ድልድዩ አካባቢ

ታሪኩ ኩማ ኡቴ ገና 20 ዓመቱ ነው። ትምህርቱንም መዝለቅ የቻለው እስከ 7ተኛ ክፍል ብቻ ነው። እስከ ሰባተኛ ክፍል የተማረው ታሪኩ፤ በትምህርት ባለመዝለቁ ሞያዊ ሥራዎችን መሥራት አልቻለም። በዚህ የተነሳ ገቢው አነስተኛ ነው። የሚሠራው በቀን ሠራተኝነት ጉልበቱን እየሸጠ በመሆኑ ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ ነው።

የታሪኩ ጓደኞችም እንደርሱ ተመሳሳይ ሥራ የሚሠሩ ሲሆኑ፤ እየዋሉ እያደሩ ትኩረታቸው በተገኘው አማራጭ ሁሉ ገንዘብ ማግኘት ላይ ብቻ ሆኗል። ሠርቶ ከማግኘት ይልቅ ሠርቆ ማግኘት ይሻላል ማለት ከጀመሩ ውለው አድረዋል።

ከጓደኞቹ ጋር አዲስ አበባ ከተማ ጉለሌ ክፍለ ከተማ አካባቢ ቀበሌ 02 የቤት ቁጥር አዲስ በሚል የመኖሪያ ቤት ይኖር የነበረው ታሪኩ፤ ከጓደኞቹ ጋር በመተባበር ሰዎችን በመግደልም ቢሆን መዝረፍ ተገቢ እና ትክክል እንደሆነ ከእነርሱ በላይ ሆኖ እርሱ ማሳመን ጀመረ። ዝርፊያ ለማከናወን ብዙ ማሰብ እና ጊዜ መፍጀት እንደማያስፈልግ ተነጋገሩ።

ጓደኛሞቹ ሰውን መዝረፍም ሆነ መግደል እስከ መጨረሻው የሕይወት ጉዟቸውን እንደሚያበላሽባቸው አልተረዱም። በደፈናው ‹‹ ከዚህ በኋላ ገድለንም ቢሆን፤ እንዘርፋለን። በአቋራጭ ሃብታም እንሆናለን። ይህ ሁላ ሕዝብ ያለፈለት ሰርቶ ሳይሆን ዘርፎ ነው። እኛም ዘርፈን ከሃብታም ሰዎች ተርታ እንሰለፋለን።›› የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰው የሚዘርፉበትን ቦታ ማጥናት ጀመሩ።

ቦታውን ብቻ ሳይሆን ዝርፊያውን እንዴት ማከናወን እንዳለባቸውም ተነጋገሩ። እነ ታሪኩ ሰዎችን የሚገድሉበት ሽጉጥም ሆነ ጩቤ አልነበራቸውም። የተማመኑት በቢላዋ እና በድንጋይ ብቻ ነበር። በመጀመሪያው ቀን በቢላዋ እንወጋለን ብለው ሶስቱም ቢላዋ ይዘው ወጡ።

ድልድዩ አካባቢ

ከጓደኞቹ በላይ ለመዝረፍ እና ወንጀል ለመፈፀም የጓጓው ታሪኩ ድርጊቱን ለመፈፀም ከሚኖርበት አካባቢ ራቅ ያለ ጨለማ ስፍራ ድልድይ አካባቢን መረጧል። በተለምዶ ፈረንሳይ ሽሮ ሜዳ መሻገሪያ ተብሎ በሚጠራው ድልድይ አካባቢ ቢላዋ ይዘው ጥቃት ማድረስ ቀላል እንደሆነና ሰዎችን ለመዝረፍ እንደሚያመች ተስማሙ። በመንገዱ ላይ የተደገሰውን ያላወቀችው አስቴር አመጫ የምትኖረው አዲስ አበባ ከተማ የካ ክፍለ ከተማ አካባቢ በተለምዶ ፈረንሳይ ሽሮ ሜዳ መሻገሪያ ተብሎ የሚጠራውን መንደር አለፍ ብሎ ነው።

እንደተለመደው የዕለት ሥራዋን አከናውና ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ተኩል አካባቢ ቤቷ ለመድረስ ፈጠን ፈጠን እያለች ስትራመድ ከድልድዩ አቅራቢያ ጨለማ አካባቢ ተደብቀው ሲጠባበቁ የነበሩ ሶስት ጎረምሶች ከበቧት። በጣም ደንግጣ ግራ ትከሻዋ ላይ ተንጠልጥሎ የነበረውን ቦርሳ ወደ ደረቷ አስጠግታ አጥብቃ ያዘችው። ወደ ኋላ ሸሽታ ለመሮጥ ብታስብም ማምለጥ እንደማትችል ገመተች።

ደረቷ እየደለቀ መንገዷን ስትቀጥል፤ የከበቧት ጎረምሶች ሊተናኮሏት እና ሊዘርፏት መሆኑን ተረድታለች። ወደ እርሷ ሲጠጉ በኃይል መጮህ ጀመረች። ቦታው ድልድይ አቅራቢያ ከቤቶች የራቀ በመሆኑ፤ ሰዎች ወዲያው ሊደርሱላት አልቻሉም። ታሪኩ ከእነ ግብራበሮቹ ስለጮኸች መተው አልፈለገም።

አስቴር ስትጮህ እነ ታሪኩ ይበልጥ የልብ ልብ ተሰማቸው። ሶስቱም ያያዟቸውን ቢለዋዎች ይዘው ተጠጉ። አልፈው ተርፈው ደጋግመው ሰነዘሩባት። አንደኛው በቀኝ በኩል አንገቷን ሲወጋ፤ ሌላኛው በቀኝ የሆዷ ጎን በታችኛው ክፍል በጥልቀት ወጋት፤ ሌላኛው ደግሞ ቀኝ ቂጧን ሲወጋ በድጋሚ ቀድሞ የወጋት እንደገና እግሮቿን እና የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቿን ወጋት።

አስቴር ላይ ሁሉም ተፈራረቁባት፤ ጩኸቷን የሰሙ የአካባቢው ሰዎች በቦታው ሲደርሱ ደጋግመው ሲወጓት የነበሩት የታሪኩ ጓደኞች ሮጠው አመለጡ። ታሪኩ ግን ከእነ ቢላዋው የአካባቢው ሰዎች እጅ ከፍንጅ ያዙት። ወንጀል መፈፀምን እንደቀልድ የተመለከተው ታሪኩ ከፖሊስ በፊት የአካባቢው ማኅበረሰብ ከቦ በቁጥጥር ስር አዋለው።

አስቴር ግን በደረቷ ተዘርራ ደሟ ይፈስ ነበር። ጨለማው ድቅድቅ በመሆኑ የሰዎች ትኩረት አስቴር ላይ ሳይሆን ወንጀል ፈፃሚውን መያዝ ላይ ብቻ ነበር። ሰዎች ጉዳቷ ከፍተኛ መሆኑን አልተረዱም። ወንጀል ፈፃሚዎቹ ደጋግመው ስለወጓትና ሰዎች የጉዳት መጠኗን ባለመረዳታቸው እንዲሁም በፍጥነት ሕክምና ቦታ ስላላደረሷት ብዙም ሳትቆይ ሕይወቷ አለፈ።

ወንጀል ፈፃሚውን ተባብረው የያዙት የአካባቢው ሰዎች ለፖሊስ ጥቆማ ሰጡ። በቦታው የተገኙት ሰዎች ቀሪ የወንጀል ፈፃሚዎች መኖራቸውን አላወቁም። ተሯሩጠው ሳይፈልጓቸው ቀሩ። ታሪኩም ሌሎች መኖራቸውን አልተናገረም። ሰዎች ሲከቡት ቢላዋውን እንደያዘ እጁን ወደ ላይ አንስቶ ተንበረከከ። ሰዎቹ ፖሊስ እስከሚደርስ ዱላ ይዘው መሬት ላይ የወደቀችውን አስቴር እና ገዳዩን ታሪኩን ሲጠብቁ ቆዩ።

የፖሊስ ምርመራ

ጥቆማ የደረሰው የፖሊስ ቡድን በፍጥነት ቦታው ላይ ተገኝቶ ድርጊቱን ፈፅሟል የተባለውን ታሪኩን በቁጥጥር ስር አዋለ። የፖሊስ የምርመራ ቡድኑ ወንጀለኛው ይዞት የነበረውን ቢላዋ፤ እንዲሁም በአካባቢው ድርጊቱ ስለመፈፀሙ የሚያመላክቱ መረጃዎችን ሰበሰበ። በጨለማ ባልታሰበ ሁኔታ የተገደለችው አስቴርም፤ አስክሬኗ ተነስቶ ለምርመራ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል የሕክምና ኮሌጅ የፎረንሲክ ሜዲስንና ቶክሲኮሎጂ ተላከ።

የፖሊስ የምርመራ ቡድኑ የተለያዩ ምርመራዎችን ሲያካሂድ ቆይቶ ድርጊቱ የተፈፀመው በታሪኩ ብቻ አለመሆኑና በቡድን መሆኑን አረጋገጠ። የድርጊቱን ፈፃሚዎች ማለትም የታሪኩን ግብረአበሮች ለማፈላለግ ቢሞክርም ለጊዜው አልተሳካም። ሌሎቹ እስኪገኙ በዋና ድርጊት ፈፃሚነት በቁጥጥር ስር የዋለው ታሪኩ ብቻ በመሆኑ፤ ዐቃቤ ሕግ ታሪኩ ላይ ክስ እንዲመሠረት ፖሊስ መረጃ እና ማስረጃውን አደራጅቶ ለዐቃቤ ሕግ አቀረበ።

የወንጀሉ ዝርዝር

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የወንጀል ዝርዝሩን ለፍርድ ቤት እንዳቀረበው፤ ሟች አስቴር አመጫ መሆኗን ተጠርጣሪ ደግሞ ታሪኩ ኩማ ኡቴ መሆኑን ገልጾ፤ ድርጊቱን ፈፃሚው ታሪኩ ዕድሜው 20 መሆኑን አስቀምጧል። የታሪኩ አድራሻ አዲስ አበባ ከተማ የካ ክፍለ ከተማ አካባቢ ቀበሌ 02 የቤት ቁጥር አዲስ የሚል ቤት ውስጥ ተከራይቶ ሲኖር እንደነበርም አመላክቷል።

ታሪኩ የሚተዳደረው በቀን ሰራተኝነት ሲሆን፤ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 32 (1)(ሀ)፣ 35 እና 539(1)(ሀ) ስር የተመለከተውን በመተላለፉ ሊከሰስ እንደሚገባ የወንጀል ዝርዝሩ ያስረዳል።

በወንጀል ዝርዝሩ ላይ በግልፅ እንደተመላከተው፤ ተከሳሹ ሰውን ለመግደል በማሰብ ለጊዜው ካልተያዙ ሁለት ግብረአበሮቹ ጋር በመሆን፤ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ ሆኖ ከባድ ወንጀል ፈፅሟል።

በሚያዚያ 18 ቀን 2015 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ 2፡30 አካባቢ አዲስ አበባ ከተማ የካ ክፍለ ከተማ አካባቢ ቀበሌ 01 በተለምዶ ፈረንሳይ ሽሮ ሜዳ መሻገሪያ ድልድይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አደገኛነቱን በሚያሳይ መልኩ ሟች አስቴር አማጫን ከግብረአበሮቹ ጋር ሕይወቷ እንዲያልፍ አድርጓል።

ሟች አስቴር አማጫ በአንድ በኩል ስለት ባለው ቢላዋ ሶስቱም እየተፈራረቁ በተደጋጋሚ ሰውነቷ ላይ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ወግተዋታል። በአስክሬን ምርመራ የተገኘው ውጤት እንደሚያሳየው፤ አንደኛ አራት በሁለት ሴንቲ ሜትር ስፋት ያለው ቁስል በቀኝ የአንገቷ ጎን የታችኛው ኋለኛው ክፍል ላይ ተገኝቷል። ሁለተኛ ሰባት ሳንቲ ሜትር በሶስት ሳንቲ ሜትር ስፋት ያለው በስለት ውጊያ ቁስል እስከ ሆድ አቃፊ ኪስ ድረስ ጥልቀት ያለው ውጊያ በቀኝ የሆድ ጎን በታችኛው ክፍል ላይ መወጋቷም በሃኪም ምርመራ ታውቋል።

ሶስተኛ አምስት በአራት ሴንቲ ሜትር ስፋት ያለው የስለት ውጊያ በቀኝ ቂጧ የላይኛው አንድ ሶስተኛ ክፍል ላይ የተወጋች ሲሆን፤ አራተኛ ሰባት በሶስት ሳንቲ ሜትር ስፋት ያለው በስለት ውጊያ ቁስል በቀኝ ቂጧ ላይ እንዲሁም በሌሎችም ሁለት ቦታዎች እግሮቿ ላይ ሃይለኛ ጉዳት በማድረሳቸው ሕይወቷ እንዲያልፍ አድርገዋል ይላል።

ጉዳት አድራሾቹ ማለትም ታሪኩ እና ግብርአበሮቹ ሟች ያሰማችውን ጩኸት ተከትሎ ለማምለጥ ቢሞክሩም፤ ታሪኩ ጥቃቱን ከናደረሰበት ቢላዋ እጅ ከፍንጅ ተይዟል። በመሆኑም ታሪኩ ከግብረአበሮቹ ጋር ሆኖ ሟች አንገቷ፣ ሆዷ እና እግሮቿ ላይ ባደረሰባት ጉዳት ሕይወቷ በማለፉ ታሪኩ ኩማ በፈፀመው ከባድ ሰው መግደል ወንጀል ተከሷል ሲል የወንጀሉ ዝርዝር ያስረዳል።

ማስረጃዎች

በከሳሽ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ እና በተከሳሽ ታሪኩ ኩማ መካከል የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ክርክር በተካሄደባቸው ጊዜያት፤ ስድስት የሰው ምስክሮች ቀርበዋል። የሰው ምስክሮቹ ያዩትን በማስረዳት ታሪኩ የወንጀል ድርጊቱን መፈፀሙን እና በዚህ ተግባሩም የአስቴር ሕይወት ማለፉን መስክረውበታል።

በተጨማሪ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል የሕክምና ኮሌጅ የፎረንሲክ ሜዲስንና ቶክሲኮሎጂ ትምህርት ክፍል በግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ.ም በተፃፈ በቁጥር 8ሀ8/4020 የተላከ የሟች የሞት ምክንያትን የሚያስረዳ የሕክምና ማስረጃም ታሪኩ ገዳይ መሆኑን ማረጋገጫ በሚሆን መልኩ ቀርቧል።

በተጨማሪ ተከሳሽ የወንጀል ድርጊቱን የፈፀመበት ቢላዋ ላይ የተደረገው ምርመራ ቢላዋው ላይ ያለው ደም የሰው ደም መሆኑን የሚያረጋግጥ ምርመራ በግንቦት 8 ቀን 2015 ዓ.ም በተፃፈ በቁጥር ፌፎ/ባ-212/5055/2015 ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ የፎረንሲክ ምርመራ ዋና ቢሮ የተፃፈ ደብዳቤ በማስረጃነት ተያይዟል።

በሌላ በኩል የሟችን የአሟሟት ሁኔታ፣ የወንጀል ስፍራ ሁኔታን እና ተከሳሹ የወንጀል ድርጊቱ የፈፀመበትን ቢላዋ የሚያሳይ ዘጠኝ ፎቶግራፎችም ድርጊቱ ስለመፈፀሙ ማረጋገጫ መሆን እንደሚችሉ ተረጋግጦ ማስረጃ ሆነው ቀርበዋል።

ውሳኔ

በከሳሽ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ እና በተከሳሽ ታሪኩ ኩማ መካከል የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የነበረው ክርክር መቋጫ አግኝቶ በጥቅምት 17 ቀን 2017 ዓ.ም ውሳኔ ተሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ ተከሳሽ ታሪኩ ኩማ በፈፀመው ከባድ ሰው የመግደል ወንጀል ድርጊት ፈፃሚውን ያርማል ሌሎችን ያስተምራል ብሎ ባመነበት በ18 ዓመት ፅኑ እስራት ይቀጣ ሲል ውሳኔ አስተላልፏል። ፍርድ ቤቱ በተጨማሪ በኤግዚቢትነት የተያዘው ቢላውም እንዲወገድ አዟል።

ምሕረት ሞገስ

 አዲስ ዘመን ህዳር 14/2017 ዓ.ም

Recommended For You