“የሀገሪቱን ዕምቅ የማዕድን ሀብት መጠቀም የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት ይገባል”- ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ

አዲስ አበባ፡ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅ የማዕድን ሀብት በዘመናዊ መንገድ አልምቶ መጠቀም የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት ይገባል ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ 3ኛውን ዓለም አቀፍ የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ 2024 ትናንት በሚሊኒየም አዳራሽ መርቀው ከፍተዋል።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንደገለጹት፤ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የማዕድን ሀብት በዘመናዊ መንገድ አውጥቶ መጠቀም የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት ይገባል።

ሀገሪቱ ያሏትን የማዕድን ሀብት ለመለየት፣ ለማልማትና ለመጠቀም ዘመናዊ ሥርዓትን መከተል እና ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንደሚገባ አመልክተው፤ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶችም የእውቀት ሽግግር ለማድረግ የሚያስችላቸውን ቴክኖሎጂዎች በስፋት መጠቀም እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የማዕድን ሀብት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት እና የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ ወሳኝ እንደሆነ ገልጸው፤ የማዕድን ዘርፉን ለማልማት ከመንግሥት በተጨማሪ ባለሀብቶች እና ባለድርሻ አካላት እገዛ ሊያደርጉ እንደሚገባም ተናግረዋል።

መንግሥት የማዕድን ዘርፉን ለማሳደግ ከአምስቱ ቁልፍ የልማት ምሰሶዎች ውስጥ በማካተት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ  አውስተው፤ መሠረተ ልማትን ማስፋፋትና ማዘመን ከሚሠሩት ሥራዎች መካከል እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

ይህም አምራቾችን ከገዢዎች ለማገናኘት እና የትራንስፖርት ወጪዎችን ለመቀነስ ያግዛል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በሀገሪቱ በቅርቡ ወደ ተግባር የገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የማዕድን ዘርፉን ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

በሀገሪቱ ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች የተለያዩ ማዕድን ሀብቶችን በባህላዊ መንገድ በማውጣት ተጠቃሚ እየሆኑ መሆኑን ጠቁመው፤ ሀገሪቱ ካላት የማዕድን ሀብት አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ስኩየር ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ቦታ ካርታ እንደተሠራለት አመላክተዋል።

በአፍሪካ ሀገራት ሁሉን አቀፍ የማዕድን ካርታ አለመሠራቱ ለዘርፉ ተግዳሮት መሆኑን አስታውቀዋል።

የማዕድን ሚኒስትር ሀብታሙ ተገኝ (ኢ/ር) በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በማዕድን ዘርፉ ያሉትን ተግዳሮቶች በመፍታት ሀገሪቱን ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እያከናወነ ይገኛል።

ማዕድን አምራቾችና ላኪዎች፣ የማዕድን ተጠቃሚዎች፣ የቴክኖሎጂ አምራችና አቅራቢዎች ምርትና አገልግሎታቸውን በማስተዋወቅ የገበያ ትስስር የሚፈጥሩበት ዓለም አቀፍ ኤክስፖ በየዓመቱ እየተካሄደ መሆኑን አመላክተዋል።

ሶስተኛውን ዓለም አቀፍ የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ ሀገሪቱ ያሏትን ወርቅ፣ የድንጋይ ከሰል፣ የከበሩ ማእድናት፣ ጌጣጌጦች፣ የኢንዱስትሪ ማዕድን፣ ቴክኖሎጂዎችን እና ሌሎች በርካታ ማዕድናትን በማቅረብ የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ህዳር 15/ 2017 ዓ.ም

Recommended For You