ዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ በሰዎችና በተሽከርካሪዎች ግርግር ተሞልቷል። ሰባት የሚሆኑ የአንበሳና የሸገር አውቶብሶች አደባባዩ ጠርዝ ላይ ተሰልፈው ቆመዋል። አውቶብሶቹ ተሳፋሪዎችን ያወርዳሉ። ያሳፍራሉ። ዐይናችንን ቀና ስናድርግ አንበሳ ሦስት ቁጥር አውቶቡስ የምታሽከረክር እንስት ላይ አረፈ። አሽከርካሪዋ እመቤት በሻዳ ለትንሽ ደቂቃ ስለ ህይወቷ እንድትነግረን ፈቃድ ጠይቀን ከእሷም በጎ ምላሽ አግኝተናል፡፡
ሦስት ቁጥር አንበሳ አውቶብስ ከፒያሳ ጊዮርጊስ ተነስታ በሜክሲኮ፤ በልደታ፤ በጦር ኃይሎች አቋርጣ አየር ጤና ማሳረጊያዋ ነው። 5፡45 ሰዓት ከፒያሳ ተነስታ ወደ አየር ጤና የምታቀናዋን የአንበሳ አውቶብስ የምታሽከረክረው ደግሞ ወይዘሮ እመቤት ናት። ይች እንስት በህይወቷ ብዙ ውጣ ውረዶች አልፋለች። በትምህርት ቤት ቆይታዋ የ12ኛ ክፍል (የቀድሞው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠቃለያ ማለት ንው) ትምህርቷን አጠናቅቃ ሥራ በመፈለግ ብዙ ተንገላታለች።
ከብዙ ፍለጋና ጥረት በኋላም በአንበሳ የከተማ አውቶብስ ድርጅት ትኬት ቆራጭነት ተቀጠረች። በዚህ ሙያም ለ10 ዓመታት ያህል ስታገለግል ሁሌም ለማደግ ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበራትና ጥረት ታደርግ እንደነበር ታስታውሳለች። በተለይ ቤተሰብ ስትመሰርትና የሁለት ልጆች እናት ስትሆን ገቢዋን ለማሳደግ ጥራለች።
ከትኬት ቆራጭነት ሻል ወዳለው ደረጃና ደመወዝ ለመድረስ ዕድል ስትፈልግ ቆይታለች። የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ ድርጅት በውስጥ ለሚሠሩ ሠራተኞች ለሾፌርነት ለማሰልጠን የሚሰጠውን ዕድል ተወዳድራ አለፈች። ስልጠናውንም በተሻለ ብቃት አጠናቅቃ የአንበሳ የከተማ አውቶብስ አሽከርካሪ ሆነች፡፡
የአውቶቡስ ገንዘብ ተቀባይ (በተለምዶ ትኬተር) የተነሳችው ወይዘሮ እመቤት የሾፌርነት ሙያ ሰልጥና ለአራት ዓመታት በአንበሳ አውቶቡስ ሾፌርነት በማገልግሏ እርካታ አግኝታለች። ያሰበችው የደመወዝ ጭማሪም ተሳክቶላታል። ቀድሞ በትኬት ቆራጭነት ይከፈላት ከነበረው ብር 1300.00 ደመወዝ አሁን ብር 6068.00 እንደምታገኝ ገልፃልናለች፡፡
“የመለወጥ ዓላማ ካለህ ምንም ሥራ አይከብድም” የምትለዋ ወይዘሮ እመቤት ህይወቷን ለመለወጥ ባደረገችው ትግልና ጥረት የሾፌርነትን ሙያ የእንጀራ ማግኛዋ ማድረጓን ነው የምትናገረው፤
ሴቶች ዓላማ ካላቸውና ውሣኔ ሰጭ ከሆኑ ወደፈለጉበት ቦታ መድረስ ይችላሉ። ሴት ሾፌር በመሆኗ ከተሳፋሪውም ሆነ ከአሽከርካሪዎችና ከትራፊክ ፖሊሶች ጥሩ ፊት እንደሚያሳዩአትና የተወሰኑ ሰዎች እንደሚገረሙ የምታወሳው ወይዘሮ እመቤት፤ ሴት አሽከርካሪ በመሆኗም ሌሎች መኪና አሸከርካሪዎች ቅድሚያ ይሰጡኛል ብላለች፡፡
“መኪና ስታሽከረክር ቤተሰብህን፤ ኑሮህንና ገጠመኝህን ጥለህ ሐሳብህን ሁሉ መኪና በማሸከርክሩ ላይ መሆን አለበት የምትለው ወይዘሮዋ፤ ዓመታት በጥንቃቄና አስተውላ ስለምትነዳ ባለፉት አራት የአሽከርካሪነተ ህይወቷ የመንገድ(የትራፊክ ሕግ ጥሳም ሆነ አጥፍታ በትራፊክ ፖሊሶችም ተቀጥታ እንደማታውቅና ምንም ግጭት እንዳላጋጠማት ነግራናለች።
ለሴቶች እህቶቿና ልጆቿም ምክር አላት። በርቱ ጠንክሮ የሠራ የማይደርስበት ቦታ እንደሌለ እኔ ማሳያ ነኝ ባይ ናት። የሚከብድ ነገር የለም። ገና አውሮፕላን እንነዳለን (በርግጥ ሴት ፓይለቶች በኢትዮጵያ አየር መንግድ እንዳሉ ታውቃለች) እምትለው ወይዘሮ እመቤት፤ ከቲኬት ቆራጭነት ተነስታ የአውቶቡስ አሽከርካሪነት ሙያ ስልጠና እስከወሰደችበትና ለአሽከርካሪነት እስከደረሰችበት ጊዜ ድረስ በርካታ ፈተናዎች አጋጥመዋታል።
“ህይወት ትግል ነው” የሚል እምነት ያላት ወይዘሮዋ፤ የአጋጠሟትን ፈተናዎች ድል በማድረጓ ከአነስተኛ ገቢ ወደ መካከለኛ ገቢ መሸጋገር ችላለች። “ፈተና አያጋጥምም አይባልም፤ ያጋጥማል ግን ጠንክሮ ከተሠራ ህልምን እውን ማድረግ እንደሚቻል ከእኔ የህይወት ተሞክሮ ማየት ይቻላል” ባይ ናት።
ነገን የተሻለ ህይወት ለመኖር ዛሬ ላይ ደፋ ቀና ብሎ መሥራት የሚጠይቅ ነው። ለዚህም ነው ሰዎች ኑሮቸውን ለመለወጥ የማይወጡት ዳገት፤ የማይወርዱት ቁልቁለት የለም የሚባለው፤ በአገራችን ቀደም ሲልም ሆነ አሁንም ሴቶች ሥራ ፈጥረውና ያላቸውን ውስን ገንዘብ፤ ጊዜ፤ እውቀትና ጉልበት ተጠቅመው ሙያቸውን ለማሳደግና ለነገ የተሻለ ህይወት ለመኖር ሳይታክቱ በመሥራት ለስኬት ለመብቃት አልመውና ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸው ወይዘሮ እመቤት በሻዳ አንዷ ማሳያ ናት።
የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት በአሁኑ ወቅት በ124 መስመሮች ለአዲስ አበባና በዙሪያዋ ለሚገኙ ኗሪዎች አገልግሎት ይሰጣል። ሠራተኞቹን በተለያዩ የውስጥ ስልጠናዎች በማብቃትም ዕውቀታቸውንና ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ ድጋፍ ያድርጋል። ከነዚህም መካከል ሴቶች ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ። በድርጅቱ መረጃ መሰረትም በአሁኑ ጊዜ በውስጥ ስልጠና አቅማቸውን ያሳደጉ 64 ሴት የአውቶቡስ አሽከካሪዎችና 79 በልዩ ልዩ የጥገና ሙያ የሰለጠኑ ሴት ሠራተኞች (መካኒኮች ) በድርጅቱ በመሥራት ላይ እንደሚገኙ ገልጿል።
እናም ሴቶች ከፍተኛ የቤተሰብ አስተዳደር ጫና ቢኖርባቸውም ዕድሉን ካገኙ የራሳቸውን የሙያ ብቃት አሳድገውና በተሻለ የሙያ መስክ ተሰማርተው ላቅ ያለ ደረጃ ላይ መድረስ እንደሚችሉ እንደ ወይዘሮ እመቤት በሻዳ ያሉ ብርቱዎች ማሳያና አርኣያ ናቸው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2/2011
በ ጌትነት ምህረቴ