የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች በኳታሩ የዓለም ዋንጫ በድራማዊ ክስተቶች የታጀቡ ጨዋታዎችን ለዓለም ሕዝብ ማስኮምኮም ቀጥለዋል። የቴራንጋ አንበሶች በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ደስታና ቁዘማን ያፈራረቀ ድራማዊ ክስተት ባስተናገደው ጨዋታ በወሳኙ ፍልሚያ ኢኳዶርን 2ለ1 በመርታት 16ቱን የተቀላቀሉ የመጀመሪያዎቹ አፍሪካዊ ቡድኖች መሆን ችለዋል። ይህም ከሃያ ዓመት በፊት በዓለም ዋንጫ የሰሩትን የማይረሳ ታሪክ የሚደግሙበትን ጎዳና እንዲደግሙና ያለፈውን ዓለም ዋንጫ ቁጭት በጣፋጭ ድል መወጣት ችለዋል።
የቴራንጋ አንበሶች በዓለም ዋንጫ ሲሳተፉ የዘንድሮው ለ3ኛ ጊዜ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፉበት እኤአ የ2002 የጃፓንና ኮሪያ የዓለም ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ ተፋላሚ የሆኑበት አጋጣሚ ወርቃማ ታሪካቸው ነው። የማይረሳው የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ድንቅ ስብስብ በዚያ ዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ጨዋታው ሳይጠበቅ ቻምፒዮን የነበረችው ፈረንሳይን ጨምሮ ዴንማርክ፣ ዩራጓይና ስዊድንን በማሸነፍ ዓለምን አስደምሞ በሩብ ፍጻሜው ጨዋታ እስከ ተጨማሪ ሰዓት ተፋላሚነት ደርሶ አስደናቂው ጉዞ በቱርክ ተገቷል።
የቴራንጋ አንበሶች ለ2ኛ ጊዜ በተሳተፉበት ያለፈው የሩሲያ የዓለም ዋንጫም በፊፋ ያልተለመደ ህግ ረጅም ለመጓዝ እድለኛ አልነበሩም። በዚያ የዓለም ዋንጫ የቴራንጋ አንበሶች ከምድብ ጨዋታቸው ለማለፍ ከጃፓን ጋር ተመሳሳይ ነጥብና ግብ ይዘው እኩል በመሆናቸው ፊፋ የሚያልፈውን ቡድን የለየው ባልተለመደ የስፖርታዊ ጨዋነት ህግ ነበር። በዚህም ሴኔጋል በስድስት ቢጫ ካርዶች ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ሳትችል ቀርታለች። ጃፓን አራት ቢጫ ካርድ ብቻ የተመዘዘባት በመሆኑ በተሻለ ስፖርታዊ ጨዋነት ሴኔጋልን ጥላ ከምድቧ ለማለፍ በለስ ቀንቷታል። ይህም ሴኔጋልን በዚህ ምክንያት ከውድድር የተሰናበተች በታሪክ የመጀመሪያዋ አገር አድርጓታል።
በዚህ የቴራንጋ አንበሶች የእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ መዘንጋት የሌለበት አንድ ሰው አለ። አሰልጣኙ አሊው ሲሴ፣ ቡድኑን እኤአ ከ2015 ጀምሮ በማሰልጠን ላይ የሚገኘው የ46 ዓመቱ ሰው ሲሴ የቴራንጋ አንበሶች በዓለም ዋንጫ ዓለምን ሲያነጋግሩ የቡድኑ አምበል ነበር። የቴራንጋ አንበሶችን መምራት ከጀመረ ወዲህም 2019 እና 2021 የአፍሪካ ዋንጫ ለፍጻሜ ተፋላሚ አድርጎ ያለፈውን አፍሪካ ዋንጫ ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ለመጀመሪያ ጊዜ ስታነሳ ቁልፉ ሰው በመሆን ሕያው ታሪክ ሰርቷል።
“ዝምተኛው አንበሣ” የሚል ስያሜን የደረበው ሲሴ የቴራንጋ አንበሶች ኩራት ነው። አሊዩ ሲሴ ሁሌም አገሩ በፈለገችው ጊዜ ከፊት የሚገኝ፣ በተጨዋችነትም በአሰልጣኝነትም ሌሎች ጎልተው እንዲወጡና አገሩ ደምቃ እንድትታይ በዝምታ ውስጥ ቁልፍ ሚናን የሚወጣ በጨለማ የሚያበራ ጥቁር አልማዝ ነው።
ሲሴ በኳታሩ ዓለም ዋንጫ ምንም እንኳን የቡድኑ ኮከብ ሳዲዮ ማኔን በጉዳት አጥቶ ሁለት ጨዋታ በማሸነፍ ጥሎ ማለፉን የተቀላቀለ የመጀመሪያው የአፍሪካ ቡድንን በማሰልጠን ታሪክ ሠርቷል። የሴኔጋል ምልክት የሆነው አልዩ ሲሴ የቴራንጋ አንበሶች ብቻ ሣይሆን ለአፍሪካ አሠልጣኞችም ኩራት ሆኗል።
ሴኔጋል በጣፋጩ ድሏ ውድ ልጇንና የቀድሞ የብሔራዊ ቡድን አምበሏን የአሁኑ አምበል ኩሊባሊ ባስቆጠራት ሁለተኛ ግብ አማካኝነት ባሰበችበት ጨዋታ ታሪክም ተገጣጥሟል።
ፓፓ ዲዮፕ በ2002 የዓለም ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታ ፈረንሳይን 1-0 ስትረታ የማሸነፍያውን ግብ ያስቆጠረ ተጨዋች ነበር። ይህ ታሪካዊ ኮከብ የቴራንጋ አንበሶች ኳታር ላይ ኢኳዶርን በመርታት ታሪክ በሰሩበት ተመሳሳይ ቀን ከሁለት ዓመት በፊት ኅዳር 20/2013 ዓ.ም ለረጅም ጊዜያት ታሞ በ42 ዓመቱ ሕይወቱ አልፏል። የቴራንጋ አንበሶች ይህን ኮከባቸውን ለማስታወስ የቡድኑ አምበል ኩሊባሊ ሟቹ ፓፓ ዲዮፕ በብሔራዊ ቡድን ይለብሰው የነበረውን 19 ቁጥር የተፃፈበት የአምበልነት ባጁ ላይ አድርጎ ወደ ሜዳ ገባ። ተሳክቶለትም የማሸነፊያ ግቧን ከመረብ አሳርፎ የታሪክ ግጥምጥሞሹን አሳምሮታል።
አሰልጣኝ ሲሴ የቴራንጋ አንበሶች ወደ ጥሎ ማለፍ መግባታቸውን ተከትሎ ድሉን ለሳዲዮ ማኔ ሰጥቶታል። “ይህን ድል ለአገሩ ያልተለመደ ነገር ለሚሰራው እና በሚያሳዝን ሁኔታ እዚህ ለሌለው ሰው መስጠት እፈልጋለሁ፣ ይህም ሰው ሳዲዮ ማኔ ነው፣ ቡድናችን ለማንኛውም ተቀናቃኝ ቡድን ጥሩ ዝግጅት ያደርጋል። በጥሎ ማለፉ ከእንግሊዝ ጋር እንገናኛለን ለኛ ይህ አዲስ መድረክ ይሆንልናል፣ ወደ ጥሎ ማለፍ ደረጃ እንደምንሸጋገር እናውቃለን፣ ከትልቅ ቡድን ጋር መጫወት ከባድ ነው ነገር ግን የተለየ ዝግጅት እናደርጋለን፣ ሁሉም ቡድን ጥሩ ነው እነሱ በዓለማችን ላይ ምርጥ ቡድኖች ናቸው ስለዚህ ከየትኛውም ቡድን ጋር ለመጫወት ዝግጁ መሆን አለብን፣ አሁን የማሸነፍ ወይም የመሸነፍ ሁኔታ ነው ያለው ሁለተኛ እድል የለም ካሸነፍክ ታልፋለህ ከተሸነፍክ ወደ አገርህ ትሄዳለህ ስለዚህ ለጊዜው ትኩረታችንን በዕረፍት ላይ በማድረግ ለቀጣይ ጨዋታ ብቁ ለመሆን እንሰራለን” ሲልም ተናግሯል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ህዳር 22/2014