አዲስ አበባ፡-የአፍሪካ ሀገራት ትብብርና አጋርነት ለአሕጉሪቱ ሠላምና ዕድገት ወሳኝ ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ፡፡
የአፍሪካ አሕጉራዊ የሠላም ኮንፈረንስ “የበለፀገችና ሠላማዊ አፍሪካን እንገንባ” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ትላንት መካሄድ ጀምሯል።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት፣ የአፍሪካ ሀገራት ትብብርና አጋርነት ለአሕጉሪቱ ሠላምና ዕድገት ወሳኝ ነው፡፡
ለአፍሪካ ሠላምና ብልፅግና የአፍሪካ አሕጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ተግባራዊ መሆን ወሳኝ መሆኑን በመግለጽ፣ ግንኙነቶችን በማጎልበት የበለጠ የተቀናጀ፣ ጠንካራና የበለፀገ አሕጉር ለመፍጠር የሚደረጉ ጥረቶች መጠናከር እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
አፍሪካ ዘላቂ ሠላምን ለማረጋገጥ በንግድና በቴክኖሎጂ ላይ ያተኮሩ ጠንካራ አሠራሮችን ልትከተል ይገባል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ አፍሪካ ያላትን አቅም ተጠቅማ ወደፊት መራመድ አለባት ብለዋል።
አፍሪካ ለሚመጡ የሠላምና የብልፅግና ተግዳሮቶችና ዕድሎች እራሷን ማዘጋጀት እንዳለባት ጠቅሰው፣ የተወሳሰቡ የሠላም ግንባታ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ተቋማትን መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአሕጉሪቱ ዘላቂ ሠላምን በማረጋገጥ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ስጋትን መቅረፍ ዘላቂ መፍትሔዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ችግር በአፍሪካዊ መፍትሔ መስጠት ይገባል የሚል ጽኑ አቋም አላት ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ የፕሪቶሪያው ስምምነት የአፍሪካውያንን ችግር በአፍሪካውያን መፈታት አለበት የሚለውን አቋም በተግባር ያሳየ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ በቀጣናው ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ገንቢ ሚና እየተወጣች መሆኑን ጠቅሰው፣ በአፍሪካ ሰላምና ደኅንነትን ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታን እየፈጠረች መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሠላምና ደኅንነት እንዲረጋገጥ ምቹ ሁኔታን እየፈጠረች ያለች ሀገር ናት ሲሉ ፕሬዚዳንት ታዬ ተናግረዋል፡፡
የሠላም ኮንፈረንሱ ቀጣናዊ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር እንዲፈጠርና እንዲስፋፋ የሚያደርግ፤ መሆኑን በመግለጽ የአፍሪካ ሠላምና ልማት የሚያበረታቱ ሀሳቦችን ለማፍለቅና ሠላምና ብልፅግናን ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በጉባኤው ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ የሠላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዱዓለምን ጨምሮ ሚኒስትሮች፣ ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የሃይማኖት አባቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ኅዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም