የሎጂስቲክስ ዘርፍን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የሚስተዋሉ ችግሮችን መፍታት ይገባል

አዲስ አበባ፡የሎጂስቲክስ ዘርፉን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት እንደሚገባ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) አሳሰቡ፡፡ በባሕር ትራንስፖርት በኩል የተደራሽነት፣ የፕሮግራም አለመጣጣም እና የዋጋ ውድነት ችግር መኖሩም ተመልክቷል፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው በዘርፉ ከተሠማሩ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመሆን የኢትዮጵያን መርከቦች ተጠቅሞ ዕቃዎችን በማጓጓዝ ሂደት ያሉት ክፍተቶች ምንድን ናቸው በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ ትናንት ከአስመጪና ላኪዎች ጋር ውይይት ሲካሄድ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው፡፡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በአዋጅ ሥልጣን እንደተረከበ አካል በሎጂስቲክስ ዘርፉ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ተወዳዳሪ ለማድረግ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

እንደ ዜጋም እንደ ተቋምም የሀገርን ጥቅም የማስጠበቅ ግዴታ አለብን ያሉት ሚኒስትሩ፤ ኢንዱ

ስትሪው የማጓጓዝ አቅሙ በመቀነሱ ምክንያት የመወዳደር አቅሙ እንዳይወድቅ፤ እንዲሁም ለሀገር ኢኮኖሚ ማበርከት ያለበትን አስተዋጽኦ እንዲያ በረክት ያለውን ችግር መፍታት ያስፈልጋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ችግሮቹን ለመፍታትም ሦስት ነገሮች ላይ መሥራት ተገቢ መሆኑን በማንሳት፤ የመጀመሪው ጊዜ መሆኑን አመልክተው፤ የማጓጓዥ ጊዜ በረዘመ ቁጥር የሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰው ጫና ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል አስመጪና ላኪዎች ለማጓጓዝ በሚፈልጉት ጊዜ የገበያን ፍላጎት አይቶ በጠየቁት ጊዜ መጫን እንደሚገባ አመልክተው፤ ከአሠራር ጋር ተያይዞ መመላለስ እንዳይኖር ደንበኞች ባሉበት ሆነው መረጃ የሚያገኙበትን መንገድ መዘርጋት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ሁለተኛው የዋጋ ጉዳይ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ የዋጋ መጨመር ከምርቶች ተወዳዳሪነት አንጻር ተጽዕኖ ስለሚያሳድር አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳለ እና እንደሌለ ማጣራት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ከተደራሽነት አንጻር ፍላጎትን መሠረት አድርጎ መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ያሏት መርከቦች 10 ብቻ መሆናቸውን የገለጹት የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር)፤ ከእዚህም መካከል ከፍተኛ የመጫን አቅም ያላቸው ሁለቱ ብቻ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የመርከብ ብዛት ለመጨመር ስድስት መርከቦች የታዘዙበት ሁኔታ ስላለ እነሱ ሲጨመሩ የመዘግየት እና የመዳረሻ ውስንነት ችግር ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸውም አስገንዝበዋል፡፡

ከአሠራር ጋር ተያይዞ አሁን ላይ ኋላ ቀር አሠራር መኖሩን በማመን ይህን ችግር በመፍታት ደንበኞች ባሉበት ሆነው መረጃ እንዲደርሳቸው ለማድረግ የሚያስችል አሠራር እየተዘረጋ እንደሚገኝ ጠቁመው፤አዲሱ አሠራርም በአንድ ወር ውስጥ ወደ ሥራ ይገባል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የዋጋ ውድነት ላይ በርካታ ቅሬታዎች ለተቋሙ መቅረቡን ተከትሎ ማሻሻያ መደረጉን በማንሳት፤ ድርጅቱ ለኮንቲነር ምንም ዓይነት ዋስትና ሳይጠይቅ እያቀረበ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የመዳረሻ ውስንነት፣ የዋጋ ውድነት፣ የማጓጓዣ ጊዜ መዘግየት፣ ድርጅቱ በወር አንዴ ወይም ሁለቴ የሚያጓጉዝ በመሆኑ በተፈለገው ጊዜ ለማጓጓዝ አለመቻል፣ እንዲሁም ከደረቅ ወደብ የሚጭኑ መኪናዎች ጥራታቸውን የጠበቁ አለመሆን ከአስመጪና ላኪ ድርጅቶች እንደችግር ተነስቷል፡፡

በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ፣ የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስ ቲክስ አገልግሎት ድርጅት፣ መሪታይም ባለሥልጣን የበላይ አመራሮች እና የተለያዩ አስመጪና ላኪ ድርጅቶች ተወካዮች መገኘታቸው ታውቋል።

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You