አወዛጋቢው ሰው ሠራሽ ዲኤንኤ የመፍጠር ፕሮጀክት ተጀመረ

በዓለም ላይ የመጀመሪያው ነው ተብሎ የታመነው እና የሰው ልጅን ሕይወት መሠረት ከባዶ ለመፍጠር የሚሞክረው አወዛጋቢ ፕሮጀክት ሥራ ጀመረ። ይህ ጥናት እስካሁን ድረስ እንደ ነውር ይቆጠር የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን የዓለማችን ትልቁ የሕክምና በጎ አድራጎት ድርጀት ገንዘብ በመስጠቱ ወደ ሥራ መግባት ተችሏል። ፕሮጀክቱ የሕጻናት ዘረመል በወላጆቻቸው እና በዶክተሮቻቸው ተመርጦ የተለየ ባሕሪ እንዲኖራቸው ያደርጋል ወይንም በቀጣዩ ትውልድ ላይ ያልታየ ለውጥ ሊያስከትል ይችላል በሚል እስካሁን ድረስ ሳይካሄድ ቆይቷል። የዓለማችን ትልቁ በጎ አድራጎት ድርጅት ዌልኮም ትረስት ፕሮጀክቱን ለማስጀመር 10 ሚሊዮን ፓውንድ የሰጠ ሲሆን፣ ምርምሩ ብዙ ለማይድኑ በሽታዎች ሕክምናዎችን በማፋጠን ከጉዳቱ የበለጠ ጥቅም የማስግኘት አቅም አለው ብሏል።

የፕሮጀክቱ አካል የሆነው በኬምብሪጅ የሚገኘው የኤምአርሲ ሞለኪውላር ባዮሎጂ ላብራቶሪ ባልደረባ ዶ/ር ጁሊያን ሳሌ ለቢቢሲ ጥናቱ በባዮሎጂ ምርምር ቀጣዩ እመርታ ነው ብለዋል። “ወሰኑ ገደብ የለውም፤ የሰዎችን ዕድሜ በሚገፋበት ጊዜ ሕይወትን የሚያሻሽሉ እና እርጅናን ተከትለው የሚመጡ ሕመሞችን የሚቀንሱ የሕክምና ዘዴዎችን እየተመለከትን ነው።”ይህን አካሄድ ተጠቅመን በሽታን የሚቋቋሙ ህዋሶችን ለመሥራት እና የተጎዱ የአካል ክፍሎች እንደ ጉበት እና ልብ ያሉ ላይ የምንጠቀምበትን እንዲሁም በሽታን የመከላከል አቅምን ለማዳበር እየሠራን ነው” ብለዋል።

ተቺዎች ግን ምርምሩ የተሻሻሉ ወይም የተለወጡ ሰዎችን ለመፍጠር ለሚፈልጉ ሕሊና ቢስ ተመራማሪዎች መንገድ ይከፍታል ብለው ይሰጋሉ። ቢዮንድ ጂኤም የተሰኘ ቡድን ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ፓት ቶማስ፣ “ሁሉም ሳይንቲስቶች ጥሩ ለመሥራት በቦታቸው ላይ እንዳሉ ማሰብ እንፈልጋለን፤ ነገር ግን ሳይንስ ለጉዳት እና ለጦርነት ሊታቀድ ይችላል” ሲሉ ገልጸዋል።

በሰው ጂኖም (በአካላችን ውስጥ ያለው የተሟላ ዲኤንኤ) ውስጥ የሚገኙት መሰላሎች ወደ ሦስት ቢሊዮን ገደማ የሚሆኑ የኬሚካል “መወጣጫዎች” አሏቸው። እያንዳንዱ መወጣጫ ከሁለት ኬሚካላዊ ንጥረ ነገሮች የተሠራ ስለሆነ የሳይንስ ሊቃውንት እነዚህን መወጣጫዎች ጥንድ ኬሚካሎች ብለው ይጠሯቸዋል፤ የኬሚካሎቹ አጠቃላይ ቁጥር ደግሞ አራት ነው። እነዚህ ንጥረ ነገሮች ኤ፣ ሲ፣ ጂ እና ቲ ተብለው የሚጠሩ ሲሆን፣ ይህን ስም ያገኙት እያንዳንዱ ቃል በእንግሊዝኛ ከሚጠራበት የመጀመሪያ ፊደል ነው። የሰው ልጅ ጂኖም ፕሮጀክት ሳይንቲስቶች ሁሉንም የሰው ልጅ ዘረመሎች እንደ ባር ኮድ እንዲያነቡ አስችሏቸዋል። በሂደት ላይ ያለው አዲሱ ጥናት፣ ሲንቴቲክ ሂውማን ጂኖም ፕሮጀክት ተብሎ ይጠራል። ይህ ምርምር የሥነ ሕይወት ምርመርን ግዙፍ እመርታ ተደርጎ ሊወስድ ይችላል መባሉን ተመልክቷል።

ተመራማሪዎች የዲኤንኤ ሞለኪውል እንዲያነቡ ብቻ ሳይሆን የተወሰኑ ክፍሎችን እንዲፈጥሩ ያስችላቸዋል። ምናልባት አንድ ቀን ሙሉ በሙሉ ሞለኪውል በሞለኪውል በቤተ ሙከራቸው ውስጥ ሊፈጥሩ ይችሉ ይሆናል። የሳይንስ ሊቃውንት የመጀመሪያ ዓላማ የሰውን ልጅ ክሮሞዞምን በተቀነባበረ መልኩ መገንባት እስከሚችሉ ድረስ ትላልቅ የሰውን ዲኤንኤዎችን የመገንባት መንገዶችን ማዘጋጀት ነው። ይህም የሰው ልጅን ዕድገት፣ ጥገና እና ክብካቤ የሚቆጣጠሩትን ዘረመሎችን ይይዛል። በዚህም የተነሳ ዘረመሎች እና ዲኤንኤ ሰውነታችንን እንዴት እንደሚቆጣጠሩ የበለጠ ለማወቅ ማጥናት እና ለመሞከር ያውላል ተብሏል።

የዌልኮም ሣንገር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ማቲው ሁልስ እንደሚሉት እነዚህ ዘረመሎች መስመር ሲስቱ ብዙ በሽታዎች ይከሰታሉ። “ዲኤንኤ ከባዶ መገንባት ዲኤንኤ እንዴት እንደሚሠራ ለመመርመር እና አዳዲስ ንድፈ ሐሳቦችን እንድንፈትሽ

ያስችለናል፤ ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ ይህን ማድረግ የምንችለው ሕይወት ባላቸው ነገሮች ውስጥ ያለውን ዲኤንኤ በማስተካከል ብቻ ነው።”የፕሮጀክቱ ሥራ በቤተ ሙከራዎች ውስጥ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሲሆን፣ ሰው ሠራሽ ሕይወት ለመፍጠር ምንም ዓይነት ሙከራ አይኖርም ነው የተባለው።

ሰው ሠራሽ ክሮሞዞም መፍጠር የሚያስችል ዘዴን የቀመሩት በኤድንብራ ዩኒቨርሲቲ የጄኔቲክ ሳይንቲስት የሆኑት ፕሮፌሰር ቢል ኤርንስሾ እንዳሉት “ባዮሎጂካል መሣሪያዎችን፣ የተሻሻሉ ሰዎችን ወይም የሰውን ዲኤንኤ ያላቸውን ፍጥረታት ለመፍጠር ሊሞክሩ ይችላሉ።””አንዴ ጂኒው ከጠርሙሱ ወጥቷል” ሲሉ ተናግረዋል። “አሁን ክልከላ የተደረገባቸው በርካታ ነገሮች ሊኖሩን ይችላሉ፤ ነገር ግን ተገቢውን መሣሪያ ማግኘት የሚችል ድርጅት ማንኛውንም ነገር ማቀናበር ከጀመረ እኛ ማቆም የምንችል አይመስለኝም። “ብለዋል። ዶ/ር ቶም ኮሊንስ ቴክኖሎጂው በጤና ላይ በሚሠሩ ኩባንያዎች ከዚህ ጥናት የሚገኙ የሕክምና ዓይነቶችን እንዴት ለገበያ ያቀርባሉ የሚለው ያሳስባቸዋል።

“ሰው ሠራሽ የሰውነት ክፍሎችን ወይም ሰው ሠራሽ ሰዎችን እንኳን መፍጠር ከቻልን ማን ነው በባለቤትነት የሚቆጣጠረው። እና የእነዚህ ፈጠራዎች መረጃን ማን በባለቤትነት ይይዘዋል?” “ቴክኖሎጂውን አላግባብ ጥቅም ላይ ሊውል መቻሉን ስታይ ዌልኮም ለምን ፕሮጀክቱን በገንዘብ መደገፍ ፈለገ የሚለውን ትጠይቃለህ። “ለዶ/ር ቶም ኮሊንስ የርዳታ ድርጅቱ ገንዘቡን ለመስጠት ቀላል ውሳኔ አላሳለፈም። “የውሳኔው ዋጋ ምን ነበር ብለን ራሳችንን ጠየቅን። “”ይህ ቴክኖሎጂ አንድ ቀን ሊሠራ ይችላል። ስለዚህ አሁን ማድረግ ቢያንስ በተቻለ መጠን ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ለመሥራት እና የሥነ ምግባር እና የሞራል ጥያቄዎችን በተቻለ መጠን በቅድሚያ ለመጋፈጥ እየሞከርን ነው።”ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You