በእያንዳንዳችን አሁን ውስጥ ዛሬን የፈጠሩ በርካታ ብርሃናማ ትናንትናዎች አሉ። ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ያጀገኑ፣ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የማይደገም አኩሪ ታሪክ የጻፉ አምናዎች አሉ። ክብር ይገባና ለአባቶቻችን ትናንትናችን ብሩህ ነበር። ክብር ይግባና ለአያቶቻችን በአንድነት የቆምን ሕዝቦች ነበርን። በአንድ እየበላንና በአንድ ላይ እየጠጣን አንተ ትብስ አንተ በሚል ድንቅ ባህላዊ ሥርዓት ውስጥ ኖረው ያለፍን ሕዝቦች ነበርን።
አሁናችን ምን ዓይነት ነው? የአባቶቻችንን ዓይነት ነፍስና ስጋ አለን? ፍቅር ያገነነው ድሮአዊ መልክ በልባችን ውስጥ ተጽፏል? እስኪ ራሳችንን እንመርምር። ምን ዓይነት ነኝ? ለኢትዮጵያ አስፈልጋታለሁ? እንደ ዜጋ፣ እንደ መንግሥት፣ እንደ ተፎካካሪ ፓርቲ ምን እየሠራሁ ነው? ስንል ራሳችንን እንጠይቅ።
በመጠየቅ ውስጥ ብዙ መልስ አለ። በመጠየቅ ውስጥ ብዙ እውነት አለ። በአሁናችን ውስጥ የአያቶቻችንን አምና እንመልስ። በዛሬአችን ውስጥ የትናንትናውን ዓይነት ኢትዮጵያዊ መልክ እንልበስ። ከአባቶቹ ሀቅ የሸሸ ትውልድ እርባና የለውም። ዘመናዊነት መነሻውም መድረሻውም የራስ የሆነን ባህልና ታሪክ ማፍቀር ነው። ኢትዮጵያን ለሳሉ እጆች፣ ላቀኑ ክንዶች፣ ለዋጁ ነፍሶች ክብር መስጠት ነው።
ታሪካችን ውብ ሆኖ የተጻፈው፣ በታሪክ ምንጣፍ ላይ በኩራት የተራመድነው ኢትዮጵያን በሳሉ ብሩካን እጆች ነው። በነፃነትና በክብር ከእዛ እዚህ የደረስነው ለኢትዮጵያ ሲሉ በሞቱ ታማኝ ነፍሶች ነው። ለእኔና ለእናንተ ክብር ሲሉ በተሰዉ ነፍሶች አጥንትና ደም ላይ ቆመን መፋቀር እንጂ መባላት፣ መተቃቀፍ እንጂ መገፋፋት አያምርብንም። ለራሳችንም ሆነ ለአገራችን አስፈላጊ የምንሆነው በአባቶቻችን ሥርዓት ውስጥ ስንኖር ነው። ያለ የነበረውን ኢትዮጵያዊ ወግና ባህላችንን ስንከተል ነው። ወደ ተውነው መሠረታችን ስናይ ነው። ወደ ረሳንው..ወደ ተጸየፍንው ድሮነት ዞረን ስናይ ብቻ ነው። አሁን ላይ ብዙዎቻችን ስህተት እየሠራን ያለንው ይሄን ድሮአዊ መልክ ባለማወቅ ወይም ደግሞ አውቆ ባለመተግበር ነው እላለሁ። ዘመናዊነት ምን እንደሆነ የማናውቅ ብዙዎች ነን። ስልጣኔ ትርጉሙ የጠፋን ሞልተናል።
ተምረንና ፊደል ቁጥረን ስለ አውሮፓና እሲያ ስናውቅ ስለአገራችን ባህልና ታሪክ የማናውቀውን ቤት ይቁጠረን። ያበቀለንን፣ ያጀገነንን፣ ሰላሳና ስልሳ መቶ እንድናፈራ የክብር አክሊል የሆነንን ሕዝብ ንቀን በብሔር የምንባላው አፍሪካን አንድ ያደረገ ታሪክ እንዳለን በመርሳታችን ነው። በአንድነት የመጣንበትን ትናንትን ረስተን የምንገነባው ዛሬ የለም። የመጣንበትን ሀበሻዊ ታሪክ ተጸይፈን የምንፈጥረው ተዐምር የለም።
አገር እንገንባ። በፍቅር፣ በአንድነት የተገመደ ድርና ማግ የተፈተለ ሕዝብ እንፍጠር። ጦር ሳያነሳ በሀሳብ ጠላቶቹን የሚጥል ትውልድ እንስራ። የሚያዋጣን ይሄ ነው። አሁን ላይ ቤቶቻችን እየፈረሱብን ያሉት፣ ህልማችን፣ ራዕያችን እየመከነ ያለው ከሥርዓት ስለወጣን ነው። ሁላችንም በአባቶቻችን ጎዳና ላይ ቆመን አዲሷን ኢትዮጵያ በጋራ መፍጠር ይጠበቅብናል። ድሮነትን በመዘንጋ፣ ድሮነትን በመካድ አሁናዊ ስልጣኔ የለም። የሁሉም አገራት ስልጣኔ በትናንት የጀመረ ነው። የሁሉም ሕዝቦች ታሪክ አምና ተጀምሮ ዘንድሮ የተጠናቀቀ ነው። የሁሉም አገራት አሁናዊ ገጽ በጥንት የተሳለ ነው። የእኛ ታሪክ ግን ሁሌ እየተጀመረ የሚቆም ነው። የእኛ ኢትዮጵያ ግን ሁሌ እየተጀመረች መንገድ ላይ የምትቀር ናት። የእኛ ስልጣኔ..የእኛ ትናንትና ግን ዛሬን ያላየ አዳፋ መልክ ነው። ለምንድነው ሄደን..ሄደን የማንደርሰው? ለምንድነው ሄደን፣ ሄደን የምንቆመው? ለምንድነው ጥግ የሌለን? ለምንድነው እንዳባቶቻችን ወደ ፊት ለመሄድ ያቃተን?።
ለምንድነው ታላቅ እውነት እያለን በትንሽ ውሸት የምንታለለው? ለምንድነው ታላቁን ፍቅር የረሳነው? ራሳችንን እንጠይቅ። በክፋትና በራስ ወዳድነት ያፈረስነው ትናንት ካልሆነ እኛ የሠራነው ዛሬ የለም። በብሔርና በጎሳ ልክፍት ያበላሸነው ታሪክ ካልሆነ በእኛ የተሠራ አዲስ ኢትዮጵያዊ ታሪክ የለንም። ከማፍረስና ከማውደም በስተቀር ጀምረን የጨረስነው አምና የለንም። ጀምረን ያቆምነው እንጂ ከፍጻሜ ያደረስነው አንዳች እውነት የለንም።
ደግሞ እኮ የሚያስጠላ አንዳች ነገር የለንም። ደግሞ እኮ ነውር የሆነ አንድም ታሪክ የለንም። ደግሞ እኮ ለብቻ የኖርነው አንድም ትናንት አንድም አምና የለም። ሁሉም ታሪኮቻችን የጋራችን ናቸው። ሁሉም ጎዳናዎች አብረን የተጓዝንባቸው ናቸው። ታዲያ ጀምሮ ለመጨረስ ምን ይሆን የከበደን? ከትናንት ወደ ዛሬ መምጣት ምን ይሆን ያስቸገረን? ውብ መልኮቻችን፣ ውብ ታሪኮቻችን እንዳለ የትናንት ሆነው ሳሉ ለምን ትናንትን ጠላነው?
አርተፊሻል ማንነታችንን ጥለን ወደቀደመ ድንቅ እኛነታችን እንመለስ። እውነታችን ያለው እዛ ነው። ኢትዮጵያን የሳሉ እጆች የእኔና የእናንተ እጆች ናቸው። ኢትዮጵያዊነትን የቀለሙ ቡሩሾች የእኔና የእናንተ ታሪኮች ናቸው። ኢትዮጵያ ብለን እኛ ካልን እኛ ብለን ኢትዮጵያ ማለት ለምን ከበደን? ወዛችን ውስጥ ያበቀልናት፣ ደማችን ውስጥ የሳደግናት አገራችን የጋራችን ናት።
የቆመችውም በጋራ ታሪክና በጋራ እሴት ነው። አሁንም ቢሆን በነፃነቷና በእኩልነቷ ከራሷ አልፋ ለአፍሪካ የምትበቃ ኢትዮጵያን ለመፍጠር በጋራ የምንኖርባት፣ በጋራ የምናስብባት፣ በጋራ የምናለማት ኢትዮጵያ ታስፈልገናለች። የድሮዋ ኢትዮጵያ ወንዝ የተሻገረችው በጋራ እያሰቡ በጋራ በሚመክሩ ልጆቿ ነው። እኛም በጋራ እያሰብን በጋራ መምከራችን አሁን ላይ ላሉብን ዘርፈ ብዙ ችግሮቻችን ብቸኛ መፍትሄ ነው።
በዛሬአችን ውስጥ የእኔና የእናንተን አሁናዊ መልክ ያደመቁ በርካታ ትናንትናዎች በታሪካችን ውስጥ አሉ። ዛሬን እንድናይ፣ ዛሬን እንድንኖር ያደረጉ አርበኛ ክንዶች። ኢትዮጵያዊነት ሲነሳ አብሮ የሚነሳ፣ ጥቁርነት ሲታወስ አብሮ የሚታወስ ታሪክና መልክ። ኢትዮጵያዊነት የዓለም ታሪክ ነው። ዓለም በእኔና በእናንተ ውስጥ አለች። እኔና እናንተ በዓለም ውስጥ ደምቀን አለን። አውጥተው አይናገሩት እንጂ በሁሉም የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ፣ በሁሉም ነጭ ነፍስ ውስጥ ኢትዮጵያዊነት አለ።
ክብር ለአባቶቻችን ይሁንና በእንዲህ ዓይነት ሰዋዊ ልዕልና በአባቶቻችን ትናንትና ውስጥ የቆምን ነን። ቀጣዩ የእኛ የቤት ሥራ ነው። ቀጣዩ ትውልድ፣ ቀጣይዋ ኢትዮጵያ የእኔና የእናንተ አስተሳሰብና ድርጊት ውጤት ይሆናል። አባቶቻችን የቤት ሥራቸውን ጨርሰው ታላቅ አገርና ሕዝብ አስረክበውን አልፈዋል። የተቀበልነውን አደራ ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ የእኛ ቀሪ የቤት ሥራ ነው።
ወደቀደመ ፍቅራችን..ወደ ቀደመ አንድነታችን በመመለስ ጀምረን ያቆምናትን ኢትዮጵያ መጨረስ አለብን። ወደ ቀደመ ሥርዓታችን በመመለስ አሻጋሪ አጥቶ መንገድ የቆመ ሕዝባችንን ማሻገር ይኖርብናል። እንደፈለገ የምንሆነው በአባቶቻችን የደም ርስት ላይ ቆመን ነው። ወጥተን የምንገባው፣ ወልደን የከበርነው፣ ተምረን ለቁም ነገር የበቃነው አገርና ሕዝብ ስላለን ነው። የነፃነት ምድር፣ የነፃነት ፋና ወጊ መሆናችሁን አትርሱ። የሥልጣኔ ማማ፣ የጥበባት እልፍኝ ጎጆ መሆናችንን አንዘንጋ።
ፍቅር በማጣት ብርሃናችንን አናጨልም። የአንድነት ሰማያችንን አናፍርስ። ለብዙዎች የሥርዓት ጥግ ነበርን። ለብዙዎች የመኖር ዋስትና ነበርን። ታዲያ ዛሬ ለምን መኖር ፈራን? ለምን በእኛ ዘንድ ሰውነት ረከሰ? ለምን ተያይዞ ለመውደቅ ተገፋፋን? በብዙ ክብርና ሥርዓት ውስጥ የኖርን አገርና ሕዝብ መሆናችንን አንርሳ። በአንድነታችን ድሮነታችንን በመመለስ የማይፈርስ ቤት እንስራ።
በአባቶቻችን በወረስነው የጽናት ክንድ በእኔና በእናንተ ውስጥም ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ዳግም ትፈጠር። ዛሬም ነገም ኢትዮጵያ ክብራችን ናት። መቼም የትም የአገራችንን ያክል፣ የሕዝባችንን ያክል ክብር የለንም.. አይኖረንምም። አገራችን የእናት ሆዳችን፣ የእናት ጀርባችን ናት.. እንደፈለገ መሆኛችን። ሕዝባችን ወጥቶ መግቢያችን፣ ሄዶ መመለሻችን ነው። ሲከፋን የምንጽናናው በአገርና በወገናችን ነው። ታዲያ ለዚህ ሕዝብ የሚሆን ክብር እንዴት አጣን?
አገራችን ኢትዮጵያ ባልተማሩ ተገንብታ በእኛ መፍረስ የለባትም። በጽኑ እጆች ጸንታ ቆማ በእኛ መደነቃቀፍ የለባትም። ነውር እንወቅ..ሥርዓት እንማር። የአባቶቹን ሥርዓት እንደሚከተል ትውልድ አራዳና ዘመናዊ አላውቅም። ነውር ማወቅ አስተዋይነት ነው። በነገራችን ላይ ነውር ማወቅ ከጥበብነት ባለፈ የአገር ፍቅር መገለጫም መሆን ይችላል። ነውር ማወቅ አገርና ሕዝብን ከሚጎዳ አስጸያፊ ሰይጣናዊ ድርጊት መታቀብ ነው።
ነውር እንደሚያውቅ አገርና ሕዝብ ስልጡን የለም። ነውር እንደሚያውቅ ሰውነት አዋቂ የለም። ነውር እንደሚያውቅ ትውልድ የተባረከ የለም። የአባቶቹን ባህል የሚያከብር መንግሥትና ሕዝብ ከፊት የቀደመ ነው። አሁን ላይ ያወቅን እየመሰለን መሳሳታችን ነው ገደል እየሰደደን ያለው። ከነውር ወጥተን ትውልድ የሚኮራበትን መልካም ሥራ እንስራ። እንደተደገፍንባቸው እንደ አባቶቻችን ጽኑ ክንዶች መጪው ትውልድም እንዲደገፍብን ክንዶቻችንን ለጽድቅ እናጠንክር።
እንደደመቅንባቸው የአባቶቻችን ብዙ ትናንቶች እኛም የልጆቻችንን ደማቅና ብሩህ ነገዎችን እንስራ። እስከዛሬ ልክ ካልነበርን ዛሬ ልክ መሆን እንችላለን። እስከዛሬ አጥፊዎች ከሆንን ዛሬ ወደልማት መመለስ እንችላለን። እስከዛሬ እልሀኛ ከሆንን ዛሬ በመነጋገር አገር መገንባት እንችላለን። ለመልካም ነገር የሚረፍድ ቀን የሚመሽ ጊዜ የለም። መቼም የትም ከነውር ወጥተን ለአገራችን አስፈላጊ ሆነን መገኘት እንችላለን። ብዙዎቻችን ከጥፋታችን ለመመለስ አልረፈደም ።
ከስህተት ወጥተን አዲስ ሕይወት ለመጀመር የመሸ የሚመስለን አለን። ወደ ኋላ ለመመለስ አቅም የምናጣም ሞልተናል እውነቱ ግን ለለውጥ የሚረፍድ ጊዜ የለም የሚለው ነው። መለወጥ ለሚፈልግ ሰው ሁሉም ቀናት የለውጥ ማለዳዎች ናቸው። ለለውጥ ነገ የሚባል ቀን የለም። ለውጣችን የሚጀምረው ለመለወጥ ቁርጠኛ የሆንን ጊዜ ነው። ልክ እንደዚህ ሁሉ አገራችንም ለእርቅ፣ ለተግባቦት ቁርጠኛ የሆነ መንግሥትና ተፎካካሪ ፓርቲ ያስፈልጋታል።
ለምንም ነገር ከአሁን የተሻለ ምቹና ትክክለኛ ጊዜ አናገኝም። ችግሮቻችንን ለመቅረፍ፣ እንቅፋቶቻችንን ገለል ለማድረግ ዛሬ የተሻለ ቀን ነው። በብሔራዊ ምክክር የአባቶቻችንን የአንድነት አገር መፍጠር አለብን። በብሔራዊ ተግባቦት መፍትሄ ያጣንባቸውን ስቃዮቻችንን መፍትሄ መስጠት አለብን። ያኔ ኢትዮጵያ ትወለዳለች። በመነጋገርና በመግባባት በብርሃናማ ሀሳብ ከጥፋት ወጥተን ኢትዮጵያን ካጀገኑ አባቶቻችን ጎን እንቁም። ለአዲሷ ኢትዮጵያ አዲስ ሀሳብ እንጂ አዲስ ንትርክ አያስፈልጋትም። አዲስ የለውጥ አስተሳሰብ እንጂ አዲስ የመከራ ቁርሾ ይበቃናል።
በወንድማማችነት መንፈስ ለጠላት የማይበገሩ ጽኑ ክንዶችን የእኛ እናድርግ። ለነፍሶቻችን ሀቅን እናስተምር። ፍቅር የሚያውቅ፣ ይቅርታን የሚያዜም ሰውነትን እንገንባ። መንገዶቻችን ሁሉ ወደ ከፍታና ወደ ኅብረብሔራዊነት የሚወስዱን ይሁኑ። የክፋትና የተንኮል ሀሳብ በእኛ ዘንድ የተጠላ ይሁን። ኢትዮጵያ ስታለቅስ እኛ ነን የምናለቅሰው። ከወንድሞቻችን ጋር ስንገፋፋ የጋራ ታሪኮቻችንን እያጣን ነው የምንሄደው። አንድነት ስናጣ፣ ህብረት ሲጎድለን ለባዕድ አገራት መጠቀሚያ እየሆንን እንደሆነ እንወቅ።
የአገራችን እያንዳንዱ ነገር እኛ ላይ የሚያርፍ ነው። የአገር ብልጽግና የሕዝቦች ብልጽግና ነው። የአገር ድህነት የዜጎቿ ድህነት ነው። ካለእኔና እናንተ ተሳትፎ የምትበለጽግ አገር የለችም። የሁሉም አገራት የስኬት ምንጩ ሕዝቦቿ ናቸው። ለዚህም ነው በጽኑ ክንድ ጽኑ አገር እንገንባ። አገር የሕዝቦች እውነት ናት። አገር የዜጎች ሀሳብ ናት። አገር የትውልድ ተስፋ ናት። አገር የሰውነት መነሻና መድረሻ ምስማክ ናት።
በዚህ እውነት ላይ ቆመን ነው የምንጋፋው። በዚህ እውነት ላይ ሆነን ነው የምንናቆረው። መጀመሪያችሁ ላይ ሆናችሁ መጨረሻችሁን አታበላሹ። መጨረሻችሁ ላይ ደርሳችሁ መጀመሪያችሁን አትርሱ። የምንም ነገር ደም ግባታችሁ ይሄ ሕዝብና ይቺ አገር ናት። የምንም ነገር ጅማሬአችሁ የአባቶቻችሁ ኢትዮጵያ ናት። ግን የአባቶቻችንን ኢትዮጵያ ወዴት ገባች? ጥንታዊ መልካችን ወዴት ተሰወረ? እዚህ እውነት ላይ ሳንደርስ የምንሄድበት መንገድ አይጠቅመንም።
ከሁሉ በፊት የአባቶቻችንን ኢትዮጵያ እንፈልጋት። ከሁሉ በፊት የአባቶቻችንን መልክ እንውረስ። ያኔ እውነት እንሆናለን። ያኔ የመነሻችንን መጨረሻ እንደርስበታለን። ሌሎችን ሳንጠብቅ ለአገራችን ትንሳኤ የመጀመሪያዎቹ እንሁን። ኢትዮጵያን እንዳጀገኑ የአባቶቻችን ብሩህ ትናንትናዎች የልጆቻችሁን ነገ በተባበረ ክንድ እንስራ። ከዛሬ የላቁ ብዙ ነገዎች ከፊታችን አሉ። ከዛሬ የተለቁ ቁመታም ነገዎች ይጠብቁናል። ለዚህ ሁሉ ተስፋችን መልካም አገር ታስፈልገናለች። ሰላማዊ ሕዝብ ግድ ይለናል።
መልካም አገር የሚሠራው በመልካም ልብ ነው። ሰላም ያስፈልገናል። ካለሰላም አገር ሕዝብና ታሪክ ምንም ናቸው። ካለሰላም የሚሳካ ህልምና ራዕይ የለም። ካለሰላም ነገ የሚባል ቀን የለም። ነጋችን ያለው በሰላማዊ ዛሬአችን ውስጥ ነው። በተባበረ ክንድ ኢትዮጵያን እንሳል።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ኅዳር 13/ 2015 ዓ.ም