ዜና ሀተታ
በኢትዮጵያ ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የስኳር ህመም እንዳለባቸው በዓለም አቀፉ የስኳር ፌደሬሽን የተደረገ ጥናት ያሳያል። ከጠቅላላው ሕዝብ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚሆነው ለህመሙ ተጋላጭ መሆኑን የሚያሳየው ጥናቱ፤ በኢትዮጵያ በህመሙ ከሚጠቁት ስልሳ ሰባት በመቶዎቹ ህመሙ እንዳለባቸው እንደማያውቁ ይገልፃል። ለዚህም ምክንያቱ ህመሙ ቅድሚያ ምልክት የማያሳይ በመሆኑ እንደሆነ በጥናቱ ተጠቁሟል።
የስኳር ህመም ታማሚ የሆነችው ፅጌ በቀለ ስሟ የተቀየረ) ህመሙ እንዳለባት ካወቀች ዓመት እንዳልሞላት ትገልፃለች። እንደ እሷ ገለፃ ህመሙ እንዳለባት ሳታውቅ ረጅም ጊዜ ቆይታለች። ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰውነቴ እየቀነሰ ሲሄድ ተደናግጬ የኤች አይቪ ምርመራ እስከማድረግ ደርሻለሁ የምትለው ፅጌ፤ አቅሟ ተዳክሞ መንቀሳቀስ እያቃታት ሲመጣ ወደ ሆስፒታል እንዳቀናች ታስታውሳለች።
ምርመራ ያደረጉላት ሀኪሞችም ስኳሯ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ገልፀው፤ ሆስፒታል ተኝታ እንድትታከም ማድረጋቸውን ትገልፃለች። ከዚህ ጊዜ አንስቶም ኢንሱሊን መጠቀም እንደጀመረች አስታውሳ፤ በቤተሰብ ደረጃ ህመሙ ያለበት ሰው ስላልነበረ፣ ዕድሜዋ ከአርባ ዓመት በታች ስለሆነና ያን ያህል አስጊ የሚባል የሰውነት ክብደት ስላልነበራት ህመሙ ይከሰታል ብላ እንዳላሰበችም ታስረዳለች።
በአንድ ወቅት በህክምና ስህተት ምክንያት በተከታታይ ያስነቀለቻቸው የመንጋጋ ጥርሶች እንደነበሩ አስታውሳ፤ በተለይ የመጨረሻውን ስትነቀል ራሷን እስከ መሳት ደርሳ እንደነበርና ከዚህ ጊዜ በኋላ አቅሟ ሲደክም ጣፋጭ የሆኑ የጁስና የለስላሳ መጠጦችን አብዝታ ትጠቀም እንደነበርም አንስታለች። ለዚህ ህመም የተጋለጠችውም በዛ ወቅት እንደሆነ ታምናለች።
አሁን ላይ መድሃኒቱን በአግባቡ እየተጠቀመች መሆኑን ገልፃ፤ አመጋገብ ላይም በተቻለ መጠን ጥንቃቄ እያደረገች መሆኑን ትገልፃለች።
በረዳት ሄልዝ ኬር የህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ሞገስ አብርሃ በበኩላቸው ሶስት አይነት የስኳር ህመሞች እንዳሉ ይገልፃሉ። እንደእርሳቸው ገለፃ ሶስቱ የስኳር በሽታ አይነቶች አይነት አንድ፣ አይነት ሁለትና አይነት ሶስት በመባል ይታወቃሉ።
አይነት አንድ ከዘረ መል ጋር ተያይዞ የሚመጣና በለጋ እድሜም ሊከሰት የሚችል፣ አይነት ሁለት ከእድሜ መጨመርና ከመጠን በላይ በሆነ ክብደት ምክንያት እንዲሁም አይነት ሶስት ከእርግዝና ጋር ተያይዞ በሆርሞን ለውጥ ምክንያት ሊፈጠር እንደሚችል ያብራራሉ። በተጨማሪም አንዳንድ መድሃኒቶችም ለስኳር ህመም መነሻ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይጠቁማሉ።
አንድ ሰው ስኳሩ ከፍ ስላለ ብቻ የስኳር በሽታ አለብህ አይባልም የሚሉት ባለሙያው፤ ጭንቀት እና እንቅልፍ ማጣት ሲኖር፣ የተመገብነው ምግብ ከፍተኛ የስኳር መጠን ሲኖረው፣ ኀዘን ውስጥ ስንሆን፣ ቀዶ ጥገና ሲኖር እንዲሁም በሌሎች ምክንያቶች የስኳር መጠን ከፍ ሊል እንደሚችል ያስረዳሉ።
አንድ ሰው ስኳሩ ከፍ ብሎ መድሃኒት ከመጀመሩ በፊት የአኗኗር ዘይቤውንና አመጋገቡን እንዲያስተካክል እንዲሁም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያደርግ እንመክራለን ይላሉ።
ሆኖም ከአንድ ዓመትም ሆነ ከስድስት ወር በኋላ በድጋሚ ተመርምሮ የስኳር ህመም እንዳለበት ከተረጋገጠ በአመጋገብ፣ በአኗኗር ዘይቤና በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ብቻ ሊታከም ስለማይችል ኢንሱሊን የተባለውን የስኳር በሽታ መድሃኒት በመጀመር እንደሚገባው ይገልፃሉ።
የስኳር ህመም በተለይም ዓይንን፣ ኩላሊትንና ነርቭን የማጥቃት ባህሪ አለው የሚሉት ባለሙያው፤ ይህንንም ለመከላከል የግድ መድሃኒቱን በአግባቡ መውሰድ ያስፈልገናል ይላሉ።
ከአኗኗር ዘይቤ መቀየርና የታሸጉ ምግቦችን አብዝቶ መጠቀም ጋር ተያይዞ በአሁኑ ሰአት በሀገራችን እንደስኳር፣ ደምግፊት፣ የልብ ችግርና ካንሰርን የመሳሰሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እየጨመሩ እንዳሉ የሚገልፁት ባለሙያው፤ ህብረተሰቡ በሚችለው ልክ የጤና ምርመራ በማድረግ፣ ችግሩ ከተከሰተም መድሃኒቱን በአግባቡ በመውሰድ የሚመጣውን ተጓዳኝ ችግር ማስወገድ እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ነፃነት አለሙ
አዲስ ዘመን ህዳር 15/ 2017 ዓ.ም