የዛሬዋ የዓለም የዴሞክራሲ ተምሳሌት የምትባለው አሜሪካ እ.ኤ.አ በ1850ዎቹ መባቻ ልጆቿ ለሁለት ጎራ ተከፍለው እርስ በእርስ የለየለት ጦርነት ውስጥ ገብተው ነበር። ያኔ በደቡባዊ ክፍል ያሉ ዜጎቿ ከግብርና መር ኢንዱስትሪ አልተላቀቁም ነበር። ስለዚህ ማሳቸውን አገላብጦ የሚያርስላቸው ከፍተኛ የሰው ኃይል ያስፈልጋቸው ስለነበር የባሪያ ንግድ መቆም የለበትም የሚል ጽንፍ ይዘው ቆሙ።
በአንጻሩ የሰሜኑ ክፍል ዜጎቿ ደግሞ በወቅቱ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ተሸጋግረው ስለነበር የሰው ኃይል አያስፈልግም የባሪያ ንግድ መቆም አለበት በሚል ጽንፍ ቆሙ።
ከዚህ ባሻገር ደቡባዊ ክፍሉ የሚያስፈልገን የኮንፌዴሬሽን ግዛት (confederation state) ነው። በአንጻሩ ደግሞ የሰሜኑ ክፍል ደግሞ አይ ኮንፌዴሬሽን አስተዳደር ሳይሆን የተባበሩት ግዛት (united states) ነው የሚያስፈልገን የሚል አቋም ያዙ። በነዚህ ሁለት መሰረታዊ ልዩነቶች አሜሪካውያን በሁለት ጎራ ተከፍለው ለሦስት ዓመታት የዘለቀ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ገብተው የአንድ አገር ልጆች ተላለቁ። ሆኖም ከዚህ በላይ በጦርነት መቀጠል ሁለቱንም ወገን የሚያጠፋና የሚያደቅ እንጂ ማንንም አሸናፊ እንደማያደርግ ዘግይቶም ቢሆን የገባቸው አሜሪካውያኖች ቁጭ ብለው ለመነጋገር ወሰኑ።
ለዚህም ቂምና ጥላቻን አርቀው ቁጭ ብለው በመነጋገር ሁሉም ዜጋ እኩል መብቱ ተከብሮ የሚኖርባት፣ ሰርቶ የሚያገኝባት፣ ዜጎች በሰላም ወጥተው የሚገቡበት ሕግና ሥርዓት ዘርግተው 54 ግዛት ያላት አንድ አገረ አሜሪካን መሰረቱ። በተለይ ለአሜሪካኖች የምንግዜም ባለውለታ በሆነው በአብርሃም ሊንከን ሀሳብ አመንጪነት አሜሪካኖች ከእርስ በእርስ እልቂት ወጥተው እጅ ለእጅ ተያይዘው ፊታቸውን ወደልማት አዞሩ። በዚህም ዛሬ ላይ አሜሪካ የዓለም የዴሞክራሲ፣ የሰላም፣ የኢኮኖሚ፣ የቴክኖሎጂ፣…. ወዘተ ቁንጮ ለመሆን በቅታለች።
በዚህ የታሪክ መንደርደሪያ ሃሳብ በዚህች አጭር ጽሁፌ ለማጠንጠን የወደድኩት ጉዳይ እኛ ኢትዮጵያዊያን በየዘመናቱ በከፍታም በዝቅታም የተጓዝንባቸው ጊዜያቶች መኖራቸውን በማሰብ ነው። ሆኖም ግን ከነዚህ ታሪካችን ተነስተን ክፉውን ትተን
እና ጥሩውን በዓርአያነቱ ወስደን አስቀጥለን ወደፊት ስንሄድበት አይስተዋልም። በአንጻሩ ደግሞ ከአደፈ ታሪካችን ተምረን ነገን የተሻለ ለማድረግ ስንታትር፣ ስንተባበር ….. አይስተዋልም።
ኢትዮጵያ በንጉሣዊ ሥርዓት እየተዳደረች በነበረበት ወቅት ዜጎቿ በመሳፍንት፣ በጭቃሹም፣ በምስለኔ ወ.ዘ.ተ እየተዳደሩ በስልጣን ሽኩቻ የተለያዩ የእርስ በርስ ግጭቶችን ለማሳለፍ ተገደዋል፤ ለዚህም ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። አንዱ አንዱን ገድሎ ለመንገስ በሚደረገው ትንቅንቅ መካከል አያሌ ንጹኋን ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
በኋላም ንጉሳዊ ሥርዓት ተገርስሶ ወታደራዊው መንግሥት ከተመሠረተ ወዲህም በነጭ እና ቀይ ሽብር አያሌ ዜጎች በሴራ ተገልለዋል። በ17 ዓመቱ ጦርነትም የአንድ እናት ልጆች በሁለት ጎራ ተከፍለው እርስ በእርስ ተጋድለዋል። የአገር ሀብት ንብረት ወድሞል።
ከዚህ ሁሉ ያደፈ ታሪካችን መማር ሲገባን ያለመታደል ሆኖ ሳንማር በመቅረታችን ያለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ በነጋ በጠባ ስንሰማቸው የነበሩ ዜናዎች የዜጎች መፈናቀልና ሞት ሲያረዱን ቆይተዋል። እንዲሁም በርካታ የመሠረተ ልማት አውታሮች፤ የህዝብ መገልገያ ተቋማትን ጨምሮ ግለሰቦች ጥረው ግረው ያፈሯቸው ንብረቶች ወድመዋል። ጦርነቱ በአንድም በሌላ መንገድ በሁሉም ዜጎች ሕይወት ላይ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሥነልቡናዊ፣ አካላዊና ሌሎችም በርካታ ጠባሳዎችን ጥሏል።
በጥቅሉ የሃሳብ ልዩነትን በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ መፍታት ተስኖን በየዘመናቱ ውሃ ቀጠነ በሚል ሰበብ ጠመንጃ በማንሳት ለእርስ በእርስ ግጭቶች ተዳርገናል። እኛ እርስ በእርስ በጠመንጃ እየተጫረስን ከቆምንበት ፈቀቅ ሳንል የዛሬ 40 እና 50 ዓመት ለእርዳታ እጃችን የዘረጋንላቸው አገሮች ዛሬ በኢኮኖሚ፣ በቴክኖሎጂ፣ በሳይንስ፣ በሰላም ግንባታ … ወዘተ የት እንደደረሱ ሲታይ የሰማይና የምድር ያህል እርቀት ነው ያለን።
እኛ ኢትዮጵያውያን ከትናንት አዳፋ ታሪካችን ተምረን ነገን በጽኑ መሰረት ልናቆም ይገባል። ለዚህ ደግሞ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል። ከላይ የአሜሪካን ታሪክ ቀንጨብ አድርገን እንዳየነው መንግስትም ሁሉም ዜጋ እኩል መብቱ ተከብሮ የሚኖርበት፣ ሰርቶ የሚያገኝበት፣ ዜጎች በሰላም ወጥተው የሚገቡበት ሕግና ሥርዓት በመዘርጋት የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል።
በአንጻሩ ህብረተሰቡ ደግሞ ልዩነትን ወደ ጎን በማለት እጅ ለጅ ተያይዞ ለልማትና ለሰላም ቆርጦ መነሳት አለበት። ሕግና ስርዓትን በማክበር ለሕግ መከበር የበኩሉን ሚና መጫወት አለበት። እንዲሁም የጦርነት ነጋዴዎችን ሊያወግዝና ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ሊያሳይ ይገባል።
“የሺ ፍልጥ ማሰሪያው ልጥ” እንደሚባለው የጦርነት መቋጫው በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ በሰላማዊ ድርድር መፍታት ነው። ስለዚህ የደም ዋጋ ተከፍሎ አሁን ላይ በነፈሰው የሰላም አየር ልክ አሜሪካኖች በ1850ዎቹ መባቻ የገጠማቸውን ችግር ቁጭ ብለው ተነጋግረው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የማያዳግም መፍትሄ ሰጥተው ችግራቸውን እንደፈቱ ሁሉ እኛ ኢትዮጵያውያንም የልብ ድርድር እና ምክክር በማድረግ አገራችን በጽኑ አለት የምናቆምበት ጊዜው አሁን ነው። ለዚህ ደግሞ ከጦርነትና ከጦርነት አሳዛኝ ወሬ ያወጣን የሰላም ሻማ እንዳይጠፋ ሁሉም ሕብረተሰብ የበኩሉን መወጣት ይጠበቅበታል።
የነፈሰው የሰላም አየርም ታይቶ ሽው ብሎ እንዳይጠፋ ውይይቱ በላይኛው የስልጣን እርከን ብቻ ሳይወሰን እስከ ታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ድረስ ወርዶ መግባባትና መተማመን ሊፈጠር ይገባል። ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ህብረተሰቡ ሊወያይበት ሊመክርበትም ይገባል።
በሁለቱ ጎራ ያሉ ተደራዳሪዎች ይህንን ምቹ ሁኔታ ሊፈጥሩ ይገባል። ህብረተሰቡም በተፈጠረው የሰላም ጭላንጭል ልባዊ ውይይት በማድረግ የትናንት ቂምና ቁርሾን በተግባር ይቅር ብሎ የተሻለች አገር ለልጁ ሊያስረክብ ይገባል። ምክንያቱም ውረድ እንውረድ መባባሉ ለማንም እንደማይጠቅም ከኢትዮጵያውያን በላይ በተግባር ያየ ሌላ እንደማይኖር እርግጠኛ ነኝ።
በጦርነቱ እንደ አገር ሁላችንም ደቀናል፤ ተዋርደናል፣ ተጎሳቁለናል፣ ደምተናል፣ ተርበናል፣ ታርዘናል …ወዘተ። ስለሆነም የተጀመረው የሰላም መንገድ የሰመረና ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም ቂምና ጥላቻን አርቆ የበኩሉን ሚና በመጫወት ለራሳችንም ሆነ ለመጭው ትውልድ የተሻለች አገር እንገንባ። አበቃሁ ቸር እንሰንብት!
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ኅዳር 20/ 2015 ዓ.ም