንዘብ የዘረፉና አሁንም በመንግስትና በህብረተሰቡ ጉያ ተሸሽገው የሚገኙ ሰዎች ተመንጥረው ለፍርድ መቅረብ ይኖርባቸዋል ።
ፍርድ ቤቶችም አስፈላጊ መረጃዎችን በማጠናቀር ተገቢውን ብይን ማስተላለፍ ይጠበቅባቸዋል ።ይህም ለሌላውም ጊዜ ሰዎች አገር ችግር ውስጥ ስትገባ ዘርፎ ማምለጥ ከህግ ጥላ መሰወር እንደማይቻል ትምህርት እንዲወስዱ ያደርጋል ። እንዲህ አይነቱ ልምምድ ነገ ዛሬ ሳይባል ከአሁኑ ሊጀመር ይገባል ።በዚህ ልክ መሄድ ከተቻለ አገርን ወደፊት ማሻገር ይቻላል ።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ኅዳር 25/ 2015 ዓ.ም