ተስፋ ማለት…
ከዓመታት በፊት ያነበብኩትን አንድ ጥቅስ በሚገባ ቃል በቃል አስታውሰዋለሁ። እንዲህ ነበር የሚለው፤ “የሰው ልጅ ያለ ምግብ አርባ ቀናት፣ ያለ ውሃ ሦስት ቀናት፣ ያለ አየር ስምንት ደቂቃ መቆየት ይችላል። ያለ ተስፋ ግን አንድም ሰከንድ መኖር ከቶም አይችልም። ” የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ ትኩረት በጥቅሱ ውስጥ ሁነኛ አጽንኦት ስለተሰጠው መሠረታዊ የሰው ልጆች ሁሉ የጋራ ጉዳይ በሆነው ተስፋ ላይ ይሆናል።
ያለ ምግብ፣ ያለ ውሃም ሆነ ያለ አየር የመቆያው ጉዳይ “ያንሳል ወይንም ይበዛል” አሰኝቶ ሊያከራክር ይችል ይሆናል። ለተስፋ የተሰጠውን ማረጋገጫ በተመለከተ ግን የክርክር አታካራ ይገጥመዋል ተብሎ አይታመንም። ምክንያቱም በማናቸውም የሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተስፋ ሁነኛ መልሕቅ መሆኑ የተረጋገጠ ነውና። የማንኛውም ግለሰብ የሕይወት ድርና ማግ የተሸመነው በተስፋ ነው። ተስፋ ቆርጫለሁ የሚል ሰው እንኳን ተስፋ ለቆረጠበት ችግር መፍትሔ አለ ብሎ ተስፋ እንደሚያደርግ ልብ ሊባል ይገባል። ።
ከአራት አምስት ዐሠርት ዓመታት በፊት በኑሯቸው ተስፋ የቆረጡ የአዲስ አበባ ወጣቶች “ግፋ ቢል አዶላ፤ ጨብጥ ቢል አካፋ” የሚል የተስፋና የመጽናኛ አባባል ነበራቸው። ቢከፋ ቢከፋ አዶላ ሄጄ በወርቅ ቁፋሮ አሰማራለሁ ማለታቸው ነበር። ወርቅ በሚታፈስበት ሀገር ተቸገርኩ ማለት የሀገራዊ ዕንቆቅልሻችንን ግዝፈት በሚገባ የሚያሳይ የወቅቱ መስታወት ብቻም ሳይሆን ዛሬም ቢሆን የተወሳሰበ ሀገራዊ ጉዳያችን እንደሆነ ቀጥሏል።
ከተስፋ መገለጫ ወይንም አመለካከቶች መካከል ጥቂት ማሳያዎችን በማከል ሃሳቡን ለማፍታታት እንሞክር። አንባቢያንም የየግላቸውን መረዳት በማከል “ተስፋ” ለሚለው ጽንሰ ሃሳብ ማብራሪያ ቢያክሉበት ያለ ጥርጥር ለአንድ መዝገበ ቃላት የሚበቃ ትንታኔ መሰብሰብ ይቻላል።
ሠላሳ ቀናት በመደበኛ ሥራችን ደፋ ቀና ስንል የምንውለው በወሩ መጨረሻ ደመወዝ እንደሚከፈለን ተስፋ በማድረግ ነው። አንድ በሉልኝ። በታክሲ ወይንም በግላችን ትራንስፖርት የምንጓጓዘው ያሰብንበት ቦታ እንደምንደርስ ተስፋ በማድረግ ነው። ሁለት ልንል እንችላለን። ወንበር ስበን ለመቀመጥ ስንዘጋጅ እንኳን መሬቱ ወንበሩንም ሆነ ተቀማጩን መሸከም እንደሚችል ስለምናምን ነው። ሦስት እንበል።
ሕጻናት “ሀ ሁ…” ብለው ፊደል እንዲቆጥሩ ወደ ቄስ ትምህርት ቤት ወይንም እንደ ኑሮ ደረጃችን ከአቅማቸው በላይ የሆነ ቦርሳ አሸክመን ወደ መዋዕለ ሕጻናት የምንልካቸው ነገ በእውቀት የበቁ ሆነው ለቤተሰብ ኩራት፣ ለሀገር በረከት እንደሚሆኑ ተስፋ ሰንቀን ነው። አራተኛ ላይ ደርሰናል። ገበሬ በክረምት የእጁን ዘር የሚበትነው የታህሣሥ አዝመራን፣ የጥር ወር ደስታን ተስፋ በማድረግ ነው። እንደ አምስተኛ ምሳሌ ይቆጠር።
ላልዘልቅበት ለምን አንድ፣ ሁለት ብዬ ለመንደርደር እንደሞከርኩ ባይገባኝም ተስፋ በቁጥር ተዘርዝሮና ተዘክሮ እንደማይዘለቅ ግን በሚገባ እረዳለሁ። “ተስፋ ቆርጫለሁ” የሚል ሰው ወደ አንድ ክፉ ውሳኔ ለመሄድ እየተንደረደረ መሆኑ ለማናችንም የተሰወረ አይደለም። ይህንን መቋጫ የሌለውን ጉዳይ እዚህ ላይ ገታ አድርገን ራሳችንንና ሀገራችንን በተስፋ መስታወት ውስጥ ለመመልከት እንሞክር።
ተስፋ መስጠት፤ ዕዳ ለመግባት መወሰን፤
የሰሜኑ የሀገራችን ጦርነት ማብቂያው መቃረቡን በተመለከተ የተደረሰበትን የሁለት ወገን ስምምነት በሰማን እለት የነበረው ደስታና በሕዝቡ ውስጥ የተፈጠረውን ተስፋ በቃላት ለመግለጽ ያዳግታል። እናቶች እንደየሃይማኖታቸው በየቤተእምነታቸው ደጀ ሰላም ላይ ተንበርክከውና ተደፍተው ፈጣሪያቸውን ያመሰገኑት ምናልባትም ለመጀመሪያ ጊዜ እንባቸውን ዋጥ አድርገውና በምሥጋና ፊታቸው ፈክቶ እንደነበር የበርካታ እምዬዎችን/አደዬዎችን ምስክርነት ሳናደምጥ አልቀረንም። “ፈጣሪ በቃችሁ ብሎ እምባችንን ሊያብስ ቀኑ የደረሰ ይመስላል” በማለት አንድ አባት/አቦይ የተናገሩት የተስፋ ቃል ሁኔታውን በሚገባ ይገልጽ ይመስለኛል።
በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ በደመና ተመስሎ የተከማቸው የተስፋ መቁረጥ ብሶትና የጭንቀት ጣር ከሰላም ስምምነቱ ማግሥት ጀምሮ ጥቂትም ቢሆን የመገፈፍ አዝማሚያ ስለታየበት ሕዝባችን ትልቅ እፎይታ ያገኘ ይመስላል። ቢያንስ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ የጦርነትን ዜና ሳንሰማ ውለን ያደርንበትን “ክፉ ቀናት” በቁጭት ስናስታውስ ሰሞንኛውን የሰላም ስምምነት ተስፋ አቅልለን ልንመለከት አይገባም። ተስፋው ዕዳም ጭምር ስለሆነ። ይህ ጉዳይ ከተስፋም ሆነ ከዕዳ በላይ ሆኖ “ሃሌሉያ” ያሰኘን የወቅቱ የደስታችን ምክንያት ስለሆነ ፈራሚዎቹና አስፈራሚዎቹ የተግባራዊነቱን ጉዳይ በጥብቅ እንዲከታተሉ መልእክታችን ይድረስልን እንላለን።
“ትኩሱ ሬሳ፤ ደረቁን አስነሳ” እንዲሉ በዛሬ ማሳያነት ያለፈውን መከራችንን ማስታወሱ የሰላም ስምምነቱን የተስፋ መልሕቅ አጥብቀን ለመጨበጥ ስለሚያግዘን ከቀዳሚዎቹ “ክፉ” ቀናት መካከል በግማሽ ክፍለ ዘመን ውስጥ አድቅቀውን ያለፉትን ጥቂቶቹን የጦርነት ታሪኮች ብቻ እንደሚከተለው እናስታውሳለን።
የደርግ ሥርዓት “ከውልደት እስከ ሞቱ” ዕድሜውን ፈጅቶ ያለፈው በጦርነት ውስጥ እንደነበር ማን ሊረሳ ይችላል? “የምሥራቁና የሰሜኑ” በመባል ይታወቁ የነበሩት ጦርነቶች ትውልዳችንን እንክት፣ እምሽክ አድርገው ለመብላታቸው ምሥክሩ ዛሬም ድረስ እናቶቻችን ያልለወጡት የሀዘን ጨርቃቸውና ያልደረቀው እምባቸው ነው።
በጦርነት ነግሦ የጦርነት ነጋሪት ሲደልቅ ኖሮ “ያሸለበው?” ኢህአዴግም ቢሆን መንበረ ሥልጣኑን ባደላደለ ማግሥት የጦረኛነቱ ሱስ አቅበዝብዞት ጠብመንጃ አስወልውሎ ትውልዱን ወደ ኢትዮ ኤርትራ ጦርነት የማገደው ገና በጠዋቱ ነበር። በዚያ ጦርነት የረገፈውንና በድኑ የአሞራ ሲሳይ ሆኖ በምድረበዳ ወድቆ የቀረውን የኢትዮጵያ ወጣትና አካለ ጎዶሎ ሆኖ የተረፈውን ቤቱ ይቁጠረው ማለቱ ይቀላል። የወደመውን የሀገር ሀብትማ ያለማስላትና ያለመቁጠሩ ይበጃል።
የሀገርን ሀብትና የሺህዎችን ነፍስ ቅርጥፍ አድርጎ አኝኮ ያደቀቀውና ብዙ ወገኖችን አፈናቅሎና ተስፋ አስቆርጦ ምድሪቱን በደም አበላ ያጨቀየው የበቀደሙ የጦርነት ወላፈንም በተስፋ በተቋጠረ ስምምነት ለጊዜውም ቢሆን ጩኸት መቆሙ “ተስፋ” ብለን የምንገልጸው ብቻም ሳይሆን እፎይታ ለማለትም አስችሎናል። በሰላም ንግግሩ ማጠቃለያ ላይ የተገባው ተስፋ ሙሉ ለሙሉ እስኪተገበር ድረስ ግን ሰፊው የዓለም ማኅበረሰብም ሆነ እኛ ባለጉዳዮቹ ዜጎች ፊርማቸውን ያኖሩት ሁለቱ አካላት ወደ ተግባር እርምጃ ፈጥነው እንዲገቡና እፎይታችን ቀጣይነት እንዲኖረው አደራችንን የምናሸክማቸው እንደየእምነታችን በጸሎትና በጾም እየደገፍናቸው ጭምር መሆኑን ሊረዱት ይገባል። ተስፋችንም መክኖ ወደ ተለማመድነው የጦርነት ዜና እንዳንመለስ አደራችንን አጥብቀን እናሸክማቸዋለን።
በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የደረሰው ሰብዓዊና ቁሳዊ ክስረት አልበቃ ብሎ ዳግም ጦርነት አገርሽቶ ሀገሪቱ በባሩድ ጭስ የምትታጠን ከሆነ ግን ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ከመገመት ይልቅ “እክሕደከ ሰይጣን” በማለት ከማማተብ ባለፈ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ የሰላም ቀበኞቹን ፍጻሜ እውን እንደሚያደርግ በብዙኃን ድምጽ እናረጋግጥላቸዋለን።
እንደ ኢትዮጵያ በብዙ ዘርፈ ችግሮች ውስጥ ተዘፍቆና ተጨንቆ የኖረ ሕዝብና ሀገር አይኖርም ማለት ባይቻልም እኛን መሰል መከራን በአናቱ እንኮኮ በማለት ተሸክሞ ሲንገዳገድ ዘመናትን ያስቆጠረ ተወዳዳሪ ይፈለግ ከተባለ ግን ሊጠቀስ የሚችለው ምናልባትም በግሪኮቹ አፈታሪክ ዝነኛ የሆነው “አትላስ” ብቻ ሳይሆን አይቀርም።
አትላስ የግሪክ አማልክት ተባብረው ያለ ጥፋቱ ዓለምን ከነጉዳጉዷና መከራዋ ለዘለዓለም በትከሻው ላይ ተሸክሞ እንዲኖር የተፈረደበት የራሳቸው የአማልእክቱ ዘመድ ነው ይባላል። ይህንን አፈ ታሪክ በተመለከተ ከአሁን ቀደም በአንድ ጽሑፌ ዘርዘር አድርጌ ታሪኩን ማስታወሴ አይዘነጋም።
ሀገሬ የዘመናት መከራዋ እየተቀረፈ በአዳዲስ የተስፋ ሙላቶች ቀና ማለት የጀመረችበት ወቅት እንደሆነ ብዙዎችን ያስማማል። ይህንን እውነታ የሚክዱት ቁጥርም ቀላል ስላይደለ ከእነርሱ ጋር እንካ ሰላንትያ መግጠሙ እጅግም አስፈላጊ ስላልሆነ ጉዳዩን የክርክር አጀንዳ አናደርገውም። ተስፋን የሚገድለው አንዱ ምክንያት የማይረባ እሰጥ አገባ ውስጥ ተዘፍቆ መቆራቆስ እንደሆነ ከማናችንም የተሰወረ አይደለም።
“የአፍሪካ ዋና ከተማ” እያልን ስናንቆለጳጵሳት የኖረችው አዲስ አበባችን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ስሟና መልኳ መቀራረብ ሲጀምር እያስተዋልን ነው። ስንጓጓለት የነበረው ሀገራዊ ምኞት ወደ ሙላት ደረጃ እየተቃረበ በመሄዱ የላሸቀው ተስፋችን በመነቃቃት ላይ ነው። በአጭር ጊዜያት ተገንብተው ለሕዝብ ይፋ የሆኑት “የአደባባይ ገነቶች” ቁጥር መበራከት እንኳን ለእኛ ለባእዳንም ቢሆን የስበት ኃይል እየሆኑ ነው። ይህ ጉዳይ አንዱ የተስፋችን እውነታ ማረጋገጫ ተደርጎ ቢጠቀስ አግባብም ተገቢም እንደሆነ ሊታመን ይገባል።
ከገበሬው ማሳ ከሚታፈሰው የዘንድሮ ምርት ውስጥ ተቆንጥሮ ለመጀመሪያ ጊዜ “ወደ ውጭ ኤክስፖርት እናደርጋለን” የሚለው ዜና ስንመኘው የኖርነው ተስፋ ምን ያህል ወደ እውነት እየተቃረበ እንደሆነ ጥሩ ማሳያ ነው። አንዳንዶች “ራስ ሳይጠና ጉተና” እያሉ ቢያሽሟጥጡም ትርጉሙ ከዘባቾቹ ምፀት ከፍ ያለ ስለሆነ ተስፋ ለማስቆረጥ አቅም አይኖረውም።
የህዳሴ ግድባችን ትሩፋትም የሀገራችን ታላቅ ህልምና ተስፋ እንደምን ወደ ተግባር እንደተለወጠ ጥሩ ማሳያ ሊሆን ይችላል። በወንዛችን እንዳንጠቀም ከወደረኞቻችን የሚሰነዘረው ኡኡታና የዲፕሎማሲ ጫና፣ የጉልበት ትምክህትና ማስፈራራት ትቢያ መልበሱን በሚገባ እያስተዋልን ነው። ይህ ስኬት በዋነኛነት የሀገራችን ተስፋ በሙላት የመገለጹ አንዱ ማስረጃ ተደርጎ ሊቆጠር ይገባል።
መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ “የመንግሥት ያለህ! የፍትሕ ያለህ!” እያለ ሲጮኽ የኖረበት የሌቦችና የሙሰኞች ጉዳይም ትኩረት እንዳገኘ መንግሥታዊ ማረጋገጫ ስለተሰጠበት ሲያጣጥር የባጀው ተስፋችን ወደ መነቃቃትና ማገገም ደረጃ ላይ እየደረሰ መሆኑን ማስታወሱ ክፋት የለውም። ምንም እንኳ ጅምሩ በተግባር መፈተን ቢኖርበትም።
“ካላዘሉኝ አላምንም” እንዳለችው ሙሽሪት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተነቃቃ ያለውን መልከ ብዙ ተስፋችንን የምንጠራጠር ከሆነ ግን ለማንም ስለማይበጅ ይሆናል ብለን በአሜንታ መቀበልና የየግላችንን ጠጠር በማዋጣት “ለተስፋችን ጋን” መደገፊያ ማድረጉ ይበልጥ የተሻለ አማራጭ ይሆናል። “ጋን በጠጠር ይደገፋል” – የሚለው ብሂል “የዜግነት ግዴታን እንዴት ልንወጣ እንችላለን?” ለሚለው የቅኖች ጥያቄ መልስ ሊሆን ይችላል።
ሁሉም ዜጋ በሀገራችን ላይ እየታየ ባለው የተስፋ መነቃቃት እኩል መረዳትም ሆነ እኩል እውቀት ይኖረዋል ተብሎ አይገመትም። ይኑረው ብሎ አታካራ መግጠምም ተገቢ አይሆንም። ለአንዳንዱ ዜጋ የሚታየው ድቅድቅ የተስፋ መቁረጥ ጨለማ ሊሆን ይችላል። አንዳንዱም ነፍስያው በተቃውሞ ስለተገራ በጎው ሀገራዊ ገጽታ እየታየውም ቢሆን ሽምጥጥ አድርጎ በመካድ ምንም እንዳልተሰራና እንዳልተፈጠረ ወገቡን ይዞ ሊከራከር ይችላል። መብታቸው ነው። ቶማሳዊው ጥርጣሬያቸው ውሎ አድሮ ሊገፈፍላቸው ስለሚችል በትእግሥት መመልከቱ ብስለት ብቻም ሳይሆን በጥበብ የመባረክ ምልክትም ጭምር ነው።
አንዳንዱ ከዛሬ ይልቅ የነገ ጀንበር ብሩህና ደማቅ እንደምትሆን ስለሚያምን ተስፋው የደደረ ነው። “የችግሮቻችን ጨለማ ሲበረታ የተስፋችን ክዋክብት ደምቀው ይታያሉ” የሚል የሕይወት ፍልስፍና ስላለው ነገን የሚጠብቀው በጉጉት ነው። “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” እንዳለችው የቤት እመቤት፤ “የጥያቀያችን ዕንቆቅልሽ ሁሉ ዛሬውኑ ካልተፈጸመ እንጦሮጦስ ይውረድ!” ባይ ድምጾች በብዛት መሰማታቸው በእና ዘንድ የተለመደ ነው። ይህን መሰሉ አመለካከትም መብት ስለሆነ “ሳያዩ የሚያምኑ ብፀዓን ናቸው” በሚል ስብከት መገዳደሩ አግባብ ላይሆን ይችላል።
በዚያም ተባለ በዚህ ኢትዮጵያ እየተራመደች ያለችው ወደ ፊት እንጂ በኋልዮሽ የእርምጃ ጉዞ አይደለም። እርግጥ ነው ሀገራዊ ችግሮቻችን ብዙ ተብለው ብቻ በወል ቋንቋ የሚገለጹ ሳይሆን በሽበሽ መሆናቸው የታወቀ ነው። የዚያንው ያህል ደግሞ ስንመኛቸው የኖረነው ተስፋዎቻችን ወደ እውነታ እየተቃረቡና የኢትዮጵያን ከፍታ እያፋጠኑ ስለሆነ እንደ ዜጎች ማመስገንና መመሰጋገን፤ ለፈጣሪም ገላታ ልናደርስ ይገባል። ሰላም ይሁን።
(በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ኅዳር 17/ 2015 ዓ.ም