የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ብሔራዊ ቡድን በምስራቅ አፍሪካ የውሃ ዋና ቻምፒዮና ለመሳተፍ ትናንት ማለዳ ወደ ታንዛኒያ ዳሬ ሰላም ተጉዟል። ብሔራዊ ቡድኑ በ ታንዛንያ ዳሬሰላም በሚካሄደው በአፍሪካ ዞን ሶስት የምስራቅ አፍሪካ የውሃ ዋና ቻምፒዮና ላይ ለመሳተፍ መሆኑን ከኢትዮጵያ ውሃ ዋና ስፖርቶች ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ አመልክቷል።
ቻምፒዮናው በፈረንጆቹ ከህዳር 16 እስከ 20 የሚካሄድ ሲሆን፣ በዚህ ቻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን ወክለው ሁለት ታዳጊ የውሃ ዋና ስፖርተኞች እንደሚሳተፉ ታውቋል። ኢትዮጵያን ወክለው በቻምፒዮናው የሚሳተፉት ታዳጊዎቹ በ17 ዓመትና በ14 ዓመት የእድሜ ካታጎሪ የሚወዳደሩ መሆናቸውም ከፌዴሬሽኑ መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በቻምፒዮናው ኢትዮጵያን ወክሎ የሚወዳደረው ብሔራዊ ቡድን በጊዮን ሆቴል ልምምድ ሲያደርግ ቆይቷል። እነዚህ ታዳጊዎች ባለፈው ነሐሴ ላይ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በቢሾፍቱ ምንም የውሃ ዋና የውድድር እድል ላላገኙ ታዳጊዎች ባዘጋጀው ውድድር ላይ ተሳታፊ የነበሩና የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ መሆናቸውም ተጠቁሟል።
ይህም ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ኢትዮጵያ በውሃ ዋና ስፖርት ተተኪና ውጤታማ ስፖርተኞችን ለማፍራት በታዳጊዎች ላይ ለመስራት በተያዘው የትኩረት አቅጣጫው መሰረት በተግባር እየተንቀሳቀሰ መሆኑ አንዱ ማሳያ እንደሚሆን ፌዴሬሽኑ ገልጿል።
በውድድሩ የሚሳተፈው ብሔራዊ ቡድን ወደ ዳሬሰላም ሲያቀና የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሰረት ደምሱን ጨምሮ፣ የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ እንዲሁም የታዳጊ ስፖርተኞቹ ወላጆች ተገኝተው አሸኛኘት በማድረግ መልካም እድል እንዲገጥማቸው ተመኝተዋል።
በወቅቱም ፕሬዚዳንቷ ወይዘሮ መሠረት ደምሱ፣ “ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ባለው አቅም ሁሉ ከጎናችሁ ይቆማል፣ እናንተም ያላችሁን አቅምና ችሎታ ሁሉ ተጠቅማችሁ ለወከላችሁት ህዝብ ጥሩ ውጤት ለማምጣት ጠንክሩ” በማለት ለታዳጊዎቹ የመልካም እድል ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንቷ አክለውም፣ ፌዴሬሽኑ ተተኪዎችን ለማፍራት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በቀጣይም አውስትራሊያ በሚካሄደው የዓለም የውሃ ዋና ቻምፒዮና ላይ የኢትዮጵያ ውሃ ዋና ስፖርቶች ብሔራዊ ቡድን በታዳጊዎች እንደሚወከል ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ታዳጊ ወጣቶች የውሃ ዋና ቻምፒዮና ባለፈው ነሐሴ ለመጀመሪያ ጊዜ በቢሾፍቱ ከተማ የተካሄደ ሲሆን፣ በመኮንኖች የውሃ ዋና ገንዳ ላይ በነበረው ፉክክር ከክለቦችና ክልሎች የተውጣጡ በርካታ ታዳጊ ዋናተኞች አቅማቸውን ማሳየት ችለዋል።
በተለያዩ ስፖርቶች በሚካሄዱ የታዳጊ ወጣቶች ውድድሮች ላይ ከእድሜ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዚህ የውሃ ዋና ቻምፒዮና ለመቅረፍ አገር አቀፍ ፌዴሬሽኑ ጠንካራ ስራዎችን አከናውኖም የተሻለ ውጤት ማሳየት ችሏል። ይህም በቻምፒዮናው በትክክለኛ እድሜ ታዳጊ ወጣቶች የውድድር እድል አግኝተው ራሳቸውን የሚያሳዩበት አጋጣሚን እንደፈጠረ ማስተዋል ተችሏል።
አገር አቀፍ ቻምፒዮናው ኢትዮጵያ በውሃ ዋና ስፖርት በታዳጊና በወጣቶች ያላትን እምቅ አቅም ለመረዳት ያስቻለ ሲሆን፣ በስፖርቱ ወደ ፊት ኦሊምፒክን በመሳሰሉ ታላላቅ መድረኮች ኢትዮጵያን የሚወክሉ ተተኪዎችን ለማፍራት ትልቅ ተስፋ የታየበትም ነበር። ፌዴሬሽኑም በእድሜ ረገድ ዘወትር ለሚፈጠሩ ችግሮች ቀደም ብሎ ከክልሎችና ከክለቦች ጋር ተነጋግሮ መግባባት ላይ በመድረሱ ተወዳዳሪዎች በትክክለኛ እድሜያቸው ወደ ውድድር መምጣት ችለዋል። ፌዴሬሽኑም ይህን መልካም ጅምር በማስቀጠል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት በመስራት በታዳጊ ወጣቶች ላይ ጠንካራ ስራ እየሰራ ይገኛል።
የዓለም አቀፉ ውሃ ስፖርቶች ማህበር (ፊና) በአፍሪካ ታዳጊ ወጣቶች ስፖርቱን ለማስፋፋትና በአህጉሪቱ ቀጣይ ትውልድ ላይ ያተኮሩ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ በዳሬሰላም የሚካሄደውም ውድድር የዚህ እንቅስቃሴ አንድ አካል ነው ሲሆን የፊፋ ፕሬዚዳንት ሁሴን አል ሙሳላም ከእውቅ የስፖርቱ ኮከቦች ጋር የተለያዩ የአፍሪካ አገራትን እንደሚጎበኙ ታውቋል፡፡ ከነዚህም መካከል ኔዘርላንዳውያኑ የ2016 ሪዮ ኦሊምፒክ የስፖርቱ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ፌሪ ዊርትማን፣ የሶስት ጊዜ የኦሊምፒክ ቻምፒዮኑ ራኖሚ ክሮሞዊጆ አፍሪካን ይጎበኛሉ፡፡ ለጉብኝቱ ከተመረጡ ሰባት የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ስትሆን ቡሩንዲ፣ ጅቡቲ፣ ግብፅ፣ ርዋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ዩጋንዳና ታንዛኒያ እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡ ጉብኝቱ በነዚህ አገራት ውስጥ የውሃ ዋና ገንዳዎችን በስፋት ለወጣቶች ተደራሽ ለማድረግ መነሳሳትን እንደሚፈጥርም ተነግሯል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ህዳር 7/2015