የሆራ አዳ ኮንሶ በዓል ነገ ይከበራል

አዲስ አበባ፦ የሆራ አዳ ኮንሶ በዓልን በድምቀት ለማክበር የተደረገው ዝግጅት መጠናቀቁን የኮንሶ ዞን ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የዞኑ ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሠራዊት ዲባባ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ ‘ሆራ አዳ ኮንሶ’ የኮንሶ ባሕላዊ መልክዓ ምድር በኢትዮጵያ ዘጠነኛው የዓለም ቅርስ ሆኖ ከተመዘገበበት ጊዜ ጀምሮ የዞኑ ሕዝብ ምክር ቤት ዓመታዊ ካላንደር አውጥቶለት በየዓመቱ ሰኔ 21 ቀን በልዩ ድምቀት የሚከበር በዓል ነው፡፡ ይህን በዓል ለማክበርም ዝግጅቶች ተጠናቀዋል ብለዋል፡፡

ዘንድሮ ለ15ኛ ጊዜ በዞኑ ዋና ከተማ ካራ ለማክበር የተደረገው ዝግጅት የተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸው፤ በዓሉ የኮንሶ ማህበረሰብ አንድነት፣ አብሮነት፣ ታታሪነት፣ ባሕልን፣ ቅርስንና እሴትን ለትውልድ ጠብቆ ማሸጋገርን ዓላማው ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዓሉ በተለያዩ የአደባባይ ሁነቶች ማለትም ባሕላዊ ስፖርትና ሙዚቃዎች፣ ውዝዋዜዎች እንዲሁም የማህበረሰቡ ቅርሶች፣ እሴቶች፣ ትውፊቶች ፣ወጎች ፣ሥነ ቃሎች ፣የምግብና መጠጥ ዓይነቶች የሚያሳይ ኤግዚቢሽን እንደሚዘጋጅ ተናግረዋል፡፡ ከአደባባይ ሁነት ባሻገር በሚኖር የፓናል ውይይት ደግሞ፤ በኮንሶ ቅርስ እንክብካቤና ጥበቃ ላይ ኅብረተሰቡ ያደረገውን አበርክቶ እንዲሁም የብሔረሰቡን እሴቶች ማስቀጠል በሚቻልበት ዙሪያ ከተጋባዥ ምሁራን ከሀገር ሽማግሌዎችና ከተተኪ ወጣቶች ጋር ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በግርማቸው ጋሻው

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You