ድሬዳዋ ከተማ አትተኛም። ከሌሎች የኢትዮጵያ ትላልቅ ከተሞች በተለየ መልኩ ሌሊትም ሕይወት ይቀጥላል። አስገራሚው ነገር እኩለ ሌሊት ላይ ያለስጋት በጎዳናዎቿ መንቀሳቀስ የሚቻል መሆኑ ነው። ታዲያ ይህ እንዲሁ የተገኘ ዕድል አይደለም። የድሬ ሌሊት ሰላማዊ የሆነው በምክንያት ነው። “ሌሊቱ የኛ ነው” የሚል መፈክር አንግቦ 500 ወጣቶችን የሚያሰማራው የሌሊት ታክሲዎች ማኅበር እና የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ወላጆቹ ናቸው።
ወጣት ቃልኪዳን ፀሐይ የሌሊት ታክሲዎች ማኅበር ሊቀመንበር ነው። ድሬዳዋ ዘጠኝ የከተማ ወረዳዎችን፣ አራት የገጠር ወረዳዎችን እና 37 ቀበሌዎችን እንደያዘች የሚናገረው ወጣቱ፤ እኛ ከዘጠኙ የከተማዋ ወረዳዎች የተውጣጣን የተለያየ ብሔርና ሃይማኖት ያለን ነገር ግን ለአንድ ዓላማ የተሰባሰብን ወጣቶች ነን ይላል።
እርሱ እንደሚያስረዳው ማኅበራቸው የተቋቋመበት ዓላማ፣ ድሬዳዋ ላይ ቀን እና ማታ አገልግሎት የሚሰጡ 16 ሺህ የሦስት እግር ተሽከርካሪዎች አሉ። በተለይ በምሽት በሦስት እግር ተሽከርካሪዎች የሚፈጸሙ ስርቆቶች ነበሩ። ማኅበራችን የተደራጀው ይህንን ስርቆት ለማስቀረትና ማኅበረሰባችንን በተመጣጣኝ ዋጋ 24 ሰዓት ለማገልገል በሚል ነው።
ማኅበሩ የተደራጀውና ወደ ሥራ እንዲገባ የተደረገው በከተማችን ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሃሳብ አመንጪነት መሆኑን ጠቅሶ፤ አባላቱ አምስት መቶ ወጣቶች ነን። ተደራጅተን ቀጥታ ወደ ሥራ አይደለም የገባነው። ለምሽት የታክሲ አገልግሎት ከተመረጥን በኋላ ወደ ሥልጠና ነው የገባነው። ለ 15 ቀናት ማይንድ ሴት፣ ሥራ ፈጠራ፣ መልካም ሥነምግባር፣ በበጎ ፍቃድ ማኅበረሰብን ማገልገል እና ወንጀልን መከላከል የሚመለከቱ ሥልጠናዎችን ወስደናል ነው የሚለው።
አክሎም ከዚያ በኋላ የሌሊት ባጃጅ መሆናችንን የሚገልጽ አንፀባራቂ ቁጥር ያላቸው መለያዎች ተሰጥተውን ወደ ሥራ ገብተናል። ወደ ሥራ ከገባን በኋላ መሰባሰባችን ካልቀረ ማኅበረሰባችንን የሚጠቅም ሥራ መሥራት አለብን የሚል ስምምነት ላይ ደረስን። ከዚያም ከተደራጀንበት ዓላማ ውጭ ከሥራችን ጎን ለጎን ማኅበረሰባችንን በተለያዩ መንገዶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ማገልገል ጀመርን ይላል።
አንድ አሽከርካሪ ለአንድ ተማሪ በሚል መሪ ሃሳብ ባለፉት አምስት ዓመታት በየዓመቱ ለ500 ተማሪዎች ዓመቱን ሙሉ የሚማሩበትን የትምህርት ቁሳቁሶችን በማሟላት እያስተማርን ነው። በየዓመቱ የአረጋውያንን ቤት እናድሳለን። በየሦስት ወሩ ደም እንለግሳለን። በድሬዳዋ ደም የሚለግስ ብቸኛው ማኅበር የኛ ነው። ከተደራጀን አምስተኛ ዓመታችንን ይዘናል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ለ15ኛ ጊዜ ደም ለግሰናል። በተጨማሪም መንግሥት ወይም ሀገር በጠራችን ጊዜ ሁሉ በአቅማችን መልስ እንሰጣለን። እያንዳንዳችን እስከ ሁለት ሺህ ብር በማዋጣት በሁለት ዙር ቦንዶች ገዝተናል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የጻፉትን የመደመር ትውልድ መጽሐፍ በመግዛት ድሬዳዋ ላይ እየተገነባ ላለው ትልቅ ቤተ መጽሐፍት እንዲውል የበኩላችንን ዐሻራ አሳርፈናል። በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ጦርነት በነበረ ጊዜም በከተማው ከሚገኙ ሌሎች ታክሲዎች ጋር በመተባበር ከሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር የሚበልጥ ገንዘብ አበርክተናል። በቅርቡ አምስት መቶ ሺህ ብር አዋጥተን ለሁለት መቶ አረጋውያን የጤና መድኅን ክፍያ ፈጽመንላቸዋል ሲልም ማኅበራቸው የሚሠራቸውን በጎ ሥራዎች ይዘረዝራል።
አያይዞም የኦርቶዶክስ፣ የእስልምና እና የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ትልልቅ በዓላት በሚኖሩበት ጊዜ እየወጣን ነፃ አገልግሎት እንሰጣለን። እንደዚሁም ድሬዳዋ የብሔር ብሔረሰብ ቀንን የመሰሉ ትልልቅ ሀገራዊ በዓላትን ስታከብር ከሌላ ክልል የሚመጡ እግዶችን በነፃ እናጓጉዛለን ይላል።
ድሬዳዋ ላይ በማታ አገልግሎት በምንሰጥበት ሰዓት ምንም አይነት ዕቃ ባጃጅ ላይ ቢረሳ በሥነሥርዓት ለባለቤቱ እንዲደርስ እናደርጋለን የሚለው የማኅበሩ ሊቀመንበር፤ እንደ ማሳያ በቅርቡ በተለያዩ የዜና ማሰራጫዎች መቶ ሃምሳ ሺህ ብር ተረስቶ የተመለሰበትን ዜና ያስታውሳል። ባጃጅ ላይ የተረሱ ቼኮች፣ ዶክመንቶች እና የተለያዩ የሽያጭና የግዢ ሰነዶች፣ ብዙ ስማርት ፎኖች፣ ላፕቶፖች እና ሌሎች ነገሮች ለባለቤቶቻቸው እንዲደርሱ ማድረጋቸውንም ይገልጻል።
የሌሊት ባጃጅ አሽከርካሪ ማኅበር አባላትም ተጠቃሚ መሆናቸውን የሚያነሳው ወጣት ቃልኪዳን፤ እኛም በመደራጀታችን ተጠቃሚ ሆነናል። ከዚህ ቀደም አብዛኞቻችን የሰው ሦስት እግር ባጃጅ ነበር የምናሽከረክረው። የድሬዳዋ ከንቲባ እና የፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ባደረጉልን ድጋፍ ከድሬዳዋ ማይክሮ ፋይናንስ ጋር በመተባበር የባጃጅ ባለቤት እንድንሆን አድርገውናል። ፍቃድ የሚሰጠው ለባለንብረቶች እንጂ ለአሽከርካሪዎች ስላልነበር ስንደራጅ ችግር ገጥሞን የነበረ ቢሆንም የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች ችግሩን ፈተውልን ሞዴል ወጣቶች እንድንሆን አድርገዋል ነው የሚለው።
እርስ በርስ ያላቸው ግንኙነት በጣም ጠንካራ መሆኑን ሲያመላክትም፤ 50 እና 60 ዓመታት የቆየ እድር እንኳን እንደ እኛ አይደጋገፍም። ባጃጅ ለተቃጠለባቸው አሁን መካከላችን ለሚገኙ አባሎቻችን አዲስ ገዝተን ሰጥተናል። በሞት ለተለዩን አባሎቻችን ቤተሰቦችም ተለቅ ተለቅ ያሉ ድጋፎችን እናደርጋለን። በኅዘን በደስታ እርስ በርስ እንደራረሳለን ብሏል።
ቃልኪዳን ድሬዳዋ በሌሊት ደኅንነቷ እንዲጠበቅ የእኛ መኖር አስፈላጊ ሆኗል። ድሬዳዋ ላይ ወንዱም ሴቱም ሌሊት ወጥቶ ያለስጋት ተዝናንቶ በሰላም መግባት የሚችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህ ደግሞ የከተማዋ አመራር እና የእኛ ሥራ ነው ብዬ አስባለሁ ሲል አስተያየቱን ይቋጫል።
የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር ማኦ ተሾመ በበኩላቸው፤ ወጣቶቹ በከተማችን ፀጥታና ሰላም ላይ ያላቸው አስተዋፅዖ እነርሱ ከሚናገሩት በላይ ነው። ዜጎች የማይሳተፉበት የፀጥታ ሥራ ውጤታማ ሊሆን አይችልም። መደበኛ ሥራቸውን ይሠራሉ ከሥራቸው ጎን ለጎን ደግሞ እያንዳንዷ የድሬዳዋ ጥግ ላይ የሚፈጸመውን ነገር ፊትለፊት ተጋፍጠው ይከላከላሉ ነው የሚሉት።
በቅርብ ጊዜ ተፈጥሯል ያሉትን አንድ ምሳሌ በመጥቀስም፤ አንድ የፀጥታ አካል መሣሪያውን ከካምፕ አውጥቶ ደብቆ ለማምለጥ ሲሞክር ባጃጅ ላይ ይሳፈራል። የባጃጅ አሽከርካሪው የተሸፈነውን እቃ ሲመለከት ይሄ ነገር መሣሪያ ሊሆን ይችላል ብሎ ተጠራጥሮ ወስዶ ፖሊስ ጣቢያ ላይ አዙሮ ለፖሊስ ያስረከበበት ሁኔታ አለ። ይሄ የመንግሥትን ንብረት መከላከል ብቻ ሳይሆን በመሣሪያው ወንጀል እንዳይፈጸምበት ወይም ፀረ-ሰላም ኃይሎች እጅ እንዳይደርስ ማድረግ ነው። በቀጥታ ወንጀልን ከመከላከል በተጨማሪ ሁሉም ሞባይላቸው ላይ በተጫነላቸው ጥቆማ የሚሰጡበት መተግበሪያ አማካኝነት በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ የሚያዩትን ነገር በምስል፣ በድምፅና በጽሑፍ ወደ እኛ ይልካሉ። በአጠቃላይ ለድሬዳዋ ሰላም የአንበሳውን ድርሻ እየተጫወቱ ነው ብለዋል።
የትራፊክ ኃላፊዋ ዋና ኢንስፔክተር ሰዓዳ ተሰማ የአሽከርካሪ ማኅበሩ አባላት በየትኛውም የድሬዳዋ ከተማ ጫፍ የትራፊክ አደጋ ሲደርስ ለእኛ ሪፖርት ያደርጉልናል። የትራፊክ አደጋ ኃላፊ ሆኜ በሠራሁባቸው ጊዜያት 500ዎቹ የማኅበሩ አባላት የትራፊክ አደጋ አድርሰው አያውቁም፤ በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናቸው እወዳለሁ። እነሱ በመኖራቸው ማንም ሰው ከተማዋ ውስጥ ወንጀል ፈጽሞ የሚያመልጥበት ሁኔታ የለም ሲሉ ወጣቶቹን ያመሰግናሉ።
ዋና ኢንስፔክተር ጌትነት ዳባ የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ትራፊክ ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት የቁጥጥርና ሕግ ማስከበር ዲቪዥን ኃላፊ ናቸው። እርሳቸው እንደሚናገሩት 500ዎቹ የባጃጅ ሹፌሮች ሁልጊዜ ከቀኑ 11 ሰዓት በድሬዳዋ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን ጠቅላይ መምሪያ መጥተው ባለፈው 24 ሰዓት ውስጥ ያጋጠማቸው ችግር ወይም የተለየ ነገር ካለ መረጃ እንለዋወጣለን። ከወቅቱ ጋር የተያያዙ የተለያዩ የትራፊክ እና የፀጥታ ጉዳዮችን የተመለከቱ መረጃዎችም እንዲያገኙ ይደረጋል።
ዛሬ አንድ የማኅበሩ አባል የሆነ አንድ አሽከርካሪ ሕገወጥ ስደተኞችን ይዞ የሚንቀሳቀስ መኪና ተመልክቶ ባደረገው ጥቆማ አስኮብላዩን ጨምሮ እጅ ከፍንጅ ይዘን ወደጣቢያ የላክንበት ሁኔታ አለ። ወጣቶቹ የትኛውም ቦታ ላይ የሚያዩትን ወንጀል ነክ ነገር እና ማኅበራዊ ቀውስ የሚያመጡ ችግሮች በቶሎ እንዲቀርፉ ለማድረግ የበኩላውን የዜግነት ግዴታቸውን እየተወጡ ያሉ እጅግ መልካም ወጣቶች ናቸው ሲሉም ያክላሉ።
የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የመንገድ ላይ ትራፊክ ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት በየጊዜው ለሌሊት የባጃጅ አሽከርካሪዎች በሙያዊ ሥነ-ምግባር ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ይሰጣል። ለወጣቶቹ በመልካም ሥነ-ምግባር አገልጋይነት ስሜት ሕገ-ወጥ ተግባራትን በመከላከል የሌሊት ባጃጅ አሽከርካሪዎች ሚና ጉልህ መሆኑ ተደጋግሞ ይነገራቸዋል።
የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በስድስት ወር አንድ ጊዜ የሚካሄድ ነው። በውይይት መድረኩ ላይ ከፌደራል ትራንስፖርት ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የድሬዳዋ ከተማ የሁሉም ፖሊስ ጣቢያ አዛዦች እና 500ዎቹ የሆኑ የሌሊት ባጃጅ አሽከርካሪዎች በሙሉ ተሳታፊ ይሆናሉ።
በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ የሚሳተፉት የባጃጅ አሽከርካሪዎች በሥልጠና መድረኩ ደስተኛ መሆናቸውን ይናገራሉ። በመድረኩ በሥራቸው ላይ በሚያጋጥማቸው ችግሮች ዙሪያ ከጣቢያ አመራሮች ጋር ሰፊ የሆነ ውይይቶች ካካሄዱ በኋላ አመራሮች በመድረኩ ያገኙትን መረጃ በግብዓትነት በመጠቀም የመፍትሔ ርምጃ እንደሚወስዱ በመግለጽ የጋራ ግንኙነት ጭምር የሚደረግበትን መድረክ መፍትሔ ማግኛ አድርገው ጭምር እንደሚገለገሉበት ነው የሚጠቅሱት።
የድሬዳዋ የሌሊት የታክሲ ሹፌሮች ማኅበር የተመሠረተበት አምስተኛ ዓመት ሰኔ 17 ቀን 2017 ዓ.ም በደማቅ ሥነሥርዓት ተከብሯል። የሌሊት የታክሲ አገልግሎት ሰጪ አሽከርካሪዎች ማኅበር ባዘጋጀው መርሐ ግብር ከድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ጋር በመተባበር የማኅበሩን አምስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ባዘጋጀው በዚህ የምስጋናና እውቅና መርሐ ግብር ደማቅ ዐሻራውን ዘክሯል።
በመድረኩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ክቡር ኮሚሽነር ዓለሙ መግራ፤ ባለፋት አምስት ዓመታት ውስጥ የሌሊት ታክሲ አሽከርካሪዎች ከትራንስፖርት አገልግሎት ባለፈ ለከተማዋ ሰላም መረጋገጥ በቁርጠኝነት ሠርተዋል ብለዋል። ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላት ሲከበሩ ነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት ከመስጠት ጀምሮ በከተማዋ በሚካሄዱ የተለያዩ ማኅበራዊ አገልግሎቶች ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ የጎላ መሆኑን ጠቁመው፣ በፅዳት ዘመቻዎች፣ በደም ልገሳና በተለያዩ በጎ ፍቃድ ሥራዎች እያደረጋችሁ ላለው አርዓያነት ያለው ተግባር ምስጋና ይገባችኋል በማለት የወጣቶቹን አስተዋፅዖ እንደሚያደንቁ ተናግረዋል ::
ኮሚሽነር በቀጣይም ለከተማዋ ሁለንተናዊ ሰላምና ኢኮኖሚያዊ እድገቶች መረጋገጥ ከከፋፋይ ሃሳቦችና የጥፋት ተግባራት እራሳችሁን በማራቅና ከተማችሁን ከዚህ ዓይነት እኩይ ተግባር በመጠበቅ ይበልጥ ኃላፊነታችሁን መወጣት ይኖርባችኋል ሲሉ የአደራ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ም/ኮሚሽነር ጉሌድ ድርዬ በበኩላቸው፤ የሌሊት ታክሲ አሽከርካሪዎች ከፖሊስ ጋር ተቀናጅቶ በመሥራትና የከተማዋን ሰላም በመጠበቅ ረገድ እያበረከቱት ያለው አስተዋፅዖ ከፍተኛ መሆኑን አንስተው፣ ይሄው ቅንጅታዊ አብሮነት ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ነው ያሉት::
የሌሊት ታክሲዎች ማኅበር ሰብሳቢ ወጣት ቃልኪዳን ፀሐይ በበኩሉ ማኅበራቸው በስሩ ያሉትን ወጣቶች እንደ ማኅበር ተጠቃሚ ከማድረግ በዘለለ ማኅበራዊ ተሳትፎን እንደዋና ተግባሩ በማድረግ ሰፊ ሥራዎችን መሥራቱን እና በቀጣይም መሰል ተግባራትን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግሯል። ለዚህ ተግባራቸው መሳካትም የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ እና የድሬዳዋ አስተዳደር ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ባለሥልጣን እንዲሁም ባለሀብቶች እና ግለሰቦች ሰፊ ድርሻ እንደነበራቸው ጠቁሞ፣ የምስጋና መድረኩ የተሰናዳበት አንዱ ዓላማ እነዚህን አካላት ለማመስገን ጭምር መሆኑን ገልጿል።
በእዚሁ የሌሊት የታክሲ አገልግሎት ሰጪ አሽከርካሪዎች ማኅበር ባዘጋጀው መርሐ ግብር ላይ ለማኅበሩ እንቅስቃሴ እገዛና ድጋፍ ላደረጉ ግለሰቦች ተቋማትና ድርጅቶች የምስጋናና መታሰቢያ ስጦታ ተበርክቷል። በፕሮግራሙ ላይ ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በከፍተኛ ውጤት ለተመረቁ የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለክቡር ኮሚሽነር ዓለሙ መግራ እና ለምክትል ኮሚሽነሮች የእንኳን ደስ አላችሁ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም