“ርሀብ ባለበት ተስፋ አይኖርም። ህመምና ብቸኝነት ይሰፍናል። ርሀብ ግጭትንና ጽንፈኝነትን ይጎነቁላል። ሰዎች የሚራቡባት ዓለም ሰላም ልትሆን አትችልም።” ይላሉ እንደ ንስር ኃይላቸውን አድሰው ወደ ብራዚል ፖለቲካ በፕሬዚዳንትነት ብቅ ያሉት ሉላ ዳ ሲሊቫ፡፡ በሰራተኛ ማህበራት እየተደገፉ ያለ አብዮት ሚሊየኖችን ከከፋ ድህነት በማውጣት ተጠቃሚ ማድረግ የቻሉ ፕሬዚዳንት በማለትም ያደንቋቸዋል። ሰራተኛውን መደብና መካከለኛ ገቢ ያለውን የሕብረተሰብ ክፍል አንድ ለማድረግ ባቀጣጠሉትና ሉሊዝም የሚል ስያሜ በተሰጠው ስርዓት ስማቸው አብሮ ይነሳል። በብራዚል ታሪክ ከሰራተኛው መደብ የወጡ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ይሏቸዋል። የዩኒቨርሲቲን ደጅ ያልረገጡና ዲግሪ የሌላቸው፤ ለሁለት ተከታታይ ጊዜ በዴሞክራሲያው ምርጫ የተመረጡ፤ ስልጣናቸውን በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ላሸነፈ መሪ በሰላማዊ መንገድ ያስረከቡ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት እና የሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ፋና ወጊ ሲሉ ያሞካሿቸዋል። ሉላ ኢናሲዎ ዳ ሲልቫን፡፡
በቅርቡ በተካሄደ የብራዚል ምርጫ ወግ አጥባቂውን ቦልሶናሮን በጠባብ ልዩነት አሸንፈው ወደ ስልጣን የተመለሱት የብራዚል ፕሬዚዳንት ሉላ ኢናሲዎ ዳ ሲሊቫ፤ በዓለማችን ካሉ ታዋቂ ሕዝበኞች/populist/፤ ከሜክሲኮው ፕሬዚዳንት አንድሬስ ማኑኤል ሎፔዝ፣ ከአሜሪካው በርኒ ሳንደርስ፣ ከብሪታኒያው ጄርሚ ኮርቢንና ከሌሎቹ ጋር ስማቸው በግንባር ቀደምትነት ይነሳል። ዓለማቀፍ የተራማጆችን ንቅናቄ በማቀጣጠልም ስማቸው ይነሳል። ሉላ ከ2003 እስከ 2011 ዓ.ም፤ ተከታታይ ሁለት ምርጫዎችን በማሸነፍ ብራዚልን መርተዋል። በስምንት ዓመታት ሚሊየኖችን ከድህነት አረንቋ ማውጣት ችለዋል። በ2018 ዓ.ም ዳግም ወደ መሪነት ለመመለስ ሲዘጋጁ ስልጣን ላይ እያሉ ያልተገባ ጥቅም አግኝተዋል በሚል ተጠርጥረው፤ ጥፋተኛ ሆነው ስለተገኙ የ12 ዓመት እስር ተፈረደባቸው። እሳቸው ግን ክሱ ፖለቲካዊና ከፕሬዚዳንታዊ ውድድሩ ለማስወጣት የተሸረበ ሴራ ነው ይላሉ። ከሕዝብ በተሰበሰበ አስተያየት 50 በመቶ የሚሆኑት የቀድሞውን መሪያቸውን ፕሬዚዳንት ሉላን በታሪክ ምርጡ ፕሬዚዳንት ናቸው ሲሉ መስክረውላቸዋል።
ከ20 ዓመታት በፊት ግራ ዘመምና ሕዝበኛ የሆኑት ሉላ ወደ ስልጣን ሲመጡ ለብራዚል ኢፍትሐዊነት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱ ከበርቴዎች፤ ፕሬዚዳንቱ ብራዚልን ወደ ሶሻሊዝም ርዕዮተ አለም ይቀይሯታል፤ የእኛም ነገር ያበቃል የሚል ስጋት አድሮባቸው እንደነበር “ታይም” ያስታውሰናል። ሉላ ኢናሲዎ ዳ ሲሊቫ የላቲን አሜሪካ ሰራተኛ ቤተሰብ እውነተኛ ልጅ ሲሆኑ፤ የብራዚልን የሰራተኛ ፓርቲ ከመሰረቱት የመጀመሪያውም ናቸው። የስራ ማቆም አድማን መርተሀል በሚል ለስር ተዳርገው እንደነበር የታይም መጽሔቱ ማይክል ሞር ያስታውሰናል። ፕሬዚዳንት ሉላ ካልተሳካ ሶስት ፕሬዚዳንታዊ ውድድር በኋላ መጨረሻ ላይ ሲያሸንፉ በመላው ብራዚላዊ ዘንድ የሚታወቅ ብሔራዊ ተክለ ሰብዕና ገንብተው ነበር ይለናል ሞር፤ ወደ ፖለቲካዊ ዓለም የተቀላቀሉት የፋብሪካ ሰራተኞች ኑሯቸውን ለማሸነፍ ምን ያህል እንደሚደክሙና ለድካማቸው ተገቢውን ክፍያ እንደማያገኙ በራሳቸው ስለ አዩት ነው። ችግረኛ ቤተሰባቸውን ለማገዝ ከ5ኛ ክፍል ትምህርታቸውን አቋርጠው በህጻንነታቸው ጫማ ጠራጊ ሊስትሮ ሆነው ሰርተዋል። እድሜያቸው ከፍ ሲል የፋብሪካ ላብ አደር ሆነው ሲሰሩ ባጋጠማቸው አደጋ ትንሽ ጣታቸውን ማጣታቸውን ሞር ይገልጻል።
የልጅነትና የወጣትነት ዘመናቸው በብዙ ውጣውረድና ፈተና የተሞላ ነው። በ25 አመታቸው የ8 ወር ነፍሰ ጡር ባለቤታቸው፤ በተሻለ ሆስፒታል የወሊድ ክትትል እንዲያደርጉ ገንዘብ ስላልነበራቸው የመጀመሪያ ልጃቸውንም ባለቤታቸውን ተነጠቁ።
ለዚህ ነው ወደ ፕሬዚዳንትነት እንደመጡ ዜሮ ርሀብ ወይም ዜሮ ስታርቬሽን አልያም በፖርቹጊዝ ፎሜ ዜሮ ብለው ንቅናቄ ያቀጣጠሉት። በዚህ ንቅናቄ በአስር ሚሊየኖች የሚቆጠሩ ከሰራተኛው መደብ የሆኑ ብራዚላውያንን ከድህነት አረንቋ ማውጣት ችለዋል። ርሀብን በከፍተኛ ደረጃ ማስወገድ፣ የትምህርትና የጤና መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት የድሀ ዜጎችን ሕይወት ቀይረዋል። ታዋቂው ብራዚላዊ ጋዜጠኛ፣ መሐንዲስና የስነ ማህበረሰብ ሰው ኢውክሊዴስ፤”War of Canudos” በሚለው መጽሐፉ፤ በፖርቹጊዝ “ኤርታኔጆ” ወይም “የምድሪቱ የቁርጥ ቀን ልጅ” የሚለው አባባል የፕሬዚዳንት ሉላ ተክለ ሰብዕና ፍንትው አድርጎ ያሳየዋል ይላሉ ደጋፊዎቻቸው።
የሰሜን ምስራቅ ብራዚል ተወላጅ የሆኑት ሉላ፤ የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ሌት ተቀን ከሚማስኑ ድሀ ገበሬ ወላጆች በ1945 ዓ.ም የተወለዱ ሰባተኛ ልጅ ናቸው። በበርሀማው የፔርናምቡኮ ዞን በሚገኘው መብራትና የቧንቧ ውሀ በሌለው ሁለት ክፍል የአፈር ቤት ነው የተወለዱት። በከፋ ድህነት ያደጉ የእግራቸው ጫማ ያልነበራቸው ያጣ የነጣ ቤተሰብ አባል ሲሆኑ፤ ሉላ እንደተረገዘ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ፤ ወደ ሳውፖሎ የተሰደዱ አባታቸውን ፍለጋ ከእናታቸው ጋር ወደ ሳውፖሎ አቀኑ።
በስምንት ዓመታቸው የመላላክ ስራ አገኙ። በሚያገኟት ገቢ ቤተሰባቸውን መደገፍ ጀመሩ። በዘጠኝ ዓመታቸው ደግሞ በሳውፖሎ ሰፋፊ አውራ ጉዳናዎች ዳርቻ፤ ሊስትሮ በመሆን ተቀጣሪነት ለምኔ አሉ። ሆኖም የሚያገኙት ገቢ የሚያወላዳ ስላልሆነ መልሰው የአንድ የልብስ ንጽህና መስጫ ሱቅ ረዳት ሆነው ተቀጠሩ። በተጣበበችው ጊዜ የ1ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተምረው በማጠናቀቅ፤ በማሽን ቤት ተቀጠሩ። የፕሬዚዳንት ጁሴሊኖ ኩቢትሼክስ ልማታዊ ፖሊሲ በብራዚል ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ መቻሉ ይወሳል።
በሳውፖሎ የሚገኘው የኢንዱስትሪ ዞን እንደ ስካኒያ፣ ቮልስዋገንና ሌሎች ታላላቅ መኪና አምራቾች ስራ ጀመሩ። በዚህ ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት እንደ ሉላ ያሉ በርካታ ወጣቶች የስራ ዕድል ተፈጠረላቸው። ሉላም የብረታብረት ሰራተኛ ሆነው ተቀጠሩ። በ1964 ዓ.ም ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ተደርጎ የስርዓት ለውጥ በመደረጉ ተነቃቅቶ የነበረው ኢኮኖሚ መልሶ ተቀዛቀዘ። ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተገደቡ፣ ቅድመ ምርመራ ስራ ላይ ዋለ፣ በሰራተኛው ላይ ይፈጸሙ የነበሩ በደሎች ተስፋፉ። የዋጋ ግሽበት ተባባሰ። ብዙዎች ስራ አጥ ሆኑ።
በስማቸው የተሰየመው የምርምር ተቋም፤ ሉላ ከትንሿና በርሀማዋ ፐርናምቡኮ መንደር በህጻንነታቸው ወጥቶ ሳውፖሎ ሲገባ መልመድ ተቸግሮ ነበር ሲል ያስታውሳል። ብዙም ሳይቆዩ ከታላቅ ወንድሞቻቸው አንደኛው፤ በህቡዕ ከሚንቀሳቀስ የኮሚኒስት ህዋስ ጋር ያስተዋውቃቸዋል። በህዋሱ ስብሰባ በሚያደርጉት ተሳትፎ በሰራተኛው ላይ የሚፈጸመው በደል ተቋማዊና መዋቅራዊ መሆኑን በደንብ ይገነዘባሉ።
ሰራተኛው በቂ ክፍያ እንደማያገኝ፣ የመደራጀት፣ የመደራደር መብት፣ የስራ ዋስትናና የስራ ላይ ደህነት ዋስትና እንደሌለው ያጤናሉ። በህቡዕ በሚንቀሳቀሰው የሰራተኛ ማህበር በሚያሳዩት ንቁ ተሳትፎ የስራ አመራር ኮሚቴው አባል ሆነው ተመረጡ። ብዙም ሳይቆዩ በ1969 ዓ.ም የሰራተኛ ማህበሩ መሪ ሆነው ጉብ አሉ ይለናል ኢንስቲትዊቶ ሉላን፤ የሰራተኛ ማህበር መሪ መሆናቸው ህይወትን ፈታኝ ቢያደርግባቸውም፤ ወላጅ እናታቸው ዱና ሊንዱ ነገ የተሻለ ይሆናል አይዞህ እያሉ ያበረታቷቸው ነበር።
የሰራተኛው መብትና ጥቅም ተሟጋች ሉላ በ23 ዓመታቸው ትዳር ቢመሰርቱም፤ ከሁለት ዓመት በኋላ፤ በጉበትና በሳንባ ምች የተነሳና በቂ ህክምና ባለማግኘት ከእርግዝና ጋር ተያይዞ በተፈጠረ ችግር ባለቤታቸውንና ጽንሱን በሞት ተነጠቁ። መሪር ሀዘኑ ከፈጠረባቸው ጭንቀት ለመሸሽ በሰራተኛ ማህበሩና በግል ስራቸው ላይ መጠመድን በጀ ብለው ተያያዙት። ከዚህ በኋላ የትዳሩም የፍቅሩም ነገር ሊሰምርላቸው አልቻለም። ሆኖም በሰራተኛ ማህበሩ ያላቸው ተሰሚነትና ተቀባይነት እያደገ መጣ።
በ1973 ዓ.ም ገና 30ኛ አመታቸውን ሳይደፍኑ የአገሪቱ የሰራተኛ ማህበር ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ። በ1970ዎች አጋማሽ የሰራተኞች ጥያቄ ከረርና ጠንከር እያለ ሲመጣ ወታደራዊው አገዛዝ በዛው ልክ በኃይል ለማፈን ተንቀሳቀሰ። ፈላጭ ቆራጩ ወታደራዊ አገዛዝ ሁሉንም ተቃውሞዎች ለመጨፍለቅ የተለያዩ የአፈና ስልቶችን መጠቀምን በጀ ብሎ ተያያዘው። ከተማሪዎች ንቅናቄ እሰከ የትጥቅ ትግል አመጾችን ያለ ልዩነት በጠመንጃ ለማፈን ይንቀሳቀስ ጀመር። የተመረጡ መሪዎች ፖለቲካዊ መብቶች ሳይቀሩ ተገደቡ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ዕግድ ተጣለ። የሰራተኛ ማህበራት ንቅናቄ ግን ለወታደራዊ አገዛዙ የራስ ምታት መሆኑ ቀጠለ። የፖለቲካ ምህዳሩ እየጠበበ ሲመጣ፤ የግራ ዘመም አቀንቃኞች ሳይቀሩ ማህበሩን በስፋት ይቀላቀሉት ያዙ። ቤተ ክሪስቲያናትና የተማሪዎች ማህበራት እንዲሁ ሰራተኛ ማህበሩን መደገፍ ጀመሩ።
ይሄን አጋጣሚ ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር ሉላ በ1978 እና 1980 ዓ.ም አገር አቀፍ የስራ ማቆም አድማ ጠሩ። አድማው ከተገመተውና ከተጠበቀው በላይ መላ ብራዚልን ዳር እስከ ዳር ከመናጡ ባሻገር የሉላንና የፓርቲውን መሠረት አጸናው። በወርሀ ሚያዚያ 1980 ዓ.ም የስራ ማቆም አድማውን በማስተባበርና በመምራት ተጠርጥረው ለ31 ቀናት ታሰሩ። ከእስር እንደተለቀቁ የፖለቲካ ፓርቲ በማቋቋም ወታደራዊ አገዛዙን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መቃወሙን ተያያዙት። ሉላ ያቋቋሙት የፖለቲካ ፓርቲ በብራዚል ታሪክ ትልቁ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከመሆኑ ባሻገር ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ግንባር ቀደም ሆነ። በሰራተኛው መደብ አስኳልነት የተመሠረተ ቢሆንም ልሒቃን፣ የኃይማኖት መሪዎች፣ አርቲስቶች፣ ተማሪዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በስፋት ይቀላቀሉት ያዙ።
ሉላ ዳ ሲልቫ የብራዚልን ፖለቲካዊ መልክዓ የቀያየረው ፓርቲ የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ፤ ከሰራተኛው ድምጽነት ወደ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መሪነት ተሸጋገሩ። በብራዚል የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሒደት ዛሬ ድረስ በእርሾነት ስማቸው በሰፊው ይወሳል። የፖለቲካ ፓርቲ መስርተው ከወጡ በኋላም በሰራተኛ ማህበራት ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ በማሳደር ይታወቃሉ። በብራዚል የሚገኙ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማስተባበርና በመምራት በ1983 ዓ.ም በአገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚጠይቅ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ።
ከሶስት ዓመት በኋላ በ1986 ዓ.ም በተካሄደ ምርጫ ለምክር ቤት አባልነት ሲወዳደሩ በታሪክ ታይቶም ሆነ ተሰምቶ በማያውቅ ከፍተኛ ድምጽ ተመረጡ። ሕገ መንግስታዊ ጉባኤ እንዲካሄድና ማሻሻያዎች እንዲደረጉ፤ የሰብዓዊና የማህበራዊ መብቶች እውቅና እንዲያገኙ፤ የወሊድ ፈቃድ አራት ወራት እንዲሆን፤ የስራ ሰዓት በሳምንት ከ48 ወደ 44 ሰዓታት ዝቅ እንዲል ብርቱ ትግል አድርገዋል። ከ29 ዓመታት በኋላ በተካሄደ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለፕሬዚዳንትነት ተወዳድረው በጠባብ የድምጽ ልዩነት ተሸንፈዋል።
በ1990 ዓ.ም የዜግነት ተቋምን በመምራት ለአገርና ለዜጋ የሚጠቅሙ የፖሊሲ ሀሳቦችን ከማመንጨታቸው ባሻገር፤ ብራዚልን ለስምንት ዓመታት የመሩት ፕሬዚዳንት ፈርናንዶ ኮሎር ላይ ስልጣንን አላግባብ መጠቀም ክስ እንደሚሰረትባቸው የአንበሳውን ድርሻ ተጫውተዋል። በብራዚል የላይኛውም ሆነ የታችኛው ምክር ቤቶች የተስተዋሉ ምዝበራና ሌሎች ብልሹ አሰራሮች ምርመራ እንዲደረግባቸው ሰርተዋል። ከወጣትነት ዘመናቸው ጀምሮ እድሜ ልካቸውን አንድ ጊዜ ለሰራተኛው በኋላ ደግሞ ለብራዚላውያን ሲታገሉ የኖሩት ሉላ፤ ከሶስት ጊዜ እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ በ2002 ዓ.ም ከፍተኛ ድምጽ በማግኘት የብራዚል ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ። በብራዚል ታሪክ ከሰራተኛው መደብ ወጥተው ፕሬዚዳንት በመሆናቸው አልቮራዶ ቤተ መንግስት ለመጀመሪያ ጊዜ የገቡ ተብለው በታሪክ ተመዘገቡ። ሁለት ተከታታይ ምርጫዎችን በማሸነፍ ስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ፍትሐዊ የገቢ ክፍፍል እንዲኖር፤
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ብራዚላውያን የምግብ፣ የህክምና፣ የትምህርትና የብድር አገልግሎት በማቅረብ፤ ሰፊ የስራ ዕድል በመፍጠርና የደመወዝ ማሻሻያ በማድረግ በአስር ሚሊየኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ከከፋ ድህነት ማውጣት ችለዋል። የመኖሪያ ቤት፣ መንገድ፣ የጤናና የትምህርት ተቋማት ግንባታን በማስፋፋት በዜጎች ኑሮ ላይ የሚጨበጥ ለውጥ አምጥተዋል። ፕሬዚዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ የስልጣን ዘመናቸውን በ2010 ዓ.ም አጠናቀው፤ ለተመራጯ ፕሬዚዳንት ዴልማ ሮሴፍ ሲያስረክቡ 87 በመቶ በሚሆኑ ብራዚላውያን ዘንድ ያለ ልዩነት አድናቆት ተችሯቸዋል። በሉላ የስልጣን ዘመን በአገሪቱ ታሪክ ከድህነት ወለል በታች የነበሩ በርካታ ዜጎች ከድህነት የተላቀቁበትና ሰፊ የስራ ዕድል የተፈጠረበት ሆኖ ተመዝግቧል።
መስከረም 22 ቀን ብራዚል በምታደርገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሉይዝ ኢናሲዎ ሉላ ዳ ሲሊቫ እንደ ንስር ኃይሌን አድሼ ተመልሻለሁ ሲሉ ደጋፊዎቻቸውን አስፈነደቁ። ግራ ዘመሙ ሉላና ስልጣን ላይ የነበሩትና ቀኝ አክራሪውና የላቲኑ ትራምፕ የሚል ቅጽል የተሰጣቸው ሀየር ቦልሶናሮ ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተፋጠጡ። ሉላ ለስምንት አመታት ፕሬዚዳንት እያለሁ ብራዚል ለዜጎቿ ከዛሬው የተሻለች ነበረች። አሁን ኢፍትሐዊነት ሰፍኗል።
በተለይ ዝቅተኛው የሕብረተሰብ ክፍልና ሰራተኛው በገዛ አገሩ ጥቂቶች ሲበለጽጉ እሱ የበይ ተመልካች ሆኗል። ብመረጥ ይሄን ኢፍትሐዊ የሆነውንና ለጥቂቶች ብቻ የቆመውን አድሎአዊ ስርዓት ለመላ ብራዚላዊ በእኩልነትና በፍትሐዊነት በሚያገለግል እተካዋለሁ አሉ። ከ2019 ዓ.ም ጀምሮ ስልጣን ላይ የነበሩትን ፕሬዚዳንት ሀየር ቦልሶናሮ ግን ለባለጠጋዎች የቆሙና ጸረ ዴሞክራሲ ናቸው ሲሉ ይከሷቸዋል። ቦልሶናሮ በበኩላቸው ሉላ አክራሪ ሶሻሊስትና ጸረ ነጻ ገበያ ስለሆነ አገሪቱን ወደ መቀመቅ ያወርዳታል። ከዚህ አደጋ ብራዚልን የምታደጋትና ብልጽግናዋን የማስቀጥለው እኔ ነኝ በማለት መራጮችን ቀሰቀሱ። ሆኖም ሉላ በመጀመሪያ ዙር ተቀናቃኛቸውን በጠባብ ልዩነት ቢመሩም ከ50 በመቶ በላይ ድምጽ ባለማግኘታቸው ለ2ኛ ዙር ተወዳድረው ዳግም በጠባብ ልዩነት አሸንፈው የብራዚል ፕሬዚዳንት ሆኑ። ደጋፊዎቻቸው አደባባይ በመውጣት ደስታቸውን በእንባ እየተራጩ ገለጹ። አማዞንም ወዳጁ ሉላ ስለተመረጡለት ሳያረግድ ይቀራል።
ፈጣሪ ሰላማችንን ያጽናልን ! አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ኅዳር 11/ 2015 ዓ.ም