
-የደንብ መተላለፍ 69 በመቶ ቀንሷል
አዲስ አበባ፡– ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ጥፋቶችን መቆጣጠር በሚያስችል ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ሥራውን ሊያከናውን መሆኑን የአዲስ አበባ የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ገለጸ።በከተማዋ ይታይ የነበረው የደንብ መተላለፍ 69 ነጥብ ስምንት በመቶ ቀንሷል ተብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ እንደገለጹት፤ በዘርፉ የሠለጠኑ ባለሙያዎችን እና አስፈላጊውን መሣሪያ በመጠቀም በ2018 ዓ.ም የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ሥራ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ቁጥጥር የሚያደርግ ይሆናል።ይህም በከተማዋ ውስጥ የሚታዩ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ እንዲቀረፉ ያደርጋል ብለዋል።
እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፤ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በተደረገ ጥናት የደንብ ማስከበር ባለሙያዎች እንዲሠለጥኑ ተደርጓል።ባለሙያዎቹ በየዘርፉ የሰለጠኑ ሲሆኑ የትምህርት ደረጃቸውም ከዲግሪ በላይ ነው።ሠልጥነው የተመረቁት በምህንድስና ፣ በጤና ፣ በኮምፒውተር እና በመሰል ዘርፎች የሠለጠኑት ባለሙያዎች ለመሬት ቁጥጥር፣ ለጤና ቁጥጥር፣ ለሕግ መተላለፍ ቁጥጥር እውቀት ያላቸው ናቸው፤ አሠራሩም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ይሆናል ብለዋል።
ለቴክኖሎጂው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለማሟላት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቃል መግባቱንም ተናግረዋል።
እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፤ በ2017 ዓ.ም በተደረገው የደንብ ማስከበር ሥራ ከስድስት ሺህ በላይ በሚሆኑ ቦታዎች 11 ሚሊዮን ካሬ ሜትር መሬት ወደ መሬት ባንክ ገብቷል።መሬቶቹ በደንብ ማስከበር ባለሥልጣን እየተጠበቁ ሲሆን፤ ለተለያዩ የመሠረተ ልማቶች እያገለገሉ እና ለሊዝ ሽያጭ እየቀረቡ ይገኛሉ።
ሕገ ወጥ ግንባታ እና የመሬት ማስፋፋት ጥፋቶችን ከማስቀረት ባሻገር፣ የጎዳና ላይ ንግዶችን እና በየሰፈሩ የሚደረጉ ሕገ ወጥ የእንስሳት እርዶችን ማስቀረት ተችሏል ብለዋል።እነዚህ ሥራዎች የተሠሩትም ከ27 የሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመሆን ነው ብለዋል።
“ሁለት ሺህ 74 ባለሙያዎች ሠልጥነው ወደ ሥራ ገብተዋል” ያሉት ሻለቃ ዘሪሁን፤ በተለይም ለሰው ልጅ ጤና የሆነውን የአካባቢ ብክለት ለማስቀረት የወንዞች ዳርቻ ጽዳት እና ልማት እየተሠራ ነው ብለዋል።በወንዞች ዳርቻ ቆሻሻ በሚጥሉ እና በካይ ፍሳሾችን ወደ ወንዞች በሚለቁ አካላት ላይ ርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል። ይህም ከአካባቢ ጥበቃ እና ከአረንጓዴ ልማት ተቋማት ጋር በጥምረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፤ በቅርቡ በተጀመረው አሠራር በአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ ንግድ ቤቶች እስከ ምሽት አራት ሰዓት እንዲሠሩ በመደረጉ የደንብ ማስከበር ሥራ እንዲኖር አድርጓል። ባለሥልጣኑም ደንብ ከማስከበር ባሻገር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየሠራ ይገኛል።ይህም የአፍሪካና የዓለም ማህበረሰብ መገኛ የሆነችው አዲስ አበባ ደረጃዋን የጠበቀች እንድትሆን እና ኅብረተሰቡም እስከ ምሽት አራት ሰዓት ድረስ አገልግሎት እንዲያገኝ ያደርጋል ብለዋል።
እንደ ሻለቃ ዘሪሁን ማብራሪያ፤ ባለሥልጣኑ ደንብ ከተላለፉ ግለሰቦች፣ የግል ድርጅቶችና የመንግሥት ተቋማት ጭምር 397 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር ቅጣት ሰብስቧል፤ ቅጣቱን ለከተማ አስተዳደሩ ገቢ ያደረገ ሲሆን፤ ከቅጣቱ የተገኘው ገቢ ደንብ የተላለፉ አካላት ያበላሹትን ልማት ለመሥራትና ለማስተካከል የሚውል ነው ብለዋል።በቁጥጥር ከተገኙ ጥፋቶች ውስጥ በአሻጥር የተደበቁ የነዳጅ ቱቦዎችም እንደተገኙ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን በ2005 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 37/2005 እና በደንብ ቁጥር 54/2005 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ተብሎ የተዋቀረ መሆኑ ይታወሳል።ተቋሙ የአደረጃጀት ማሻሻያ በማድረግ በደንብ ቁጥር 150/2015 የተቋቋመ ሲሆን፤ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን እና አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በጋራ ደንብ ቁጥር 180/2017 ሆነው በመሥራት ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም