የኦሊምፒክ ለዛና ውበት በመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች

በኦሊምፒክና በመላ አፍሪካ ጨዋታዎች መርህና ፅንሰ ሃሳብ መሠረት የሚካሄደው መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ለዘጠኝ ዓመት ተቋርጦ ዘንድሮ በአዲስ መልኩ በጅማ 4500 ስፖርተኞችን በማሳተፍ ትናንት ተጠናቋል።

በ26 የስፖርት አይነቶች በተደረጉ ፉክክሮች ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ መግባት ችለዋል። ከሦስት ክልሎች በስተቀር ሌሎቹ አንድና ከአንድ በላይ የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘት የቻሉበትም ሆኗል። በበርካታ የስፖርት አይነቶችም የትኛው ክልል/ አካባቢ በየትኛው የስፖርት አይነት እምቅ አቅም እንዳለው የታየበት ሆኖ አልፏል።

ኦሮሚያ ክልል በኦሊምፒክና የኦሊምፒክ ባልሆኑ ስፖርቶች በአጠቃላይ 88 ወርቅ፣ 81 ብር፣ 55 ነሐስ በመሰብሰብ የውድድሩ አሸናፊ ሆኗል። በሁለቱም ፆታ በእግር ኳስ ብቻ ያልተሳተፈው አዲስ አበባ ከተማ በበርካታ የስፖርት አይነቶች ብርቱ ተፎካካሪ በመሆን በአጠቃላይ 84 ወርቅ፣ 67 ብር፣ 70 ነሐስ በማስመዝገብ ሁለተኛ ነው። ሌላኛው ጠንካራ ተፎካካሪና በተለይም በውሃ ዋና ስፖርቶች በርካታ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ጠቅልሎ የወሰደው አማራ ክልል በአጠቃላይ 46 ወርቅ፣ 46 ብር፣ 51 ነሐስ በመሰብሰብ ሦስተኛ ሆኖ ፈፅሟል።

በውድድሩ የመዝጊያ ሥነሥርዓት ኦሮሚያ ከደቡብ ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው የእግር ኳስ የፍፃሜ ጨዋታ ኦሮሚያ በወንድም በሴትም በማሸነፍ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል። የመዝጊያ መርሃግብሩ ልክ እንደመክፈቻው ሁሉ በተለያዩ ውብ ትርዒቶች የታጀበ፣ የኦሊምፒክ ለዛና ውበት የታየበት ሲሆን፣ የውድድሩን መሪ ቃል “ስፖርት ለህብር ኢትዮጵያ አርበኝነት” ለማንፀባረቅ ጥረት የተደረገበት ሆኖ ታይቷል።

በየውድድር አይነቱ ድንቅ ፉክክሮች በስፖርታዊ ጨዋነት ታጅበው ፍፃሜ ሲያገኙ፣ የጅማ ዩኒቨርሲቲ የተሟሉ የስፖርት መሠረተ ልማቶች ውድድሮችን በብቃት አስተናግደዋል። የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ማደሪያም ሁሉንም ተሳታፊዎች እንደ አንድ የኦሊምፒክ መንደር በአንድ ጥላ ስር በማሰባሰብ የአስሩን ቀን ቆይታ የተለየና ተናፋቂ አድርገውታል። በነዚህ ቀናት ውድድሩ ከሁሉም አካባቢዎች የመጡ ኢትዮጵያውያን በኦሊምፒክ መንፈስ ባህል፣ እሴት፣ ልምድና ተሞክሮ እንዲለዋወጡ እድል ፈጥሯል። አዘጋጇ ጅማም የኦሊምፒክ ለዛና ጣዕም በተላበሰ ድባብ ድግሷን አገባዳ ለቀጣዩ የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች አስተናጋጅ ትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ችቦውን አስረክባለች።

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር 7ኛውን መላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች የማዘጋጀት ፍላጎት እንዲያሳውቁ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት የትግራይ ክልል በደብዳቤ ምላሽ የሰጠ ሲሆን ከሰላምና ፀጥታ፣ ከማረፊያ ቦታ፣ ትራንስፖርት እና መወዳደሪያ ስፍራዎች አኳያ በቀጣይ ዓመታት አስፈላጊውን ዝግጅት እንደሚያደርግ የክልሉ ልዑክ ቡድን ከትናንት በስቲያ ምሽት ገለፃ አድርጓል። ገለፃውን ተከትሎም 10 ክልሎች እና 1 ከተማ አስተዳደር ድምፅ ሰጥተው ትግራይ ክልል በሙሉ ድምፅ 7ኛው የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች አዘጋጅ ሆኖ መመረጡ ታውቋል።

ከዘጠኝ ዓመት በፊት 6ኛው የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች አዘጋጅ የነበረው ትግራይ ክልል በተለያዩ ምክንያቶች ውድድሩ ተሰርዞ ዘንድሮ በመቆየቱና ከነበረው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ወደ ኦሮሚያ ክልል መቀየሩን ያስታወሱት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሐመድ፤ “7ኛው የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች የማዘጋጀት ፍላጎት አሳይታችሁ በመመረጣችሁ እንኳን ደስ አላችሁ፣ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ከተማ ከተደረገው 6ኛው የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ተሞክሮን ወስዳችሁ ጥሩ ዝግጅት እንደምታደርጉም አምናለሁ” ብለዋል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You