ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሰሞኑን ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል። በምክር ቤቱ አባላት ጥያቄ ከተነሳባቸው እና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽና ማብራሪያ ከተሰጠባቸው ጉዳዮች አንዱ በቅርቡ በኢፌዴሪ መንግሥት እና በሕወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነትን የሚመለከት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፣ አሁን ለተደረሰበት የሰላም ስምምነት እውን መሆን እና በቀጣይም ሰላሙን ዘላቂ ለማድረግ በትኩረት መሥራት ይገባል ብለዋል።
ሁሉም ስለ ሰላም ቅድሚያ ሰጥቶና የሰላምን ከፍ ያለ ዋጋ ተገንዝቦ ከሰራ ይሄን ማድረግ እንደሚቻል የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሰላሙን ዘላቂ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ግን ፈተና አልቦ እንዳልሆነም ነው ያስረዱት። ምክንያቱም ሰላምን የሚፈልጉ እንዳሉ ሁሉ ሰላምን የማይፈልጉ የጦርነት ነጋዴዎች ስላሉ፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሰላም ስምምነቱ እንዲሰምር ለሰላም መትጋት፣ ለሰላም መሥራት እና ለሰላም መጣር ያስፈልጋል ብለዋል። የሰላም ስምምነቱ እንዲሰምርም የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፤ ይህ የሰላም ስምምነት ፈተና አልቦ ሊሆን እንደማይችል ሳይታለም የተፈታ ነው። ለዚህ የሰላም ስምምነት እውን መሆን እንቅፋት ሊሆኑ ከሚችሉ ነገሮች አንዱ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ከየአቅጣጫው የሚለቀቁ ብሽሽቆች፣ የተበረዙ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮች ተጠቃሽ ናቸው።
የኒዮርክ ታይምስ ጋዜጠኛና ጸሐፊ ማክስ ፊሸር በቅርቡ ባሳተመው «ዘ ኬኦስ ማሽን» በተሰኘው መጽሐፉ ማህበራዊ ሚዲያ የሰው ልጆችን በማጋጨት ዓለምን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እየወሰዳት መሆኑን አትቷል። ማህበራዊ ሚዲያዎች ለመልካም ተግባር የመዋል ሰፊ ዕድል ያላቸው ቢሆንም፤ ፌስቡክን ጨምሮ ሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች እና ድረገጾች እንደ ሀሺሽ ሰዎችን ሱሰኛ ከማድረጉ ባሻገር እንደ ፌስቡክ፣ ቲዊተር፣ ዩቲዩብ እና ቲክቶክ ያሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሰዎችን አስተሳሰብ በአሉታዊ መንገድ
እየቀየረ መሆኑን አመላክቷል። በሕዝቦች መካከል ያሉ መጠነኛ ልዩነቶችን የበለጠ በማስፋት ለግጭቶች መንስኤ እየሆነ መሆኑን ከማስረጃ ጋር አቅርቧል።
በአገራችን ላለፉት ሁለት ዓመታት የተካሄደው እጅግ አውዳሚ ጦርነት ከመጀመሩ አስቀድሞ ለጦርነቱ መንገድ በመጥረግ ረገድ ማክስ ፊሸር የቀውሶች መፈልፈያ ያላቸው ማህበራዊ ሚዲያዎች የነበራቸው ሚና ቀላል የሚባል አይደለም። የአንድ አገር ልጆች ጎራ ለይተው እኛና እነሱ በሚል ተከፋፍለው የጦርነት ነጋሪት ሲጎስሙ የነበሩት አንዱ መንገድ እነዚህን የቀውስ መፈልፈያዎችን ማሽኖችን በመጠቀም ነው።
በእርግጥ ማህበራዊ ሚዲያ ብቻውን የችግሮቻችን መንስኤ ነው ማለት ባይቻልም፤ መጠነኛ ልዩነቶች እየሰፉ እንዲሄዱ እና አለመግባባቶች በንግግር እንዳይፈቱ ትልቁን ሚና ተጫውቷል። እንዲህ እንደ አሁኑ በኢትዮጵያ በሰሜኑ ጦርነት የተገኘውን ዓይነት የሰላም አየር ሲነፍስ እና ጦርነቱ ጋብ ሊል ሲል በሁለቱም አቅጣጫዎች በጦርነቱ ምክንያት የደረሱ ውድመቶች እና ጉዳቶችን በማህበራዊ ሚዲያዎች ደጋግሞ በማስታወስ ቢችሉ የሰላም ውይይቶች እንዳይጀመሩ፤ ካልቻሉ ደግሞ በሰላም ውይይቶች የተደረሱ ስምምነቶች ወደ ተግባር እንዳይለወጡ እና አውዳሚው ጦርነት እንዲቀጥል የበኩሉን ሚና የሚወጣ መድረክ ሆኗል።
እጅግ የሚያሳዝነው ከሁለት ዓመት አውዳሚ ጦርነት በኋላ በቅርቡ በደቡብ አፍሪካና በኬንያ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በሕወሓት መካከል ስምምነት ከተደረሰ በኋላም የቀውስ መፈልፈያዎቹን በመጠቀም አሁንም ጦርነቱን ለማስቀጠል ደፋ ቀና የሚሉ አልጠፉም። የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ሁለቱ አካላት ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች በሚገኙበት በናይሮቢ እና በፕሪቶሪያ ጊዜ ወስደው ሰፊ ውይይቶች በሚያካሂዱበት ሰዓት ጭምር በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ስለጦርነት እና ስለ አሸናፊ ተሸናፊ ትርክት አብዝተው የሚጽፉ በርካቶች ነበሩ። በእርግጥ የነዚህ አካላት ምኞት ለጊዜው አልሰመረም። ባለፉት ሁለት ዓመታት ከተካሄደው አውዳሚ ጦርነት ማንም አትራፊ እንዳልነበር በመገንዘብ የሰላም ስምምነቱን ተፈራርመዋል። ሰላሙ ዘላቂ እንዲሆን የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉም ቃል ገብተዋል።
ይሁን እንጂ የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላም በድርድር የሚፈታ ችግር እንደሌለ እና ጦርነት ብቸኛው አማራጭ እንደሆነ መረጃዎች በድፍረት በስፋት በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚያሰራጩ አልጠፉም። እነዚህ አካላት በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚያሰራጯቸው መረጃዎች የሰላም ስምምነቱን አደጋ ውስጥ የመጣል አቅም ያላቸው ናቸው።
ማህበራዊ ሚዲያዎችን ተጠቅመው ለሚያገኙዋት ጥቂት ገንዘብ ብለው የአገሪቱን እና የሕዝቦቿን የመከራ ዘመን ለማራዘም ጥረት የሚያደርጉ የቀውስ ነጋዴዎችን አደብ ማስገዛት ያስፈልጋል። አደብ ለመግዛት ፈቃደኛ ካልሆኑ ደግሞ ኢትዮጵያ ባላት የሳይበር ሕግ መሠረት እንዲሁም በዓለምአቀፍ ሕጎች አጋዥነት እንዲጠየቁ ማድረግ ይገባል። በዚህ ረገድ መንግሥት ቆራጥ ሊሆን ይገባል። ሰላምን ለማደናቀፍ የሚጥር የትኛውም ግለሰብም ሆነ ቡድን ላይ አስተማሪ እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል። ይሄን በማድረግም ከዚህ በፊት የሆነው የግፍና መከራ ጊዜ እንዳይደገም ማድረግ ይጠበቅበታል።
ምክንያቱም ከዚህ በፊት በነበረው ጦርነት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለሞት ተዳርገዋል፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን ተፈናቅለዋል፤ አገሪቱ በብዙ ችግር ውስጥ ሆና የገነባቻቸው መሠረተ ልማቶች እንዳልነበሩ ሆነዋል። ሌላ ዙር ጦርነት በማካሄድ የሚፈናቀል እና የሚሞት ዜጋ እንዲሁም የሚወድም ንብረት ሊኖር አይገባም።
ከመንግሥት ባሻገር መላው ኢትዮጵያውያን የሰላም ስምምነቱ እንዲሰምር የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል። ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም የጦርነት ነጋሪት የሚጎስሙት ተከታይ ሊያጡ ይገባል። ሲቀጥልም ለሚመለከተው አካላት በማመልከት እነዚህ የቀውስ ነጋዴዎች በማህበራዊ ሚዲያ ምህዳር ውስጥ ያላቸው ተጽዕኖ እንዲቀንስ ማድረግ ያስፈልጋል። ይሄን ማድረግ የህልውና ጉዳይ፣ አገርን ከብተና፣ ወገንን ከሞትና ሰቆቃ የመታደግ ውሳኔ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። በመሆኑም የተደረሰው የሰላም ስምምነት ይሰምር ዘንድ እነዚህን የማህበራዊ ሚዲያ ቀውስ ጠማቂዎች ሁሉም አካል በቃ ሊላቸው፤ ከአገር ህልውና፣ ከሕዝብም ደህንነት በላይ ስላይደሉም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የሚያደርጋቸውን ሁሉን አቀፍ ርምጃም ሊወስድባቸው ይገባል!
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ኅዳር 13/ 2015 ዓ.ም