ሆርስት ሲበርት በአለም አቀፍ ደረጃ ስመጥር የኢኮኖሚ ምሁር ነው።ስለ ኢኮኖሚ ሲነሳ‹‹ኮብራ ኢፌክት፣Cobra effect››በሚለው እሳቤው ይበልጡን ይታወቃል።በጀርመናዊ ሰው እሳቤ‹‹ኮብራ ኢፌክት››ለአንድ ችግር በምንሰጠው መፍትሄና መፍትሄው ላስከተለው ችግር የምንሰነዝረው ምላሽ የከፋ ችግር ሲፈጥር እንደማለት ነው።
‹‹የኮብራ ኢፌክት›› እሳቤ ምሳሌ ሆኖ በተለያዩ ክስተቶች ላይ ይጠቀሳል።እንግሊዛውያን ህንድን በቅኝ ግዛት ያስተዳድሩ በነበረበት ጊዜ የተከሰተው ታሪክ ደግሞ በግንባር ቀደምትነት ይታወሳል።ወቅቱ በህንድ ሀገር በደልሂ ከተማ የመርዘኛ ኮብራ እባቦች መበራከት አሳሳቢ ደረጃ ይደርሳል።እንግሊዞችም የእባቦቹን ቁጥር ለመቀነስ እባቡን ገድሎ ይዞ ለሚመጣ ማንኛውም ግለሰብ ከመንግስት ሽልማት እንደሚበረከትለት አዋጅ አስነገሩ።ይህን ተከትሎ የእባቦቹን ቁጥር ለጥቂት ጊዜ በእጅጉ ቀነሰ።
ከጊዜ በኋላ ግን ህንዳውያኑ ሽልማት ለማገኘት ሲሉ በየጓሮቸው እባብ ያረቡ ጀመር።ይህን የተረዳው የእንግሊዝ መንግስትም አዋጁን ሽሮ ሽልማት መስጠት አቆመ።በዚህ የተናደዱት ህንዳውያንም እያረቧቸው የነበሩትን እባቦች ለቀቋቸው።የመርዘኛ ኮብራ እባቦች ቁጥርም ከፊቱ የባሰ ሆነ።
ይሕ ታሪክ አመታትን ያስቆጥር እንጂ ዛሬም በአለም አቀፍ ደረጃ አገራት የተለያዩ ችግሮች ለመሻገር የፖሊስ እርምጃዎች ሲወሰዱ ውሳኔው ያስከተለው ተፅዕኖ፣ተፅዕኖውን ለመቀነስ የተወሰደው ማስተካከያ የባሰ ተፅዕኖ ሲፈጥር እንደምሳሌነት ይጠቀሳል።
ኮብራ ኢፌክት በኢትዮጵያም ላለፉት በርካታ አመታት በተለያዩ መንግስታት የፖሊሲና ሌሎች ማሻሻያ ውሳኔዎች ላይ ተደጋግሞ ታይታል።በዚህም እንደ አገር ውድ ዋጋ ተከፍሏል።የጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ አህመድ አስተዳደር ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህም ችግሮች ለመፍታት የተለያዩ የፖሊሲ ለውጦችና ማሻሻያዎችን እያደረገ ይገኛል። የፖሊሲ ማሻሻያ ከተደረገባቸው መካካል የፋይንስ ዘርፍ ተጠቃሽ ነው።
እንደሚታወሰው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሳለፍነው አመት የካቲት ወር አጋማሽ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሲሠጡ ካነሳቸው አበይት ጉዳዮች መካከል የባንክ ኢንዱስትሪው አንዱ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ‹‹የኢትዮጵያ ባንኮች ላለፉት 20 ዓመታት ብቻቸውን የሚሰሩበትን እድል አግኝተው ቆይተዋል፣የውጪ ባንክ አለማሳገባት እስካሁን ላለው ሁኔታ ጠቅሟል፣አሁን ግን ይህንን ማስቀጠል አይቻልም፤ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪና ሀብት ስለሚያስፈልግ የውጭ ባንኮች መምጣታቸው አይቀርም›› ብለዋል። ባንኮች በቴክኖሎጂ እና በዘመናዊ አሰራር ራሳቸውን በማደራጀት ከፍ ላለ ውድድር ራሳቸውን ማዘጋጀት እንዳላበቻውም አፅእኖት ሰጥተው አስገንዝበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያስገነባው ህንጻ በተመረቀበት ወቅትም ካስተላለፏቸው መልዕክቶች አንዱ በቀጣይ የውጭ ባንኮች ስለሚገቡ የሀገር ውስጥ ባንኮች ከወዲሁ እራሳቸውን እንዲያዘጋጁ የሚመክር ነበር።ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ያህል የውጭ ባንኮችን ገድቦ የቆየው ይሕ አሰራር በአሁን ወቅት በለውጥ ሂደት ላይ ይገኛል። በእኔ እምነትም ውሳኔ እጅጉን ወሳኝ ነው። ምክንያቱ ኢትዮጵያ በየትኛውም መስፈርት ከአለም አቀፉ የፋይናንስ ስርአት ውጪ ልትራመድ አይገባም።አለም በደረሰበት የፋይንንስ ደረጃ እድገት ላይ መድረስ ይኖርባታል።የኢትዮጵያ ህዝብም ማግኘት ያለበትን የተቀላጠፈ፣ የተሳለጠና የተሟላ አገልግሎት ማግኘት አለበት። በአሁን ወቅት የኢትዮጵያ ባንኮች በአገር ውስጥ ባላቸው ተሳትፎ ውጤታማና አትራፊ ናቸው። ሀብታቸው ከአመት አመት እያደረገ መጥቷል።የባለድርሻዎች የሀብት መጠንም እንዲሁ ጭማሪ እያሳየ ይገኛል።የባንኮች የቅርጫፍ መጠንም ከፍ እያለ መጥተዋል።
ይሑንና አለም ከደረሰበት የፋይንናስ ኢንዱስትሪ አንፃር ረጅም እድሜ ያስቆጠሩትን ጨምሮ ቁመናቸው ሲፈተሸ በቴክኖሎጂ፣በተደራሽነትም ሆነ በካፒታል አቅም ጀማሪ ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው።አንዳንዶቹ ባንኮች ደግሞ እንኳን ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪ ሊሆኑ ቀርቶ የሀገር ውስጥ ደንበኞችንም የማርካት አቅም እንደሌላቸው በርካቶች ይስማሙበታል።ይሕ ማለት ግን የአገር ውስጥ ባንኮቹ ራሳቸውን አልቻሉምና ‹‹አትምጡባቸው››ማለት ብዙ ርቀትን አያስኬድም።
የውጭ አገራቱ ባንኮች መግባትም የተለያዩ አገር ኢንቨስተሮች በአንድ አገር ኢንቨስት ለማድረግ ሲፈልጉ ከሚጠይቋቸው ጥያቄዎች አንዱና ዋነኛው የባንክ ዘርፉ ሁለናተናዊ አቅም ነው።ኢንዱስትሪው ለውጭ ተዋናዮች ክፍት መሆኑም በተለይም በሀገሪቱ የሚከናወኑ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በብድርና በልመና ከመስራት ተላቀው የሚፈልጉትን ብድር የሚያገኙበትን አማራጭ የመፍጠር አቅሙ ከፍተኛ ነው።
በአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ብቃትን ለመጨመር ያግዛል።ከውድድር በተጨማሪ ቴክኖሎጂ፣እውቀትና አዳዲስ አሰራሮችም ያስተዋውቃል።የአገር ውስጥ ተቋማት በሥጋት ሳቢያ ገሸሽ ያደረጓቸውን ዘርፎች በመድፈር ጭምር አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉበት አግባብ ሊፈጥርም ይችላል።አንዳንዶች የቢዝነስ እውቀት፣ አቅምና ችሎታ ኖሯቸው ማስያዣ ስለሌላቸው ብቻ ብድር ማግኘት የማይችሉበትን አሰራር የማስቀረት አቅም ይኖረዋል።
ይሕ ማለት ግን ስጋቶች አይኖሩም ማለት አይደለም።የውጭ ባንኮቹ የፋይናንስ ኢንዱትሪውን መቀላቀል በቅርብ ለተቋቋሙ አዳዲስ ባንኮች አይደለም ለነባሮቹ ጭምር ከባድ ውድድርን ይዞ እንደሚመጣም እርግጥ ነው።በተለይ እነዚህ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ የማቅረብ አቅማቸው ከፍተኛ ስለሆነ ብዙ የውጭ ምንዛሪ ይዘው መጥተው ትልልቅ እና ዋነኛ ደንበኞችን ከአገር ውስጥ ባንኮች ሊነጥቁ የሚችሉበት እድልም ሰፊ ነው።ይህ ከሆነ ደግሞ የታሰበው ቀርቶ ያልታሰበው መምጣቱ እና በመግቢያ ላይ እንደጠቀሰውን አይነት ‹‹ኮብራ ኢፌክት›› መከሰቱ አይቀሬ ይሆናል።
ይሑንና ከተሰራበት ኮብራ ኢፌክት እንዳይከሰት ማድረግም በጣሙን ቀላል ነው።ስራው ግን ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ አይነት ፈፅሞ መሆን የለበትም።ከወዲሁ ከፍተኛ ዝግጅት ማድረግና አስፈላጊውን የቤት ስራ ሰርቶ መጠበቅ የግድ ይላል። በተለይ ባንኮቹ ተወዳዳሪ በሌለበት ይህን ያክል ትርፍ አግኝተናል እያሉ መኮፈስ ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ እርምጃ ከወዲሁ ደንበኞቻቸውን ማስቀጠል የሚችሉባቸውን አሰራሮች ከመዘርጋት ጀምሮ ለሁሉ አቀፍ ተወዳዳሪነት ራሳቸውን ዝግጁ ማድረግ ግድ ይላቸዋል።
ከሁሉ በላይ የሀገር ውስጥ ባንኮች በሃይማኖት፣ፖለቲካ በዘር ሳይሆን ዓለም አቀፍ ገበያው ላይ አቅም የሚፈጥሩበትና ከሀገር ውስጥ መውጣት የሚችሉበት አደረጃጀት ይዘው ስለመምጣት ሊጨነቁ ይገባል።በተለይ ግዙፍ አቅም ለመገንባት ነባሮችም ሆነ አዳዲስ ባንኮች ጥምረትን እንደ አንድና ዋነኛ አማራጭ ቢመለከቱት አትራፊ እንጂ ተጎጂ እንደማይሆኑ ማሰብም ይኖርባቸዋል። በተለይ ባንኮች ተወዳዳሪ ሆነው በኢንዱስትሪው ለመዝለቅ በካፒታል ሊጎለብቱ በሰው ኃይል ረገድ ብቃት ባለው አመራርና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ሊያዘምኑ ይገባል።የአገልግሎታቸውን ተደራሽነትና ጥራት በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግም ደንበኞቻቸውን ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ አጓጊ ፓኬጆችን ተግባራዊ ማድረግና ደንበኞችን የሚያሸሹ አላስፈላጊ ድርጊቶችን ማስወገድም የግድ ይላቸዋል።
የውጭ ባንኮች ተዋናይ ሆነው ወደ ኢንዱስትሪው ሲመጡ በተለይ ብሄራዊ ባንክ የሀገሪቱን የፋይናንስ ዘርፍና የህዝብን ንብረት ለመቆጣጠርና ደህንነትን ለማስጠበቅ አሁን ካለው የበለጠ አቅም መፈጠር ይኖርበታል። ባንኮቹ የሚሰጡት አገልግሎት አንዳንዴ የተወሳሰበ ስለሚሆን መመሪያዎቹም ለዚያ በሚመጥኑ መልኩ መቀመር የግድ ይላል።ለውጭ ባንኮች በራቸውን ክፍት አድርገው ከኪሳራ ይልቅ ትርፋማ ከሆኑት ሲንጋፖር፣ ሆንግ ኮንግ፣ ቻይናን የመሳሰሉ አገራት ተሞክሮ መቀመር መዘንጋትም የለበትም።
በተለይም ባንኮቹ እንዴት ወደ መግባትና አገልግሎት መስጠት አለባቸው?አገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ ባንኮች ጋር የሚኖራቸው ትብብርስ ምን መምሰል አለበት?በተወዳዳሪነት ወይንስ በተባባሪነት?የሚለውን በጥልቀት በመቃኘት መሆን ያለበትን በአግባቡ መቀመር የግድ ይላል። የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን በምሳሌነት አነሳን እንጂ ‹‹ኮብራ ኢፌክት››በሌሎችም ዘርፎች እንዳይከሰት አስፈላጊውን ሁሉ ጥንቃቄና ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ፈፅሞ ሊዘነጋ አይገባም።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ኅዳር 17/ 2015 ዓ.ም