የመንደሩ ነዋሪዎች በመንገድ ዕጦት በመሰቃየታቸው ካለምንም ትልልቅ ማሽኖች ዶማ፣ አካፋ እና መፍለጫን ብቻ ተጠቅሞ እየቆፈረ አንድ ግለሰብ ብቻውን አንድ ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር መንገድ መገንባቱን ቢቢሲ አስነብቧል።
ኬኒያዊው ሚስተር ኒኮላስ ሙቻሚ መንገዱን ለመስራት ያነሳሳው በቅርቡ የካጋንዳ መንደር ነዋሪዎች በባህላዊ መንገድ ወደ ገበያም ሆነ ወደ ሌላ አካባቢ የሚጓጓዙበት መንገድ በመዘጋቱ እና የአካባቢው አስተዳደሮችም ጉዳይ ችላ በማለታቸው ተበሳጭቶ መሆኑን ጠቁሟል።
ማህበራዊ ሚዲያን ሳይቀር ተጠቅመው ለአካባቢው አስተዳደር መንገድ እንዲሰራ ጥያቄ ቢያቀርቡም ምላሽ አለማግኘታቸው የኬኒያው ሙቻሚን እና የመንደሩን ነዋሪዎች ያበሳጨ ሲሆን፤ በተለየ ሁኔታ እርሱን ግን ችግሩን ለማቃለል በፈቃደኛነት ለብቻውን መንገድ ለመገንባት እንዳስወሰነው ተናግሯል። ምንም እንኳ የአካባቢው መስተዳድሮችም ሆኑ ነዋሪዎቹ ባያግዙትም በየቀኑ ለአስር ሰዓት በተከታታይ ለስድስት ቀናት በመቆፈር የአንድ ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር መንገድ ገንብቷል።
መንደሩ ከገበያ ማዕከላት፣ ከትምህርት ቤት እና ከሌሎችም ማህበራዊ አገልግሎቶች በመራቁ የመንደሯ ነዋሪዎች ስቃይ እና እንግልት ያሳዘነው የ45 ዓመቱ ኬኒያዊ ማልዶ ተነስቶ ከጠዋት እስከ ማታ መስራቱ ያስገረማቸው ሰዎች ‹‹ ክፍያ ሳይኖረው እንዴት ትሰራለህ?›› እያሉ በተደጋጋሚ ይጠይቁት እንደነበር ተናግሯል።
የመንደሩን ነዋሪዎች የእርሱ ጥረት ያስገረማቸው ሲሆን፤ ለሰራው ሥራም ምስጋና አቅርበዋል። በተለይ ያለምንም ክፍያ ህብረተሰቡን ለማገልገል መንገድ በመስራቱ ‹‹ጀግና›› አሰኝቶታል። ‹‹በውስጤ ብዙ ሃይል እንዳለ አውቃለሁ፤ ስለዚህ በፈቃደኝነት ሃይሌን ተጠቅሜ ህዝቡን ለማገልገል ወሰንኩ›› የሚለው ሚስተር ሙቻሚ፤ በዚህ ተግባሩ ነዋሪዎቹ መደሰታቸው እርሱንም የበለጠ ደስተኛ እንዳደረገው ለቢቢሲ ጠቁሟል።
ለገበያ ማዕከላት 4ኪሎ ሜትር ብቻ የሚቀረው መንደር በሙቻሚ ጥረት የተስተካከለ መንገድ ለማግኘት ጥቂት የሚቀረው ሲሆን፤ በጎ ፈቃደኛውም የመንገድ ሰሪ ቁፋሮውን እስከመጨረሻው ለመቀጠል ዕቅድ እንዳለው ተናግሯል። ሚስተር ሙቻሚ የአካባቢው ነዋሪዎች ከሃሳብ ውጪ በጉልበት ባያግዙትም የአካባቢው መስተዳድሮችም ለመርዳት ፈቃደኛ ባይሆኑም፤ መንደሯን ከናይሮቢ ጋር የሚያገናኝ መንገድ ለመገንባት ማቀዱን ተናግሯል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 4/2011
በምህረት ሞገስ