ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ እምብዛም በማትታወቅባቸው ስፖርቶች ተስፋ ያለው ውጤት እያስመዘገበች ትገኛለች። ይህ የተገኘው ደግሞ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ሀገራቸውን ወክለው ተካፋይ በሆኑ ታዳጊዎች ነው። በእርግጥም መሰረቱን በታዳጊዎች ላይ ያደረገ ስፖርት ውጤታማ የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነው። በዚህም ምክንያት ሀገራት በታዳጊና ወጣቶች ላይ በማተኮር እና ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ይሰራሉ።
ስፖርተኞችን ከታዳጊነታቸው አንስቶ በዘመናዊ ስልጠና አቅማቸውን ማጎልበት እንዲሁም ልምድ እንዲያገኙ በውድድሮች ላይ ማሳተፍ ሀገርን ለረጅም ጊዜ በስኬታማነት እንዲወክሉ በማድረግ ረገድ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። በመሆኑም በሀገር አቀፍ ደረጃ የታዳጊ ፕሮጀክቶች አተኩሮ የሚሰራ ፕሮግራም ተቀርጾ እየተሰራበት ይገኛል። ከትምህርት ቤቶችና ከፕሮጀክቶች የተገኙ ታዳጊ ስፖርተኞችም በእድሜያቸው ከሚካሄድ ውድድር ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገርን እስከማኩራት መድረሳቸውም በተግባር እየታየ ይገኛል። ለአብነት ያህልም ኢትዮጵያ በማትታወቅበት የወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት ከዓለም ቻምፒዮና እስከ ኦሊምፒክ የደረሰ ተሳትፎ ያገኘችው በታዳጊ ስፖርተኛ ነው። በቅርቡም በፈረስ ስፖርት የተገኘውን ስኬት ማንሳት ይቻላል።
ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ታዳጊ ዋናተኞችን የሚያበረታታና ስፖርቱንም በዘላቂነት ለማሳደግ የሚችል እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል። የአፍሪካ የውሃ ማማ በመባል የምትታወቀው ኢትዮጵያ ካላት የተፈጥሮ ጸጋ አንጻር ምቹ ከሆኑ ስፖርቶች መካከል አንዱ የውሃ ዋና ነው። ሀገሪቷ በውሃ ሃብት የበለጸገች ትሁን እንጂ በስፖርቱ ያለችበት ሁኔታ እንዲሁም ተዘውታሪነት ግን አነስተኛ ሊባል የሚችል ነው። ከዚህ ባለፈ ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ሁለት ኦሊምፒኮች ላይ (ሪዮ እና ቶኪዮ ኦሊምፒኮች) በውዝግብ የታጀበ ተሳትፎ ማድረጓ ስፖርቱ ያለው ስም እንዲጠለሽ ምክንያት ሆኗል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ትኩረቱን በተለይ ታዳጊዎች ላይ አድርጎ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሰረት ደምሱ ይጠቁማሉ። ለዚህ ማሳያ የሚሆነውም ከትላንት አንስቶ በታንዛኒያ እየተካሄደ ባለው የምስራቅ አፍሪካ ዞን ሶስት የውሃ ዋና ቻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ በታዳጊዎች እንድትወከል መደረጉን ነው። ቻምፒዮናው የሚካሄደው በተለያዩ የዕድሜ ደረጃዎች ቢሆንም ፌዴሬሽኑ የሚያሳትፈው ግን ከ14 እና 17 ዓመት በታች ዋናተኞችን ብቻ ነው። እነዚህ ስፖርተኞች የተመረጡት ከኢትዮጵያ ቻምፒዮና ላይ ሲሆን፤ በውድድሩ ተካፋይ የነበሩት ምንም ዓይነት የውድድር እድል ያላገኙና በታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክቶች የተወጣጡ ዋናተኞች ብቻ ነበሩ።
ይህም የሚደረገው እንደ ሀገር ለውጥ መምጣት ስላለበት እና ተተኪዎችን ለማፍራት እንደሆነም ፕሬዚዳንቷ ያስገነዝባሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ፌዴሬሽኑ ከዓለም አቀፉ የውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ጋር በመሆን የታዳጊ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽና የተለያዩ ድጋፎችንም በማድረግ እየሰራ ይገኛል። በተለያዩ ክልሎች ለተከፈቱት ፕሮጀክቶች የስልጠና መሳሪያዎች፣ የዋና ልብሶች እና ሌሎች ድጋፎችን ከመስጠት ባለፈ ከክልል የውሃ ስፖርት ፌዴሬሽኖች ጋር በቅርበት በመነጋገር እንዲሁም ክትትልና ቁጥጥር በማድረግም እየሰሩ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የውሃ ስፖርት ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅ መሆኑ ግልጽ ነው፤ ነገር ግን ባለው ነገር የተሻለ ለመሆን መስራት የሚለው በአሁኑ ወቅት ፌዴሬሽኑን እየመራ የሚገኘው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የአራት ዓመት የስራ ዕቅድ ነው። በመሆኑም የታዳጊ ፕሮጀክቶችን ከማቋቋምና ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ፣ በሀገር ውስጥ ውድድሮችን በማዘጋጀትና በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይም በመሳተፍ ልምድ እንዲገኝ እየተደረገ መሆኑንም ወይዘሮ መሰረት ይገልጻሉ። ይህም በቶሎ ውጤታማ ባያደርግም በጊዜ ሂደት ግን በስፖርቱ ተተኪዎችን ለማፍራትና እንደሀገርም ስኬታማ ለመሆን የሚያስችል ነው። ለዚህም ባለድርሻ የሆኑ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡና ከፌዴሬሽኑ ጎን እንዲቆሙም ነው ፕሬዚዳንቷ ጥሪ ያቀረቡት።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ህዳር 8/2015