የአውሮፓ ቅኝ ገዥ ኢፔሪያሊስቶችን በከፍተኛ ተጋድሎ ከአህጉረ አፍሪካ ያስወጡት አፍሪካዊያን ዛሬም ላይ አይለፍላችሁ ተብለው የተረገሙ ይመስላል። አፍሪካዊያን የአውሮፓ ኢፔሪያሊስቶችን ከአህጉራቸው ያስወጡ እንጂ ሰርተው ከማደግ ይልቅ በአቋራጭ ዘርፈው መክበርን በሚሹ የአፍሪካ ባለስልጣናት፣ ደላሎች እና ባለሃብቶች ክፉኛ እየተፈተኑ ኑሯቸውም ተመሰቃቅሎ ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ሆኖባቸዋል።
አሁን ላይ አፍሪካ በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ኩነቶች ላይ እድገቶች እንዳይጎበኟት እና ምንም አይነት እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳትችል እንደ ጎን ውጋት ቀስፎ የያዛት እና አንድም እርምጃ ወደ ፊት መሄድ እንዳትችል ጋሬጣ ሆኖ ከፊቷ የቆመው ስርቆት ወይም ሌብነት ነው። ይህም ሆኖ ግን ይህንን ደንቃራ አንድም ሰው በስሙ ለመጥራት የደፈረ አልተገኘም። ይልቁንም «ሙስና » እያሉ ያሽሞነሙኑታል እንጂ።
ስርቆት ስለምን ይሽሞነሞናል ? ሌብነት ሌብነት ነው! ስለምን የመንግስት አካላት ስልጣናቸውን ተጠቅመው ሲሰርቁ ሙስና የሚል የዳቦ ስም ይሰጠዋል ? ይህ ስህተት ነው። ሌባ … ሌባ ነው ! ግለሰብ ሲሰርቅ ሌባ፤ ባለስልጣን ሲሰርቅ ሙስና የሚባል ስም ሊሰጠው አይገባም!
የህግ የበላይነት በአንድ አገር የሚረጋገጠው ባለስልጣናት እና ዜጎች በህግ ፊት እኩል ሲሆኑ ነው። ባለስልጣን ሲሰርቅ ሙስና ብሎ ማሽሞንሞን ዜጎች ሲርቁ ሌባ ማለት የህግ የበላይነትንም የዘነጋ አካሄድ ስለሆነ ሁሉንም ሌባ አልያም ሁሉንም ሙሰኛ ብሎ መጥራት ያስፈልጋል። እንደኔ ግን ሌባን … ሌባ ! ብሎ መጥራቱ ብቻ እና ብቻ አዋጭ ይመስለኛል።
ለእኔ ! ቅኝ ገዥዎች እና ሌቦች (ሙሰኞች) ሁለቱም አንድ ናቸው። ሁለቱም አገርን ዘርፈው እና አመንምነው ይገድላሉ። ሁለቱም ሁሉንም ነገር ለራሳቸውና ለራሳቸው ጥቅም ብቻ ማዋልን ይፈልጋሉ። እነሱ ካጠገቡ ሌሎች በርሃብ እና በችግር ቢሞቱም ደንታቸው አይደለም።
የሌብነት ጥሩነት ባይኖረውም የአፍሪካ ሌባ ባለስልጣናት የስርቆት አካሄድ ግን እጅጉን ግብዝነት የሚስተዋልበት በመሆኑ ዜጎችን ከማራቆት በዘለለ የአንድን አገረ መንግስት ካስማ እና ማገር የሚሰባብር እና አገርንም የሚያፈርስ ነው። ይህን ስል በዓመክንዮ እንጂ እንዲሁ በግብዝነት ስላለመሆኑ በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል። ነገር ግን ከሚኖረን ጊዜ አንጻር ሁሉንም መጥቀስ ስለማይቻል የሞቡቱ ሴሴኮን ሌብነት እና የዛየርን እጣ ፈንታ በወፍ በረር ላስመለከትቻሁ ወደድኩ።
የበፊቷ ዛየር የአሁኗ ኮንጎ የአፍሪካ ብሄርተኝነት ምልክት የሆነውን የመጀመሪያውን የኮንጎ ጠቅላይ ሚኒስትር ፓትሪስ ሉሙምባን በሴራ አስገድሎ ወደስልጣን የመጣው ሞቡቱ ሴሴኮ አገሩን ዘርፎ በዓለማችን ቱጃሮች ተርታ መቀመጥ የቻለ አፍሪካዊ መሪ ነው። ቅንጡ መኪና፣ መነጸር፣ ሽቶ፣ አልባሳትን ወዘተ መግዛት መታወቂያው ነበር።
በወቅቱ ዛየራውያንም ቢሆኑ የአገራቸውን አንጡራ ሃብት የሰረቀውን ሞቡቱ ሴሴኮን ከማውገዝ ይልቅ ሞቡቱ ሰርቆ ስለሚገዛቸው የቅንጦት እቃዎች ማውራት ይቀናቸው ነበር። በዛየር የነበረው የባለስልጣናት ስርቆት ለውስጥ እና ለውጭ ደላሎች በዛየር ኢኮኖሚ ላይ እንደፈለጉ መወሰን እንዲችሉ በሩን ከፈተላቸው።
በዛየር የኢኮኖሚ ላይ እንደፈለጉ መወሰን እንዲችሉ በር የተከፈተላቸው ሌቦች በስርቆት የሚያገኙትን ገንዘብ ለማግበስበስ በነበራቸው ውድድር የዛየርን አንጡራ ሃብት ተስማምተው መዝረፍ ተሳናቸው። በአልማዝ ማዕድን የምትታወቀውን ዛየርንም ለበርካታ ትናንሽ ኮንጎዎች ከፋፈሏት።
ይህም አልበቃ ብሏቸው ! እነኝህ ክፍልፋይ ኮንጎዎች እስከዛሬ ድረስ በማያባራ እና መውጫ በሌለው የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ገብተው እንዲጨራረሱ ተፈርዶባቸዋል። በርሃብ እና በበሽታ የሚጎዳው የኮንጎ ህዝብ በጦርነት ከሚረግፈው በላይ ሆኗል። የዚህ ሁሉ መነሻ ምክንያት የሆነው ህዝብ የሰጣቸውን አደራ በዘነጉ የባለስልጣናት ስርቆርት (ሙስና ) ነው።
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ደግሞ ሌቦች መዝረፋቸው ብቻ አይደለም አገርን እየጎዳ ያለው። ይልቁንም ስለመስረቃቸው በመረጃ እና በማስረጃ ሲደረስባቸው ስርቆታቸውን ለመሸፋፈን ወይም ለማደባበስ ጎሳን እና ሃይማኖትን እንደ ሽፋን መጠቀማቸው ነው። ይህ አካሄድ በብሄር ብሄረሰቦች እና በተለያዩ ሃይማኖትች መካከል ቅራኔ ከመፍጠር ባለፈ እስከደም መፋሰስ እንዳደረሰ በተደጋጋሚ አይተናል። ይህ አካሄድ በአፋጣኝ መላ ሊበጅለት የሚገባ እጅጉን አደገኛ እውነታ ነው።
ሌላው በኢትዮጵያ ከሚሰራው ሙስና ጋር ተያይዞ ማንሳት የምፈልገው ጉዳይ ሌብነት/ሙስና በሚሰሩ ሰዎች ላይ ከሚወሰደው እርምጃ ጋር የተያያዘ ነው። እደንሚታወቀው ሙስና የአገርን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ይገድላል። ነገር ግን በአገራችን ሙስና በሰሩ ሰዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ አይደለም አገርን የገደለ ሰው ላይ የሚወሰድ እርምጃ ሊመስል ይቅርና አንድ ሰው በገደለ ሰው ላይ የሚወሰድ እርምጃ እንኳን አይመስልም።
ስርቆት አገርን እንደሚገድል ከታወቀና አንድ ባለስልጣን ወይም ደላላ ያለውን ኃይል ተጠቅሞ አገሩን የሚሰርቅ ከሆነ በመጀመሪያ ደረጃ ያ ባለስልጣን ወይም ደላላ አገር እየገደለ መሆኑን ሊታመንበት ይገባል። አገር ሲሞት ደግሞ በውስጧ ያለው ህዝብ አብሮ ይሞታል። ስለሆነም አገርን እና ህዝቡን የሰረቀ ሰው አገርን እንደገደለ ተቆጥሮ የሚጣልበትም ቅጣት በዚያው ልክ መሆን አለበት።
ለምሳሌ የ20 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ቅርጥፍ አድርጎ የበላን ሌባ ሙስና በሚባል መሸፋፈኛ ስም በመስጠት ሁለት ዓመት ብቻ ታስሮ የሚፈታ ከሆነ ሌላ ባለስልጣንም 20 ሚሊዮን ብር በ20 ዓመታት ሰርቶ እንደማያገኝ ስለማያውቅ ሁለት ዓመት ታስሮ 20 ሚሊዮን ብር ማግኘትን ይመርጣል።
ከዚህ ይልቅ በሌቦቹ ላይ የሚጣለው ቅጣት የሌቦቹን ሰብአዊ ክብር/ስብእና ጭምር የሚነካ/በማህበረሰቡ ውስጥ አንገት የሚያስደፋ ደረጃ ላይ የሚደርስ ከሆነ ሌቦቹ እጃቸውን ይሰበስባሉ። አገርን ማቁሰል፣ ማቆርቆዝ እና አመንምኖ ከመግደል ይታቀባሉ።
ይህንን በቁርጠኝነት ማድረግ ካልተቻለ ግን በአገራችን የቱንም ያህል ስርቆትን ወይም ሙስናን ለማስቆም ኮሚቴዎች ቢቋቋሙ ሌቦችን እንዳይሰርቁ ሊያገድ አይችልም። ከስርቆት (ሙስና) ጋር ተያይዞ እንደ አገር ያለን ህግ ጠንከር ብሎ ሊሻሻልም ይገባል። ከእነ ቻይና እና መሰል አገራት ብዙ ተሞክሮዎችን ቢወሰድም መልካም ነው።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ኅዳር 21/ 2015 ዓ.ም