እነሆ ! የሰላም አየር ሊነፍስ፣ የጦርነቱ እሳት ሊጠፋ ጊዜው ደርሷል። ስደት መፈናቀል፣ ርሀብና ስቃይ ‹‹ነበር›› ተብለው ሊጻፉ መንገዱ ጀምሯል። ሞትና ውድመት ፣ ለቅሶና ዋይታ ዝምታ ሊውጣቸው ከጫፍ ደርሷል። አሁን እነዚህን ቅስፈቶች የማናይ፣ የማንሰማበት ቅያስ ላይ ቆመናል።
ይህ መንገድ አቅጣጫው ወደ አንድ መስመር ይወስዳል። ምሪቱን ይዞ ለተጓዘ፣ ምልክቱን አይቶ ለተራመደ ደግሞ መዳረሻው አንድ አንድ ነው። ቀስቱ ከሰላም መንደር ያገባል። ወገግታው ጨለማን ገፎ ከንጋት ያደርሳል። ይህን የብርሀን መስመር የተከተሉ ሁሉ እፎይታቸው የበዛ፣ ተስፋቸው ያበበ ነው። የዘወትር፣ ህልማቸው ከራሳቸው ያድር ዘንድ መተማመኛን ይዘዋል።
ሰላም እስትንፋስ ላለው ሁሉ ታላቅ ዋጋ ያለው ዋስትና መሆኑ አያጠያይቅም። በተለይ ህይወታቸው በጦርነት እሳት የተፈጀ፣ ኑሯቸው በዚህ መቅሰፍት የተነጠቀ ወገኖች የሰላምን ትርጉም አሳምረው ያውቁታል። አገራችን ላለፉት ሁለት ዓመታት በጦርነት እጅጉን ስትፈተን ቆይታለች። ይህ መቅሰፍት የመዘዘው ጫፍም በቃላት ሊገለፁ የማይችሉ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳቶችን አሳርፎብናል ። አሁንም ድረስ ጠባሳው ባልሻረው መቅሰፍት ብዙሀን ህይወታቸውን ተነጥቀዋል። ቤት ንብረት ወድሟል፣ ስደትና መፈናቀል አይሏል።
ይህ እውነታ ለዓመታት ሰላማዊ ሆኖ የኖረውን ህዝብ በእጅጉ ፈትኖታል። ለልማትና ብልጽግና ስትንደርደር የኖረችውን አገር ህልም አጨናግፏል። የጦርነቱ እሳት የበርካቶችን ኑሮና ህይወት የኋሊት እንደማራመዱ ኪሳረው የበዛ፣ ችግሩ የሰፋ ሆኖ ቀጥሏል ።
ዓመታትን ያስቆጠረው የጦርነት እሳት ይበቃ ዘንድም እስከዛሬ የሰላማዊ አማራጮች ሲሞከሩ ቆይተዋል። አስካሁን በነበሩ መልካም አጋጣሚዎች በአገራችን ሰላም ይሰፍን ዘንድ ሲጥሩ የቆዩ አካላት አሁን ድካማቸው ፍሬ ይዞ ከመልካም ውጤት ደርሰዋል።
የሰላምን ዋጋና ቱርፋት የማይሹ አንዳንድ ልበ ክፉዎች ግን ጦርነቱን እንደምክንያት ተጠቅመው ህልማቸውን ሲፈቱ ዓላማቸውን ሲያሳኩ ቆይተዋል። ለእነዚህ አካላት ጠብና ሁከት ደስታቸው፣ ግጭትና ጦርነት ህይወታቸው ነው። ደም በፈሰሰ ቁጥር ገቢያቸው ያድጋል። አገር ሲወድም፣ ህዝብ ሲያልቅ፣ መፈናቀል ሲያይል ቋታቸው በሀሴት ይሞላል።
እነሱ ሰላም ይሉትን ቃል አይወዱትም ። መግባባት፣ መስማማት ይሏቸው እውነቶች የመንገዳቸው ዕንቅፋት ናቸው። ሁሌም እግርን ከእግር እያጋጩ ጠልፎ በመጣል አባዜ ሲስቁ ይውላሉ። አንደበታቸውን ሞርደው የኪሳቸውን ጸጋ ሲያደልቡ ይሉኝታና ሀፍረትን አያውቁም።
በውጭ አገራት የሚኖሩ አንዳንድ ዳያስፖራ ተብዬዎች ንጹሀንን ከእሳት ማግደው በፍሙ ራሳቸውን ሲያሞቁ መዋላቸውን እንደጀብዱ ሲቆጥሩት ኖረዋል። ዛሬም ድረስ ለሰላም ያላቸው ንቀት ከአደባባይ አውሎ የውስጣቸውን ጉድ እያጋለጠው ይገኛል። ሰላምን አንፈልግም ባዮቹ ሁከት ናፋቂዎች አሁን በሰላም ስምምነቱ በእጅጉ ተከፍተዋል።
ሰላምን እንደጦር የሚፈሩት ሁከት ናፋቂዎች በግላቸው በከፈቷቸው የሚዲያ መረቦች ራሳቸውን ለመሸጥ ጦርነቱን ሲጠቀሙበት ኖረዋል። በየጊዜው በሚነዟቸው የሀሰት ትርክቶችም የበርካቶችን ልብ አሸፍተው ተከታዮችን ለማብዛት ሲጥሩ ነበር። ይህ ሁሉ የሆነው እነሱ ጠርገው በደለደሉት የጦርነቱ ሜዳ ላይ ነበር ።
እነዚህ ሰላም ጠል አካላት ጆሮ ለሰጣቸው ሁሉ የሀሰት ወሬዎችን በማቀበል፣ ባልተገቡ መረጃዎች ልቦናን በማባበል የሚያህላቸው የለም። በእነሱ እሳቤ ጦርነቱ ለዝንት ዓለም ከቀጠለ ህልውናቸው ያብባል። የመኖር ህልማቸው ይፈታል።
አንዳንድ የውጭ አካላት ዓላማ ደግሞ የሰብአዊነት ድጋፍን በማሳበብ የጦርነቱን ዕድሜ ማራዘም ነው። የተፈጠረውን ግጭት በመከተል በእርዳታ ሰበብ ወደ አገራችን የሚገቡ ተላላኪዎች እሳቱን እያዳፈኑ ባሻቸው ጊዜ ለማንደድ ሰበብ ሲፈጥሩ ቆይተዋል። በእርዳታ ሰበብ እግራቸው ምድራችንን በረገጠ ቁጥርም ከመጡበት ዓላማ በተቃራኒው የመቆማቸው እውነት ‹‹ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ›› ን አስተርቷል።
ይህ ብቻ አይደለም። ‹‹ፖለቲከኞች ነን›› የሚሉና ከጦርነቱ የበዛ ትርፍን የሚሹ አካላትም አጋጣሚውን እንደ መልካም ዕድል ሲጠቀሙበት ቆይተዋል። መንግስትን ‹‹እንቃወማለን›› ባዮቹ ሀይሎች ራሳቸውን በውጭ አገራት ጓዳዎች ወሽቀው በሚረጩት መርዝ ሰላም እንዳይወርድ፣ ጦርነቱ በጥልቀት እንዲቀጥል ሲጥሩ ኖረዋል።
ምላሰ ረጃጅሞቹና ዕንቅልፍ የለሾች በተለይ ለትግራይ ህዝብ ህልውና በማሳያነት የሚያቀርቡት እሴት የለም። ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ መፍትሄ የለሽ ንግግሮችን በመደስኮር ለራሳቸው ዕውቅናን ሲሸልሙ ከርመዋል። እነዚህ ተጽእኖ እንፍጠር ባዮች የውጭ አካላትን ምኞትና ፍላጎት ለማሳካት አበክረው የሚተጉ ናቸው።
እንደ ጋዜጠኛ ማርቲን ፕላውት አይነቶቹ በኢትዮጵያ ላይ ሀሰተኛ ዜናዎችን ሲያሰራጩ ቆይተዋል። ፕላውትን የመሰሉ የውጭ አገራት ተላላኪዎች ጦርነቱን አባብሶ ለማንደድም እንደቤንዚን አቀጣጣዮች ነበሩ። ይህ የቀድሞ የቢቢሲ ዜና ወኪል መረጃዎችን ፈብርኮ በማሰራጨት በኩል የሚያህለው አልነበረም። በሁለት ወገኖች መሀል ተገኝቶ ግጭትን በማባባስ በኩል ጥበቡን ተክኖበታል።
እንዲህ አይነቶቹን የውጭ አገራት ተላላኪዎች በማድነቅ ለጦርነቱ ድምቀት የሚሰጡ ሀይሎች የሚያገኙትን ትርፍ ከማሰብ የዘለለ የረባ ዓላማ የላቸውም። ሰላምን ከማወክ ባሻገር ከሚገኘው የነገ ህልም ላይ ተቀምጠው የነገዋን ትግራይ ያስባሉ። እነሱ ሌሎች በከፈሉት መስዋዕትነት የሚመጣን ሲሳይ በዋዛ ማለፍ ፈጽሞ ፍላጎታቸው አይደለም። የነገን ስልጣን ይናፍቃሉ።
ይህን ክፉ ዓላማ ከዳር ለማድረስ ሌት ተቀን የሚተጉት ሀይሎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሰላም እንዳይኖር፣ እርቅ እንዳይፈጠር ለማድረግ እጃቸው ሰፊና ረጅም ነው። በእነሱ ህልም ውስጥ ይህ ዕውን እንዲሆን ያለመሻታቸው እውነትም የሰሞኑን የሰላም ንግግር በግልጽ ሲቃወሙት ተስተውሏል።
በእነዚህ ጸረ ሰላም ሀይሎች ማንንነት ውስጥ ጠብና ጦርነት፣ ግጭትና መፈናቀል ቤቱን ሰርቷል። ሁሌም በንጹሀን ደም መፍሰስ፤ በእናት አባቶች ሞትና ስደት በአገር ውድመትና ታሪክ መጥፋት ውስጣቸው ይፈካል። ክፉ ዓላማቸው ያብባል።
እኛ ግን ዛሬ በታላቁ የሰላም ጎዳና ላይ ቆመናል። ፍቅርን ለሚሹ፣ ሰላምን ለሚፈልጉ ሁሉ ፈጽሞ ፊታችን አይዞርም፣ እጃችን አይታጠፍም። እነሆ! የሰላም አየርን እንፈልጋለን። የምንከተለው መንገድ የምንጓዝበት አቅጣጫ ሰላምና ፍቅር፣ እርቅና ስምምነት እንዲኖረው እንሻለን።
አሁን የጦርነትን ኮሽታ በእጅጉ ጠልተነዋል። ያለፍንበት መንገድ እሾህና ጋሬጣ የበዛበት ነበርና ልንመለስበት አንወድም። አዎ! መንገዶች ሁሉ ወደሰላም እንዲወስዱን፣ ከእርቅ መንደር እንዲያሳድሩን እንመኛለን።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ኅዳር 11/ 2015 ዓ.ም