– ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ብሔራዊ የጥራት መንደርን መርቀው ከፈቱ
አዲስ አበባ፡– ብሔራዊ የጥራት መንደር የኢትዮጵያ ማንሠራራት ዘመን ጅማሪ ተደርጎ የሚወሰድ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ብሔራዊ የጥራት መንደርን ትናንት መርቀው ከፍተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጥራት መንደር ምረቃ መርሐ ግብር ላይ እንደገለፁት፣ በግብርና፣ በጤና፣ በግንባታና በሌሎች ዘርፍ ጥራት ያለው ምርትና አገልግሎት ለማቅረብ የጥራት መንደሩ ወሳኝ ነው። ይህም መንደሩ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ጥራት በማረጋገጥ በምርት ጥራት ጉድለት የሚያጋጥሙ ጉዳቶችን ያስወግዳል፣ ለዜጎችም ጥራቱ የተረጋገጠ ምርትና አገልግሎት እንዲያገኙ ያደርጋል ብለዋል።
የጥራት መሠረተ ልማት የሌላቸው ሀገራት ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ያዳግታቸዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ምርትና አገልግሎት ለማቅረብ ጥራትን ማረጋገጥ ቀዳሚ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
የጥራት መንደሩ መመረቅ ለኢትዮጵያ ትርጉም ብዙ መሆኑን አመልክተው፤ ለሀገር ውስጥ ሆነ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ጥራታቸውን ማረጋገጥ የሚቻለው የተሟላ የጥራት መሠረተ ልማት ሲኖር መሆኑን ተናግረዋል።
0ለምሳሌም በርካታ የታሸጉ የምግብ ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገቡ ጠቁመው፤ እነዚህ የታሸጉ ምግቦች በጥራት መንደሩ ገብተው ጥራታቸው በቤተ ሙከራ (ላብራቶሪ)ተፈትሾ ችግር ካለበት ወደ ገበያ እንዳይሰራጭ በማድረግ ጉዳቱን ማስቀረት እንደሚቻል ነው የገለጹት።
0የጥራት መንደሩ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረው አመልክተው፤ ተቋሙ በተሟላ አቅም ሥራውን ሲጀምር የወጪ ንግድ እንደሚያድግና ወደ ሀገር ውስጥ የምናስገባቸውም ጥራታቸው የተረጋገጠ ይሆናል ብለዋል። ይህም ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ ምርጥ ምርጡን የምትቀበል፣ ጥራቱ የተረጋገጠ ምርት የምትቀበል ሀገር እንደሚያደርጋት ገልጸዋል።
0የጥራት መንደሩ ቁልፍ ተቋማትን ያቀፈ ሲሆን፤ እነዚህም የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት፣ የኢትዮጵያ የሥነ ልክ ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለሥልጣን መሆናቸው ተጠቅሷል።
ብሄራዊ የጥራት መንደሩ የጥራት ማረጋገጫ ቤተ ሙከራዎች (ላብራቶሪዎች) የተሟሉለትና መንደሩም በሰባት ነጥብ ሁለት ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን ዘመናዊ ቤተ ሙከራዎችን ጨምሮ ስምንት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሆነበት በምረቃ በመርሃ ግብሩ ተገልጿል።
ጌትነት ምህረቴ
አዲስ ዘመን ህዳር 15/ 2017 ዓ.ም