የዜግነት አገልግሎት – በገዳ ሥርዓት የማኅበራዊ እሴት ቅኝት

ወይዘሮ ጠጅቱ አረዶ ይባላሉ፤ በኦሮሚያ ክልል የባቱ ከተማ ነዋሪ ናቸው። እድሜያቸው ከዘጠና አልፎ ወደ መቶ የተጠጋ የእድሜ ባለጠጋ ሲሆኑ፣ ድንገት ለተመለከታቸው ከደሳሳ ጎጇቸው ደጃፍ ላይ ከወንበር ላይ ቁጭ ብለው የማለዳዋን ፀሐይ የሚሞቁ ይመስላሉ። አዛውንቷ ግን ዓይናቸውም ሀሳባቸውም ያለው አንዲት ቤት እየቀየሱ ባሉ ወጣቶች ላይ ነው።

ወጣቶቹን በተቀመጡባት መቀመጫ የተማመኑ በማይመስል መልኩ ምርኩዛቸውን ደገፍ ብለው አሻግረው በዓይናቸው ይቃኙዋቸዋል። ወይዘሮዋ ለልጅ ያልታደሉ መሃን ናቸውና ‹‹የኔንም ቤት በነካ እጃችሁ›› የሚሉ ይመስላሉ።

ዛሬ በጡረታ ዘመናቸው በልጅ እጅ ሆነው ለመጦር ያልታደሉት ወይዘሮ ጠጅቱ፣ እድሜ ለባቱ ከተማ አስተዳደር በሰጣቸው አንዲት ደሳሳ የጭቃ ቤት ውስጥ ይኖራሉ። የቅርብ በሚሏቸው ቤተሰቦችና በአካባቢው ሕብረተሰብ እየታገዙም ዛሬን በተስፋ ያድራሉ። አጋዦቻቸውንም ፈጣሪያቸውንም እያመሰገኑም ይኖራሉ።

ኑሮ ግን እንዲህ ቀላል አልሆነላቸውም። በተለይ ክረምት በመጣ ቁጥር ብርድና ዝናቡ እጅጉን ይፈትናቸዋል። ሆኖም ትንሽም ቢሆን ሃሳብና ጭንቀታቸው የሚቀንሰው ለዓመታት ክረምት በመጣ ቁጥር ወጣቶች እየተባበሩ ጎጇቸውን እየጠገኑላቸው መቆየታቸው ነው። ዛሬ ደግሞ ያው ሀሳብና ጭንቀታቸው ተመልሶ መጥቷል። ምክንያቱም መጪው የክረምት ወቅት ነው። እናም ከወዲሁ የክረምቱ መግባት ከባድ ሃሳብ ጥሎባቸዋል።

የዘንድሮውን ክረምትም አዛውንቷ በብዙ ፈርተውታል። ምክንያቱም ቤታቸው ከመዝመም አልፋ ወደ መውደቁ ተቃርባለች። በዚህ ቁመናዋ ላይ ዝናብ ከታከለባት ደግሞ መውደቋ የግድ ነው። እንደ ቀድሞው ለዝናብና ብርድ አጋልጣ አትሰጠኝም ብለው አያስቡም። ይልቁንም አንድ ቀን በተኙበት ላያቸው ላይ እንደምትፈርስባቸው አምነዋል።

ዛሬ ጎጇቸው ደጃፍ ላይ በወንበራቸውም፣ በምርኩዛቸውም ላይ አረፍ ብለው አሻግረው በወጣቶቹ ላይ ዐይናቸውን መጣላቸው ከዘመመች ጎጆ የመውጣት ተስፋን አብዝቶ መሻታቸውም ነው። ይህ ፍላጎታቸው ግን መና አልቀረም። የሚያያቸውን አካል ላከላቸው። ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ሴቶችና ሕጻናት ቢሮ አስተባባሪነት የሚከናወነው የክረምት የዜግነት አገልግሎት መርሃ ግብርም ለእርሳቸው ተስፋ የሰጣቸው ሆኗል። የተመኙት ቤት በአዲስ መልኩ ለመገንባት ሥራው ተጀምሯል።

የእርሳቸው እድሜ ሲገፋ፣ አቅማቸው ሲደክም እና ጆሯቸውም እንደልብ አልሰማ ሲላቸው፤ ቤታቸውም አብራ ደክማ ለብርድም፣ ለዝናብም እያጋለጠቻቸው ከፍ ያለ ጭንቀትና ችግር ውስጥ ገብተዋል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ አዲስ ቤት ተገንብቶ ሊሰጣቸው መሆኑን ሲሰሙ ማመን አልቻሉም።

በዚህ ደስታ ውስጥ እያሉም “ዛሬ ለእኔ ያ የጨለማ ዘመን አልፎ ብርሃን ወጣልኝ፤ በእርጅናዬም አንደገና ተወለድኩ፤ ይሄን መሰል በጎነት በልባቸው አድሮ ቤቴን ለሚሰሩ ፈጣሪ ይባርካቸው፤ እኔም እድሜ ሰጥቶኝ በቤቱ ለመኖር ያብቃኝ፤” ሲሉም ምኞትና ፍላጎታቸውን ለታዳሚው አጋርተዋል።

እንደ ወይዘሮ ጠጂቱ ሁሉ አቶ ገመቹ ፎዬ እና ወይዘሮ ጫልቱ ቴሶ፣ ትዳራቸው በአራት ልጆች የተባረከ ጥንዶች ናቸው። ይሁን እንጂ በልጅ የተባረከው ትዳራቸው በኢኮኖሚው የቀጠለ አይደለም። ከእጅ ወዳፍ በሆነ ሕይወት በእጅጉ ይፈተናሉ።

በጎልማሳነት እድሜ ላይ የሚገኙት እነዚህ ጥንዶች፤ ከአራት ልጆቻቸው ጋር በአንዲት ክፍል ያውም ጣራዋ በቅጡ ባልተደራጀ ሳርና ላስቲክ በተሸፈነ ቤት ውስጥ ይኖራሉ። የራሳቸውንም ሆነ የልጆቻቸውን ልብስና ጉርስ ለመሸፈን የቀን ሥራም ሆነ ሌላ ያገኙትን ሥራ ሠርተው ያድራሉ።

በአንዲት ክፍል ያውም ከፀሐይ እንጂ ከዝናብና ብርድ የማታድን ቤት ውስጥ አራት ልጆችን ይዞ መኖራቸው ሕይወታቸውን እጅጉን ከባድ እንዳደረገባቸው የሚናገሩት ጥንዶቹ፤ ይህችን ቤት ለማደስም ሆነ በሌላ ለመተካት የሚሆን አቅም በማጣታቸው ምክንያት ክረምት በመጣ ቁጥር ኑሯቸው ከድጡ ወደ ማጡ እንደሚሆንባቸው ያስረዳሉ። በክልሉ ሴቶችና ሕጻናት ቢሮ አስተባባሪነት በተጀመረው የክረምት የዜግነት አገልግሎት መርሃ ግብርም አንዱ የእነርሱ ቤት እድሳት መሆኑ እንዳስደሰታቸው ይገልጻሉ።

አቶ ገመቹ እና ባለቤታቸው፤ በማይበርድና በማያፈስ ቤት ውስጥ ኖረው ክረምትን እንዲያሳልፉ እድል ለፈጠሩላቸውና ይሄን ላደረጉላቸው ሁሉ ምስጋናቸውን ይቸራሉ። ይሄን መሰሉ የተቸገሩ እና አቅመ ደካማ የሆኑ ወገኖችን ችግር መጋራትና ማቃለል ከፍ ያለ የልብ ቅንነትን፤ የሰብዓዊ ስሪትን ይፈልጋል። ከዚህ አንጻርም እንደ ሀገር በዚህ መልኩ መሠራቱ እጅጉን የሚያስደስት እንደሆነም አስረድተዋል። በእርግጥ የዜግነት አገልግሎት ጉዳይ ዛሬ የተጀመረ አይደለም። ድሮም ቢሆን በሀገራዊ እሴቶቻችን በተለያየ መልኩ ሲከወን የቆየ ነው። እንደ ኦሮምያ ክልል ብቻ ብናነሳው የኦሮሞ ሕዝብ ማንነት ውጤት የሆነው የገዳ ሥርዓት አንዱ ማሳያ ነው።

የገዳ ሥርዓት በርካታ ማኅበራዊ ስሪቶችና እሴቶች ያሉት፣ የመደጋገፍ ልዕልና ከፍ ብሎ የሚገለጽበት ሥርዓት ነው። በዚህ ሥርዓት ውስጥ አይደለም ሰው ለሰው፤ ሰው ለእንስሳትና ለእጽዋት ከፍ ያለ ርህራሄን ያሳያል። ለሚራራለትም ነገር ጥበቃና ከለላ ያደርጋል። ይሄ ማኅበራዊ እሴት ታዲያ ሕዝባዊ መሰረት ያለውና በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ እንደየአውዱ የሚገለጥ ቢሆንም በተቀናጀና ተቋማዊ በሆነ መልኩ ተሰርቶበታል ለማለት ያስቸግራል።

በሀገር ደረጃ ይሄ የበጎነት ሥራ፣ የመተጋገዝና የመተሳሰብ እሴት፤ ባልተቆራረጠና በተደራጀ መልኩ ከፍ ብሎ ሊሄድ የተገባው፤ ተቋምና አደረጃጀት ተፈጥሮለትም ለሁሉም የሰው ልጆች በሚደርስ መልኩ ሊተገበር የግድ ነው። ከዚህ አንጻርም እንደ ኦሮምያ ክልል በጨፌ ኦሮሚያም በአዋጅ ፀድቆ በሕግና በአሰራር ታግዞ እንዲተገበር በ2011 ዓ.ም ተወስኗል። በ2012 ዓ.ም የዜግነት አገልግሎት በክልል ደረጃ ይፋ ተደርጎ ወደ ሥራ ተገብቶበታል።

ይሄን ሁነትና ሂደት በተመለከተ የኦሮሚያ ክልል ገንዘብ ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የዜግነት አገልግሎት ኃላፊ መሐመድናስር አባጀማል (ዶ/ር) እንደሚያስረዱት፤ የዜግነት አገልግሎት ሲጀመር በሕዝቡ ውስጥ ያለውን የመደጋገፍና የመረዳዳት እሴት በተደራጀና በሕግ አግባብ መምራትን ታሳቢ ያደረገ ነው። ወደ ሥራም ሲገባ የመተጋገዝና የመደጋገፍ ሰዋዊ ጉዳዮችን ማዕከል ያደረጉ አስር ዘርፎች ላይ በማተኮር ነበር።

ሥራው ሳይቆራረጥ እንዲጓዝ በመደረጉ በ2017 በጀት ዓመት ላይ በዜግነት አገልግሎት የሚከናወኑ ሥራዎች ወደ 58 ዘርፍ አድገዋል። በተሳታፊም ሆነ በተጠቃሚ ቁጥርም በእጅጉ እየጨመሩ መጥተዋል። ለምሳሌ፣ በ2012 ላይ አገልግሎቱ ሲጀመር ወደ 13 ነጥብ ስድስት ቢሊዬን ብር የሚገመት ሥራ ተከናውኗል። ተግባሩም መሰረቱ ሰው፣ ዓላማውም ሰብዓዊነት በመሆኑ እያደገ መጥቶ በ2017 በጀት ዓመት ብቻ ወደ 329 ቢሊዬን ብር የሚገመት ሥራ በመሥራት የዜጎችን ችግር ማቃለል ስለመቻሉም ኃላፊው አስረድተዋል።

እንደ መሐመድናስር (ዶ/ር) ማብራሪያ፤ በዚህ መልኩ ሕዝባዊ መሰረቱን አጽንቶ የተጓዘው ተግባር ከ2012 እስከ 2017 ድረስ በዜግነት አገልግሎት ብቻ በየዓመቱ በአማካይ ወደ 30 ሚሊዬን የሚጠጋ ሰው እየተሳተፈበት 654 ቢሊዬን ብር የሚገመት ሥራን በማከናወን 23 ነጥብ አራት ሚሊዬን ሰዎችን ተጠቃሚ ያደረገ አገልግሎት ለመስጠት አስችሏል።

ይሄው ተግባር ተጠናክሮ በ2018 በጀት ዓመት ወደ 72 የሥራ ዘርፎች ከፍ እንዲልና 360 ቢሊዬን ብር የሚገመት ሥራ የሚከናወንበት እንዲሆን ታቅዷል። በዚህም ለተቸገሩ ወገኖች እና አቅመ ደካሞች ቤት ከመሥራትና ከማደስ ጀምሮ፤ ደም ልገሳ፣ የዐረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ፤ ትምህርትና ጤናን የመሳሰሉ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማቶች ግንባታ፣ ጥገናና ግብዓት የማሟላት ተግባራትን እንዲሁም ሌሎች የበጎ ፈቃድ ነጻ አገልግሎችን በመሳሰሉ ዘርፎች ላይ አገልግሎት የሚሰጥበት ይሆናል ብለውናልም።

የዚህ ተግባር አንድ ማሳያ እና በዕለቱም የክረምት ወቅት የአገልግሎቱ ጅማሬ ቦታ የሆነው ባቱ ከተማ፤ የወይዘሮ ጠጂቱን ድካም ተመልክቶ፤ የአቶ ገመቹንና ባለቤቱን እንግልት በትኩረት ለይቶ እንዲታገዙ እድል ፈጥሯል። ከዚያም ባሻገር በከተማ ደረጃም መሰል ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

የከተማዋ ከንቲባ አቶ አህመዲን ኡስማኤል እንደሚሉትም፤ የዜግነት አገልግሎት እንደ ከተማ አስተዳደር በሚደረጉት ሰብዓዊም፣ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማኅበራዊ ግንባታ ሂደቶች ከፍ ያለ አበርክቶ አለው። ለምሳሌ በ2017 ብቻ እንደ ከተማ አስተዳደር ሕዝቡን በማሳተፍ 233 እናቶች ቤት ተሰርቶላቸው ወደተሻለ ኑሮ እንዲሸጋገሩ ማድረግ ተችሏል። በቀጣይም በ30 የአገልግሎት ዘርፎች ዜጎችን ለማገዝ ይሰራል።

የዜግነት አገልግሎት፣ በሕዝቡ ውስጥ የነበረውን የቆየውንና የገዳ ሥርዓት አንዱ እሴት የሆነውን የመተጋገዝ ባሕል ከፍ አድርጎ በሕግና አሠራር እንዲሁም በተቋማዊ አደረጃጀት ታግዞ እንዲተገበር ያስቻለ ስለመሆኑ የሚናገሩት ደግሞ በክልሉ የሴቶችና ሕጻናት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ መብራት ባጫ ናቸው።

እንደ ወይዘሮ መብራት ገለጻ፤ ከገዳ ሥርዓት እሴቶች ውስጥ አንዱ የሆነው የመደጋገፍ ባሕል ለዘመናት በሕዝቡ ውስጥ ሰርጾ ኖሯል። በዚህም ዜጎች ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ እውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውንና ሀሳባቸውን ጭምር በማዋጣት በየዘርፉ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች መድረስ ችለዋል። ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውንም ተወጥተዋል። በተለይ በተለያዩ ምክንያቶች ለአደጋም፣ ለችግርም ተጋላጭ የሆኑትን ሴቶች፣ ሕጻናትና አረጋውያንን በመደገፍና በመንከባከብ በኩል የተሠሩ ተግባራት በእጅጉ የሚበረታቱ ናቸው። ይሄም ሕዝቡ ከገዳ ሥርዓቱ የወረሰው ሃብቱ ነው።

‹‹የክልሉ ሴቶችና ሕጻናት ቢሮ የዜግነት አገልግሎትን አንዱ የሥራው አካል አድርጎ ሲሠራ፤ ይሄንኑ ማኅበራዊ እሴት እሴቱ አድርጎ ነው።›› የሚሉት ኃላፊዋ፣ ቢሮው የሴቶች፣ ሕጻናትና የአቅመ ደካሞች(አረጋውያን) መብትና ጥቅሞች ማስከበር ግዴታው ቢሆንም ከዚህ ሥራው በተጓዳኝ በዜግነት አገልግሎት ታግዞ የእነዚህን የሕብረተሰብ ክፍሎች ችግር የማቃለል ተግባርን ያከናውናል። አሁን ደግሞ አጠናክሮ እየሄደበትም እንደሚገኝ አንስተዋል።

በዚህ ረገድ ከ2012 ጀምሮ ሰፊ ሥራ የተሠራ መሆኑን የጠቆሙት ወይዘሮ መብራት፤ በ2017 ብቻ ሕብረተሰቡንና የተለያዩ አደረጃጀቶችን በማሳተፍ 134 ሺህ 615 ቤቶችን በመሥራት አቅም ለሌላቸው እናቶች በመስጠት ከዝናብና ብርድ እንዲያርፉ መደረጉን ተናግረዋል።

እናቶችን ከማገዝና እፎይታን ከመስጠት ባለፈም፣ ለሦስት ነጥብ ሰባት ሚሊዬን ያህል የተቸገሩ ሕጻናት ድጋፍ የሚውል የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል። በዚህ መልኩ ቢሮው በሠራቸው ተግባራትም 10 ነጥብ ሰባት ሚሊዬን ሰው የተሳተፈበት 57 ነጥብ ሰባት ቢሊዬን ብር የሚገመት ሥራን በማከናወን፤ 13 ነጥብ ስምንት ሚሊዬን ሰዎችን ተጠቃሚ ስለማድረጉም አብራርተዋል።

ሥራው የአንድ ሰሞን ዘመቻ ወይም የአንድ ወቅት ሥራ አይደለም ያሉት ኃላፊዋ፤ ሕዝቡ ለዘመናት በሥርዓቱ ውስጥ ተቀርጾና ጠብቆ ያቆየው እሴት በመሆኑ ቀጣይነት ይኖረዋል። እንደ ክልሉ መንግሥትም በአደረጃጀት ታግዞ በትኩረት የሚሠራበት እንደሚሆን ገልጸዋል።

ቢሮው አሁን በተጀመረው መርሃ ግብር 12 ነጥብ ስምንት ሚሊዬን ሰው የሚሳተፍበት የ60 ነጥብ ሁለት ቢሊዬን ብር ግምት ያለው የዜግነት አገልግሎት ሥራን በማከናወን፤ 16 ነጥብ አምስት ሚሊዬን ዜጎችን ተጠቃሚ የማድረግ እቅድ ስለመያዙም አንስተው፣ ይሄ ደግሞ የበርካታ እናቶችን፣ አቅመ ደካሞችን፣ ሕጻናትን፣ በጥቅሉም የወገኖቻቸውን እገዛ የሚሹ ሰዎችን እንባ በእጅጉ የሚያብስ መሆኑን ተናግረዋል።

ድጋፉ የቅንነት፣ ለማኅበራዊ እሴት የመገዛት፣ ለሕግና አሠራሮችም ዋጋ የመስጠት ጉዞ በመሆኑ ሊበረታታና ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል ብለውም፣ እንደ ክልል በኦሮሚያ የተጀመረው የክረምት የዜግነት አገልግሎት መርሃ ግብር ከመረዳዳት አኳያ የሚገለፀው የገዳ ሥርዓት እሴት ማጽኛ ነውና ሁሉም ሕዝባዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You