ኢትዮጵያ ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ በምታደርገው ግስጋሴ የትራንስፖርቱ ዘርፍ ምርትንና ተፈላጊ ግብዓቶችን ከቦታ ቦታ በማዘዋወር ለኢኮኖሚው ዕድገት የሚጫወተው ሚና ላቅ ያለ ነው፡፡ በተለይም ድንበር ተሻጋሪ የደረቅ ጭነት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች የወጪና ገቢ ጭነቶችን በማሳለጥ ለኢኮኖሚ እድገታችን ትልቅ አቅም መሆናቸው አሌ አይባልም፡፡
ዘርፉ እየሰጠ ያለውን ሀገራዊ ጥቅም ለማሳደግና ለማዘመን የትራንስፖርት ሚኒስቴር እና ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በተለያዩ ጊዜያት አሰራሮችን ለማሻሻል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክሯል፡፡ ያም ሆኖ አሁንም ድረስ በትራንስፖርተሮች እና ከዘርፉ ጋር የሥራ ትስስር ባላቸው መንግስታዊ ተቋማት መካከል ያለው ትብብር ክፍተት ያለበትና የተሽከርካሪዎቹን እንቅስቃሴ የሚያደናቅፍ እንደሆነ ይነሳል፡፡
በመሆኑም በትራንስፖርት ባለስልጣን አስተ ባባሪነት በድንበር ተሸጋሪ የደረቅ ጭነት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች ላይ እየታዩ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተገኙ በት ሰሞኑን በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት ተደርጓል፡፡
የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሄር በውይይቱ ተገኝተው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የትራንስፖርት አገልግሎት ለአንድ ሀገር ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ ዘርፉም የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት ነው ብለዋል፡፡ ትራንስፖርት እንደ ማጣፈጫ ጨው የማይገባበት ዘርፍ የለም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ በአግባቡ ካልተጠቀምንበት የሚያስከትለው አሉታዊ የኢኮኖሚ ተፅእኖ ሀገርን ይጎዳል ብለዋል፡፡
አምራች ምርቱን ለገበያና ለተጠቃሚ የሚያደ ርሰው ሌሎች ማህበራዊ መገልገያዎችም ለታለሙለት አላማ የሚደርሱት በትራንስፖርት ነው፡፡ ዓለማችን በገበያ ውድድር በምትመራበት በዚህ ወቅት የጭነት ትራንስፖርት የሎጂስቲክ አገልግሎት አሰጣጣችን ቀልጣፋና አዋጭ ሊሆን ይገባል፡፡ ምርታማነቱንም ለማሳደግ ችግሮችን ለይቶ መፍትሄ መስጠት እንደሚያስፈልግና ዘርፉ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ማደግ ያለውን አስተዋጽኦ የበለጠ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
በተለይም ሀገሪቱ በዋናነት ከውጭ የምታስገባቸው እንደ ማዳበሪያ ፣ስንዴ፣ ብረትና ዘይትን የመሳሰሉት ምርቶች ከወደብ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ የሚያጋጥሙትን እንቅፋቶችና መጓተቶች ለማስቀረት ትራንስፖርተሮችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተናበው መሥራት እንዳለባቸው ጠቅሰዋል፡፡
ወይዘሮ ሙሉ ዘመናዊነትን የተከተለና አሁን ያለንበትን የለውጥ ሂደት የሚመጥን በእውቀት የሚመራ የትራንስፖርት አመራር ሥርዓት ሊኖረን እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡ ዘርፉን በቴክኖሎጂ እና በእውቀት በመምራት እየታየ ያለውን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ለማስቀጠል እንቅፋት የሆኑ ነገሮችን ፈትሾ የህግ ማዕቀፍ ማውጣትና አሰራሮችን ማዘመን ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ከወደብ እቃዎችን የማንሳት እና ወደ ወደብ በፍጥነት የማድረስ አቅምን ለማሳደግ ያለአግባብ ከእስታንዳርድ በላይ መኪኖችን ያስቆመና የስራ ጊዜያቸውን ያባከነ አካል በዲሜሬጅ ህጉ መሰረት ተጠያቂ መሆን ይኖርበታል፡፡ ተሽከርካሪዎች የምልልስ ጊዜያቸውን በማሻሻል የራሳቸውንም ሆነ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እድገት ማስቀጠል እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በትራንስፖርት ባለስልጣን የትራንስፖርት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አልማዝ በየሮ በበኩላቸው፤ የውይይቱ ዋነኛ ምክንያት በሀገራችን ያለው የጭነት ትራንስፖርት ምርታማነትን ለማሳደግ ውጤታማ የሆነ ሥራ መስራት እንደሚያስፈልግና ከጭነት መነሻ እስከ መድረሻ ባለው ሂደት ውስጥ ምን ምን ችግሮች አሉ? እነዚህንስ እንዴት መቅረፍ እንችላለን? በሚሉት ጉዳዮች ላይ የጭነቱ ባለቤቶች፣ ትራንስፖርተሮችና ከጭነት አገልግሎት ጋር የተያያዘ ሥራ የሚያከናውኑ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት መደረጉ ሁሉም የራሱን ድርሻ አውቆ የማስተካከያ እርምጃዎችን እንዲወስድ ያግዛል ብለዋል፡፡
የችግሩ ባለቤት ማነው? እንዴትስ ችግሩን መቅረፍ ይቻላል? በሚል መነጋገር የሀገራችን የጭነት ትራንስፖርት ውጤታማ ሆኖ እንዲቀጥል ከማድረጉም በተጨማሪ የጭነት አገልግሎታችን ድንበር ተሻጋሪ እንደመሆኑ ከአፍሪካ ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲቀርብ የሚረዳ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ከዓመት ዓመት በዘርፉ ያሉ ችግሮች እየተሻሻሉ ቢመጡም አሁንም መቀረፍ ያልቻሉ ተግዳሮቶች መኖራቸውን በመጥቀስ እነዚህን ማረም የሁላችንም ኃላፊነት ነው ብለዋል፡፡
ድንበር ተሻጋሪ የጭነት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች ስራቸውን በተቀላጠፈ መንገድ እንዳ ይሰሩ እንቅፋት ናቸው የተባሉ ጉዳዮች በባለሙያዎች በቀረቡ ጥናታዊ ጽሁፎች ተለይተው የቀረቡ ሲሆን ተሳታፊዎቹም ሃሳብ ሰጥተውባቸዋል፡፡
በመሆኑም የስራ ሰዓትን ያለማሻሻል፣ ተሽከርካ ሪዎች በመነሻ /በወደብ / እና በመድረሻ /በመጋዘኖች / ለቀናት መቆም፣ በመጋዘን ቦታ የሰራተኞች ውስንነት፣ የመጋዘን እጥረት፣ የመንገድ ምቹ አለመ ሆን፣ የመረጃ እጥረት፣ ጭነትን በፕሮግራምና ዕቅድ ያለመምራት ፣ በኬላዎችና ቀረጥ ቦታዎች ቀልጣፋ አገልግሎት ያለመስጠት ፣ የገቢ ምርቶች ስታንዳርድ ችግር መኖር እንደምሳሌ የተጠቀሱ ሲሆን እነዚህ ችግሮች መኪኖቹ ፈጣን ምልልስ እንዳያደርጉ እንቅፋት መሆናቸው በጥናቱ ተመላክቷል፡፡
ጥናቱ እንደ ችግር ካነሳቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ እሁድን ያለመስራት ነው፡፡ በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት 40 የሚሆኑ እሁዶች እንደባከኑ የተገለጠ ሲሆን 20 ሺ 440 ተሽከርካሪዎች 24 ሠዓት ያለሥራ እንደቆሙ ተገልጧል፡፡ በተለይም በማዳበሪያ መጫኛና ማራገፊያ ቦታዎች 5 ሺህ 352 ተሽከርካሪዎች በአማካይ 3 ቀን በመቆማቸው የማንሳት አቅማቸው ተገድቧል፡፡
በአጠቃላይ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ጠቅላላ የባከነ ሠዓት 61 ሺ 9 መቶ 8 ሲሆን ይህም በአማካይ 4ሺ 299 ተሽከርካሪዎች ያለ አግባብ ለ6 ቀናት እንደቆሙ ያመላክታል ተብሏል፡፡ ወደ ገንዘብ ሲቀየርም 400 መቶ ኩንታል የመጫን አቅም ያላቸው 4 ሺ 299 ተሽከርካሪዎች በዝቅተኛ ዋጋ ከ230 ሚሊየን ብር በላይ ማግኘት የሚችሉበትን ዕድል እንዳሳጣቸው የጥናቱ ውጤት ማመላከቱ ተገልጿል፡፡
ይህም ብቻ ሳይሆን መርከቦች የጫኑትን በፍጥነት አራግፈው ወደ ሥራ እንዳይሰማሩና በወደብ ላይ በሚያደርጉት ቆይታ የዲሜሬጅ ክፍያ እንዲከፍሉ ስለሚገደዱ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንደሚጎዳ ተጠ ቅሷል።
መንግሥት በተለይም ለግብርናው ዘርፍ በሰጠው ትኩረትና ሀገራችን የምትከተለውን ግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ለማሸጋጋር በሚደረገው ጥረት እንደ ማዳበሪያ ያሉ አስፈላጊ የግብርና ግብዓቶችን በወቅቱ ያለማድረስም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት እንደሚያሳድር የጥናቱ አቅራቢ አብራርተዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ትራንስፖርተሮች ፣ባለ ጭነቶችና ከመንግስታዊ ተቋማት የመጡ ባለድርሻ አካላትም የየበኩላችውን ሃሳብ ሰንዝረ ዥዋል።ትራንስፖርተሮች በሚያሰማሯቸው ተሽከርካ ሪዎች ከመነሻ እስከ መድረሻ ድረስ ባሉ የአሰራር እንከኖች ለተለያዩ ወጪዎች እንደሚዳረጉ ገልጸዋል።
በተለይም በጉምሩክ ጣቢያዎች፣ በፍተሻ ኬላዎችና በመመዘኛ ቦታዎች ያሉ አሰራሮች ኋላ ቀር መሆናቸውን በመግለጽ መሻሻል እንደሚገባቸው ተናግረዋል። በእነዚህ ቦታዎች ላይ በተለያዩ ምክንያቶች ተሽከርካሪዎች ለረዥም ሰዓት እንዲቆሙ መደረጉ የባለሀብቱንም ሆነ የሀገርን ኢኮኖሚ እንደሚጎዳ በመግለጽ አሰራሩን ማዘመን እና የሙያተኞችንም አቅም ማጎልበት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
በተያያዘም የወጪ ገቢ ንግድ የሚካሄድበት የኢትዮ-ጅቡቲ መንገድ አመቺነት ስለሌለው በተሽከር ካሪዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ተገል ጧል። በተለይም በጅቡቲ በኩል የሚገኘው መንገድ ፍጹም ለጭነት ትራንስፖርት የማይመች በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት ከጅቡቲ መንግስት ጋር ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ መነጋገር እንደሚገባው በተሳታፊዎቹ ተጠቅሷል፡፡
በተጨማሪም መኪና በቆመ ቁጥር በየመንገዱ ተሰልፈው የኮቴ ክፈሉ የሚሉ ህገወጥ ሰዎች በሥራው ላይ እንቅፋት እየሆኑ ስለሆነ ሥርዓት እንዲይዙ ማደረግ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡ በብልሽትና በአደጋ ምክንያት መንገድ ዘግተው የሚቆሙ መኪ ኖችን በፍጥነት ለማንሳት የሚያግዝ የክሬን አገልግሎት ውሱን መሆኑም እንደችግር ተነስቷል፡፡
በአጠቃላይ መስመሩ ብዛት ያለው የጭነት ተሽከርካሪ ፍሰት የሚታይበትና ላቅ ያለ ሀገራዊ ጥቅም የሚያስገኝ እንደመሆኑ በሚሰጠው አገልግሎት ልክ ትኩረት እንዳላገኘ ተሳታፊዎቹ ጠቅሰዋል፡፡ በቀ ጣይም የተነሱትን ችግሮች ለመቅረፍ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል የእኔ ጉዳይ ነው የሚለውን ችግር ተረድቶ ማስተካከያ እንዲያደርግ ተመ ክሯል፡፡
ያም ሆኖ ድንበር ተሻጋሪ የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት በ2010 ዓ.ም ከነበረበት ዘርፈ ብዙ ችግር አንጻር ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ መሻሻል እንደታየበት የተገለጸ ሲሆን አሁን የተነሱትን ችግሮች ለመቅረፍም ሁሉም ባለድርሻ አካል በኃላፊነት መስራት እንደሚገባው ተገልጿል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2011
በኢያሱ መሰለ