ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 2ተኛ ዓመት የጋራ የሥራ ዘመን መክፈቻ ላይ ያደረጉት ንግግር ተከትሎ፤ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ትናንት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች መነሻ በማድረግ የሰጡት ማብራሪያና ምላሽ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
የተከበሩ አፈጉባኤ፣ የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት፤ ክቡር ፕሬዚዳንት በሁለቱ ምክር ቤት መክፈቻ ላይ ያቀረቡትን ንግግር አስመልክቶ እንዲሁም ተጨማሪ ሃሳቦችን ምላሽ ለመስጠት ዕድል ስላገኘሁ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ። በተቻለ መጠን የተነሱ ጥያቄዎችን አድሬስ ለማድረግ እሞክራለሁ።
በመጀመሪያ ከኢኮኖሚ ጋር ተያይዞ ለተነሱ ጥያቄዎች የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታችን ምን ይመስላል? ዕድገታችን በንግግሩ አልተመላከተም፤ የዘንድሮ ዓመት የዕድገት ዕቅዳችን ምን ይመስላል የባለፈው ዕድገታችንስ ምን ያህል ነው? የሚል እና መሰል ጥያቄዎች ተነስተዋል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላለፉት ዓመታት በተለይም ባለፈው ዓመት በርከት ያሉ ሰው ሰራሽ ፈተናዎች እና አደጋዎች ገጥመውት እንደነበር ሁላችሁም ታስታውሳላችሁ። ከፍተኛ ፈተና ከፍተኛ (ቻሌንጅ) የነበረበት ዓመት ስለነበረ፤ ጦርነት በአገር ውስጥ በውጪም የዩክሬን እና የራሺያ ጦርነት በዓለም ደረጃ የፈጠረው ጫና፣ እንዲሁም ድርቅ፣ ኮረና ተያይዘው የመጡ ጫናዎች በስፋት ዱቀሳ ያሳረፉበት ዓመት ነበር ማለት ይቻላል።
ነገር ግን አንድ ሰው በፈተና ውስጥ ሲያልፍ፣ በችግር ውስጥ ሲያልፍ ያ ሰው ጠንክሮ በርትቶ እንደሚወጣው ሁሉ፤ የኢትዮጵያም ኢኮኖሚ (ረዚሊያንት) መሆኑን በቀላሉ የማይሰበር መሆኑን፤ የጀመረውን የዕድገት ትራጀክተሪ ማስቀጠል የሚችል መሆኑን ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚስቶች ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ይህንን ጉዳይ የሚገመግሙ ሰዎችን ግራ እስኪያጋባቸው ድረስ ኢኮኖሚው ያጋጠመውን ፈተና ተቋቁሞ መሻገር ችሏል። ጫና ተቋቁሞ መሻገር ችሏል ሲባል፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2014 የበጀት ዓመት መጨረሻ ላይ 6 ነጥብ 16 ትሪሊየን ደርሷል። ይህም ማለት በዶላር ሲሰላ 126 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር ደርሷል። ታስታውሳላችሁ 100 ቢሊየን ለመድረስ ከ100 ቢሊየን ለመሻገር ያለንን ጉጉት በዚሁ ምክር ቤት አቅርቤ ነበር። የነፍስ ወከፍ ገቢ ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ 1ሺህ 212 ዶላር ደርሷል።
ይህ ብቻ ሳይሆን ከምስራቅ አፍሪካ አንደኛው ግዙፉ ኢኮኖሚ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሆኗል። ከሰብ ሰሃራን አፍሪካን አገራት ሶስተኛው ግዙፍ ኢኮኖሚ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሆኗል። ይህ ዳታ የመንግስታችን ዳታ አይደለም። የዎርልድ ባንክ ዳታ ነው። ዎርልድ ባንክ ዘንድሮ ባደረገው ግምገማ ከምስራቅ አፍሪካ አንደኛው ኢኮኖሚ ተበልጦ የነበረውን አስተካክሎ፤ በሰብ ሰሃራም ሶስተኛው ግዙፉ ኢኮኖሚ መሆኑን እና ቅድም ያስቀመጥኳቸውን ፊገሮች አስቀምጧል። በዚህ ፊገር ሙሉ ለሙሉ እኛ አንስማማም። ምክንያቱም ሁላችሁም እንደምትገነዘቡት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፎርማል ከሆነው
ኢኮኖሚ ያልተናነሰ ኢንፎርማል ኢኮኖሚ አካውንት ለማድረግ የሚያስቸግሩ የኢኮኖሚ ትስስር አለው። ኮንትሮባንዱ ይታወቃል። ካሽ በእጅ የማቆየት ልምምዱ ይታወቃል። ለምሳሌ፣ በአንዳንድ የአፍሪካ አገራት አርሶ አደሮች ግብር እንዲከፍሉ ስለሚደረግ፤ አብዛኛው እርሻም ኮሜርሻላይዝድ እየተደረገ ስለሆነ ምን ያህል ሃብት እዛ አካባቢ እንደሚንቀሳቀስ በቀላሉ ማወቅ ይቻላል። የኢትዮጵያ አርሶ አደር እንደምታውቁት ግብር እምብዛም የሚከፍል አይደለም። ስንዴ አመረተ ሸጠ ብንልም በግብር ውስጥ የሚያልፈው ትራንዛክሽኖችን ማየት ስለማንችል፤ በቤት የማስቀመጥ ልምምዱም ሰፊ ስለሆነ አዳዲስ የጀመርናቸውን ሀገራዊ ሥራዎችም ታሳቢ የማያደርግ ስለሆነ እዚህ ካስቀመጥኩት ቁጥር በእጅጉ የገዘፈ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ነገር ግን ሁላችንንም እንዲያስማማን ዎርልድ ባንክ ያስቀመጠውን ዳታ ብቻ ነው ያስቀመጥኩላችሁ።
ይህ የኛ ፍላጎት ነው። የብልፅግና ፍላጎት በአፍሪካ ገዘፍ ካሉ ኢኮኖሚዎች ውስጥ አንዱ ማድረግ አለብን። ራቅ ብሏል፤ በሕዝቡ ቁጥር እና ባለው ፖቴንሺያል የሚመጥን አልነበረም የሚል ጉጉት፣ ጥያቄ ፣ ፍላጎት እና ትጋት ነበር። የዛ ውጤት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ይሔ ነገር ጦርነት ባይኖር ኮረና ባይኖር ምን ልንሰራ እንችል ነበር የሚለውን እኔም አነሳለሁ ፤ሌሎችም ያነሳሉ። እኔ ባለኝ ግምት ፈተናዎቹ እና ቻሌንጁ ይበልጥ እንድንሰራ፤ እንዳንተኛ አግዞናል። የራሱ ስብራት ቢኖረውም፤ ጠንክሮ ለመስራት ግን ዕድል ፈጥሯል የሚል የፀና እምነት አለኝ። አሁንም ጠንክረን ከሰራን ይሔን ውጤት ማሻሻል እንደምንችል መንግስት ያምናል ፤እኔም አምናለሁ።
የባለፈው ዓመት የጂዲፒ እድገት ስድስት ነጥብ አራት ፐርሰንት ነው። ቅድም ያነሳኋቸውን ፈተናዎች እንዳለ ይዞ ስድስት ነጥብ አራት ፐርሰንት ዕድገት ተመዝግቧል። በዚህ ዓመት ያለን ዕቅድ ቢያነስ ሰባት ነጥብ አምስት በተለይ አሁን የተፈጠረው የሰላም ሁኔታ ማስጠበቅ ከቻልን ቢያንስ ሰባት ነጥብ አምስት ፐርሰንት እናድጋለን ብለን እናስባለን። የባለፈው ዓመት ስድስት ነጥብ አራት ዕድገት የተረጋገጠው ቀደም ሲል እንዳነሳችሁት ብዝሃ ዘርፍ፣ ብዝሃ ተዋናይ መሆን አለበት። ኢኮኖሚያችን፣ ግብርና መር ኢንደስትሪ መር እያልን በተወሰነ ሴክተር መታቀብ የለብንም። ሰፋ ያሉ የልማት ዘርፎችን እንደዋና መንቀሳቀሻ አድርገን ብንሰራባቸው ፖቴንሺያሎች ስላሉ ሊወጡ ይችላሉ። ልናድግ እንችላለን የሚል እሳቤ ስለነበረ ነው በክብር ፕሬዚዳንቷ ንግግር ላይ ያልተካተተው፤ ይህ ምክር ቤቱ ባፀደቀው የዕድገት ፍኖተ ካርታ ላይ በዚህ ዓመትም ባለፈው ዓመትም ግምት (ትልም) ዕቅድ ተቀምጧል። ስለዚህ በዚህ ዓመትም ምን ያህል ማደግ እንደምንፈልግ በዕቅዳችን ስለተቀመጠ ነው። በንግግራቸው ያልተቀመጠው ነገር ግን አሁን ካለው ሁኔታ ጋር ተያይዞ ከመጣው ሁኔታ ጋር ቢያንስ ሰባት ነጥብ አምስት በመቶ ዕድገት ይጠበቃል በዚህ ዓመት።
የባለፈው ዓመት ስድስት ነጥብ አራት ፐርሰንት ዕድገት በሴክተር ከፍለን ብናይ አንደኛው ግብርና ነው። ስድስት ነጥብ አንድ ፐርሰንት ዕድገት አስመዝግቧል። በግብርና ሁላችሁም በየምርጫ አካባቢያችሁ ስትሄዱ እንዳያችሁት በስንዴ እጅግ አበረታች ውጤት ተገኝቷል። ከስንዴ ባሻገር ብዙ ባንናገርለትም ሩዝ ከባለፈው ዓመት (2013 ዓ.ም) አካባቢ እስከ አምስት ሚሊየን ኩንታል እናስገባ ነበር ከውጭ፤ ዘንድሮ አማራ ክልል በሩዝ ምርት የጀመረውን ጥሩ ልምድ በኦሮሚያ እና በደቡብ አስፋፍተን ቢያንስ ስምንት ሚሊየን ኩንታል እንጠብቃለን። እንደ ስንዴ ኤክስፖርት ባንልም ሩዝ ኢንፖርት ማድረግ አያስፈልገንም። በአገር ውስጥ ሩዝ ለማምረት የሚያስችል፤ በአገር ውስጥ የተመረተውን ሩዝ ለመጠቀም የሚያስችል ቁጥር እንዳለ ዘንድሮ ማየት ተችሏል።
ከዛ ባሻገር ግን ሩዝ ወደፊትም ኢትዮጵያ ከፍተኛ ፖቴንሺያል እንዳላት ትምህርት ተወስዶበታል። አንደኛ፣ ምርታማነቱ፤ ሰባ ሰማኒያ ኩንታል በሔክታር የተገኘባቸው ቦታዎች አሉ። ከፍተኛ ምርታማነት አለው። ሁለተኛ፣ የሚጠቀምበት አካባቢም ከዚህ ቀደም በስፋት ለእርሻ ፐርፐዝ ያልዋሉ ቦታዎችንም ጭምር ማስፋት ስለሚቻል ሩዝ በሚቀጥሉት ዓመታት ልክ እንደስንዴው በከፍተኛ ዕምርታ ወደ ኤክስፖርት የሚያድግ እንደሚሆን ይጠበቃል። ዘንድሮ ግን ቢያንስ ከውጪ የምናስገባውን ለማስቀረት የሚያስችል ውጤት ተገኝቷል።
በቆሎም እንደዚሁ ነው። በበቆሎ ከፍተኛ ምርት ነው የተገኘው። ስንዴ ስንዴ የሚባልበት ምክንያት ስንዴ ስላልነበር ከዚህ ቀደም በዚህ ማግኒቲውድ እና በስፋት ስለተሰራ እንጂ በቆሎ ላይም ያለው ውጤት እጅግ አበረታች ነው። ከፍላጎታችን በላይ የሆነ የበቆሎ ምርት በዘንድሮ ክረምት ተገኝቷል። በፍሩት ያው የምታውቁት ነው ጅማሮዎቹን፤ በቅርቡ አንድ ቦታ ላይ የዛሬ ሰባት ወር ተኩል ስምንት ወር የተተከለ ፓፓያ ከአንድ ግንድ እስከ ሰማኒያ እስከ ዘጠና ፍሬ የሚያበቅል ፓፓያ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በሰባት ሔክታር ላይ የለማ ማየት ችያለሁ። በፍሩት ኢትዮጵያ ከፍተኛ ፖቴንሺያል አላት። ጅማሯችን የግብርና ሴክተሩ ዕድገት እንዲያመጣ አድርጓል። ቡና ባለፉት አራት አመታት ከአራት ነጥብ ሰባት ቢሊየን በግሪን ሌጋሲ ውስጥ ከተቀመጠው ውጪ ከአራት ነጥብ ሰባት ቢሊየን በላይ አዳዲስ የቡና ችግኞች ተተክለዋል። ዘንድሮ በቡና ምርት ከ20 በመቶ በላይ ዕድገት ይጠበቃል።
እነዚህ ተደምረው ሲታዩ በኤክስፖርቱ በምግብ ራስን በመቻልም አጠቃላይ በማሳደግ ደረጃ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው። ግብርና ላይ የጀመርነው ሥራ የእናንተም ድጋፍ፣ የመንግስት ቁርጠኛ አመራር ተጠናክሮ ከቀጠለ ኢትዮጵያን የዳቦ ቅርጫት ማድረግ የሚያስችል መሠረት እንዳለ ያመላክታል። ነገር ግን አሁንም ጅማሮ ነው። መስራት ከሚገባን በእጅጉ ገና ሩቅ ነን ያለነው። ዋናው ፍላጎታችን ገበሬን እና በሬን መለያየት ነው። ገበሬ እና በሬ ከመሬት ጋር ባለ ከእርሻ ጋር ባለ ትስስራቸው ተላቀው በሌላ መንገድ ለምግብነት የሚውል የደለበ በሬ ማርባትና ማዘጋጀት የገበሬ ሥራ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ለእርሻ ፐርፐዝ በሬን እየገፉ ማረስ የሚቀርበት ደረጃ እስከምንደርስ በግብርና የተጀመረው ጥረት መቀጠል ይኖርበታል። ከዚህ አንፃር ብዙ ሥራ ይጠበቅብናል፤ ብዙ ርቀት አልሔድንም፤ ውጤቱ ተስፋ የሚሰጥ ቢሆንም።
ሁለተኛው ዕድገት፣ ኢንደስትሪ ነው። ኢንደስትሪ ዘንድሮ አራት ነጥብ ዘጠኝ ፐርሰንት ዕድገት አስመዝግቧል። ኢንደስትሪ ከአምናው በተወሰነ ደረጃ ቅናሽ አሳይቷል። ቅናሽ ያሳየበት ምክንያት በኮንስትራክሽን ዘርፍ ከሲሚንቶ ጋር ተያይዞ ያለው ዕድገት ያዝ የተደረገ ስለሆነና እንደአምናው ስላልሆነ አጠቃላይ ኢንደስትሪው ላይ ያሳደረው ጫና ቢኖርም፤ በማኑፋክቸሪንግ ግን ጥሩ ውጤት ተገኝቷል። በተለይ ኢትዮጵያ ታምርት በሚለው የኢንደስትሪ ሚኒስቴር የጀመረው እጅግ ተስፋ ሰጪ ሥራ በርከት ያሉ የቆሙ ኢንደስትሪዎች ሥራ እንዲጀምሩ ለማድረግ ጥረት በመደረጉ በማኑፋክቸሪንግ የተሻለ ውጤት ተገኝቷል። በዚህ ዓመት ይህንኑ ጥረት በከፍተኛ ደረጃ በማጠናከር ከፍ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል።
ሶስተኛው፣ ሰርቪስ ነው። ሰርቪስ ሰባት ነጥብ ስድስት ፐርሰንት ዕድገት አስመዝግቧል። ድርሻውም ከአጠቃላይ ጂዲፒ ከፍተኛ ነው። ሰርቪስ ውስጥ ብዙ የሚጠቀሱ ሴክተሮች ያሉ ቢሆኑም፤ ከዋና ዋናዎቹ አንደኛ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኮረና ጊዜ ጀምሮ የነበረውን ጫና ተቋቁሞ ተደራሽነቱን እያሰፋ የአፍሪካ ኩራት፤ የኢትዮጵያ ኩራት መሆን በመቻሉ እና ትርፋማ ስለሆነ አንዱ የሰርቪስ የትራንስፖርት ሴክተሩን ከፍ ያደረገው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው። ሁለተኛው፣ ኢትዮ ቴሌኮም ነው። ኢትዮ ቴሌኮም በለውጡ ማግስት 37 ሚሊዮን ገደማ ሰብስክራይበር ነበረው። ዛሬ 68 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሰብስክራይበር አለው። ከፍተኛ እምርታ ከታየባቸው ሴክተሮች አንዱ ኢትዮ ቴሌኮም ነው። የሰብስክራይበር ቁጥር ብቻ ሳይሆን በዚያው ልክ ተደራሽነት በዚያው ልክ ትርፋማነትም አድጓል። በግጭት ምክንያት የተስተጓጎሉ ቦታዎች ቢኖሩም።
አምና የምታስታውሱት የጀመርነው የሞባይል ባንኪንግ እንኳን እንደ ምሳሌ ቢወሰድ 25 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎች በቴሌ ብር መጠቀም ጀምረዋል። 25 ነጥብ 5 ሚሊዮን በአንድ ዓመት ውስጥ እጅግ የሚያበረታታ ውጤት ነው። በእነዚህ ሰዎች የነበረው ትራንዛክሽን ግን ከ134 ቢሊዮን ብር በላይ ነው። ቴሌ ብር እያደገ፤ ብዙዎችን እያገናኘ በቀለጠፈ መንገድ ሰርቪስ ለመስጠት እድል እየከፈተ መሆኑን ነው ያመላከተው።
ከዚሁ ከቴሌ ጋር ተያይዞ አንደኛው አዕማድ አንደኛው የእድገታችን ምሰሶ ቴክኖሎጂ አይ.ሲ.ቲ ስለሆነ ባለፉት ዓመት፣ ዓመት ተኩል ገደማ በ20 የሚጠጉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከ40 በላይ ሰርቪስ ኦቶሜት ተደርጓል። ለምሳሌ ትራፊክ ሲቀጣን ከዚህ ቀደም መንጃ ፈቃዳችን ተወስዶ ቢሮ ሔደን ነው የምንወስደው፤ አሁን ቅጣት በስልካችን ከዚያው ቦታ እንከፍላለን። እንደዚህ አይነት ሰርቪሶች በመንግስት ከ40 በላይ በግል ኩባንያዎች ከ200 በላይ ሰርቪስ መስጠት ተጀምሯል። በቴሌኮሙኒኬሽን ብቻ። እያንዳንዱ ተቋም በራሱ ሶፍትዌር ዲቨሎፕ አድርጎ የሚሰራውን አያካትትም። ይህ የኦቶሜሽን ስራ እና እድገት ለሰርቪስ ኢንዱስትሪው ማደግ የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል።
ሶስተኛው፣ ፋይናንስ ነው፤ ሰርቪስ ላይ ትርጉም ያለው እድገት እንድናገኝ ያደረገው የፋይናንስ ሴክተሩ ነው። የፋይናንስ ሴክተር በ21 በመቶ አድጓል። የፋይናንስ ሴክተር አጠቃላይ ያለው ሀብት 2 ነጥብ 3 ትሪሊየን ብር ደርሷል። ታስታውሳላችሁ ትሪሊየን ተሻገርን ያልንበትን ጊዜ፤ እዚሁ ፓርላማ ውስጥ። የፋይናንስ ሴክተር ብቻ 2 ነጥብ 3 ትሪሊየን አጠቃላይ ሀብት መያዝ ችሏል።
ቅድም በቴሌኮም 25 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎች የቴሌ ብር ደንበኛ ሆነው ይጠቀማሉ ያልኳችሁን በባንክ አገልግሎት ግን 82 ነጥብ 2 ሚሊዮን ደብተሮች (አንዳንድ ሰው አምስትም አስርም ስለሚኖረው በሰው ሊለካ አይችልም) ደብተሮች ከ80 ሚሊዮን በላይ የባንክ ደንበኞች ተፈጥረዋል። በዚህም በዲፖዚት መልክ ባንክ በዚህ ዓመት የተቀመጠው 1 ነጥብ 6 ትሪሊየን ብር ነው። የፋይናንሻል ሴክተሩ በከፍተኛ ደረጃ እምርታ እያሳየ መሆኑን ያመላክታል። ብድር በዚህ ዓመት 29 በመቶ ነው ያደገው፤ አምና ከነበረው። 353 ቢሊዮን ብር ብድር ተሰጥቷል። ይህ የፋይናንሻል ሴክተር እድገት የቴሌኮሙንና የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ የሰርቪስ ኢንዱስትሪው በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ አስችሏል። በዚህም ዓመት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተስፋ ይደረጋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ፕሮጀክቶቻችን ሁሉም ማለት በሚቻል ደረጃ እጅግ ፈታኝ የሆነ ጊዜ ቢሆንም፣ ሜጋ የሚባሉ ፕሮጀክቶቻችን በሙሉ በገባነው ቃል መሰረት እየተፈጸሙ መሆናቸውን እናንተም ስለምታውቁ ዘርዘር አድርጌ መግለጽ አይኖርብኝም። ሁሉም ቃል የገባናቸው ፕሮጀክቶች ጊዜያቸውን ጠብቀው ሪቫን እየቆረጥን እና ሰርቪስ እየሰጡ ይቀጥላሉ። ለዚህ መንግስት ከፍተኛ የሆነ ርብርብ አድርጓል፤ ውጤቱም እጅግ ተስፋ የሚሰጥ ነው።
አጠቃላይ ማክሮ አምና 6 ነጥብ 4 ፣ ዘንድሮ ቢያንስ ከአንድ በመቶ በላይ ጨምሮ 7 ነጥብ 5 በመቶ እድገት ያስመዘግባል ተብሎ ይጠበቃል። የሁላችንም ርብርብ ከታከለበት ይህ ውጤት ሊመዘገብ እንደሚችል ይታመናል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የዋጋ ግሽበትን በሚመለከት፣ የሸቀጦች አቅርቦት መዛነፍን በሚመለከት የተነሳ ጥያቄ አለ። የዋጋ ንረት የዓለም ሁሉ ፈተና ነው። በሚዲያ እንደምትሰሙት በማደግ ላይ ያሉ ብቻ ሳይሆኑ ያደጉ፣ የበለጸጉ አገራት ጭምር ዘንድሮ በዋጋ ንረት ምክንያት ብዙ ፈተና /ቻሌንጆች/ ገጥሟቸዋል። ለዚህ የዋጋ ንረት መነሾ የሆነው ጉዳይ በአንድ በኩል የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ሲሆን፣ በሌላ በኩል ምርቶች ወደሚፈልጋቸው ገበያ እንዳይሄዱ በጦርነት በግጭት ምክንያት መስተጓጎላቸው ነው። ይህ በዓለም ላይ ያለው ፈተና ለእኛ ደግሞ ለኢትዮጵያ ማክሮ ኢንፊሌሽን ስብራት ነው። የዋጋ ግሽበት የማክሮአችን ስብራት ነው። ብዙ ውጤት ያመጣንባቸው ሴክተሮች ያሉ ቢሆንም በግሽበት የተገኘ ውጤት አሁንም ገና ብዙ ስራ ይጠይቃል።
ነገር ግን ባለፉት አራት ወራት የኢትዮጵያ ኢንፊሌሽን የዋጋ ግሽበት እያደገ ሳይሆን ዲክሪዚንግ ሬት ላይ ነው ያለው። የአራት ዓመት የስታቲስቲክስ ውጤት የሚያሳየው ኢንፊሌሽን በዲክሪዚንግ ሬት ላይ (በመቀነስ ሒደት ላይ) እንዳለ ነው የሚያመለክተው። በመቀነስ ሒደት ላይ ማለት የአንድ ምርት ሸቀጥ ዋጋ መቀነስ ሳይሆን የአንድ ምርት እድገት እያሳየ የነበረው እድገት ተገቶ በቅናሽ ላይ ነው ያለው ማለት ነው። ይህ የሆነበት በጣም በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል። ባለፈው ታስታውሱ ከሆነ ብዙ ርብርብ እናደርጋለን ብዬ ለተከበረው ምክር ቤት አቅርቤ ነበር። ከዚህ ውስጥ አንዱ በዘመን መለወጫ በአዲሱ ዓመት እንደሚታወቀው የዶሮ፣ የእንቁላል፣ የስጋ ፍላጎት ይጨምራል። ብዙ ጊዜ ገበያ ይወደዳል። ይህ ደግሞ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎችን ይጎዳል።
ያ እንዳይሆን ጠንካራ ኮሚቴ አቋቁመን በከፍተኛ ትጋት ነው የሰራነው። ስንት ኩንታል ጤፍ ከተማ መግባት እንዳለበት፤ ምን ያህል ሽንኩርት ከተማ መግባት እንዳለበት ጭምር ማለት ነው። በዚህም ጤፍ ለበዓል ወደ አዲስ አበባ በመንግስት ተገዝቶ በተለያየ ማርኬት ውስጥ እንዲውል ተደርጓል። ምክንያቱም ጤፉ አለ። እዚህ ሲቀርብ በዓሉን ተስታክኮ ዋጋው ስለሚጨምር እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ስለሚጎዱ፤ የበዓላት ዋጋ የምታስታውሱት በከፍተኛ ኢንተርቬንሽን ነው ለማረጋጋት ሙከራ የተደረገው። ይህ ቢቀጥል በእጅጉ ሊያግዝ ይችላል።
ሁለተኛው፣ ሰንዴይ ማርኬት ነው፤ በየእሁዱ በየሰንበቱ አንዳንድ ቦታ ላይ አርሶ አደሩ እየመጣ በቀጥታ እንዲሸጥ የተደረገው ሙከራ በርከት ያሉ ቦታዎች አዲስ አበባ ላይ ያ የገበያ ስርዓት እየተለመደ መጥቷል። በዚያም ገበያ ለማረጋጋት የራሱን ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ሶስተኛው፣ እጅግ የሚያስደስተው እና የተከበረው ምክር ቤትንም ሊያኮራ የሚገባው የተማሪዎች ምገባ ነው። ኢትዮጵያ ዛሬ ከ9 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች በቀን ሁለቴ ትመግባለች። ባለፈው ዓመት 9 ነጥብ 4 ነበር። አሁን ከ200 ሺ በላይ ሰዎች ለመጨመር የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል። 9 ነጥብ 5 ሚሊዮን ህጻናት በቀን ሁለቴ መግባ ማስተማር ማለት የአንዳንድ አገራት ፖፕሌሽን ማለት ነው።
እነዚህ ልጆች ምግብ ስላጡ ቁርስ ስላጡ ከትምህርት ቢቀሩ ስንት ሳይንቲስት ስንት ዶክተር ስንት ኢንጂነር ኢትዮጵያ ሊቀርባት እንደሆነ አስቡ። የነገር ሁሉ መሰረቱ ፋውንዴሽኑ ኢለመንታሪ ስኩል ነው። እዛ ጋ መግበን ካስተማርናቸው እድሜያች ከፍ ሲል ምናልባት ተላልከውም ሊማሩ ይችላሉ። ራሳቸውን መርዳት በማይችሉበት ደረጃ ምግብ ካጡ ግን ትምህርት ብቻ ሳይሆን ሕይወታቸው ይደናቀፋል። ይህ ነገር መጠናከር አለበት። እናንተም ልትኮሩ ይገባል። እንደ አገርም አበክረን ልንሰራበት የሚገባው ኤሪያ ታዳጊ ሕጻናት ትምህርት ቤት መሄድ ሲገባቸው በዳቦ ምክንያት ከትምህርት እንዳይስተጓጎሉ ማድረግ ነው። ይህ በቀጥታ ከኑሮ ውድነት ጋር ይያያዛል። አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት መላክ እንዳይቸገሩ የሚያግዝ ስለሆነ።
እዚሁ ጋ ለመመለስ የዩኒቨርሲቲ ጥያቄ ተነስቷል። ሁላችሁም እንደምታስታውሱት ላለፉት አራት ዓመታት አንድም ዩኒቨርሲቲ አልከፈትንም በኢትዮጵያ ደረጃ። አሁንም አንከፍትም። አንድም ዩኒቨርሲቲ አንከፍትም በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ። ዋናው ምክንያት ምንድን ነው ዩኒቨርሲቲ እንደ ሃይስኩል በየቦታው ኮንዶሚኒየም እያበዛን ዩኒቨርሲቲ ብንል አጠቃላይ የትምህርት ስርዓት ላይ የሚያመጣው ኢምፓክት ካልተቀየረ በስተቀር ውጤቱ አነስተኛ ነው የሚሆነው። በአንጻሩ ሚኒመም ከስምንት ሺ እስከ አስር ሺ የሚጠጉ ኬጂዎች ሰርተናል። በሕዝብ ሀብትና ድጋፍ በአገር ደረጃ በስፋት ኬጂዎች፤ ኬጂ ማለት የሙዓለ ሕጻናት ትምህርት ቤት እየተከፈተ ይገኛል። እዛ ያልተማረ ተማሪ ዩኒቨርሲቲ ሲደርስ የሚያመጣው ውጤት ውስን ስለሚሆን ታች ላይ ያሉትን አበክረን ገንዘቡን ወደዛ ብናወርደው፤ አቅሙን፣ ጊዜውን ብናወረደው ስለሚሻል። በርከት ያለ ኢለመንታሪ ስኩል፣ በርከት ያለ ሃይስኩል ገንብተናል።
የቀዳማዊ እመቤት ኦፊስ ብቻ 28 ሃይስኩል ገንብቷል። በሚቀጥሉት አራት ዓመታት የመንግስት ትኩረት ኬጂ ላይ፣ ኢለመንታሪ ላይ፣ ሃይስኩል ላይ አስተማማኝ መሰረት መጣል ይሆናል። ዩኒቨርሲቲዎችስ? ዩኒቨርሲቲዎች መምሰል አለባቸው። የጀመሩ አሉ። ከዚህ ቀደም የነበረውን ምስል የቀየሩ አሉ። ለምሳሌ፣ የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ፣ የዩኒቨርሲቲ ቅርጽና ምስል የያዘ ነው። በብሎኬት ቁጥር ከብዙዎቹ ያንሳል። ብሎኬት የለውም። ግንብ የለውም። ነገር ግን ግቢ ውስጥ የገባ ተማሪ ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ፣ ሀብት እንዴት እንደሚፈራ አውቆ፣ አፈር አቡክቶ እንዴት ማደግ እንደሚቻል ተምሮ ይወጣል። የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች “ምናልባት ሶስት ዓመት ከዚያ በኋላ ከመንግስት በጀት አንፈልግም” ነው ያሉት። ዩኒቨርሲቲ ማለት እንደዚህ ነው። ወደዛ ደረጃ ያልደረሱ በጣም ብዙ አሉ።
በእርግጥ አሁን ምናልባት በሁለት ወር ሶስት ወር ጊዜ ውስጥ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከዚህ ቀደም እንዳነሳሁላችሁ ሙሉ ለሙሉ ኦቶኖመስ ሆኖ ይወጣል ፤ከመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ካታጎሪ ውስጥ ማለት። እሱን ተከትለን የባህር ዳር፣ ሃሮማያ፣ ጂማ፣ መቀሌ፣ ሐዋሳ ትላልቆቹ ዩኒቨርሲቲዎች በፍጥነት ከመንግስት በጀት ወጥተው ኦቶኖመስ መሆን አለባቸው። ኳሊቱ ኢጁኬሽን የሚባል ነገር መጀመር አለበት። መመረቅ ብቻ ሳይሆን ተመርቆ ችግርን የሚፈታ ዜጋ መፍጠር ይኖርብናል። ወደዛ ስለምንሄድ ባለፉት ጥቂት አመታት ቀደም ሲል የተነሳው ምእራብ ጎጃም ብቻ ሳይሆን በጣም በርካታ ቦታዎች የዩኒቨርሲቲ ጥያቄ ያላቸው አሉ። እነዚህን ለጊዜው አቆይተን አሁን የምለው ሲሳካልን ግን ትክክለኛ ጥያቄ ያለባቸውን ቦታዎች አድሬስ ለማድረግ ወደፊት የሚሰራበት ይሆናል። አሁን የኛ ትኩረት የእናንተም ትኩረት ቢሆን የሚሻለው ታች ፋውንዴሽን ላይ ቢሆን ይሻላል። ዩኒቨርሲቲዎች በደንብ ጠንክረው ግሪን ሆነው አርሰው አርሶ አደር አግዘው በምርምር ደግፈው ጠንካራ እየሆኑ ሲሄዱ ኦቶኖመስ ሲሆኑ ደግሞ እኛ አዲስ እያስፋፋን መሄድ አንቸገረምና በዚህ መልኩ ታሳቢ ቢደረግ።
ዋናው ፖይንቴ ግን ኢንፍሌሽን ስለነበረ፤ ኢንፍሌሽን ውስጥ ሌላው ማዕድ ማጋራት ነው። ማዕድ ማጋራት ምን ያክል ሰው እየጠቀመ እንደሆነ በየአካባቢያችሁ የምታስተውሉ ይመስለኛል። በተለይ አዲስ አበባ ላይ ግን ምንም ገቢ የሌላቸው ከ30 ሺህ በላይ ሰዎች በየቀኑ ልክ አንድ ሆቴል ሄደው አስራ አንድ ገደማ መመገቢያ ቤቶች ውስጥ ይመገባሉ። ሄደው ሰአት ሲደርስ እንጀራ በወጥ ይበላሉ። ሄዳችሁ አይታችሁ ከሆነ አላውቅም። 30 ነው፤ ሃምሳ ፣መቶ፣ ሁለት መቶ ሺ ማድረግ አለብን። ማስፋት አለብን ግን ቀላል ነገር አይደለም። ሰለሳ ሺ ሰው ለምሳው ሳያስብ ሄዶ የሚበላበት ስፍራ አበጅተን ምግብ ማቅረብ መቻላችን ትልቅ እድገት ነው።
ከዚህ ባሻገር በየሰፈሩ በየሃይማኖት ተቋማቱ በየኩባንያው በማዕድ ማጋራት የሚታገዙ አሉ። እሱም በተወሰነ ደረጃ የሚያግዘው ነገር አለ። ይሄ ሁሉ ጥረት ተደርጎ ግን የገበያ ትስስር ችግር አለበት። ለምሳሌ ብላቴ ላይ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ሙዝ ፓፓያ ያመረቱ ሰዎች አዲስ አበባ ገበያ ላይ መተሳሰር ተቸግረው ይበሰብስባቸዋል ፤ይጥላሉ። ጨንቻና ጅማ ላይ በስፋት አፕል ተመርቶ ገበያ ሊቀርብ አይችልም፤ እኛ ግን አፕል ኢንፖርት እናደርጋለን። የገበያ ትስስሩ ላይ የተነሳው ጥያቄ በጣም ወሳኝና ብዙ ስራ የሚያስፈልገን መሆኑን ታሳቢ የሚደረግ የሚሰራበት ቢሆንም ኢንፍሌሽን ላይ ግን ባለፉት አራት ወራት የነበረውን ውጤት ለማስቀጠል የሚያስችል ሙከራዎች እንዳሉ ያመላክታል።
ኢንፍሌሽን ላይ ልክ እንደ ኮቪድ ነው። በኮቪድ ላይ ያመጣነውን ውጤት የተጎናፀፍነውን ድል መድገም እንችላለን። ኮቪድ ኮሮና ሲመጣ አለም በሙሉ ሎክ ዳውን ነው ያለው። አለም በሙሉ ግቢዬን ከተማዬን እዘጋለሁ ነው ያለው። አንዘጋም እንጠነቀቃለን መሬት ግን ጦም አናሳድርም ብለን ያኔ የጀመረነው ስንዴ ነው ዛሬ ስለ ኤክስፖርት እየተወራ ያለው። ኮሮናን እንደ ችግር ሳይሆን እንደ እድል መጠቀም ስለቻልን። አየር መንገድ በአለም ላይ ያሉ አየር መንገዶች ከሞላ ጎደል ኪሳራ ውስጥ ሲገቡ የኛው አይ የሰው ማጓጓዣው ቀርቶ የካርጎ ማጓጓዣ ማድረግ ይቻላል በሚል ኦልሞስት አለምን የሚያገናኝ አየር መንገድ ነው የነበረው። እናም ትርፋማ ነበር እንደምታወቁት። ልክ እንደዛው ኢንፍሌሽን ላይ አበክረን ብንሰራ አሁን የተጀመረው ውጤት ሊጠናከር ይችላል።
የዚህ ማጠናከሪያ መንገድ ግልፅ ነው። አንደኛው ግሪን ሌጋሲ ነው። ግሪን ሌጋሲ ውስጥ ስንዴ አለ፣ ሩዝ አለ፣ ቡና አለ፣ ፓፓያ አለ፣ ምግብ አለ። ግሪን ሌጋሲ የሚናገረው ስለ ምግብ ነው። አሁን ደግሞ የሌማት ቱሩፋት ብለናል። የሌማት ቱሩፋት ከምግብ ባሻገር ነው። ኒውትርሽን ነው። የተመጣጠነ ምግብ ነው። የሌማት ቱሩፋት የሚያካትተው አንደኛ ማር ነው፤ መትከላችን ካልቀረ ችግኝ በየቦታው ዘመናዊ ቀፎ ብናስርበት በቀላሉ ማር ልናገኝ እንችላለን። በየከተማው ዶሮ /ጫጩት/ በዘመናዊ መንገድ ማርባት ብንችል እንቁላልም ዶሮም ለኢትዮጵያ መከራና ፈተና ሊሆኑ አይችሉም። ላም ኢትዮጵያ ከሰባ ሚሊየን በላይ የከብት ሀብት እንዳላት ይነገራል። በአፍሪካ ቀዳሚው ከፍተኛ ቁጥር ያለው የከብት ሀብት አላት ይባላል። ነገር ግን ከእነሱ የምናገኘው ወተት በጣም አነስተኛ ነው።
አሁን ዘመናዊ የሚባሉ ከብቶች በቀን ከ25 እስከ 30 አንዳንዴም ከዛ በላይ ሊትር ወተት በቀን ይሰጣሉ። ሰላሳ ሊትር ወተት በቀን የሚያገኝ ሰው ለራሱ አምስት ሊትር ቢጠጣና 25ቱን ቢሸጥ፤ በምግብ እራስን ከመቻል አንፃርም ሆነ ከገበያ አንፃር ያለውን ጥቅም ተመልከቱ። የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች አምስት ስድስት አንዳንዴም በመቶ የሚቆጠር ላምና በሬ ከሚኖራቸው ሰላሳ ሊትር የምትሰጥ አንድ ላም ብቻ በትክክል መግበው መጠቀም ቢችሉ ከወተት ጋር ከስጋ ጋር ያለው ጉዳይ ይፈታል ኢትዮጵያን የቀነጨረ የሚባል ታሪካችን ይቀየራል።
ስለምግብ አራት አመት ሰርተናል ውጤት አምጥተናል፤ በሩዝ በስንዴ በቦቆሎ በጤፍም ጭምር ውጤት ታይቷል። ምግብ ብቻውን በቂ አይደለም ኒውትሪሽን ያስፈልገናል። በሚቀጥሉት አራት አመታት እንደ ህዝብ ተባብረን የተከበረው ፓርላማ ረድቶን ከሰራን በእርግጠኝነት የዶሮ፣ የማር፣ የእንቁላል ጉዳይ መልስ ያገኛል። ይሄ ግን እንደ ግሪን ሌጋሲ ተባብሮ መስራትን ይጠይቃል። ያሉንን ቦታዎች ሁሉ መጠቀም ይጠይቃል። መንግስት ዝርዝር ጥናት አጥንቶ እቅድ አውጥቶ በይፋ ፕሮግራሙን አስጀምሯል። የእናንተ ድጋፍ ታክሎበት ከህዝባችን ጋር ሆነን ኢትዮጵያ ውስጥ ምግብ አጀንዳ የማይሆንበትን መንገድ እንፈጥራለን።
የተከበረው ምክር ቤት ቢገነዘብ መልካም የሚሆን ነገር፣ ለብዙ ነገር አንቲ ፔን እየወሰዱ መኖር ለኢትዮጵያ አያዋጣም። ነዳጅ ውድ ሆነ፣ ሰብ ሲዲ እናድርግ፤ ማዳበሪያ ተወደደ ድጎማ ይደረግ፤ እህል ውድ ሆነ እህል መንግስት ገዝቶ ያቅርብ፤ እንደዚህ አይነት የአንቲ ፔን አካሄድ ዘላቂ ውጤት አያመጣም። አንዴ ጨከን አድርገን እየታመምንም ቢሆን መሰረታዊ ስራ ሰርተን እንደ አንዳንድ እራሳቸውን ከችግር እንደ ገላገሉ ሀገራት መገላገል ካልቻልን በስተቀር ሁልጊዜ ውሃ ሲጠማን ውሃ ለምነን እየጠጣን ሳይሆን ውሃ ቆፍረን እያወጣን በዘላቂነት መፍትሄ የምናበጅበትን መንገድ መከተል ካልቻልን ዘላቂ የሆነ ችግር መፍቻ ሊሆን አይችልም። የኢንፍሌሽን መሰረታዊ መፍትሄ ምርት ነው። በጓሮ ማረስ ተጀምሮ ነበር ፋሽን መሆን የለበትም መቆም የለበትም። ከተሜው ቆስጣ ሰላጣ ቲማቲም ሽንኩርት የሚያበቀል ከሆነ ከውጭ በገፍ ስንዴና ሩዝ የምናገኝ ከሆነ በአቅራቢያችን እንቁላል ዶሮ ማር የምናገኝ ከሆነ፤ ቢያንስ ገዝተን አለያም በሆነ በሆነ መንገድ መመገብ ችግር ላይሆን ይችላል። ያንን ማድረግ ካልቻልን ፖፑሌሽን እያደገ ሲሄድ እንደ ከዚህ ቀደሙ ቀለል ላይል ይችላል።
ከዚህ አንፃር መንግስት ብናደርግ ብሎ የሚያስበው አንደኛው መቀነስ ነው። ብክነት መቀነስ። ለምን መቀነስ እንላለን በአለም ላይ በቀን ከሚመረተው ምግብ 17 ፐርሰንት ይደፋል በቀን። በቀን አንድ ሚሊየን የሚጠጋ ህዝብ እራት የሚበላውን አጥቶ ጦሙን ያድራል። ያ የሚደፋውን ምግብና የተራበውን ሰው ማገናኘት ቢቻል ረሀብ የለም ወይም በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል። አንዳንዱ የሚደፋው አንዳንዱ የሚራብበትን ነገር ማጥበብ ያስፈልጋል። መቀነስ ስንል አንደኛው ብክነት ነው፤ ብክነት መቀነስ ያስፈልጋል። አንድ ሰው ማዕድ ላይ ይዞ መቅረብ ያለበት የሚጨርሰውን ምግብ ብቻ መሆን አለበት። የማይጨርሰውን አቅርቦ ሲተርፍ መደፋት የለበትም፤ ጥሩ ልምምድ አይደለም። ምክንያቱም፣ ያንን የሚያጡ ሰዎች እንዳሉ ደግሞ ማሰብ ያስፈልጋል።
ሁለተኛው፣ ማጋራት ነው። በሆነ መንገድ ያለው የተረፈው ካለ ለሌለው ማጋራት እንደ ልምድ መወሰድ አለበት። አሁንም ወደፊትም ስለሚሰራ። ብልፅግና ቢረጋገጥም የሚቸገሩ ዜጎች ይኖራሉ። በበለፀጉ በአለም አንደኛ ኢኮኖሚ ባላቸው ሀገራት በሚሊየን የሚቆጠር ሰው በየቀኑ በፉድ አስታምብ ይኖራል በምግብ እርዳታ። አይቀርም እሱ። ሀገር መመገብ የሚችል አቅም እንዲኖራት የሚሰራው እንጂ፤ ምግብ ለምነው የሚበሉ ሰዎች ዜሮ ማድረግ አይቻልም። ብክነት መቀነስ ማዕድ ማጋራት፤ ሶሰተኛው ማምረት ነው። በጓሮ ማምረት በማሳ ማምረት ራቅ ራቅ እያሉ ማምረት ያስፈልጋል። ሲመረት አንዳንዱ ለገበያ ይውላል፤ አንዳንዱ አስፈላጊ ከሆነ ለወፍም ይዋል፤ ግን ማምረት ጥሩ ነው። የበሰበሰባቸው ሰዎች፣ የተበላሸባቸው ሰዎች ኮምፕሌን ያደርጋሉ፤ ከምንም ተመርቶ የተበላሸውን ወደ ገበያ ማስተካከሉ ነው የሚሻለውና የሚቀልለው። በመሆኑም ማምረት መጀመር አለብን በሁሉም ቦታ ላይ። ቨርቲካሊም፣ ሆሪዞንታሊም ምርት ማደግ አለበት። የተጀመረውን ማጠናከር ነው። ….
ይቀጥላል…
አዲስ ዘመን ህዳር 7/2015