
አዲስ አበባ፡– የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ሥራ ውጤታማ እንዲሆን ማህበረሰቡን በአሳተፈ እና ተጠቃሚነቱን በአረጋገጠ መልኩ መሥራት እንደሚገባ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፤ ገለጹ።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ከክልል ቢሮ ኃላፊዎች ጋር ትናንት ውይይት ሲደረግ እንደገለጹት፤ የብዝሃ ሕይወት መመናመንን ለመከላከል የሚሠሩ ሥራዎች የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት በአረጋገጠ መልኩ ሊሆኑ ይገባል።
አብዛኛውን ጊዜ ከብዝሃ ሕይወት ጥበቃ አኳያ ማህበረሰቡ ወደ ደኖች እንዳይገባ የመከልከል ሁኔታ መኖሩን በማንሳት፤ማህበረሰቡ በአካባቢው የሚገኙ የብዝሃ ሕይወቶችን እንዲጠብቅ በቅድሚያ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ አስረድተዋል።
ለአብነት ያህል አደባ ዶዶላ አካባቢ የአካባቢው ነዋሪዎች ተደራጅተው በመሥራት ከካርቦን ሽያጭ እና ከተለያዩ ነገሮች 70 በመቶ የሚሆነውን እንዲጠቀሙ የተደረገበት ሁኔታ እንዳለ በማንሳት፤ ከእዚህ በኋላ ማህበረሰቡ በአካባቢው የሚገኙ የደን እንስሳቶችን ከአደን ከመከላከል ባለፈ ልክ እንደ ፍየሎቹ መንከባከብ ጀመረ ሲሉ ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፤ የብዝሃ ሕይወት አጠቃላይ ከሰው ሕይወት እና ደህንነት ጋር የተያያዘ ነው። በመሆኑም ተጠብቀው እንዲቆዩ ካልተደረገ የሰው ልጅ ሕይወት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያደርሳል።
በዓለም ኢትዮጵያ ሰፊ የብዝሃ ሕይወት ካላቸው ሀገራት አንዷ ናት። ከስድስት ሺህ በላይ እፅዋት እና ከሰባት ሺህ በላይ የየብስና የውሃ የእንስሳት ዝርያ ያላት ሲሆን፤ 10 በመቶ ያህሉ በሀገር ውስጥ ብቻ የሚገኙ ናቸው ብለዋል።
የብዝሃ ሕይወት በስፋት መኖር ያለው ጠቀሜታ ምንድነው የሚለውን መረዳት እና ለበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን ምን ማድረግ ያስፈልጋል የሚለውን ማወቅ የብዝሃ ሕይወትን ለመጠበቅ እጅግ በጣም አስፈላጊ መሆኑን አመልክተው፤ ለዘርፉ እድገት በእውቀት ላይ የተመሠረተ አመራር ወሳኝ እንደሆነም ተናግረዋል።
አሁን ከአጋጠመው የአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ለመጥፋት የተቃረቡ የብዝሃ ሕይወቶች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ለአብነትም ቀይ ቀበሮ አንደኛው ሲሆን፤ በተሠሩ ሥራዎች ከአጋጠው አደጋ ለማንሠራራት መቻሉን ጠቁመዋል።
ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)፤በዓለም ላይ በርካታ እንስሳት ደን ውስጥ መኖራቸውን በማንሳት፤ ደን ሲመናመን የብዝሃ ሕይወት አብሮ ይመናመናል። በተቃራኒው ደግሞ የደን ሀብት ሲጨምር የብዝሃ ሕይወት ይጨምራል ብለዋል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚሠሩ ሥራዎችን አያይዞ ማሰብ ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትሩ፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የደን ሀብት መጨመር ለብዝሃ ሕይወት መጠበቅና መጨመር ትልቅ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።
በዓለም ደረጃ የብዝሃ ሕይወት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲያስገኙ የተቀመጠ አሠራር መኖሩን አውስተው፤ አንድ ጎብኚ አንድ የደጋ አጋዘን በሚያድንበት ወቅት 15 ሺህ ዶላር ይከፍላል። ከእዚህ አኳያ እንስሳቱ ከብርቅነት ባለፈ ገቢ ያስገኛል፤ ከእዚህ ጥቅም ማህበረሰቡ እንዲጠቀም ማድረግ በአካባቢው ያሉትን የብዝሃ ሕይወቶች እንዲጠብቅ ያበረታታዋል ሲሉ አስረድተዋል።
ሚኒስትሩ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ባሕላዊ ግብርናን በስፋት ተግባራዊ ከማድረጓ ጋር ተያይዞ የአርሶና አርብቶ አደሩ ኑሮ ከብዝሃ ሕይወት ጋር የተሳሰረ ነው። የብዝሃ ሕይወትን ለመጠበቅ ክልሎች በቅንጅት መሥራት እና ለሌሎች ተሞክሮ መሆን እንደሚገባም አመላክተዋል።
በዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም