በፌደራል መንግስት እና በሕወሓት መካከል ሲደረግ የነበረው ጦርነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተደረሰ የሰላም ስምምነት ታሪክ ሊሆን የተቃረበ ይመስላል፡፡ ታሪክ እንዲሆንም የብዙዎች ምኞት ነው፡፡
ጦርነቱ ካስከተለው ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት በተጨማሪ የኑሮ ውድነቱ ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ጫና አሳድሯል፡፡ በርካታ ተቋማት እና መሠረተ ልማቶች ወድመዋል በዚህም ከፍ ያለ የአገሪቱ ሀብት ባክኗል፡፡ ሠዎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው እንዳይሰሩም እንቅፋት ፈጥሯል፡፡
ጦርነቱ በተካሄደባቸው ሁለት ዓመታት ብዙዎቻችን ለጆሮ የሚሰቀጥጡ የጦርነት ዜናዎችን ሰምተናል፤ በተቃራኒውም ደግሞ አንዱ አንዱን ለመደገፍ የተሄደበትን ጥረትንም ለመመልከት ችለናል፡፡ የመረዳዳት ባህላችንም ተሟጦ እንዳለቀ በተስፋ እንድንሞላም ያደረጉ ብዙ ክስተቶች ተፈጥረዋል።
በዚህም የጦርነቱን አስከፊ ገጽታ በገለጽንበት ልክም መልካ የሚባሉ ታሪኮችንም ማየትና መስማት ችለናል፤ እነዚህ ታሪኮች ለነገዋ ኢትዮጵያ አንዳች የአስተማሪነት ፋይዳ እንደሚኖራቸው መገመት ብዙ የሚከብድ አይደለም፡፡
በጦርነቱ ወቅት አንዱ ከአንዱ ተለያይቶ በጎሪጥ ሲተተያይ እና የማይገባ ብሽሽቅ ውስጥ ሲገባ መመልከታችን ለችግሩ ተጨማሪ አቅም በመሆን አላስፈላጊ ዋጋ እንድንከፍል አድርጎናል።
በየትኛውም አይነት ምክንያት የተፈጠሩ ግጭቶችን/ አለመግባባቶችን በመፍታት አገርን እንደ አገር ለመሻገር እንዲህ ያሉ የማያንጹ ድርጊቶችአላስፈላጊ ዋጋ ከማስከፈል ባለፈ ምንም ፋይዳ የላቸውም፤ ሊኖራቸውም አይችልም።
ሠላምን፤ የሚጠላ ጤነኛ አይምሮ የለም፤ ከሠላም ብዙ ብናተርፍ እንጂ የምንጎዳው አንዳችም ነገር አይኖርም፡፡ በሀለቱ ተደራዳሪዎች መካከል ሠላም ሰፍኖ ልክ እንደትላንቱ በመቀሌ አደባባይ ላይ ብዙዎች መንሸራሸር ይፈልጋሉ፤ ሌሎችም ከመቀሌ ወደ ሌሎች ከተሞች እንደልባቸው ያለምንም ከልካይ እና መሸማቀቀ መንቀሳቀስ ይፈልጋሉ፡፡ በለቅሶ እና በሰቀቀን አልቆም ያለው የእናቶች እንባም የሚታበስ ይሆናል፡፡
ይህ የሚሆነው ድርድሩ በሠላም ሲጠናቀቅ እና ከሁለቱም ወገን ስምምነት ላይ ሲደረስ ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም ለጉዳዩ እውቀት የሌላቸው ሰዎች ‹‹ድርድሩ እኮ እንዲህ ሆነ ››፣ ‹‹ድርድሩ የማይሳካባቸው ምክንያቶች››፣ ‹‹ድርድሩ አይሳካም›› የሚሉትን እና መሰል አይነት አሉባልታዎችን ሊታቀቡ ይገባል።
መብራራት ያለባቸውን ጉዳዮች ሲያጋጥሙም በሚመለከታቸው አካላት ትንታኔ እና ማብራሪያ እንዲሰጥበት በማድረግ ስምምነቱ በስኬት እንዲጠናቀቅ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በዚህም ለስምምነቱ ተግባራዊነት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ፡፡
የስምምነቱን ተግባራዊነት የሚፈታተኑ የተዛቡ መረጃዎች በማሕበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ ሀሰተኛ ዜናዎችን የማሰራጨቱ ነገር እየተንሰራፋ የመጣ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፤ ምናልባትም ይህንን አጋጣሚ ለመጠቀም አስቦ ድርድሩ እንዳይሳካ ለማድረግ የሚንቀሳቀሰውን አካል በሚገባ ተከታትሎ ሪፖርት በማድረግ እርምጃ እንዲወሰድበት መሥራት ያስፈልጋል፡፡
አንዳንድ ጊዜም በሞኝነት ወይም በየዋህነት መረጃዎችን ለሕብረተሰቡ አካፈልን ብለው ሀሰተኛ ማስረጃዎችን የሚያሰራጩ ሰዎችንም ቢሆን እነርሱ የሚያሰራጩት መረጃ የሚያርሰውን ችግር በማስገንዘብ ድርድር እስኪጠናቀቅ ድረስ ድርሻቸውን በዝምታ እና በስክነት እንዲወጡ መሥራትም ይጠበቃል።
በከተማ ለምንኖር ለእኛ ጦርነቱ በተከሰተባቸው በአፋር፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች ላይ የደረሰውን ችግር ለመረዳት አዳጋች ሊሆንብን ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ ጦርነቱ ያደረሰው ችግር ለመረዳት የግድ የጦርነቱ ቦታ ላይ መገኘት አስፈላጊ ባለመሆኑ ስለ ሠላም እና ስለ እርቅ ሲባል እርስ በእርሳችን በመደጋገፍ እና በመወያየት ይህንን ክፉ ጊዜ በማለፍ ለነገ አገር ተረካቢ ዜጎች ሰላም የሠፈነባት አገር ለማስረከብ ብንሠራ ጥቅሙ መልሶ ለራስ ነው፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ ዛሬ ላይ አገራችን አሁን ባለችበት ቁመና ላይ እንድትገኝ የብዙ ድምር ውጤቶች ለዚህ ያድርሷት እንጂ፤ በአንድ ወቅት አገራችን በጦርነት ውስጥ የነበሩ አገራት በማስታረቅ ወደ ሠላም እንዲመጡ ከማድረግ አኳያ ሚናዋን በሚገባ ወመጣቷን በሚገባ ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ ስለሆነም መውደቅ እና መነሳት በየትኛው አጋጣሚ ያለ መሆኑን በመረዳት አገራችንን ከወደቀችበት ለማንሳት የሁላችንም ኃላፊነት መሆኑን መረዳትም ያሻል፡፡
አሁን ላይ መወቃቀሱም ይሁን መወነጃጀሉ ለማንም የሚፈይደው ነገር የለም፤ ይልቁንም ‹‹ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል ›› የሚለውን የአገራችንን ተረት በሚገባ በመረዳት እንዲህ ያለውን አጋጣሚ ለመጠቀም የአገር ውስጥ እና የውጭ ጠላት የማይቆፍሩት ነገር እንደማይኖራቸው በመገንዘብ እንዲህ ያለውን ነገር በንቃት እና በትኩረት ማየት ያስፈልጋል፡፡
ሌላው መነሳት ያለበት እንደ አገር ከሌሎች አገራት ጋር ሠላማዊ ግንኙነትን መፍጠር ያፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ ሠላም እንዲሰፍን ብርቱ ጥረት የሚያርጉ አገራትን ማመስገን የሚያስፈልግ ሲሆን፤ ነገር ግን ድብቅ አላማ ይኖራቸዋል ብሎ ማሳቡም አያስከፋም፡፡ ይህንን ደግሞ በጦርነቱ ወቅት ማን ምን እንዳደረገ አገር የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ ታዲያ በእንደዚህ አይነቱ ወቅት እጅ ለመጠምዘዝ ብዙ ሴራዎችን ሊያሴሩ የሚችሉ አገራት ሊኖሩ እንደሚችሉ በመገመት በብልጠት እና በንቃት መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡
በአጠቃላይ ስለ እናቶች፣ ስለ ህፃናቱ፣ አካላቸው ስለተጎዱት እና በዚህ ጦርነት ውስጥ ሕይወታቸውን አሳልፈው የሰጡትን ሁሉ በማሰብ ባቻ ሳይሆን ዜጎች እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው እንዲማሩ ብሎም እንዲሠሩ እና ሠላም የሠፈነባት አገር እንድትሆን ዛሬም ነገም ስለ ሠላም ማዜም የሚገባበት ወቅት ላይ መሆናችን በማመን ለሠላም መከፈል ያለበትን ዋጋ ሁሉ ለመክፈል እራስን ማዘጋጀት ተገቢና ወቅቱ የሚጠይቀው ትልቁ ጉዳይ ነው።
በምስጋና ፍቅሩ
አዲስ ዘመን ኅዳር 10/ 2015 ዓ.ም