የስነ ምግባር ቋንቋዊ ትርጉሙ ባህሪ ማለት ነው። ስነ-ምግባር ከነፍስ ጋር ጥልቅ ቁርኝትና የፀና መሰረት ያለው ሲሆን ፍላጎታችንና ምርጫችን፤ በጎና መጥፎ እንዲሁም ፀያፍም ሆነ ውብ ሥራዎቻችን የሚመነጩበት የህይወታችን ክፍል ነው። ነፍስ በባህሪዋ ለሁሉም ነገር ምቹ ናት። ይህም ማለት መጥፎን ወይም የጥሩ ተፅዕኖን ለመቀበል ሁሌም ዝግጁ ነች።
ነፍሳችን በሃይማኖትም ሆነ በትምህርት ቤት አሊያም በሕይወታችን ጥቂት ስልጠና ብታገኝ ሐቅንና መልካምን የመውደድ፤ በጥሩ ነገር መነሳሳት፤ ቆንጆን ነገር ማፍቀር፤ መጥፎን የመጥላት ባህሪን እንድትላበስ ማድረግ ይቻላል።
ይህ ባህሪዋ መልካምና ተወዳጅ ተግባራትን ያለ ማንም አስገዳጅነት ወደመተግበር ያሸጋግራታል። ይሄኔ ነፍሳችን “የመልካም ስነምግባር” ባለቤት ትሆናለች። ለምሳሌ፡- ሆደ ሰፊነትና እርጋታ፤ ታጋሽነትና ቻይነት፤ ቸርነትና ጀግንነት፤ ፍትሐዊነትና በጎነት ወዘተ የመልካም ስነ-ምግባር መገለጫዎች ናቸው።
በተቃራኒው ነፍስ ሊደረግላት የሚገባውን እንክብካቤ ካልተደረገላት ወይም በመጥፎ አስተዳደር ካደገች መጥፎውን ጥሩ፤ ቆንጆውን ደግሞ የሚያስጠላ አድርጋ መመልከት ባህሪዋ ይሆናል። ከዚያም ቆሻሻና ርካሽ ተግባራትንና ንግግሮችን ያለምንም አስገዳጅነት ትተገብራለች፤ ትናገራለች። እንድን መጥፎ ሥራ በንግግርም ሆነ በተግባር የምንሠራውና ያለማንም አስገዳጅነት የምንፈፅመው ከሆነ መጥፎ ስነ-ምግባር የሚል ስም እንሰጠዋለን።
ከእነዚህ ሥራዎች መካከል እንደ ሸፍጥ፣ ሐሰትን መናገር፣ ትዕግስት ማጣት፣ ስግብግብነት፤ ድርቅና፤ ፈላጭ ቆራጭ መሆን፤ መጥፎ መናገር፤ ብልግና ወዘተ የመጥፎ ስነ-ምግባር ምሳሌዎች ናቸው። እነዚህ በድምሩ የአንድን ማህበረሰብ ወይም ግለሰብ ለህግ የመገዛትና አለመገዛት ባህል በቀጥታ ይወስኑታል። በመሆኑም ስነ ምግባር ዝቅጠት ካለ ለህግ የመገዛት ባህላችንም የዚያኑ ልክ ቅጥ ያጣል ማለት ነው።
ከዚህ መሰረታዊ ጉዳይ ስንነሳ አገራችን ኢትዮጵያ በስነ ምግባር የታነፁ ዜጎችን ለማፍራት ዘራሁ የምትለውን ያህል መልካም ፍሬ አግኝታለች ለማለት የሚያስደፍር ውጤት አልታየም።
በዚህ ረገድ የእምነት ተቋማት ስነ ምግባር ያለው ምዕመን ለማፍራት ከሠሩት ሥራ ጀምሮ፤ መንግሥት የስነ ዜጋና የስነ ምግባር ትምህርትን በማስረፅ ሂደት ያከናወናቸው ግምገማዎች ያመለከቱት በአመራሩ ቁልፍ ድክመት የሚፈለገውን ያህል ውጤት አለመምጣቱን በጥናት ጭምር አስደግፎ ነግሮናል። ጥናቱም የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት ስርዓተ ትምህርት እንዲከለስ አስገድዷል።
በዓለም የፍትሕ ፕሮጀክት ተጠንቶ በቅርቡ ይፋ የተደረገው የዓለም የሕግ የበላይነት መለኪያ መሠረት፣ ኢትዮጵያ ከ126 አገሮች 118ኛ ደረጃን መያዟ ተመልክቷል። ጥናቱ ለሕግ ተገዥነትን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመለካት 120ሺ የቤት ለቤትና የ3 ሺ 800 ባለሙያዎችን አስተያየት ዳሰሳ ጥናት በማድረግ ነው። አገሪቱ ያስመዘገበችው ይህ ውጤት የሚያመለክተው በስነ ምግባር የታነፀ ዜጋ በመገንባት ለህግ የሚገዛ ማህበረሰብ በመፍጠር ረገድ ፈቅ ያለ ነገር አለመኖሩን ነው።
አንድ ዓመት ያስቆጠረውን የለውጥ ጉዞ ተከትሎ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የሚስተዋሉት የህግ ጥሰቶችና ሥርዓት አልበኝነት መነሻቸው ግለሰቦች አሊያም የተደራጁ አካልት ያሉበት የስነ ምግባር ዝቅጠት ልኬቱ የከፋ ደረጃ ላይ መሆኑን ያሳያል።
በዚህ ሁኔታ ቤተሰብ፣ የሃይማኖትና የፍትህ ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች በስነ ምግባር የታነፀ ዜጋን በማፍራት ትልቅ ኃላፊነት የተጣለባቸው ቢሆንም እንደ አገር ግን መጥፎ ስነ ምግባር ያለው ዜጋ ቁጥሩ በዝቶ ይታያል። በመሆኑም ተቋማቱ ዛሬም ድረስ አመድ አፋሽ ሆነዋል።
በአጠቃላይ ይህ ትውልድ የደረሰበት የስነ ምግባር ልኬት ምን መልክ ይዟል? ብሎ ሐቁን ማወቅ ለቀጣይ ሥራ ትልቅ መሰረት ነው። በመሆኑም እኛ የሦስት ሺ ዘመን ታሪክ ባለቤት ናቸው የተባለልንን ያህል ነን ወይ? ከቀደምት ወላጆቻችን የተቀበልነውን፤ የነበርነውን መልካም ባህል ይዘናል ወይ? ብሎ በመጠየቅ ተገቢ መልስ ማግኘት ይገባል። ምክንያቱም አባቶች እንዳሉት ጣራውን ምን ብናሳምረው መሰረቱን የምንቆፍረው ቤት መፍረሱ አይቀርምና ነው።
እንደ ሀገር የዜጎችን የስነ ምግባር ሁኔታ ለማጎልበት ተቋማትና ሲቪክ ማህበረሰብን በሚፈለገው ልክ ማጠንከር ይገባል፤ ማጠንከር ብቻ ሳይሆን የሚፈለግባቸውን ሥራ መሥራት እንዳለባቸው ግልጽ አቋም ሊኖር ይገባል። የሃይማኖት እና የትምህርት ተቋማት ከመሰረታዊ ዓላማቸው እንዳይራራቁ ማህበረሰባዊ የስነምግባር ብልሽታችንን ሊታደጉት ጊዜው ያስገድዳል።
የመገናኛ ብዙሃን ለማህበረሰባዊ ስነምግባር ዝቅጠት ያበረከቱት አስተዋፅኦ እጅግ የላቀ መሆኑን ተገንዝበው የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል። በዚህ ሂደት በተለይ በመንግሥት በኩል የሚደረጉ ፖለቲካዊ ውይይቶች አስፈላጊ ቢሆኑም ስነምግባራዊ የውይይት መድረኮች በዝተው የበለጠ ትኩረት ሊቸሩ ይገባል። ስለዚህ የስነ ምግባር ዝቅጠቶችን ለማረም ሁሉም የድርሻውን ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2011