ቡታፍሊካና አልበሽርን እንደ ማሳያ
ብዙ የአፍሪካ መሪዎች አሁንም ድረስ በግዴታ ካልሆነ በውዴታ ከስልጣን ለመውረድ ሲቸገሩ ይታያሉ፡፡ በእርግጥ መንበሩ ላይ የሚወጡት በኃይል ስለሆነ ለመውረድም ኃይል ቢፈልጉ የሚያስገርም አይደለም፡፡ ግን ደግሞ አሁን ላይ ሲሆን አጸያፊ ነው፡፡ ዓለም ሰልጥናለችና ስልጣንም የሚያዘው በሰለጠነ መንገድ ነው፡፡ የአፍሪካ ማፈሪያዎች ግን አሁንም በኃይል ካልሆነ ከወንበራችን ወይ ንቅንቅ እያሉ ነው፡፡
የአልጀሪያው አብዱላዚዝ ቡታፍሊካና የሱዳኑ ኦማር ሃሰን አልበሽር ደግሞ ከእነዚህ አምባገነን የአፍሪካ መሪዎች መካከል ዋነኞቹ ናቸው ሲል ኒው አፍሪካ መጽሄት ይገልፃል፡፡ በዛሬው የዓለም አቀፍ ጉዳዮች አምዳችን እነዚህን መሪዎች አስመልክቶ መጽሄቱ ያቀረበውን ጠለቅ ያለ ትንታኔና ሌሎችም የዜና አውታሮች ዋቢ አድርገን ልናቀርብላችሁ ወደድን፡፡
“ምክንያቱም ፕሬዚዳንት አብድላዚዝ ቡተፍ ሊካ በኃይል ተገደው ለመውረድ ቀናቸውን እየተጠባበቁ የሚገኙ ሲሆን ፕሬዚዳንት አልበሽር ደግሞ ከህዝባቸው ፍላጎት በተቃርኖ ቆመው አሁንም ወንበራቸውን የሙጥኝ እንዳሉ ነው”። የመሪዎችን ከስልጣን አንወርድም ባይነት ተከትሎ ደግሞ አልጀሪያና ሱዳን በከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ እየተናጡ ይገኛሉ፡፡ ቀጥሎ ምን ሊፈጠር ይችላል? የትንታኔው መነሻና መድረሻም በዚህ ጥያቄ ዙሪያ የሚያጠነጥን ይሆናል፡፡
የቁጣ ማዕበል
አልጀሪያ
ፕሬዚዳንት አብድላዚዝ ቡታፍሊካ በአል ጀሪያ የፕሬዚዳንትነቱን መንበር ከተረከቡ ሁለት ድፍን አስርታት ሞልቷቸዋል፡፡ በአውሮፓውያኑ 1989 መፈንቅለ መንግስት በጠብመንጃ ታግዘው ወደ ስልጣን የመጡት ፕሬዚዳንት ኦማር ሃሰን አልበሽር በበኩላቸው የሱዳን መሪ (ገዥ የሚለው የበለጠ ይስማማቸዋል) ከሆኑ የአንድ ትውልድ ዕድሜን አስቆጥረዋል፡፡ ጥቁሩ ፈርዖን አሁንም በስልጣን ላይ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ሁለቱ ‹‹ስልጣን አይጠግቤ›› መሪዎች ለዘመናት የታፈነና የተጨቆነ የህዝብ ቁጣ እንደ ማዕበል ፈንድቶ ዙሪያቸውን እስኪከባቸው ድረስ ከወንበራቸው መውረድ አልፈለጉም፡፡
ሞቴን ከስልጣን ጋር ያድርገው ብለው ዙፋን ላይ የሙጥኝ ተጣብቆ መቅረቱን መርጠዋል፡ ፡ እናም ከዛሬ ነገ ያሻሽላሉ በሚል አምባገነን
መሪዎቹን በጨዋነት ሲያስታምም የኖረው ህዝብ የመሪዎቹ ልብ እንደ ፈርዖን ቢደነድንበት የለውጥ ቀንም እንደ ምፅአት ቢረዝምበት ትግስቱ አለቀ። በአምባገነኖቹ ንቀት ህዝብ ተቆጣ፡፡ ስልጣን በኃይል ጨብጠው በግዴታ ሲገዙት የኖሩትን ጨቋኝ መሪዎቹን በግዴታ ለማውረድና ነጻነቱንና እኩልነቱን ለማወጅ በሁለቱም አገራት ህዝብ ወደ አደባባይ ከወጣ ሰነባበተ፡፡
በአልጀሪያ ባለፈው የካቲት ፕሬዚዳንት አብድላዚዝ ቡተፍሊካ ለአምስትኛ ጊዜ ለፕሬዚዳን ትነት እንደሚወዳደሩ መግለጻቸውን ተከትሎ የህዝብ አመፅ ከተቀሰቀሰ ሦስተኛ ወሩን ይዟል፡ ፡ መላ አገሪቱን ባዳረሰው ተከታታይ የአደባባይ ተቃውሞ ጫና የበዛባቸው ፕሬዚዳንት ቡተፍሊካ ትቻለሁ በቀጣዩ ምርጫ አልወዳደርም ቢሉም ህዝባዊ አመጹ አልበረደም፡፡
ምክንያቱም ፕሬዚዳንቱ የተውት ለፕሬዚ ዳንትነት መወዳደሩን ነው እንጂ ከስልጣን አልወረዱም፤ የስልጣን ዘመናቸው እስኪጠናቀቅ እስከ ቀጣዩ የሚያዝያ 28 ምርጫ በስልጣን ላይ ይቆያሉ፡፡ እናም ሰላማዊ ሰልፈኞችና ተቃዋሚዎች “ከውድድር ራሳቸውን ማግለል ብቻ በቂ አይደለም፤ ፕሬዚዳንቱ ከስልጣንም መውረድ አለባቸው” ብለዋል፡፡ ለተቃውሞ ከወጣው ህዝብ መካከል አብዛኞቹ ወጣቶቸ ሲሆኑ “እኛ የምንፈልገው አጠቃላይ የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ ብቻ ሳይሆኑ ገዥው የናሽናል ሊብሬሽን ፍሮንት ፓርቲም›› ማለታቸውንና የፕሬዚዳንቱ ከስልጣን መውረድ በራሱ በቂ አለመሆኑንና የሚፈልጉት ለውጥ እስኪመጣ ተቃውሟቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ መግለ ጻቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ሱዳን
በተመሳሳይ ባለፈው የፈረንጆቹ ታህሳስ 19 በዳቦ ዋጋ መናር ምክንያት በሱዳን ህዝባዊ ተቃውሞ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ በአገሪቱ ውጥረት ነግሶ በከፍተኛ አመጽ እየታመሰች ትገኛለች፡፡ ለህዝቡ የዳቦ ጥያቄ ሰላማዊና ተገቢውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ለተቃውሞ የወጡ ወጣቶችን በመግደልና በማሰር በአሮጌው ፈርዖናዊ መንገድ የህዝብን ድምጽ ለማፈንና ስልጣኑን ለማስቀጠል የሞከረው የአልበሽር መንግስት እርምጃም ሱዳናውያንን ክፉኛ አስቆጥቷል፡፡ “ዳቦ ሰጥተህ ግዛን” ያለን ህዝብ “እንዲያውም አትገዛንም” አስብሏል፡፡
ጥያቄውም ከዳቦ ወደ ፖለቲካ ተቀይሯል ይላል የሮይተርስ ዘገባ፡፡ ሰላሳ ዓመት አንሶባቸው ሌላ ሰላሳ ዓመት በስልጣን ላይ ለመቆየት ሰላሳ ዓመት ያልሞላቸው ወጣቶችን በጥይት ያስደበደቡት ዓይነ ጠባቡ አምባገነን ፕሬዚዳንት አልበሽርም የገዛ ውሳኔያቸው እንደ ቡመራንግ ተመልሶ ወጋቸው፡ ፡ ከእቅዳቸው በተቃራኒ የህዝቡ ተቃውሞ የበለጠ ተባብሶ ያላሰቡት ቅርቃር ውስጥ ቢከታቸው
አልበሽርም እንደቡተፍሊካ በ2020 ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ ስልጣኔን ለምክትሌ አስረክቤ እቆያለሁ አሉ፡፡
ሆኖም አልበሽር የሚያምናቸው አላገኙም። ከዚህ ቀደም በ2013 እንደዚሁ ስልጣኔን አስረክባለሁ ብለው በቃላቸው አልተገኙምና። እናም ህዝቡ “ብልህ ሁለት ጊዜ አይሸወድም፤ አናምንዎትም፤ አሁኑኑ ከስልጣን ይውረዱና ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ እስኪደረግ ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት ይቋቋም” የሚል ተቃውሞውን የበለጠ አስፋፍቶና አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ፕሬዚዳንቱ የህዝብ ተቃውሞን በኃይል ለማፈን የጣሉትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም በአስቸኳይ እንዲያነሱ ተጠይቀዋል፡፡
ከታሪክ መማር ያልቻሉት የአፍሪካ አምባገነን መሪዎች
“ብልህ ከሌላው፤ ጅል ከራሱ ይማራል” የሚል አገርኛ አባባል አለ፡፡ በእርግጥም ትልቅ ቁም ነገር የያዘ አባባል ነው፡፡ ምክንያቱም ሰው ከመልካም ነገር ብቻ ሳይሆን ከመጥፎ ተሞክሮም መማር ይችላል፡፡ ከዚህ መርሆ አኳያ ስንመዝናቸው አብዛኞቹ የአፍሪካ አምባገነን መሪዎች ጅሎች ናቸው፡፡ ከሌሎች አቻዎቻቸው ስህተት ትምህርት አልወሰዱም፣ ከታሪክ አልተማሩም፤ መሰሎቻቸውን እንዳልነበሩ ያደረገው የጥፋት ውሃ እነርሱንም ጠራርጎ እስኪወስዳቸው ቆመው እየተጠባበቁ ነውና፡፡
ለዚህም ዋነኞቹ ማሳያዎች የህዝብን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ተቀብሎ ህዝብ የሚፈልገውን ከማድረግ ይልቅ በተለመደው የአፈናና የግድያ ስልት የጭቆና ቀንበራቸውን ለማጥበቅ ላይ ታች እያሉ የሚገኙት ፕሬዚዳንት ቡተፍሊካና የሱዳኑ አቻቸው ናቸው፡፡ ህዝብ እያለ ያለው “የምንፈልገው እርገጤን በእርገጤ መቀየር አይደለም፤ የእናንተ የጭቆና መሳሪያ የሆነው የፖለቲካ ሥርዓት እንዲለወጥ ነው ፤ ስልጣን ከእናንተ ወደ እኛ እንዲሸጋገር ህዝብ የስልጣን ባለቤት እንዲሆን እንፈልጋለን” ነው፡፡
ሁለቱ አምባገነኖች በበኩላቸው “ስልጣኔን ለምክትሌ አስተላልፋለሁ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማሻሻያ አደርጋለሁ፣ ምርጫ እስኪደረግ ታገሱን ቅበጥርሴ” በሚሉ ማታለያዎች የስልጣን ዕድሜያ ቸውን ለማራዘም አበክረው ሲጥሩ ይስተዋላሉ፡፡ እንዲያም ሲል ለተቃውሞ የወጡ ዜጎችን በግላጭ በአደባባይ በጥይት ያስረሽናሉ፡፡
ከዚህም ባሻገር የህዝቡን የለውጥ ጥያቄ ለመቀልበስና ስልጣናቸውን ለማስቀጠል በርካታ ሴራዎችንና ስራዎችን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ሰማንያ በመቶ የሚሆነው የሱዳን አጠቃላይ ገቢ የሚመደበው ከህዝብና ከሀገር ጠባቂነት ወደ የአልበሽር የጭቆና አገዛዝ ዋና አስፈጻሚነት ለተለወጠው የሀገሪቱ መከላከያና ጦር ሰራዊት ነው፡፡
ኢኮኖሚን በሚመለከትም “አደህይቶ መግዛት” እንዳሉት የእኛው ፕሮፍ አልጀሪያም ሆነ ሱዳን ዳቦ የጠገበ ህዝብ ነጻነት እንዳይጠይቃቸው (አልበሽርን ክፉኛ እያስጨነቀ የሚገኘው የአሁኑ የሱዳን አመጽ በዳቦ ጥያቄ የተጀመረ ቢሆንም) በሰፊው ህዝብና በ “መንግስታውያን ቤተሰቡ” መካከል እንደሰማይና መሬት የተራራቀ የሀብት ልዩነት እንዲኖር ዘመናቸውን ሁሉ ለፍተዋል፡፡
ስለሆነም የናጠጠ ሀብታም መንግስትና የተ ራቆተ ድሃ ህዝብ ፈጥረዋል፡፡ አይነኬዎቹን የሊቢያው ሙአመር ጋዳፊንና የዚምባብዌው ሮበርት ሙጋቤን ጨምሮ የቱኒዝያው ቤን አሊ፣ የግብጹ ሆስኒ ሙባረክ ሌሎች የአፍሪካ አምባገነኖችም እንዲህ በሰላማዊ መንገድ ከህዝባቸው የቀረበላቸውን “ይብቃችሁ በሰላም ልቀቁን” ጥያቄ በኃይል ለማፈን ከምንጊዜውም በላይ ጭቆናቸውን አክብደው እንደነበር ታሪክ ይመሰክራል፡፡
ሆኖም ግን በጥቂቱም ቢሆን የራሱ የተገዥው ፈቃድ ካልተጨመረበት ገዥ ተገዥን መንግስትም ህዝብን ማሸነፍ አይችሉምና ከመጠን ያለፈ ጭቆና ሰላማዊ ጥያቄን ወደ ኃይል አመጽ ቀይሮ እነ ጋዳፊ በህዝብ የቁጣ ማዕበል ተገፍትረው በደራሽ ውሃ እንደተወሰደ ግንድ ቱቦ ውስጥ ተወሽቀው ከስልጣናቸው ብቻ ሳይሆን ከህይወታቸውም እስከወዲያኛው ተሰናበቱ፡፡
እነ አልበሽርና ቡተፍሊካም ከታሪክ ካልተማሩ ዕጣ ፈንታቸው የሚሆነው ይኸው ነው፡፡ ምርጫው በእጃቸው ነው፡፡ አንድም ህዝቡ የሰጣቸውን ዕድል በአግባቡ ተጠቅመው በሰላማዊ መንገድ ስልጣናቸውን ማስረከብና ህዝቡ የፈለገው ለውጥ እንዲመጣ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፤ ወይም የህዝብን ጥያቄ በኃይል ለማፈን የጀመሩትን የጭቆና መንገድ አጠናክረው መቀጥልና እንደነ ጋዳፊ ጆሯቸውን ተይዘው ተጎትተው መውረድ፡፡ እነ ጓድ አልበሽር አሁን እየሄዱበት ያለው መንገድ ግን ለሁለተኛው ምርጫ የቀረበ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም በጭቆና ብዛት የፈነዳን የህዝብ ቁጣ ሊያስቆም የሚችል ምንም ዓይነት ኃይል በምድር ላይ የለምና፤ ቸር እንሰንብት፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2011
በይበል ካሳ